የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጸሎት ቤት የንግድ ቤት ሲሆን

“በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ”/ዮሐ. 2፡14/፡፡
ጌታችን በፋሲካ በዓል ወደ ቤተ መቅደስ እንደ ገባ የሚናገር ክፍል ነው፡፡ በቤተ መቅደስም የሚገኙትን ሻጮችና ለዋጮች እንዳስወጣ ይናገራል ፡፡ ስለዚህ ጌታችን በአገልግሎቱ የቤተ መቅደስ ነጋዴዎችን ያስወጣው ሁለት ጊዜ ነው ፡፡ የመጀመሪያው በሠላሣ ዓመቱ ሲሆን ሁለተኛው በሠላሣ ሦስት ዓመቱ ነው ፡፡ የአገልግሎቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ ቤተ መቅደሱን አጽድቷል ፡፡ በዚህም ቤቱ የእርሱ መሆኑን ተናግሯል ፡፡ እንደ ፈለጉ ለመሆን ቤቱ የእነርሱ አይደለም ፡፡ የቤቱ ባለ መብት እርሱ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የእኛ ቤት ሲመስለን የሚከሰቱ ነገሮች አሉ ፡፡ የመጀመሪያው ከመጠን በላይ መጨነቅ እንጀምራለን ፡፡ ጭንቀት መልካምነት ቢመስልም ግን አለማመን ነው ፡፡ የመሥራት ጉልበትንም የሚይዝ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ቤቱን አይተውም ፡፡ ሁለተኛው የእግዚአብሔር ቤት የእኛ ሲመስለን የራሳችን የንግድ ስፍራ እናደርገዋለን ፡፡ ሕዝቡንም እንደ ደንበኛችን እንጂ እንደ ወገናችን ማየት ያቅተናል ፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የራሳችን ቤት ሲመስለን በሚገጥመን ጭንቀት መረጋጋት አግኝተን መጸለይና ቃሉን ማሰላሰል አንችልም ፡፡ ስለዚህ የሌሎችን ስንፍና ማየት ይህ ደመወዝ ይህ ጥቅም አይገባቸውም የሚል ጥላቻና ክስ ውስጥ እንገባለን ፡፡ ለእግዚአብሔር ያለነው እኛ ብቻ መስሎ ይሰማናል ፡፡ በዚህ ድካምም እግዚአብሔርን ማማረር እንጀምራለን ፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የራሳችን የንግድ ስፍራ ሲመስለን ጨካኞችና ገንዘብ ያልሰጠውን የምንጸየፍ እንሆናለን ፡፡ ሁለት ዓይነት ወንበርም በማዘጋጀት የሰጡትን የቤተ እግዚአብሔር ዋልታ ፣ ያልሰጡትን ቢሄዱም የማያጎዱ አድርገን እንመለከታለን፡፡
በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የነበሩት ሻጮችና ለዋጮች ጸጥታውን አጥፍተውት ነበር ፡፡ በዚህ የበሬዎች ግሣት ፣ በዚህ የበጎች ጩኸት ፣ በዚህ የገንዘብ ለዋጮች ክርክር አምልኮውን ልማዳዊ ብቻ አድርጎት ነበር ፡፡ ሰው ከልቡ ሁኖ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት አልቻለም ነበር ፡፡ የቤተ መቅደሱም ንጽሕና በከብቶቹ ሽታ ተበክሎ ነበር ፡፡ ይልቁንም የፋሲካን በዓል ለማክበር ከመላው ዓለም ያሉ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበርና ምን ዓይነት ግርግር እንዳለ ከግምት በላይ ነው ፡፡ በሬዎቹና በጎቹ የባለጠጎች መሥዋዕት ሲሆኑ ርግቦቹ ደግሞ የድሆች መሥዋዕት ናቸው፡፡ ባለጠጎችም ሆኑ ድሆች ጠብታም ቢሆን ደም ማፍሰስ ነበረባቸው ፡፡ ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና /ዕብ. 9፡22/፡፡ እግዚአብሔር አምልኮንና ስርየትን በመሥዋዕት ያደረገው ለምድነው ስንል፡-
1-  መሥዋዕት ከባከነ በኋላ መልሶ ጥሬ ዕቃ መሆን አይችልም ፡፡ እውነተኛ አምልኮም ለእግዚአብሔር የሰጡትን ዳግም አለመቀበል ነው ፡፡ አሳብንና ጭንቀትንም ከሰጡ በኋላ መልሶ አለመቀበል ይህ የእምነት መሥዋዕት ነው ፡፡
2-  የሰው ልጅ ከበደል በኋላ ቤዛ ያስፈልገዋል ፡፡ ለምሳሌ በገነት ሳለ ምግቡ አትክልት ነበር ፡፡ ከበደል በኋላ ግን ሥጋ መብላት ጀመረ፡፡ ለመኖር እንስሳትን መግደል ጀመረ ፡፡ እንዲሁም በነፍሱ ስርየት ለማግኘት የሚዋሰው ቤዛ አስፈላጊው ሆነ ፡፡ ሰው ዋስ የሚያስፈልገው ባለ ዕዳ በሆነ ጊዜ ነው ፡፡
3-  መሥዋዕት ዋጋ የወጣበት ነገር ነው ፡፡ ኃጢአትም ዋጋ የሚያስከፍል ነው ፡፡ ኃጢአት ዋጋ ማስከፈሉን ተረድተው ጠንቃቃ እንዲሆኑ የሚያስጠነቅቅም ነው ፡፡
4-  መሥዋዕት የሚሆኑት ገድለው የሚበሉ ወይም ሥጋ በል የሆኑት እንስሳት አይደሉም ፡፡ ገዳይ ቤዛ መሆን አይችልምና ፡፡
5-  መሥዋዕት የሚያቀርበው ሁሉም በአቅሙ ነው ፡፡ ስህተቱ የአቅሙን ያህል ነውና ፡፡ አንድ መርዝን ትንሽ እንስሳ ብትበላው መላ አካሏን ይበክላል ፡፡ ያንን መርዝ ትልቅ እንስሳ ቢበላው አሁን በአካሉ ልክ ይበከላል ፡፡ ኃጢአትም መርዝ ነውና የአቅምን ያህል ይበክላል ፡፡ ድሃው በአቅሙ ንጉሡም በአቅሙ ይበከላል ፡፡
6-  እውነተኛው መሥዋዕት የሆነውን ክርስቶስን እንዲያስታውሱና አዳኙ እንዲናፈቅ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ታዟል ፡፡
7-  ለካህናቱ የመሥዋዕቱ ተረፍ ምግብ እንዲሆን አምልኮ በመሥዋዕት ሁኗል ፡፡ ይህ ዛሬም ሳይለወጥ በገንዘባችን እግዚአብሔርን እናመለካለን ፡፡ ያ ገንዘብም ለእግዚአብሔር ሥራና ለካህናት መኖሪያ ይሆናል ፡፡ በዚህ ምክንያት የስርየትና የአምልኮ መንገድ በመሥዋዕት እንዲሆን ታዘዘ ፡፡
መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች ከሩቅ እየነዱ ከሚመጡ በቅርብ ገዝተው ማቅረባቸው ከድካም ይገላግላቸዋል ፡፡ ዓመጸኛን በሬ ፣ ሞኙን በግ ፣ በራሪዋን ርግብ ይዞ ከሩቅ መምጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ የግሪክና የሮማ ገንዘብ ይዘው የሚመጡ ገንዘባቸውን መለወጥ አለባቸው ፡፡ ምክንያም በገንዘባቸው ላይ የጣዖት መልክ ስላለ ያንን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስጦታ አድርጎ ማቅረብ አይፈቀድም ነበር ፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ለዋጮች የግሪክና የሮማን ገንዘብ ሰቅል ወደተባለው ገንዘብ ይለውጡ ነበር፡፡  ይህ ሁሉ የሚሆነው በቤተ መቅደሱ ነው ፡፡ ቤተ መቅደሱ ከአምልኮ ስፍራነት ወደ ገበያ ስፍራነት ተለወጠ፡፡ ገበያውንም በበላይነት የሚመሩት ካህናት ሳይሆኑ አይቀሩም ፡፡ ምክንያቱም በሚሆነው ነገር ግዴለሽ ነበሩና ፡፡ ካህናቱ የቤተ መቅደሱን ጸጥታና ንጽሕና ደግሞም ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው ፡፡ ያለ ማሳሰቢያ ሊያስቡት የሚገባው ተግባራቸው ይህ ነው ፡፡ እነርሱ ግን ከሚሸጠው በሬና በግ ከሚለወጠውም ገንዘብ ቀጥተኛ ነጋዴና ትርፍ ተካፋይ ስለነበሩ ቤተ መቅደሱ ከሰው ቤት ባነሰ ሥርዓትና ሁከት ላይ ይገኝ ነበር ፡፡
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አገልጋዮች በቂ የሆነ ኑሮ ካላገኙ ራሳቸውን ለንግድ ፣ የእግዚአብሔር ቤትንም ለመደብርነት ይጠቀማሉ ፡፡ በዚህ ምክንያት የቤተ መቅደሱ ጸጥታ እየተናጋ ይመጣል ፡፡ ዓለም በብዙ መንገድ ያወከችው ሰው ለማረፍ ሲመጣ ዓለም ቀድማ በእግዚአብሔር ቤት ትጠብቀዋለች ፡፡ አምልኮቱም ጫጫታውን ለመሻር ሲል የበለጠ ጩኸት ስለሚሆን ጆሮን የሚያደነቁር እንጂ ዕረፍት የሚሰጥ አይሆንም ፡፡ በአደባባዩም የሚወራው ስለ ሒሳብ ስለሆነ ሕዝብን ለስድብ ሲያነሣሣ የሰጠውን ገንዘብ የእኔ ብሎ እንዲያስብ በዚህም ከበረከት እንዲራቆት ያደርገዋል ፡፡ የተጨነቀውና ገንዘብ እርካታ ሊሰጠው ያልቻለው ሰው መሄጃ እስኪያጣ ነፍሱ ትጠበባለች ፡፡ በዚህ ጊዜ እንፈውሳለን ይታየናል የሚሉ ጮሌዎች አስተዳደሩን እያወገዙ ይስቡታል ፡፡ እነርሱም ኪሱ እስኪራቆት ካደናገሩት በኋላ እንደ ሸንኮራ መጥጠው ይጥሉታል ፡፡ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምረው ማኅበራዊ ቀውስ ማንም ሊያበርደው የማይችል ይሆናል ፡፡ ልብ አድርጉ ጌታችን በቅንዓት ተነሥቶ ገበታውን ሲገለብጥ ሣንቲሙን ሲደፋ ሰዎቹን ግን ውጡ አላለም ፡፡ የሚሠሩትን እንዲገነዘቡ ወቀሳቸው ፡፡ በፍቅር ገሰጻቸው ፡፡ ዛሬም ክፋትንና ሰዎቹን መለየት ያስፈልገናል ፡፡ ዛሬ ቢሆን የምናስወጣው ሰዎቹን ነው ፡፡ በሬዎቹ ይቀመጡ ሰዎቹ ይውጡ እንላለን ፡፡ ጌታችን ግን ሰዎችን የሚያድን ግሣጼ አደረገ ፡፡
     ካህናቱ የጣዖታት ምስል ያለባቸው የግሪክ ገንዘቦች ወደ ቤተ መቅደስ እንዳይገቡ ይጠነቀቁ ነበር ፡፡ ገንዘብ ግን ጣዖት ሁኖባቸው ቤተ መቅደሱን የንግድ ስፍራ አድርገውት ነበር ፡፡ አንድ መሥዋዕት አሳርገው እንዴት ነው ገበያው ለማለት ሳይመጡ አይቀሩም ፡፡ አፍ ከልብ ሁነው ማገልገል ባለመቻላቸው አገልግሎቱ ግዳጅን የሚፈጽም ፣ ምሕረት የሚያወርድ አልሆነም፡፡ ድካሙ አለ ፣ ፍሬው ግን የለም ፡፡ ሌዋውያን ከርስት ውጭ የተደረጉት ስለ ርስት በማሰብ በተከፈለ ልብ እንዳያገለግሉ ነው ፡፡ የአገልጋዮችን የሥጋ ፍላጎት ማሟላት ካልቻልን በቂ አገልግሎት ማግኘት አንችልም ፡፡ ከሩጫቸው መልስ የሚነግሩን ቃለ እግዚአብሔር ሰዓቱን ብቻ ለመሙላት ይሆናል ፡፡ ከድካም ቀጥሎ የሚያሳርጉት ጸሎት ልማድን ለመወጣት ብቻ ይሆናል ፡፡ በተቆራረጠ ልብ የሚያገለግል አገልጋይ የተቆራረጠ መልእክት ያመጣል ፡፡ በዚህም ጣዕምና ኃይል ያለው ክርስትና መኖር እየቸገረን ይመጣል ፡፡ በነፍሳችን የሚያገለግሉንን በሥጋቸው የማገልገል ግዴታ አለብን ፡፡ አሊያ አገልጋዮች ወደ ንግድ ይገባሉ ፡፡ ሲያጽናኑን ቃላቸው ይማርከን የነበረ አሁን ስለ ንግድ ሲያወሩብን ነፍሳችን እያዘነች ትመጣለች ፡፡ ስለዚህ ምእመናን ለሚያገለግሉአቸው ሊያንሡ አይገባም ፡፡ አገልጋዮችን መደገፍ እንዳለብን ቃሉ ከነገረን የምንችልበት አቅም ስላለን እንጂ እንዲሁ አይደለም ፡፡ “የማይሰጥ ድሃ ፣ የማይቀበል ባለጠጋ የለም” የሚለውን ማሰብ አለብን ፡፡  በዚያ ቤተ መቅደስ በሬው እየገባ አገልጋይ እየወጣ ነበር ፡፡ ካህናቱ በተከፈለ ልብ ቢያገለግሉም በሙሉ ልብ ግን ይነግዱ ነበር ፡፡ ጣዖታትን በደጅ ያስቀሩ ቢመስላቸው በልባቸው ግን ይዘው ገብተዋል ፡፡
“የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም፡- ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው”/ዮሐ. 2፡15-16/፡፡  
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን ከገለጠበት ክፍል አንዱ ይህ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አባቱ እንደሆነ በእግዚአብሔር ቤት ላይ ባለመብቱ እርሱ እንደሆነ ገለጠላቸው ፡፡ ጅራፉን የሰነዘረው ለበጎችና ለበሬዎች ነው ፡፡ ለሰዎች ግን መልእክት አስተላለፈ ፡፡ ቤተ መቅደሱን የሚቆጭለት እንዳለው እነርሱ አደራቸውን ባይወጡ የሚያዝን ባለሥልጣን እንዳለ ገለጠላቸው ፡፡ የጸሎት ቤት የንግድ ቤት መሆን እንደሌለበት ነገራቸው ፡፡ በንግድ ቤትና በጸሎት ቤት ብዙ ልዩነት አለ ፡-
1-  በንግድ ቤት የሚመጣው ደንበኛ ነው ፤ በእግዚአብሔር ቤት ግን የሚመጣው ሕዝብ ግን የእግዚአብሔር ወገን ነው ፡፡
2-  በንግድ ቤት ደንበኛ ንጉሥ ነው ፤ በእግዚአብሔር ቤት የሚያስፈልገው የንስሐ ልብ ነው ፡፡
3-  በንግድ ቤት ያለው ብቻ ይስተናገዳል ፤ በእግዚአብሔር ቤት ምስኪን ይጠጋል ፡፡
4-  በንግድ ቤት ካላዋጣ ሁሉም ነገር ያበቃል ወይም ዘርፍ ይቀየራል ፤ በእግዚአብሔር ቤት በመከራና በፈተና እንኳ ደስታ ይሰበካል ፡፡
ጌታችን የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ሲላቸው ሁሉን እንደ ወገናችሁ ተቀበሉ ፣ የተሰበረ ልብ ይኑራችሁ ፣ ልባችሁ ሙሉ ይሁን ፣ በሁሉ አትናወጡ ማለቱ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ጸጥታ ያስፈልገዋል ፡፡ ሁከት የሞላበት አምልኮ ሥጋን የሚያስደስት ነው ፡፡ እግዚአብሔር የሚወደውን ሳይሆን ለሰው ጆሮ የሚጥመውን የሚያቀርብ ንግድ ተኮር አገልግሎት ነው ፡፡ እውነትን እያቀጣጠኑ ለማቅረብ የሚሞከርበት ያለ ማንበብና ያለ ማስተዋል ችግር ነው ፡፡ ደግሞም የአሳብ ድህነት የሚወልደው ጩኸትን ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ከዘፈንና ከዳንኪራ ቤት የሚለየው በጸጥታው ነው ፡፡ ዛሬ የሚያገሱ በሬዎች ፣ የሚጮኹ በጎች ባይኖሩ እንኳ አምልኮቱ ጸጥታ የሌለው እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡ ዘመኑን ዋጁ በሚል ሰበብ ወደ ዘመን መሄድ ተገቢ አይደለም ፡፡ ዘመኑን ዋጁ ማለት ዘመንን ወደ መንፈሳዊነት ማምጣት ነው ፡፡ ጌታ የመጀመሪያው ተግሣጽ ስለ ነበር አልጠነከረባቸውም ፡፡ ሆሳዕና እየተባለለት ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ግን በጽኑ ቁጣ ገስጾአቸዋል ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ መናገሩ ነበርና ፡፡ 
ጌታችን ቤቴ ብሎ ጅራፉን ቢያነሣ ይሻለናል ፡፡ ቤታችሁ ብሎ ቢተወን ከባድ ነው ፡፡ “እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል”/ማቴ. 23፡38/፡፡ የእርሱ ጅራፉም ፍቅር ነው ፡፡ ለራሳችን ከተወን ግብ የለንም ፡፡ ለሁሉም ነገር መቆሚያው ወይም በመኪና ቋንቋ ፍሬኑ የእግዚአብሔር ቃል ነው ፡፡
“ደቀ መዛሙርቱም፡- የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ”/ዮሐ. 2፡17/ ፡፡ ጌታችን የተጻፈውን የሚያጸና አገልግሎት ነበረው ፡፡ ነገሥታት ወደ አንድ አገር ሲሄዱ እያንዳንዱ ንግግራቸውና ጉብኝታቸው የተተመነ እንደሆነ ጌታችንም አስቀድሞ መርሐ ግብሩን በነቢያት አስታውቆ ፍጻሜውንም አበሰረ ፡፡ ቅናት ሁለት ዓይነት እንደሆነ ይነገራል ፡፡ አንዱ ሥጋዊ ሲሆን ሁለተኛው ግን መንፈሳዊ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ የሚሠራው ፣ ሌሎችን ለማዳን ዋጋ የሚከፈለው ፣ ፍትሕን ለማምጣት ብርቱ ጥረት የሚደረገው ፣ ራእይን ከመጽነስ እስከ መውለድ የሚደረሰው በቅናት ነው ፡፡ እንደ መቃብር ጸጥ ያለ ፣ እንደ ብረት የቀዘቀዘ ልብ ያላቸው የእግዚአብሔርን ሥራ ሊሠሩ አይችሉም ፡፡ የተከለከለው በስሜታዊነት ማገልገል እንጂ በስሜት ማገልገል ይገባል ፡፡ ይህ ግለት ከሌለ መንፈሳዊ ሥራ ትግል እንጂ ድል ያለው አይሆንም ፡፡ ጌታችን የቤቱ ቅናት ይበላው ወይም ያቃጥለው ነበር ፡፡ የቤትህ ቅናት ያቃጥለኛል በሚል ስሜት አባቶችን ማዋረድ ፣ አገልጋዮችን ማራቆት ይህ ሥጋዊ ቅናት ነው ፡፡ መንፈሳዊ ቅናት ቅዱስ ነው ፡፡ ሌሎች ያጎደሉትን የሚያይ ብቻ ሳይሆን እኔ እንዴት ልሙላው የሚል ነው ፡፡ ሥጋዊ ቅናት ስድብን ቀጥሎም መገዳደልን ያመጣል ፡፡ መንፈሳዊ ቅናት ግን ከቅዱስ እግዚአብሔር የሚገኝ ነውና መገለጫው ቅድስና ነው ፡፡ ጌታ የገሰጸው በእኔነት ስሜት ነው ፡፡ ሩቅ ሁኖ መተኮስ ይህ ቅናት አይደለም ፡፡ የሚመለከታቸውን ሰዎች በማይመለከታቸው ወገኖች ፊት መናገር ይህ ቅናት አይደለም ፡፡ መንፈሳዊ ቅናት ቤተኛ እንጂ ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጥ ፣ ከዚያ አልፎ የተሳደብኩትን እዩልኝ ስሙልኝ ብሎ በኃጢአቱ የሚኮራ አይደለም ፡፡ የጥቅስ ካባ የለበሱ ሥጋዊ ቅናቶች ቶሎ አይላቀቁም ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ቃሉ እያደረገ መሆኑን ያስተውሉ ነበር ፡፡ ስለ ብሉይ ኪዳንም በቂ እውቀት እንዳላቸው እንረዳለን ፡፡ ጌታ ምን እንዳደረገ ብቻ ሳይሆን ለምን እንዳደረገ ያውቁ ነበር ፡፡
እግዚአብሔር አንድ ልጅን ለቤዛ ዓለም የላከበት አንዱ ምክንያት ቅንዓት ነው /ኢሳ. 9፡6-7/ ፡፡
ዛሬም ጌታ በቅናቱ እንዲያድነን መለመን ያስፈልጋል ፡፡ የእርሱ ቅናት ቅዱስና የሚታደግ ሰውን ለንስሐ የሚያበቃ ነው  ፡፡ የገበታ እንጀራ እያለለት ደጅ ወጥቶ ከመሬት እያነሣ የሚበላ ልጅ ያላቸው “ሳይቸግርህ” በማለት በቅናት ያለቅሳሉ ፡፡ የጌታ ቅናትም ጽድቅ ሳለ ኩነኔ ሳይቸግራችሁ የሚል ከፍቅር የመነጨ ነው ፡፡ “የወፍ ዘፈን አውራጁ አይታወቅም” እንደሚባለው ዛሬ መንጫጫት ብቻ ነው ፡፡ ሊቅ በዛ ፡፡ ሁሉም አዋቂ ነኝ አለ ፡፡ የመረጃ እውቀት የሕይወት እውቀት ያህል ክብር አገኘ ፡፡ ስለዚህ ጆሮ ተቆርጦ አፍ ብቻ የተከፈተበት ዘመን ነው ፡፡ የበላይ ለበታች አያዝንም ፣ የበታችም ለበላይ አይገዛም ፡፡ ብቻ መንጫጫት ነው ፡፡ ይህን የበሬ ግሣት ወይም ፉከራ ጌታ ያርቅልን ፡፡ ፈሪ ሲበዛ ማስፈራራት እየበዛ ይመጣል ፡፡ ዛሬ ሁሉም እያስፈራራ ነው ፡፡ እግዚአብሔር በጅራፉ ፍርሃትን ይገስጽልን ፡፡ የእኛ ነገር ግድ የሚለው እርሱ ብቻ ነውና በመልካም ያስበን ፡፡

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።