የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዓድዋ ድልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን አስተዋጽኦ

በዲ/ን ኒቆዲሞስ         ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ የካቲት ፳፫ ቀን ፪ ሺ ፰ ዓ.ም. እትም
የዓድዋ ጦርነት ከመካኼዱ አምስት ዓመት በፊት አለቃ ለማ ኃይሉ በአዲስ አበባ ሥላሴ ቤ/ን የሐምሌ ሚካኤል ዕለት፣ የሚከተለውን ትንቢታዊ ቅኔ መቀኘታቸውን ልጃቸው- ደማሙ ብዕረኛ መንግሥቱ ለማ፣ ‹‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ›› በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፡፡ ቅኔው እነሆ፡-
ምኒልክ ግበር ላዕለ ሮምያ/ሮማ መጠነ እዴከ ትክል፣
አምጣነ ለአጺድ በጽሐ ማእረራ ወመዋዕሊሃ ለኃጉል፣
ዓዲ ተዘከር ውስተ ወንጌል፣
ላዕለ ሮምያ በለስ ኢሀሎ አስካል፣
ከመ ይቤ ወልደ ያሬድ ቃል፡፡
ትርጉም፡- ምኒልክ በሮማ ላይ እጅህ እንደቻለ መጠን አድርግ፣
መከሯ ለመታጨድ፣ ቀኗም ለጥፋት ቀርቧልና፡፡
ዳግመኛ በወንጌል ያለውን አስብ፣
በሮምያ/በበለስ ላይ ፍሬ የለም እንዳለ ወልደ ያሬድ/ቃል (ወልድ)፡፡ ብዬ ፲፰፻፹፫ ተቀኘኹ፡፡ ምኒልክ በቤተስኪያን የሉም ይኸ ሲባል፡፡ ይኸ ጥንቆላ ነው፤ ያድዋ ጦርነት ሳይደረግ ነው፡፡ ኸጣልያን ጋር ስምም ናቸው ያን ጊዜ አጤ ምኒልክ፡፡ አለቃ ወልድ ያሬድ መልካም መልካም!አሉና፣ እሑድን ዋልነ፡፡ ሰኞ ጉባዔ አለ፤ አለቃ ተጠምቆ ናቸው እሚያኼዱ፡፡ አለቃ ወልደ ያሬድ እርሳቸው እልፍኝ አጠገብ ቤት ሰጥተውናል፡፡ እርሳቸው መጥተው ይቀመጣሉ ኸጉባዔ ለመስማት፡፡
የኔታ ተጠምቆ
አቤት!
ኸኒያ ክፉዎች ጋር እኮ ጠብ ላይቀርልን ነው አሉ፡፡
እንግዴህ ትግሬ ናቸው አለቃ ተጠምቆ እነ ራስ አሉላ፣ እነ ራስ መንገሻ አሉ ኸኒያ መስሏቸው፤
ኸነማን ጌታዬ? ኸነማን? አሉ ደንግጠው አለቃ ተጠምቆ፡፡
ኸነጮቹ
ምነው፣ ምነው? አሉ፡፡
እንዴ! የልጅዎን ቅኔ በቀደም አልሰሙትም?
በለማ ቅኔ ሆነ እንዴ ጦርነት?! አሉ አለቃ ተጠምቆ፡፡
አናጋሪው ማን ይመስልዎታል? አሉ፡፡
አለቃ ለማ በዚኹ ቅኔያቸው እንደተነበዩትም ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ ታወቀ፣ ተረጋገጠ፡፡ አለቃ ለማ በቅኔያቸው እንደተነበዩትም በዓድዋ ግንባር ሮማ/ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ጀግኖች አማካኝነት ታላቅ ውርደትንና ሽንፈትን ተከናነበች፡፡ ያ ሽንፈትም ዓለምን ኹሉ ያሰደነቀና የአውሮፓውያንን ቅኝ ገዢ ኃይሎችን ያሸማቀቀ ድል ነበር፡፡
ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ኪነ-ሕንፃ፣ ሥነ ጽሑፍወዘተ ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለ ነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ናት፡፡
ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ አገር ክብር፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው፡፡ እናም ይህች ጠንካራ ሃማኖታዊ ተቋም መምታት ለብዙዎቹ የአገሪቱን የነፃነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤ/ን ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነጻነቱና ሰብአዊ ክብሩ ቀናኢ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች መኾኗ በታሪክ ድርሳናት የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡
ከዚህ የታሪክ ዕውነታ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ቤ/ን በዓድዋው ጦርነት ከክተት ዘመቻ ጥሪው አንስቶ እስከ ጦርነቱ ፍልሚያና ድሉ ድረስ ደማቅ አሻራ አለበት፡፡ የዓድዋው ጦርነት ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዢ ኃይሎችና ለጦርነቱ ታዛቢዎች በታላቂቱና ጥንታዊቷ ሮማ እና በአፍሪካዊቷ ብቸኛ ነፃ አገር፣ ‹ድኃና ያልሰለጠነ ሕዝብ› የሚኖርባት ተብላ በምትቆጠረው አቢሲኒያ፣ በሮማ ካቶሊክና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን መካከል የተደረገ የኃይል ሚዛንን ያልጠበቀ ጦርነት ተደርጎ ነበር የተቆጠረው፡፡
ይህን የሁለቱ አገራት ፍጥጫና የዓድዋው ጦርነት ብዙዎችን፡- ግዙፉ ጎልያድና ብላቴናው ዳዊት በጦር ግንባር የተፋጠጡበትን፣ የአይሁዳውያኑንና የፍልስጤማውያኑን የጦርነት ታሪክን ከቅዱስ መጽሐፍ ዞር ብለው እንዲያስታውሱ የተገደዱበትን አጋጣሚ የፈጠረ፣ ዓለምን ሁሉ ያስደመመ፣ የቅኝ ገዢ ኃይሎችን ደግሞ አንገት ያስደፋ ታሪካዊ ጦርነት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡
ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው የጎበኙ አያሌ የውጭ ሀገራት ተጓዦች፣ አሳሾችና የታሪክ ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕዝቦቿ በጋራ የሚመሰክሩትና የሚስማሙበት አንድ እውነት አለ፡፡ ይኸውም፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፡፡›› የሚል ነው፡፡
በአንድ ወቅትም ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ እ.ኤ.አ ፲፱፻፷፫ አክሌዥያ በሚባል በፓሪስ ከተማ ለሚታተም ጋዜጣ፡- ‹‹የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቃላችሁን?!›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-
‹‹…ኢትዮጵያ ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነፃነቷን መልሳ አግኝታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ-ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡
ከሁለት ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ ቆይታለች…፡፡›› በማለት ጽፏል፡፡
ይኽችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በዓድዋው ጦርነት ወቅትም ለጦርነቱ ዘመቻ የክተት ጥሪ ከማስተላለፍ ጀምሮ በተለያዩ የጦርነት ዓውድ ግንባሮች ሁሉ ላይ ሣይቀር በመሳተፍ ጭምር ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ አደራዋን ተወጥታለች፡፡
በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ ነው በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በሚሊተሪ ሳይንስ ከሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ጋር ለመጋጠም ‹‹ስንቁን በአህያ ዓመሉን በጉያው›› አድርጎ፣ የኢትዮጵያን አምላክ ተስፋ አድርጎ ወደ ጦርነቱ የተመመው፡፡
ዐፄ ምኒልክ ሠራዊታቸውን ክተት ብለው ወደ ዓድዋ የዘመቱት የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት፣ ሊቀ ጳጳሱን ግብፃዊውን አቡነ ማቴዎስን፣ በርካታ ካህናትንና መነኮሳትን ጭምር አስከትለው ነበር፡፡ የዓድዋን ጦርነት በሰፊው የዘገቡ የውጭ አገራትና የአገር ውስጥ ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች እንደጻፉትም፡-
በጦርነቱ ቀን ብዙ መነኮሳት የሰሌን ቆባቸውን እንደደፉ፣ ወይባ ካባቸውን እንደደረቡ የቆዳ ቀሚስ ለብሰው ግማሹ ከንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ፣ ግማሹ ከእቴጌ ጣይቱ ዘንድ የቀሩትም በተዋጊው መኳንንትና ወታደር ዘንድ ሆነው ወዲያና ወዲህ እየተላለፉ ሊዋጋ ወደ ጦርነቱ የሚገባውን እያናዘዙና ከጦርነቱ ሊሸሽ ያለውንም እየገዘቱ፣ ሲያበራቱና ሲያዋጉ መዋላቸውን ጽፈዋል፡፡
የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ትዕዛዝ የሆኑት አለቃ ገ/ሥላሴ በዓድዋ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ ስለ ዓፄ ምኒልክ ታሪክ በፃፉት መጽሐፋቸው እንዲህ በሥዕላዊ መንገድ አስቀምጠውታል፡፡
ንጉሡ ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲደርሱ አቡነ ማቴዎስና የማርያም ታቦት የያዙት ካህናት በኋላቸው ነበሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱም ከዘበኞቻቸውና ከሠራዊቱ ጋር ሆነው በአቡነ ማቴዎስና በታቦቷ ጎን ነበሩ፡፡ የአክሱም ካህናት ቅዳሜ ማታ እንደ ጥንቱ አስተዳድሩን ብለው ለንጉሡ ለማመልከት መጥተው አድረው የነበሩት፣ በዚህን ጊዜ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕልና ሰንደቀ ዓላማ ይዘው በእቴጌ ጣይቱ ግንባር ተሰልፈው ነበር፡፡
የጽዮን እምቢልተኞችም መለከታቸውንና እምቢልታቸውን እየነፉ በእቴጌይቱ ፊትና በሠራዊቱ ፊት ይጫወቱ ነበር፡፡ … ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ ይላሉ አለቃ ገ/ሥላሴ ከሌሊቱ ፲፩ ጀምሮ እስከ ፬ ሰዓት ድረስ ተኩስ ሳያቋርጥ ከሁለቱም ወገን ሲተኮስ ድምፁ እንደ ሐምሌ ነጎድጓድ፣ ከተኩስም የሚወጣውም ጢስ የተቃጠለ ቤት ይመስል ነበር፡፡
በዚህ ቀን በዓድዋ በዓይናችን ያየነውንና በጆሮአችን የሰማነውን ለመጻፍ ችግር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው በጋለ ጸሎት ወደ ኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር፡፡ በማለት ጽፈዋል፡፡
በሌላ በኩል ታዋቂው ታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ ‹‹ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፡-
እቴጌ ጣይቱ በተፋፋመው የዓድዋው ጦርነት ውስጥ ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮች ታጅበው በጦርነቱ መካከል መገኘታቸውን ጽፈዋል፡፡ አቡነ ማቴዎስም የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ በፊት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን ጽፈዋል፡፡
ኢጣሊያዊው ጸሐፊና የታሪክ ምሁር ኮንቲ ሩሲኒም ስለ ዓድዋው ጦርነት ውሎ ሲመሰክርም፡-
ከልዩ ልዩ ምንጭ እንዳገኘሁት፣ ከሐበሾችም ጽሑፍ እንደተረዳሁት፣ ጦርነቱ ሲጀመር ዓፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ሌሎችም የጦር ሹማምንትና መሳፍንቱ ሁሉ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ጀምሮ በዓድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያስቀድሱና በጸሎት ሲማጸኑ ነበር…፡፡ ሲል ስለ ዓድዋ ጦርነት በተወው ማስታወሻው ላይ አስፍሮታል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓድዋው የጦር ግንባርና በአጠቃላይ በአገራችን ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ያበረከተችው ጉልህ አስተዋጽኦ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ አሜሪካና በመላው ዓለም ድረስ ዘልቆ የተሰማና ዕውቅና የተሰጠው ነው፡፡ ይህን የሚያረጋግጡ አንዳንድ ታሪካዊ ሰነዶችን እንፈትሽ እስቲ፡፡
አሜሪካዊው የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁር እና በኢትዮጵያ ዙሪያ ሰፊ የኾነ ምርምርና ጥናት ያደረጉት ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን በተለይ ደግሞ በብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን ዘንድ ‹Wax and Gold› በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው የሚታወቁት እኚህ ምሁር ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት ጎሳ፣ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለዩ፤ ወንድ፣ ሴት፣ ቄስ፣ መነኩሴ ሳይባል ተባብረው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበትን ጦርነት በጸሎት ተጋድሎና በማስተባበር ያደረገችው ተሳትፎ በአፍሪካና በመላው ጥቁር ዓለም ልዩ ስፍራና ክብር ሊያሰጣት እንዳቻለ The Battle of Adowa as Historic Event› በሚለው ጥናታዊ ጹሑፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-
For a number of colonized African countries, the Ethiopian victory at Adowa symbolized and signaled the possibility of the future emancipation. Hence the Black South African of the Ethiopian Church came to identify with the Christian kingdom in the Horn, a connection that leads South African leaders to write Menelik for help in caring for the Christian communities of Egypt and the Sudan.
አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይ፣ አርበኛ፣ የዓለም የሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆኑት ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ ስለ ዐድዋ ድል፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በኋላም በአገራቸው በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነፃይቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስምና ጥላ ስር የተቀጣጠሉ የፀረ-ቅኝ ግዛትና የጸረ-አፓርታይድየነፃነት እንቅስቃሴዎችን በማስመልከት ከእስር በተፈቱ ማግሥት በደቡብ አፍሪካ በነጻነት የኢትዮጵያ ቤ/ን ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው፡-
Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. …The Adwa victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.
(Nelson Mandela, Speech to the Free Ethiopian Church of South Africa)
በዚህ በዐድዋ ጦርነት በወራሪው የኢጣሊያ ጦር ላይ ኢትዮጵውያን የተጎናጸፉት ድል በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ትልቅ የሆነ ኩራትንና ጽናትን ፈጥሮ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አስቀድሞ ክርስትናን የተቀበለችና በተደጋጋሚም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰች ሀገር በመሆኗ ደቡብ አፍሪካውያን ከአውሮፓውያን እምነት ይልቅ ጥንታዊና ሐዋርያዊ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለመከተልም ወሰኑ፡፡
ይህን የታሪክ ሐቅ አስመልክቶ በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ፪ሺ ፪ዓ.ም. በሕግ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሆኑት ታቦ እምቤኪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ- ለጥቁር ሕዝብ በተለይም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን የነፃነትና የፀረ-አፓርታይድ ትግል ትልቅ ኩራትና መነቃቃት የፈጠረች መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር፡-
…The Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church ….
የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕ/ት ታምቦ ኢምቤኪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለ አገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የነጻነት ታሪክና በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ቤ/ን ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ያደረገችውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ያደረጉት ንግግራቸውን የአማርኛ ትርጉም በጥቂቱ ቀንጭቤ ላስነብባችኹ፡-
ዘመናዊው የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ የመነጨው ወደ ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ነበር፣ የዚህ ንቅናቄ የቀድሞ መስራቾች የሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ አፍሪካውያ ልሂቃን ናቸው፤ የተነሱትም ከአብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ነበሩ፡፡
እነዚህ ዘመናዊ የአፍሪካ ልሂቃን ከአውሮፓውያን ሚስዮኖች እራሳቸውን አላቀው በቤተክርስቲያናቱ ላይ ባለቤትነታቸውን ሲያውጁ፣ እንደመነሻ የተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፰ ላይ ይገኛል፤ ይህም፡- ‹‹መኳንት ከግብጽ ይመጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡›› የሚለው ነው፡፡
እንደ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቀድድም ሰለባ ሆና በኖረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መነሳሳትን ይሰጣቸው ነበር፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተተነበየው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ስትዘረጋ ቤተክርስቲያናችን በአፍሪካዊ ስነ ምግባር ትሞላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡
ይህች እውነተኛ የአፍሪካ ቤተክርስቲን ደግሞ አፍሪካያን በሙሉ ነፃነታቸው፣ ባህላቸው፣ ልዑላዊነታቸው፣ ማንነታቸውና ሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡
ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሀቅ ላይ ተመስርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት እራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡ በአህጉራችን ላይ የመጀመሪያው ዘመናዊ የብሔራዊ ንቅናቄ የሆነው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ANC) የተወለደውም ከነዚሁ ከሀገራችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው. . . ፡፡
ከዓድዋ በፊትም ኾነ ከዓድዋ በኋላ የተደረጉ የነጻነት ተጋድሎዎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለዩ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወታደር፣ ገበሬ፣ ካህን፣ መነኩሴ … ሳይባል ሁሉም የተሳተፉበት ነው፡፡ የድሉ መንሥዔም ይኸው የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ አንድነትና ልዩ ኅብረት ነው፡፡ ከዓድዋው ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ለውጭ አገራት ወዳጆቻቸውና መንግሥታት በፃፉትም ደብዳቤያቸውም፣ ድሉ ከእግዚአብሔር ዕርዳታና ኃይል የተገኘ እንደሆነ ከመግለፃቸውም በላይ የክርስቲያኖች ደም በከንቱ ስለ መፍሰሱ የተሰማቸውን ኀዘኔታም በመጋቢት ፳፫ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-
… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ ዕርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡
ዐፄ ምኒልክ ለሞስኮብ ንጉሥ ኒቆላዎስም በላኩት ደብዳቤያቸውም፡-
እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…፡፡ በማለት ድሉ ከኢትዮጵያ አምላክ ዘንድ የተገኘ መኾኑን ጽፈውላቸዋል፡፡
በዓድዋው አንጸባራቂ ድልም ኾነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ኢትዮጵውያንን ሁሉ በማስተባበር የተጫወተችው ሚና እጅግ ታላቅ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ አንጸባራቂ በኾነው በዐድዋ ግንባር- ከዘመቻው ጀምሮ እስከ ጉዞውና ጦርነቱ በኋላም በድሉም ወቅት ውስጥ የነበራት ደማቅ አሻራና ጉልህ ድርሻ ሁልጊዜም ታሪክ የሚያስታውሰውና የሚዘክረው ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ሕያው የታሪክ ቅርስ ነው፡፡ ሰላም!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ