መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የወገናችን የዓለም ደቻሳ የውርደት ሞት የሀገራችን ስብራት፣ ሐዘንና ዋይታ ነው፡-

የትምህርቱ ርዕስ | የወገናችን የዓለም ደቻሳ የውርደት ሞት የሀገራችን ስብራት፣ ሐዘንና ዋይታ ነው፡-

ኢትዮጵያ፣ እናታችን፣ እማማዬ የልጆችሽ  ዕንባና ዋይታ የሚታበሰው መቼ ይሆን. . . !?
‹‹. . .ዓይኔ በዕንባ ደከመ፣ አንጀቴም ታወከ፡፡ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ አንጀቴ በምድር ላይ  ተዘረገፈ፡፡ አቤቱ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ. . .፡፡›› (ሰቆ ፪፣፲፩ ፤ ፭፣፩) ፡፡

                                                                       ረቡዕ፣ መጋቢት 19 2004ዓ.ም

ይህን ቃል የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ዘንድ ‹‹አልቃሻው ነቢይ›› በመባል የሚታወቀው አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ ነው፡፡ ይህንን ነቢይ እንዲህ እንደ ርኁሩኋ እናት አንጀቱን ያላወሰው፣ ዕንባው እንደ ክረምት ጎርፍ እንዲፈስ ያደረገውና ነፍሱ ድረስ ዘልቆ ብርቱ ሐዘንና ቅጥቃጤን የፈጠረበት ኢየሩሳሌም በጠላቶቿ ተማርካ፣ ሕዝቦቿም ተዋርደው፣ ከአገራቸውና ከምድረ ርስታቸው ተነቅለው፣ መቅደሳቸው ፈርሶ በግዞት የነበሩትን የሕዝቡን ሰቆቃና መከራ በዓይኑ በማየትና የመከራቸውም ተካፋይ በመሆኑ ነበር ይህንን የሐዘን እንጉርጉሮ ሙሾ ያወረደው፡፡ ጸሎተኛውና ሐዘንተኛው ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም ኃጢአትና በደል በዚህም ስለደረሰባት ከባድ ውርደትና መከራ ዓይኔ ምነው የዕንባ ምንጮች በሆኑልኝ በማለት የተመኘ፣ የጸለየና የማለደ የሀገሩ፣ የሕዝቡ ውርደት፣ ጭንቀትና መከራ እንቅልፍ የነሣው ብርቱ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር፡፡
ከራብ የተነሳ እናቶች የአብራካቸውን ክፋይ ልጆቻቸውን የበሉበትን፣ በቅምጥልነት የኖሩ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅትና ደናግላን በጠላቶቻቸው ብርቱና ጨካኝ ክንድ ከሰውነት ክብር ተዋርደው፣ ከመፈራትና ከመወደድ ሰገነት ተሸቀንጥረው፣ ተንቀውና ተጥለው በጎዳና ያለ ምንም ተስፋ ሲንከራተቱና የአሕዛብ መጫወቻና መላገጫ ሲሆኑ፣ ሕፃናት በእናቶቻቸው ደረቅ ጡት ላይ አፋቸው ተጣብቆ በጣእረ ሞት ተይዘው ሲጨነቁ፣ አባቶችና እናቶች የጥንቱን የበረከትና የድሎት ኑሮአቸውን እያሰቡ ዕንባ ሲቀድማቸው፣ ከክፉ ጠኔ የተነሳ ወላዶች የማሕፀናቸውን ፍሬ እንኳን ለመብላት ያስጨከናቸውን ያን ክፉ ቀን የታዘበ ነቢዩ ስለ ቅድስት ምድሩ እና ሕዝቡ ሰቆቃ ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጎበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል ዕንባን ታፈሳለች፡፡›› (ሰቆ ፫፣፵፱፣፶) በማለት በመጮኽና በመቃተት ሌት ተቀን በዕንባ ባሕር እንደዋኘ ውሎ የሚያድር ሐዘንተኛ ነቢይ ነበር፡፡

ከሰሞኑ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ነቢይ ኤርምያስ አንገታችንን የሚያስደፋና በሐፍረት የሚያሸማቅቅ፣ የወላዶችን አንጀት የሚያላውስና በዕንባ እንዲታጠቡ የሚያደርግ ሌላ የሞት፣ ሌላ የውርደት፣ ማብቂያ የሌለው የሚመስል መሪር የሆነ የመርዶ ዜና ከወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተሰምቷል፡፡ ሰሞኑን በሊባኖስ የምትሠራ አንዲት ኢትዮጵያዊ በአሠሪዋ መንገድ ለመንገድ ሰብአዊነት በጎደለው ሁኔታ እየተጎተተች ያውም በሀገሯ ኤምባሲ ፊት ለፊት ጥቃት ሲፈጸምባት በሊባኖስ ቲቪ ለዓለም ሁሉ ታይቶ ነበር፡፡ ይህም ዜና በሊባኖስ ያሉ ወገኖቻችንና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችንና ድርጅቶች መካከል ትልቅ ቁጣን የቀሰቀሰ ነበር ሲል ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በቤት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸሙ የግፍ ተግባራትን ለማስቆም የሚሰራው KAFA የተባለ ተቋም የፕሮግራም ኮርዲኔተር የሆኑት ሮላ አቢሞርችዴ፡- ‹‹በሊባኖስ ውስጥ በቤት ሠራተኞች ላይ ግፍ መፈጸም እጅጉን የተለመደ ነው፡፡›› ኢትዮጵያዊቷ ዓለም ደቻሳ በሊባኖስ ሕይወቷን ያጣች የመጀመሪያዋ ሴት አይደለችም ያሉት አቢሞርችዴ እ.ኤ.አ ከ1997-1999 ዓ.ም ባሉት ሁለት ዓመታት ብቻ 67 ኢትዮጵያውያን ሴቶች በቤይሩት በሥራ ላይ እያሉ ዘግናኝ በሆነና ሰብአዊነት በጎደለው ሁናቴ ለሕልፈት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የዚህች ወገናችን ዘግናኝ ወሬ ገና ባልደበዘዘበት ሁኔታ ከአሠሪዋ ዘንድ በደረሰባት በደልና እንግልት የተነሣ ተስፋ ቆርጣ ወደ ሀገሯም መመለስ እንደማትፈልግ ገልጻለች ተብሎ በተዘገበ ማግሥት ይህችው ምስኪን እህታችን ራስዋን የማጥፋቷ ሌላው የባሰ ዜና በዛ ያሉ ወገኖቿንና ወሬውን የሰሙትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሐዘን ያባባሰና አንገት ያስደፋ እንደሆነ በዚህች ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰው ግፍና እንግልት ዳግም በሊባኖስና በሌሎች ዐረብ ሀገራት በስደት የሚገኙ ዜጎችን ሰብአዊ መብት በተመለከተ ሲካሄድ የነበረውን ውይይት እንደ አዲስ እንደቀሰቀሰውም ዴይሊ ማቭሪክ የተባለ ለብዙ ኢትዮጵያውን ወጣት ስደተኞች እንደ ከነዓን ምድር በምትቆጠረው በደቡብ አፍሪካ የሚታተም ጋዜጣ በሰፊው ዘግቧል፡፡
እንደ አንዳንድ መረጃዎች ይህችን እህታችንን ጨምሮ በሊባኖስና በሌሎች ዐረብ ሀገራት ብዙ ኢትዮጵያውያን በአሠሪዎቻቸው በሚደርስባቸው፣ እንግልት፣ የመብት ረገጣ፣ የወሲብ ትንኮሳና መደፈር የተነሣ ለሞት እንደሚዳረጉ ይናገራሉ፡፡ ከፎቅ ላይ ተወርውረው ለአሰቃቂ ሞት የሚዳረጉ፣ በሚደርስባቸው የቤት ውስጥ ጥቃት የተነሣ ለአካለ ጎዶሎነትና ለከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ የተዳረጉ እህቶቻችን በርካታ መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ዛሬም የእህቶቻችን መከራ፣ ውርደትና ጉስቁልና የብዙዎች መነጋገሪያ ርዕስ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ቢሮዎችም ችግሩን ለመቅረፍ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንዳለ ቢነግሩንም ከችግሩ ስፋትና እንዲሁም ሴቶቻችንን ወደ ዐረቡ ዓለም በማሻገር እጃቸው ያለበት ሕገ ወጥ ደላሎችና ኤጀንሲዎች የወገኖቻችንን ሰቆቃ በማባባስ ረገድ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። መንግሥት የቱንም ያህል ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ጥረት ቢያደርግም አሁንም ብዙ ወገኖቻችን በአጭበርባሪዎች በመታለል፣ ሕጋዊ እውቅና በሌላቸው ኤጀንሲዎች ነን ተብዬዎች ምክንያት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በመሰደድ ለብዙ እንግልትና መከራ ይዳረጋሉ፡፡
ዛሬም ሴቶቻችን በሚያስደነግጥ ፍልሰት ወደ ዐረቡ ዓለም በገፍ እየተሰደዱ ነው፡፡ ይህን እውነት በዓይኑ ዓይቶ ለማረጋገጥ የሚፈልግ አንድ ማለዳ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ኢሚግሬሽን ቢሮ ጎራ በማለት በመሥሪያ ቤቱ አጥር ዙሪያ ጥምጥም ተሰልፈው የሚያያቸውን ‹‹ስደት ቤቴ›› ብለው የቆረጡ ሴቶቻችንን ብዛት ላየ ሰው ሴቶቻችን በሀገር የቀሩ አይመስልም፣ በእርግጥም የሚያስደነግጥና የነገ የወጣቶቻችን ዕጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ነው ብለን እንድንጠይቅ የሚስገድደን አስገራሚ ትዕይንት ነው በአካባቢው የሚታየው፡፡
በማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሚሠራ አንድ የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ የሆነና እነዚሁን ወደ ዐረብ ሀገራት የሚጓዙ ወገኖቻችን መንግሥት በሚሄዱበት ሀገር ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ግንዛቤ እንዲኖራውቸውና በዛም በሥራቸው ላይ እያሉ ለሚደርስባቸው ማንኛውም ዓይነት በደል አስፈላጊ የሆነ የሕግ ከለላ ለማድረግ የተዘጋጀውን ሥልጠና እና ምክር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ይኸው ወዳጄ እንደነገረኝ በየቀኑ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን በማስተናገድ ትንፋሽ እንዳጡና አብዛኛው እነዚህ እህቶቻችንም ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስማቸውን እንኳን አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ እንደሆኑ በሀዘን ድባብ ውስጥ ሆኖ አጫውቶኛል፡፡
ይኸው ጓደኛዬ እንዳጫወተኝም በዚሁ የሥራ አጋጣሚው ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞች የመጡና በተለያዩ የሙያ መስኮች በሰርተፍኬትና በዲፕሎማ የተመረቁ፣ በእናት ምድራቸው በሚያዩትና በሚሰሙት ተሰፋ የቆረጡ ራሳቸውን ለዐረቡ ዓለም ሥራና የኑሮ ፈተና ያዘጋጁ ወጣት ሴቶች እንዳጋጠሙትና እነዚህን ወጣቶች ለምን በተማሩት ትምህርት በሀገራቸው እንደማይሠሩ ለጠየቃቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፡-
ቤተሰብ ከሕጻንነት ወራት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሚችሉት ዓቅማቸው ሁሉ ተንከባክበው አስተማሩን፣ በኮሌጅ የትምህርት ቆይታችንም የቤተሰብ እርዳታ አልተለየንም፣ ትምህርታችንን ከጨረስንም በኋላ የረባ ሥራ ማግኘትም አልቻልንም፡፡ እንደው ይሁን ከመቀመጥ ይሻላል ብለን የጀመርነው ሥራም ከቤተሰብ ጥገኝነት ለመውጣት የሚያስችለን አቅም አልፈጠረልንም፡፡ ሥራ ያለን የቤተሰብ ጥገኞች ከምንባል እዛው ዐረብ ሀገር ሄደን የፈለገው ነገር ቢሆን ይሻላል፤ ከዚህ ከኢትዮጵያ የተረት ተረት ኑሮ የማይሻል ምንም ነገር የለም፡፡ እንደምታውቀው የሀገራችን ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሰቃቂ ትራጀዲ ወደ መሆን እየተሸጋገረ ነው፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ከአንድ ሺህ ብር በላይ በሚሸጥበት፣ ሁሉም ነገር ጣራ በነካበትና ድህነት በአካል ቆሞ በሚሄድባት በምስኪኗ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በልቶ ማደር፣ ተኝቶ መነሣትም ተረት እንዳይሆንብን ሌት ተቀን በሥጋት የምናልቅ የዓለም ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ  ሕዝቦች እየሆንን ነው፤ ማን አጽናኝ ማን ተጽናኝ እንደሚሆን ግራ ገብቶናል… ወንድማችን ለምክርህ እናመሰግናለን፣ ይልቅስ በጊዜ ለራስህም እወቅበት…፡፡
 በማለት ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ምላሽ እንደሰጡት በሐዘን ተውጦ አጫውቶኛል፡፡
ለመሆኑ እንደ ክርስቲያን እኛና ሕዝባችን ስለምንዋኝበት የውርደት፣ የጉስቁልናና የመከራ ኑሮአችን እንጠይቅና እናስብ ይሆን…? እንደ ነቢዩ ኤርምያስ፡- አቤቱ የሆነብንን አስብ፣ ስድባችንንም ተመልከት… የሚሉ የሃይማኖት አባቶችና አገልጋዮች፣ የምንልስ ምእመናን በዚህ ዘመን እንኖር ይሆን? ለዚህ ሁሉ ውርደታችንና ጉስቁልናችን ተጠያቂውስ ማን ይሆን…? መንግሥታትን፣ ፖለቲካውን፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችንን፣ ተፈጥሮን… የጠየቅንበትና የሞገትንበት ጊዜ የትናንት የቅርብ ትዝታችን ነው፡፡ ዘመን በጠባ ቁጥር ስለ ኢትዮጵያችን ህዳሴ፣ ስለ ሀገራችን ትንሣኤ፣ ስለ ብልጽግናዋ የተስፋ ዋዜማ ሻማ ለኩሰን ዘምረናል፣ ፎክረናል፡፡ ግና መጣ ስንለው እየራቀን፣ ያዝነው ስንለው እያመለጠን ያለው የሀገራችን ትንሣኤ፣ የሀገራችን ህዳሴ፣ የሀገራችን መጎብኘት በእጅጉ እየናፈቀን መሽቶ ይነጋል፡፡ ከዚህም የተነሣ በታላቅ ስብራትና በሰቀቀን ውስጥ ያለን ሁሉም ከንፈሩን የሚመጥልን ሕዝቦች ወደ መሆን ተሸጋግረናል፡፡
እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሀገራችን ደናግላንና ቆነጃጅት መጎሳቆል፣ ውርደትና መከራ ፊታቸው በዕንባ የሚታጠብ፣ ለዚህ ታላቅ ስብራታችን መፍትሔ የሚሆነንን ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያመጡልን ነቢያት አድራሻቸው የት ይሆን? እስከ መቼ በእንዲህ ዓይነት ውርደትና ጉስቁልና ዘመናችን ያልቃል? የዛሬ ሃምሳ ዓመት ራብተኞች ዛሬም  ከሃምሳ ዓመት በኋላ በቀን አንድ ጊዜ በልቶ ለማደር እንኳን በሚያሳዝን የልመና ዜማ ነጋ አልነጋ ብለን የለጋሽ ሀገሮችን በር የምናኳኳና የምንማጠን ምንዱባኖች… እግዚኦ እናት ሀገራችን! እግዚኦ ኢትዮጵያ! የሚያጽናናሽ፣ በደልሽንም በመግለጽ ፈውስሽን የሚያፈጥንልሽ፣ በፈረሰው ቅጥርሽ በኩልስ የሚቆምልሽ ትጉህና ታማኝ የቁርጥ ቀን ሰዎችሽ አድራሻቸው የት ይሆን. . .?
ዘወትር ሌት ተቀን ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ሰዓታቱ፣ ውዳሴው ምስጋናው በማይቋረጥባት ኢትዮጵያችን እንዲህ ዓይነቱ ቅጥ የለሽ፣ የማያባራ የመከራ ውርጅብኝና ዶፍ መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጣን የሃይማኖት አባቶቻችን የሚሉን ነገር ይኖራቸው ይሆን…? ሁላችንም ክርስቲያኖች ቆም ብለን አንድ ጥያቄ መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡- እንዴት ከሚሰማ፣ ከሚያይ አምላክ ጋር እየተነጋገርን እንዲህ በረከታችንና መጎበኘታችን የሰማይ ያህል የራቀብን ሕዝቦች ሆንን?
አሳዛኙ እውነታ ዛሬም የሀገር የነገ ተረካቢና ተስፋ ነው የሚባለው ወጣቱ ትውልድ በድኑ እንጂ መላ እሱነቱ ባሕር ማዶ ከተሻገረ ሰነባብቷል፡፡ እናም ሴት፣ ወንድ፣ የተማረ፣ ያልተማረ ሁሉም የሚያስበውና እንደ ትልቅ አማራጭ አድርጎ የወሰደው ስደትን ነው፡፡ የማህበራዊ ሳይንስና (Sociologists) የምጣኔ ሀብት (Economists) ምሁራንና አጥኚዎች ደካማ የሥራ ባህል፣ የበዓላት መብዛት ስንፍናችን ላለማደጋችን ምክንያት ናቸው በማለት በጥናት ጽሑፋቸው ይገልጻሉ፡፡ ግና ክርስቲያን የትጋት፣ የታታሪነት፣ የተስፋ ሕይወት ባለቤትና ብርቱ ሠራተኛ ሕዝብ እንደሆነ የእምነት መጻሕፍቶቻችን በሚገልጹበት እኛ ክርስቲያኖች እየኖርነውን ያለውን ሕይወት በመመርመር እንዴት ለራሳችን ብሎም ለሀገራችን ብልጽግና እና እድገት የረባ ድርሻ ሳይኖረን ሊቀር ቻለ የሚለውን የዘመናትን ጥያቄ ለመጠየቅ ጊዜው አሁን ይመስለናል፡፡
ለዘመናት እንደ መዥገር ለተጣበቁብን ችግሮች እኛ ክርስቲያኖች የመፍትሔ አካል መሆን ካልቻልን የክርስትናችን ትርጉሙ ምንድነው? እንደ ክርስቲያን የእህታችን የዓለም ደቻሳና የሌሎችም ወገኖቻችን ውርደትና ጉስቁልና፣ የሀገራችንና የሕዝባችን መከራና እሮሮ ለእኛ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ የጸሎት ርዕሳችንና ወደ ጸባዖት የምናነባበት ጉዳያችን ካልሆነልንና እኛም እንደ ሌሎች ለአንድ ሰሞን ብቻ ጉድ ጉድ ብለንና ከንፈራችን መጠን የምናልፍ ከሆንን የሃይማኖታችን ራስና ፈጻሚ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን የፍቅር ሕይወት እየኖርነው አይደለንምና ክርስትናችን በትልቅ ጥያቄ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ 
በሌላም በኩል አስገራሚው ነገር ቀኑን ሙሉ ከነመፈጠራችን ስለማያውቁን የአውሮፓ ተጫዋቾች ሳምንታዊ ደመወዛቸውን፣ ስለበሉትና የጠጡት የምግብና የመጠጥ ዓይነት፣ ስለ ገቡበት ሆቴል፣ ስለተዝናኑበት መዝናኛ ስፍራዎች ሰፊና ዝርዝር መረጃዎችን ሲያደርሱን የሚውሉትና ያልበላንን የሚያኩልን የሀገራች መገናኛ ብዙኃኖች/ በተለይም ኤፌሞቻችን ምናለ እንዲህ ዓይነቱን ዜና በሰፊው በመዘገብ ለሕዝብ አጋርነታቸውን ቢያሳዩ፡፡ ትውልድ ከሞራል ውድቀት፣ ስንፍና እና ከስደት ሕይወት የሚወጣበትን፣ ወጣቱ ለመልካምና ለበጎ ሥራ የሚነሣሣበትን ትምህርት ሰጪ መልእክቶችን ትልቅ ትኩረትን ችረው ደግመው ደጋግመው ቢያስደምጡን፡፡ ይህ ክስተት የመገናኛ ብዙኃኖቻችን የአንድ ቀን ዜና፣ የደቂቃዎች ወሬ ብቻ ሆኖ ማለፍ ያለበት ነበር እንዴ?! እንደ ኢትዮጵያዊ፣ እንደ ዜጋ በእህታችን ላይ የደረሰው ግፍና መከራ የሁላችንም ውርደት፣ የሁላችንም ሐዘንና የልብ ስብራት ነበር እኮ?!

ለእህታችን ለዓለም ደቻሳ ቤተሰቦችና የሐዘናቸው ተካፋዬች ለሆናችሁ ሁሉ መጽናናቱን ይስጥልን ለማለት እንወዳለን፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም