የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የክብር አባት

“ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ ፥ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም ፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ ።” ኤፌ. 1፡15-17 ።

ሐዋርያው ስለ ኤፌሶን ክርስቲያኖች በርቀት ይሰማው የነበረው እግዚአብሔርን ስለ ማመንና ወንድሞችን ስለ መውደድ ነው ። የኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዲህ ነበሩ ። ይህም ሕይወታቸውን የተሟላ ያደርገዋል ። ኦሪትም ሐዲስም ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽን የሚሰብኩ ናቸው ። እግዚአብሔርን የወደደ ወንድሙን ሳይወድ አይቀርም ፣ ወንድሙን የሚወድም እግዚአብሔርን ለመውደዱ ምስክር ነው ። ከወንድም ፍቅር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር ይቀድማልና ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል ። እግዚአብሔርን አምኖ ወንድሙን መውደድ የቸገረው ፣ ወንድሙን ወድዶ እግዚአብሔርን ማመን የተሳነው ካለ ኑሮው ከባድ ነው ። እግዚአብሔርን እወዳለሁ ብሎ ወንድሙን የሚጠላ የዓይን ቅርጽ ያለው ነገር ግን የማያይ ነው ። ወንድሙን ወድዶ እግዚአብሔርን አላምንም የሚል መሠረት የሌለው ረጅም ካብ የሚክብ ነው ። እምነት ያፋቅራል ፣ ፍቅርም ያምናል ። በሚወድድ እምነት ፣ በሚያምን ፍቅር መኖር ጸጋ ነው ።

ሰዎችን በግላዊ ጥንካሬአቸው ፣ በሰዎች ዘንድ ባላቸው ተጽእኖ ፈጣሪነት ፣ አያስነኩኝም ተብለው በታመኑት ልክ ፣ ኃይላቸው የሚጥል በመሆኑ ፣ ጊዜ ያከበራቸው የቀን ጎበዞች በመሆናቸው ፣ በግል ጽድቃቸው ፣ በአገልግሎት ትጋታቸው ሊታመኑ ይችላሉ ። የሚያስመሰግንና የማያሳፍር እምነት ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው ።

ክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደዳቸው ምስክርነት ነው ። ክርስቲያኖች ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ከማኅበረሰቡና ከምድራዊ ጥቅም መገለል ፣ መነጠልና መሰደድ ይገጥማቸዋል ። የቀስት መለማመጃ ሁነው ፣ ስድብ ለማጅ እንኳ ስሜት እንዳላቸው ረስቶ በእነርሱ ላይ ያሟሻል ። የክርስቲያኖች ሕይወት የተኩስ ወረዳ ነው ። በክርስቲያኖች ላይ ዱዳ የሚናገርበት ፣ ፈሪው ደፋር ሁኖ ካላጠፋኋችሁ የሚልበት ነው ። መስቀል በክርስትና ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ። የሥጋ ዘመዶቻቸው ሳይቀር አሳልፈው ሲሰጡአቸው ትልቅ ትምክሕት ይሰማቸዋል ። የክርስቲያኖችን አንገት መቅላት ለሃይማኖታቸው ቸብቸቦ እንደ ማቅረብ የሚቆጥሩት አያሌ ናቸው ። አንዳንዶችም ወደ አምላካቸው መንግሥት የሚገቡት በክርስቲያኖች እልቂት መሆኑን ያምናሉ ። የፈጠረውን ግደሉልኝ የሚል ፈጣሪ መኖሩ ግራ ያጋባል ። በዚህ ሁሉ ምክንያት ይህን መራራ ዓለም ለማሸነፍ ክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ አለባቸው ።

በዓለም ላይ እኛ ትንሾች ነን ፣ የተጠላን ነን ። ሁሉ ሊያጠፋን ይፈልጋል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ይፋቀራሉ ። የክርስቲያኖች ፍቅር ግን የመጥፋት ስሜት የወለደው ሳይሆን በክርስቶስ የመዳን ፍሬ ነው ። በፍቅር የተገለጠ ፣ ራሱንም ፍቅር ብሎ የጠራ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የባዕድ አምልኮ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ድምፃቸው ጎርናና ፣ ቃላቸው ጭንቁር ነው ። የሚመለኩበትም ስልት ማስፈራራት ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ግን ተወድዶ የሚመለክ አምላክ ነው ። ሐዋርያው በርቀት ሁኖ የሰማው የኤፌሶን ክርስቲያኖችን እምነትና ፍቅር ነው ። እምነት ለማይታየው እግዚአብሔር የሚቀርብ መባ ነው ፣ ፍቅር ለሚታየው ባልንጀራ የሚቀርብ እንጀራ ነው ። ክርስቶስን በማመን መጽናት ፣ ወንድሞችን በመውደድ መታወቅ ትልቅ ዕድል ነው ። እግዚአብሔር በህልውናው እንደማይጠረጠር አማንያንም ሌላውን በማፍቀር መጠርጠር የለባቸውም ።

ዛሬ በርቀት ያሉ መንገድ የመሩን አስተማሪዎቻችን ፣ ስለ እኛ ሕይወት የተጨነቁ የሃይማኖት አባቶቻችን ምን እየሰሙብን ይሆን  ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። የዘረኝነት ቀስቃሽ ሁነን ሲያዩን ምን ብለውን ይሆን  ሌላውን እየማገድን ለመኖር ስንጨክን ደጉን ክርስቶስ አልተማሩም ነበር ወይ  ብለው ተጠራጥረውን ይሆን  በሌብነት ዓይን ስናወጣ ድሀ ሁነን የወደደንን አምላክ በመካዳችን አዝነው ይሆን  የኤፌሶን ክርስቲያኖች የሚሰማ ቃል ሳይሆን የሚሰማ ሕይወት ነበራቸው ። እርሱም እምነትና ፍቅር ነው ።

የማይታየው እምነት በሚታየው ወንድምን መውደድ ይገለጣል ። ሰውን መውደድ እግዚአብሔር በሰው ላይ ያለው ዓላማ ማፍቀር ነው ። የክርስቶስ ስም እንዳይሰደብ ክርስቲያን ሀነው በችግር ውስጥ እያለፉ ያሉትን ዛሬ መጎብኘት ያስፈልገናል ። ይህ በቀራንዮ የተሰቀለውን የክርስቶስን ዕርቃን መሸፈን ነው ።

ሐዋርያው በሰማው ነገር ተደስቶ ሦስት ነገሮችን አደረገ ። ማመስገን ፣ መጸለይ ፣ ማሳሰብ ። ማመስገን ስላለፈው ኑሮአቸው ፣ መጸለይ ስለ ዛሬው ሕይወታቸው ፣ ማሳሰብ ያለማቋረጥ ጸጋን መመኘት ነው ። በመልካም መንገድ ላይ ስላሉ ሰዎች እግዚአብሔርን ማመስገን እንጀምር ። ያን ጊዜ ደስታ በልባችን ይሞላል ። ሰዎቹም ጸጋ ይበዛላቸዋል ። ሕይወታቸው ርእስ ሁኖ እግዚአብሔር ተመስግኖበታልና ። ደግሞም እንዲጸኑ መጸለይ ይገባል ። ታይቶ ጠፊ ፣ ጀምሮ ቀሪ ፣ ወጥቶ ዱር አዳሪ እንዳይሆኑ መጸለይ ግድ ይላል ። ተጠርተው ያልተመረጡ ፣ ራሳቸውን ከሕይወት መዝገብ የሰረዙ አሉና ። ማሳሰብም ወሳኝ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ስላሉት ብቻ ሳይሆን ስለ ሞቱትም ማሳሰብን አትተውም ። ይህን ስፋትና እምነት መያዝ መታደል ነው ።

የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ” ይላል ። ሥላሴን ያነሣል ። የክብር አባት ብሎ አብን ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብሎ ወልድን ፣ የጥበብና የመገለጥ መንፈስ ብሎ መንፈስ ቅዱስን ያነሣል ። ደግሞም ምሥጢረ ሥጋዌን ያትታል ። የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ይላልና ። ጌታችን ለለበሰው ሥጋ አብም እርሱም ፈጣሪ ናቸውና ። ለለበሰው ሥጋ አብ አምላኩ ነው ። ያንን ሥጋ በመቃብር ጥሎት እንዳልሄደ ፣ ያ ሥጋ ባለ መለወጥ ፣ ባለ መጥፋትና ባለ መለየት አሁን በየማነ አብ እንዳለ እያስረዳን ነው ። መንፈስ ቅዱስ የመገለጥና የጥበብ መንፈስ ነው ። መገለጥ የዋሆችን ብልህ የሚያደርግ የመለኮት መብራት ነው ። ጥበብም ክርስቶስን ምርጫ ማድረግ ነው ። የክብር አባት ይላል ። ክብር ሰጪ ሳይሆን ራሱ ክብር ነውና ። ጌታችን ይለዋል ። ኢየሱስ ማለት ችግር የለውም ። እንደ ሐዋርያው ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማለት ተገቢ ነው ። ኢየሱስ የሚሉት የታሪክ ተመራማሪዎች አሉ ። ነቢይ የሚያደርጉትም አይጠፉም ። እርሱን ጌታ ማለት ግን ከሁሉ በላይ ነው ፣ የክርስትናም መለያ ነው ። “እለምናለሁ” ይላል ። ተለማኝ አምላክ ነውና ። ስለ ሌሎች ስንለምነው የሚወድድ ፣ ለእኛም በእጥፍ የሚሰጥ ነው ።

አሜን።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /25

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ