የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የወዳጅ ድምጽ

Yewodaj demts, read in pdf
            የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ ሕዳር 26/2006 ዓ.ም.
አንድ የድሮ ጌታ የዛሬ ከርታታ፣ አንድ የድሮ አሰሪ የዛሬ ታሳሪ የሆኑ ወዳጄ፡- “ጽሑፍና ቀናተኛ ሚስት ሁለቱም አንድ ናቸው፣ አትልቀቁኝ ይላሉ” በማለት የነገሩኝን አስታውሳለሁ፡፡ እኔም ከጽሑፍ መለየት የተቸገርኩባቸው ጊዜያት፣ ካልጻፉሁ ያልኖርኩ የመሰለኝ ቀናት ብዙ ናቸው፡፡ የጻፍኩአቸውን ማስቀመጫ አጥቼ አንዳንዶቹን ሳስወግድ አሁን ትዝ ይለኛል፡፡ የእሳት ወላፈኑ በፊቴ ያበራል፣ የምጽፍበት ቦታ የቤተ ክርስቲያኑ ጫካ፣ ጠረጴዛው ጉልበቴ ነበር፡፡ የማናግረው ሰው ካገኘሁ በዚያው ስሰብክ መዋሌ፣ ሲርበኝ የእናቴን እንጀራ ለመብላት ወደ ተከፈተው ደጃፍ የምነጉድበት ጊዜ አሁን ይኸው በፊቴ እያለፈ ነው፡፡ ወታደራዊ ሰላምታን እንደሚቀበል ንጉሥ እኔም ብዙ ነገሮች ሰላምታ እየሰጡኝ ያልፋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ቆም ብለው እንዲያናግሩኝ እፈልጋለሁ፡፡ በማይከለስ ጊዜ ለማለፍ ሲቸኩሉ አዝናለሁ፡፡ ስንት መልካም ቀኖች፣ ስንት መልካም ሰዎች አለፉ!!
          
      ወረቀት ላይ መጻፍን የማከብረውን ያህል ሰው ላይ ለመጻፍ እንዲያ አልተጋሁም፡፡ ሰዎች እያተነኑ ስላስቸገሩኝ ወደዚህ ስሜት ሳልገባ አልቀረሁም፡፡ ቃሌ በደከመ ቀን ጽሑፌ እንዲቀጥል ምነው ብዙ መጻፍ በሆነልኝ እላለሁ፡፡ ጽሑፍ ጓደኛ ነው፣ ሳይታዘብ የሚሰማ የደስታና የሀዘን ተካፋይ ነው፡፡ ጣዕም እንዳለው እንቅልፍ፣ በአባት ጉያ ውስጥ እንዳለ ሙቀት ሊለዩት የሚያስቸግር ነው፡፡ ጽሑፍ ባይኖር ኖሮ ብዙ ፀሐፍት በሀዘን ተሰብረው በቀሩ ነበር፡፡ ጽሑፍ የተነፈሰ እሳተ ገሞራ ነው፡፡
         ሰሞኑን ከጽሑፍ የተለያየሁ መሰለኝና ልቤ ሀዘን ተሰማው፡፡ ጸጋ ርቆኝ ይሆን? ብዬ የጠላቴን ሹክሹክታ ማቅለም ጀመርሁ፡፡ ንቀን ያለፍናቸው ክፉ ቃላት፣ በይቅርታ የዘጋናቸው የሰዎች የአንደበት ፍላፃ መንፈሳዊ ድካም ሲሰማን እንደገና መቀስቀስ ይጀምራሉ፡፡ ከበሽታ መዳን ማለት እኛ በርትተን በሽታው ፍጹም መድከሙ እንጂ ፍጹም መሞቱ አይደለም፡፡ እኛ የደከምን ቀን የደከመው በሽታ መበርታት ይጀምራል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም የተቀዳጀናቸው ድሎች ፍጹም ከእጃችን የማይወጡ ተኝተን የምናደንቃቸው አይደሉም፡፡ ከመንፈሳዊ ድል አንዱ የክፉ አንደበትን ጅረት ማለፍ ነው፡፡ ሁለተኛው በማያቋርጥ ይቅርታ ሰዎችን ይቅር ማለት ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን መድከም ስንጀምር የናቅነውን ቃል ማሰብ፣ የተውነውን የሰዎች በደል እንደገና ማዘከር እንጀምራለን፡፡ ድካም የጠላታችንን ተስፋ አስቆራጭ ድምፅ እውነት ብሎ ማሰብ ይጀምራል፡፡ ከዚያም መናወጥ ይመጣል፣ መናወጥም ጸሎትን ያስጥላል፣ ጸሎትን መጣልም ለትካዜና ለሀዘን ራስን እያዩ ለመበሳጨት ይዳርጋል፡፡ 
         ታዲያ ያልጻፍኩት ጊዜ አጥቼ ነው ወይስ ልቡን አጥቼ ነው? ጽሑፍ የራሱ የሆነ የጽሞናና የሥነ ሥርዓት ድንጋጌ አለው፡፡ በአዳዲስ ነገር እንደ ሕጻን መቦረቅ፣ በዓለም ወረት መንጎድ፣ አእምሮን በከንቱ ነገር ማጣበብ የጽሑፍ ባላጋራ ነው፡፡ ጽሑፍ የኑዛዜ ቃል በመሆኑ በጥንቃቄና በማስተዋል መስፈር አለበት፡፡ ጊዜው አለ፣ አቅርቦቱ ከቀድሞ ይልቅ ዛሬ የተሻለ ይሆናል፡፡ ጽሑፍ ግን ከምቾት ይልቅ ለእውነት ቅንዓት ያደላል፡፡ ሲመቸን እንደውም ይጠፋናል፡፡ ቅንዓት ግን እውነትን ያቀጣጥላል፡፡ አንድ ሰው፡- “ገንዘብ የለኝም ብለህ መጻፍ አታቋርጥ፣ ገንዘቡ የተገኘ ቀን የሚጻፈው ይጠፋል” ያሉት ለዚህ ነው፡፡  
         የዛሬው የማለዳው ዕቅዴ ቢያንስ አንድ ነገር ለመጻፍ ነው፡፡ መልሼ ደግሞ ተጽፈው ተቀብረው የተቀመጡን ማገላበጥ ፈለግሁ፡፡ እነርሱን ማሰባሰብ ቀኑን የሚጨርስብኝ መሰለኝ፡፡ ታዲያ አንድ ርዕስ መርጬ ለመጻፍ ስሰናዳ ጉልበት የሚሆነኝን ነገር ፈለግሁ፡፡ እርሱም የወዳጅ ድምፅ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ወዳጄን በስልክ ማግኘት አስፈለገኝ፡፡ አዎ የወዳጅ ድምፅ ጉልበት አለው፡፡ የጽሑፌም ርዕስ ተገኘ፡፡ “የወዳጅ ድምፅ!”
         ጓደኛዬ ጋ በምኖርበት ዘመን በቤቱ የነበረች አንዲት የምታገለግላቸው እህት ነበረች፡፡ አንድ ማለዳ ቢያንስ 11፡30 ተነሥቼ ጊቢው ውስጥ ስንጎራደድ ይህች እህት እጅግ አኩርፋ ቧንቧው አጠገብ ታጥባለች፡፡ “ምነው ከዚህ በፊት የተነሣ ሰው የለም ማን ተናግሮሽ ነው እንዲህ የተከፋሽው?” አልኳት፡፡ መልሷ አጭርና ቍጣ የሞላበት ነበር፡፡ በአጭር ቃል፡- “ያደረስ ቢሆን!” አለችኝ፡፡ አዎ በማለዳ የሚያስኮርፈን ያደሩ ብስጭቶች፣ ዛሬም ራሳችንን በማንፈልገው ቦታ ማግኘታችን፣ አጠገባችን ካሉት ሰዎች የጠበቅነውን ምላሽ በማጣታችን ሊሆን ይችላል፡፡ የማለዳውን ብርሃን ስለማየታችን ምስጋና ቢኖረን ኖሮ ጨለማ አሳቦችና ፍርሃቶች ባላስጨነቁን ነበር፡፡ ካላመሰገንን መራገማችን አይቀርም፡፡ እግዚአብሔርን ካላየን ጠላታችን ይተልቅብናል፡፡ አዎ በማለዳ የወዳጅ ድምፅ ያስፈልገናል፡፡
         ወዳጅ ማን ነው? በዛሬው ዘመን በትዳሩ ያላዘነ ወንድና ሴት ያለ አይመስልም፡፡ በልጁ ተስፋ ያልቆረጠ ወዳጅ ጥቂት ነው፡፡ በተወዳጀው ያልተከፋ ወዳጅ ማን ነው? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ጥቂቶችን ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩን የሚያስወግድ እርዳታን ሳይሆን አይዞህ የሚል ቃል ተርበናል፡፡ መልካም ካደረግንላቸው መልካም ቃል እንኳ እንዳጣን ተሰምቶ ይሆናል፡፡ የኖርንላቸው እግዚአብሔር ይግደልህ እንኳ ሳይሉን በሕመማችን ጨክነውብን ይሆናል፡፡ ታዲያ ከዚህ ሁሉ የኅሊና ክርክር በኋላ ወዳጄ ማን ነው? ማለታችን አይቀርም፡፡
         ይህ ዓለም በድምፅ የተሞላ ዓለም ነው፡፡ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚሰሙ ብቻ ሳይሆን የምናስበው ነገር ድምፅ የሚሆንበትና የሚያውከን ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ያሰብነውን ነገር እንደ እውነት መቁጠር፣ የተሰማንን ነገር ሁሉ እንደ ቋሚ ሐቅ መመልከት ከባድ ነው፡፡ ይህ ችግር ሰዎች የተናገሩትን በተናገሩበት መንፈስ ሳይሆን በራሳችን መንፈስ/ትርጉም/ እንድንሰማቸው ያደርገናል፡፡ በዚህ ምክንያት ሰላማችን ይናጋል፡፡ በዓለም ላይ ቋንቋ የሚገልፀው ነገር ጥቂት ነው፡፡ ነገሮችን ከቋንቋ ይልቅ የሚያብራራልን ቅንነት ነው፡፡ ስሜትን ማመን ተገቢ አይደለም፡፡ ስሜት ዛሬ የሚግል ነገ የሚበርድ ነገር ነው፡፡ ስሜት እውነትነት ይጎድለዋል፡፡ ወቅታዊ የሆነ ሞቅታ ነው፡፡ ወቅታዊ የደስታና የሀዘን ስሜት ነው፡፡ ደስታውንም ሆነ ሀዘኑን በእውነት መመዘን ያስፈልገናል፡፡ ስሜት የእውነትን ቦታ ከያዘ ኑሮአችን የተዘባረቀ ይሆናል፡፡ ከሚሰማን ነገር ተነሥተን ሰዎችን ስንናገር ያልወለዱትን ልናሳቅፋቸው፣ ያላሰቡትን ልናሳስባቸው እንችላለን፡፡ የብዙ ሕብረቶች መደፍረስ ምክንያቱ ይህ ነው፡፡ ሰው ለስሜት ድምፅ ሰፊ ቦታ መስጠቱ ነው፡፡ “ልቤ ሲጠራጠር እንዲህ ሊሆን ነው፣ ትከሻዬን ሲከብደኝ እገሌ ሊከዳኝ ነው” የሚሉ ማረጋገጫዎችን መጠቀም በጣም ከባድ ነው፡፡ ስሜታችንን አምነነው ከሰዎች ጋር በቍጣ መንፈስ እንገናኛለን፡፡
         እንኳን የተሰማንን የሆነውን ነገርም መመልከት የሚገባን በፍቅርና በእውነት ነው፡፡ አሊያ ስሜትን ማመን የሌለውን ነገር ወደ መኖር አምጥተን እንድንለያይ ያደርገናል፡፡ በመጨረሻም ሰዎቹ በሚሰጡን የአፀፋ ምላሽ ውስጥ እንደበቃለን፡፡ ቀድሞም ለካ የተሰማኝ ልክ ነበር ወደሚል እሳቤ እንደርሳለን፡፡ ይህም አሳብ ከይቅርታ ያዘገየናል፡፡ ያልተጨበጠ ስሜት የተጨበጠ ችግርን በዓለም ላይ ያመጣል፡፡
         ታዲያ ይህንን የስሜት ድምፅ የምናስተካክለው በወዳጅ ድምፅ ነው፡፡ ያ ወዳጅም እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ ዓለም ለመኖር የሚረዳ ንጹሕ አየር የሌለው የታፈነ ዓለም ነው፡፡ ወደዚህ ዓለም ስንቀላቀል በማለዳ የወዳጅን ድምፅ መስማት ይገባናል፡፡ የወዳጅ ድምፅ ለመኖር የሚረዳ አዲስ አየር ነው፡፡ ያም ወዳጅ እግዚአብሔር ነው፡፡ ድምፁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀምጦልናል፡፡ ቃሉን ስንሰማና ስናነብ ቀኑን በተስፋና በብርታት እንጀምራለን፡፡ በእምነትና በሥርዓት ካጠናነው ደግሞ ለቀኑ የሚሆን መረጃና መልስም በቃሉ ውስጥ እናገኛለን፡፡
         ሥጋዊውን ተግባር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊውን ተግባር ከማከናወናችን በፊት የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና መስማት ያስፈልገናል፡፡ የቀኑ ተግዳሮት ያለ መንፈሳዊ ኃይል የሚዘለቅ አይደለም፡፡ አዎ የወዳጅ ድምፅ ብርታት ይሰጣል፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ነው፡፡
ወዳጅ፣ ወዳጅ ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን የሚወዱን ሰዎች እንዳሉ እርግጠኞች ነን፡፡ ማየት ያለመቻል ካልሆነ በቀር እግዚአብሔር ሰውን ያለ ሰው አልተወዉም፡፡ ስለዚህ ጉልበታችን ሲዝል፣ ትጥቃችን ሲላላ የሚወዱንን ሰዎች ድምፅ እንስማ፡፡ ያን ጊዜ በፍቅር ኃይልን እንሞላለን፡፡ የወዳጅ ድምፅ ያድሳል፡፡ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ