የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰውነቱ ቤተ መቅደስ

“ስለዚህ አይሁድ መልሰው፡- ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት” /ዮሐ. 2፡18/ ፡፡
አይሁድ ምልክት ናፋቂዎች ናቸው ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው”ይላል /1ቆሮ.1፡22-23/ ፡፡ ምልክት ፈላጊነት የጨው ውኃ እንደ ጠጡ መልሶ የሚያስጠማ ብቻ ሳይሆን እየጠጡ ሳለም የሚያስጠማ ነው፡፡ ምልክት ሁኔታውን እንጂ ሰውዬውን አይለውጥም ፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ሳይወጡ አሥር ታላላቅ ተአምራቶችን አይተዋል ፡፡ በኤርትራ ባሕር ዳርቻ ላይ ሁነው ግን አጉረምርመዋል /ዘጸ.14፡10-14/ ፡፡ የኤርትራ ባሕር መከፈል እስከ ዛሬ ያልተደገመ ተአምራት ነው ፡፡ የኤርትራን ባሕር ተሻግረው ግን በማራ ውኃ ወዲያው አንጎራጉረዋል እንጂ እግዚአብሔር ይህን ውኃ ይፈውሰዋል አላሉም /ዘጸ.15፡24/ ፡፡ አልዓዛር ከሞት ከተነሣ በኋላ ጌታችን ለመግደል ተነሡ እንጂ ለማመን አልተነሡም /ዮሐ. 12፡45-53/ ፡፡ መንፈሳዊ ክንዋኔዎች አማንያንን የበለጠ ሲያጸኑ ፣ የማያምኑትንም ባለማመናቸው የበለጠ ሊያጸኑ ይችላሉ ፡፡ በአንድ ትምህርት ፣ በአንድ ጉባዔ ፣ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ከማያጸኑ ጠባያት አንዱ ተአምር ፈላጊነት ነው ፡፡ ጌታችንም እነዚህን አይሁድ ሲወቅስ ፡- “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል”ብሏል /ማቴ. 16፡4/ ፡፡ ምልክት ፈላጊነት የዘማ ጠባይ ነው ፡፡ ዘማ ማለት ሁልጊዜ በኪዳኑ ወይም በትዳሩ ላይ የሚሄድ አይደለም ፡፡ ዘማነት የእውቀት ፣ የሃይማኖት ፣ የፍቅር ፣ የትምህርት አለው ፡፡ በአንድ አለመርጋት ፣ የጀመሩትን አለመጨረስ ነው ፡፡ አንዱን እውቀት ሳያደላድሉ ሌላውን መጀመር ፣ አንዱን ሃይማኖት በቅጡ ሳያውቁ እዚያ ነበርሁ እያሉ መግለጫ መስጠት ፣ አንዱን ፍቅር ዳር ሳያደርሱ ከሌሎች ጋር እፍ ማለት ፣ አንዱን ትምህርት ሳይፈጽሙ ሌላ መጀመር ወይም የትምህርት ስስት ውስጥ መግባት ይህ ዘማነት ነው ፡፡ ምልክት ፈላጊዎችም ዘማዎች ናቸው ፡፡ እንደ ቀላዋጭ የየቤቱን ወጥ ያውቁታል ፡፡ ሐፍረት የላቸውም ፡፡ የሚሰበስባቸው ወላጅ የላቸውም ፡፡
በሃይማኖት ምሥጢር ተአምራት ፍርፋሪው ሲሆን መዳን ግን የገበታው እንጀራ ነው ፡፡ ይህንን ጌታችን ለከነናዊቷ ሴት የገለጠው ነው ፡፡ “የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ”/ማቴ. 15፡26/፡፡ ይህች ሴት በአሚነ እግዚአብሔር ያለች አይደለችም ፡፡ ግን ተአምራት ትፈልጋለች ፡፡ ባለጸጋውን ጠልቶ ጸጋውን መናፈቅ ማለት ይህ ነው ፡፡ የልጆች እንጀራ የተባለው በሥላሴ ማመን ፣ አምልኮተ እግዚአብሔር ፣ ቃለ እግዚአብሔርን መመገብ ነው ፡፡ ዛሬ ተአምር አድራጊ መጣ ሲባል ሲያዝን የሚያጽናናውን ፣ ሲበድል የሚገስጽውን ፣ ሲያገባ የሚድረውን ፣ ሲወልድ የሚያጠምቅለትን ፣ ሲጣላ የሚያስታርቀውን ፣ ሲሞት የሚቀብረውን ፣ ሲረሳ የሚያስታውሰውን አገልጋይ ትቶ ይሄዳል ፡፡ ተአምር አድራጊዎች ከእግዚአብሔር የተላኩ ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡ አንዷን ቤተ ክርስቲያንና ተዋረዷን ግን አደጋ ላይ የማይጥሉ ሊሆኑ ይገባቸዋል ፡፡ ተአምራት ማድረግ አንዱ ጸጋ እንጂ ጠቅላይ ጸጋ አይደለምና ለብቻ ተነጥሎ የሚያስቀምጥና ሕዝብ የሚሰበስብ መሆን በፍጹም የለበትም ፡፡ ብዙ እንደ ታየው ተአምር አድራጊ ነን የሚሉ እንደ ውሽማ ፍቅር ብነው የሚጠፉ ናቸው ፡፡ በአገራችን አንድ ተረት አለ ፡- “አገባ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” በእነዚህ ወገኖች ፍቅር እፍ ብለው ትተዋቸው የሄዱ ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሔር ቤት ተለይተው ብቻቸውን በመንቀፍ ይኖራሉ ፡፡ አገባለሁ ያለው ባል መሄዱ ችግሩን አያቀለውም ፡፡ ከኖረው ባል ጋር መቃቃር ይፈጠራል ፡፡ ያች ሴትም ከሁለት ያጣች ትሆናለች ፡፡ ዛሬ ላይ በጣም የሚወድና በጣም የሚጋብዝ ነገ ስለ ሌለ ነው፡፡ ዛሬ እፍ የማይለው ባል ግን ነገም አለሁ ብሎ ስለሚያስብ ነው ፡፡ ስለዚህ ምእመናን በወረት ፍቅር በሐሰተኛ ቃል ኪዳን አብረዋችሁ ከሚኖሩት አገልጋዮች አትጣሉ ፡፡
አይሁድ ጌታ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አደረጋችሁት ሲላቸው ይህንን እንድንቀበልህ ምልክት አሳየን አሉት ፡፡ እውነትን ለመቀበል ምልክት አስፈላጊ አይደለም ፡፡ እውነት ተዳሳሽና ቋሚ ነው ፡፡ ተአምራት ግን ተመላላሽ እንጂ ቋሚ አይደለም ፡፡ ቋሚውን እውነት በተመላላሽ ተአምራት መለወጥ ተገቢ አይደለም ፡፡ ዛሬም ምልክት የሌለበት አገልግሎት ደረቅና ሙሉ አይደለም የሚሉ ካሉ አጽዳቂና ኮናኝ የሆነውን ቃል አቃለዋልና ፍርድ ይጠብቃቸዋል ፡፡
አይሁድ የጌታን ምክር ለመቀበል ምልክት አሳየን አሉ ፡፡ እውነትን ለመቀበል የምልክት መደራደሪያ አቀረቡ ፡፡ ጌታችን ግን ስለ ሞቱ ነገራቸው፡፡ ዛሬ ቃሌን ካልተቀበላችሁ ነገ ትገድሉኛላችሁ የሚል መልእክት አስተላለፈ ፡፡ ታላላቅ ክንውኖች እንደ ምልክት ተቆጥረዋል ፡፡ እነዚያ ምልክቶች ግን በሰው ዘንድ እንደ ምልክት የሚታዩ አልነበሩም ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ትልቅ ምልክቶች ናቸው ፡፡ ምልክት ያልተለመደ ነገር ፣ እንግዳ ክስተት ነው ፡፡ የጌታችን በድንግልና መወለድ ምልክት ተብሏል /ኢሳ. 7፡14/ ፡፡ ይህም ያልተለመደና እንግዳ ነገር ነው፡፡ ትንሣኤውም ትልቅ ምልክት እንደሆነ ተነግሯል /ማቴ. 16፡4/ ፡፡ አማንያን ሊገረሙበት የሚገባና እግዚአብሔርን ለማመስገን ትልቅ ርእስ የሚሆናቸው የጌታችን አስደናቂ ልደቱና ትንሣኤው ነው ፡፡ በእነዚህ መለኮታዊ ክንውኖች ውስጥ ሰላም ፣ ተስፋና እምነት ይገኛል ፡፡  
“ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው” /ዮሐ. 2፡19/፡፡ ጌታችን የመቅደስ ነጋዴነት ወደ መቅደስ አፍራሽት እንደሚሄድ ተናገረ ፡፡ ይህን ቤተ መቅደስ ያለው የገዛ አካሉን ነው፡፡ ወደ መግደል እንደሚያድጉ መጨረሻው ግን ትንሣኤ እንደሚሆን ነገራቸው ፡፡ ጌታችን ሞቱን ለጠላቶቹም ለወዳጆቹም ያሳስብ ነበር ፡፡ ጠላቶቹም በመግደላቸው ፈጽመው እንዳይደሰቱ ፣ ወዳጆቹም በመሞቱ ፈጽመው እንዳያዝኑ ጌታ አስቀድሞ ይናገር ነበር ፡፡ አዳምና ሔዋን በኃጢአት በወደቁ ጊዜ እባቡ ወይም ሰይጣን ሲረገም የክርስቶስ ሞት ተነሥቷል /ዘፍ. 3፡15/፡፡ የክርስቶስ ሞት የተነሣው ሰይጣን በመጣሉ ፈጽሞ ደስ እንዳይለው ፣ አዳምና ሔዋንም በመውደቃቸው ፈጽሞ እንዳያዝኑ ነው፡፡
እነርሱ ማፍረስ ይችላሉ ፡፡ እርሱ ግን ማስነሣት ይችላል ፡፡ ዛሬም ሰዎች ማቁሰል ይችሉ ይሆናል ፤ እግዚአብሔር ግን ያጽናናል ፡፡ ሰዎች ማሳደድ ይችሉ ሆናል ፤ እግዚአብሔር ግን ያስጠጋል ፡፡ የምድር ኃይለኞች የመጨረሻ አቅማቸው መግደል ነው ፡፡ የሞት ጉዞ ከተጀመረ ከሦስት ደቂቃ በኋላ መመለስ ከባድ ነው ፡፡ የሞት ሠረገላ ከብርሃን ይፈጥናል ፡፡ ጌታችን ከሦስት ቀን በኋላ አነሣዋለሁ አለ ፡፡ ማሰብ ያለብን ስለ መፍረስ ሳይሆን ስለ መነሣት ነው ፡፡ እግዚአብሔር ሞት የማይመልሰው ወዳጃችን ነው ፡፡ 
ጌታችን ቅዱስ አካሉን መቅደስ በማለት ይጠራዋል ፡፡ ሐዋርያው ፡- “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” ይላል /ቆላ.2፡9/፡፡ ይህ መቅደስ ለሦስት ቀን እንደሚፈርስ ማለት እንደሚሞት ነገራቸው ፡፡ አፍርሱት ስላላቸው ቆም ብለው ማሰብ ነበረባቸው ፡፡ ጌታችን በሦስት ቀን አነሣዋለሁ አለ ፡፡ በገዛ ሥልጣኑ እንደሚነሣ ተናገረ ፡፡ በትንሣኤው የተገለጠው ኃይል ብርቱና ሰብአዊ ኃይል ሊይዘው የማይችል ነው ፡፡ ማፍረስ የሚችሉት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነው ፡፡ ከዚያ በኋላ ሞት ለዘላለም ላይዘው ይነሣል ፡፡
“ስለዚህ አይሁድ፡- ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት” /ዮሐ. 2፡20/፡፡ መቅደሱ ከክርስቶስ ልደት 16 ዓመት በፊት የተጀመረ ብርቱ እድሳትና ማስፋፋት ላይ ነበረ ፡፡ ይህ መቅደስም በልዩ ሁኔታ እየተሠራ ነበር ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ተደንቀው ለጌታ አሳይተውታል ፡፡ ማቴዎስ እንደ ዘገበው፡- “ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ” /ማቴ. 24፡1/፡፡ ይህ መቅደስ እድሳቱን በ64 ዓ.ም ጨርሶ በ70 ዓ.ም. በሮማውያን ፈርሷል ፡፡ በዚህም የመቅደሱን ድንጋዮች ሲያሳዩት ጌታችን የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ ፡፡ “እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው” /ማቴ. 24፡2/፡፡
አይሁድም ጌታችንን ፡- “ስለዚህ አይሁድ፡- ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት” /ዮሐ. 2፡20/፡፡ አልተግባቡም ፡፡ ዮሐንስም የጌታችንን ንግግር ሲተረጉም ፡- “እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ” ይላል /ዮሐ. 2፡21-22/፡፡ ሳይነሣ ያመኑት ደቀ መዛሙርት ከተነሣ በኋላም ያመኑት እነርሱ ናቸው ፡፡
“በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ” /ዮሐ. 2፡23/፡፡ በመቀጠልም ፡- “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና” ይላል /ዮሐ. 2፡24-25/፡፡ ምልክትን አይተው ያመኑበትን እነዚያን ሕዝቦች ጌታ አይተማመንባቸውም ነበር ፡፡ ጌታችን ፍቅር ነው ፡፡ ፍቅር ደግሞ ሁሉን ያምናል ፡፡ ታዲያ እንዴት አይተማመንባቸውም ነበር ተባለ ስንል ልቡን አይጥልባቸውም ነበር ፡፡ እርሱ ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ከአፋቸው ጋር ሳይሆን ከልባቸው ጋር ነው ፡፡ ሰዎችን ያውቅ ነበር ፡፡ ሰዎች አምነው እንደሚክዱ ፣ ወደው እንደሚጠሉ ያውቃል ፡፡ በውስጣቸው ያለውንም ከዳተኝነትና ሐሰተኛ ፈገግታ መርምሮ ያውቃል ፡፡ የሚደንቀው ጌታችን አለመተማመኑ ሳይሆን ይህን ሁሉ እያወቀ ሰውን መውደዱ ነው ፡፡ እኛ ከጠለለውና ከትንሹ ከፈሰሰው ተንኮል ስናውቅ እንታመማለን ፡፡ ከእነርሱ በላይ ክፉ እንሆናለን ፡፡ ጌታችን ግን ያልተጣራውን ድፍድፉን ክፋት ከልብ ላይ እያየ ሰውን መውደዱ ይገርማል ፡፡ ሰዎች የሚጠሉትን ሰው ከሚወዱት ሰው በላይ ሲንከባከቡ ይታያሉ ፡፡ አስብተው የማረድ ስልት ነው ፡፡ ልባቸውን አስቀምጠው በአፋቸው ያጫውቱታል ፡፡ እኛ በሰው ያለውን ሁሉ አለማወቃችን መልካም ነው ፡፡ ሰዎችም በእኛ ያለውን ሁሉ እንኳን አላወቁ ብለን ደስ ይለናል ፡፡ አንዴ ራሳችንን አምነን ስንኮንናቸው ሌላ ጊዜ በግምት እንዲህና እንዲያ ያደረጉ ሲመስለንና ስንጠላቸው የምንውል ነን ፡፡ እንኳን በሰው ልብ ያለውን ክፋት አይደለም ፣ መልካምነታቸውንም አትኩረን ማየት አይገባንም ፡፡
ጌታችን ባመኑት አልተማመነም ፡፡ የዛሬ አገልጋይ ደግሞ በደገፉት ደጋፊዎች ተማምኖ ይዘላል ፡፡  አለማመንና አለመተማመን ልዩነት አለው፡፡ ፍቅር ያምናል ስንል በሰዎች መለወጥ ተስፋ ያደርጋል ማለት ነው ፡፡ መተማመን ግን በሰዎች ላይ ተደግፎ መፎከር ነው ፡፡ ሰዎች ፍቅርን መሸከም ሲችሉ መተማመንን ግን መሸከም አይችሉም ፡፡ ጌታችን ስላለመታመናቸው አልነቀፋቸውም ፡፡ እርሱ ግን በገደብና በጥንቃቄ ከሰዎች ጋር ይገናኝ እንደ ነበር የሚናገር ነው ፡፡ ይህ ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚጎዳ አይደለም ፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚጠብቅ ነው ፡፡ እፍ ማለት ለሁለት ነገር ይሆናል ፡፡ እሳቱን ለማንደድም ለማጥፋትም ሁለቱም እፍ ነው ፡፡ እፍ ያነዳል እፍ ያበርዳል ፡፡ እፍ ያበራል እፍ ያጠፋል ፡፡
በስምንተኛው ሺህ ሰው በረከሰበት
እኔም እብድ ሆኛለሁ አንተን ያመንኩበት
በማለት አንዲት ሕመምተኛ በጎዳና ስትናገር ሰምቻለሁ፡፡ አሁን ያለችበት የችግሩን ምንጭ እየጠቀሰች ነው ፡፡ የሰው ልጅ በአንድ ጊዜ ሃያ ዓይነት የተለያዩ አስተሳሰቦችን ያስባል ፡፡ በአንድ ጊዜ ይህን ካሰበ በአንድ ቀን ምን ያህል ያስብ ይሆን ብለን ብንጠይቅ ሰው ቢለዋወጥ አይደንቀንም ፡፡ ስለተጎዳነው ብቻ ሳይሆን ገና ለመጎዳት የምንኖር ነንና በጣም ማሰብ ያስፈልገናል ፡፡ የሄደው ይመለሳል ፣ ያለውም ይሄዳል ፡፡ ለዚህ ነው የአገራችን ሰዎች ኀዘናቸውን ሲገልጡ ፡-
እባቡሩ መንገድ የቆምኩት አሁን
ስንቱን አሳልፌ እዘልቀው ይሆን 
የሚሉት ፡፡ ሁሉም ያልፋል ፡፡ ሁሌ መፋቀር ሁሌም መጠላት የለም ፡፡ ሁሉን በመጠኑ ፣ ሁሉን በልኩ መያዝ ግን ለሁሉም ይጠቅማል ፡፡ ተረኛ ወዳጅ እንጂ ቋሚ ወዳጅ በጠፋበት በዛሬ ዘመን ታማኝ መሆን ይገባናል ፡፡ በፍቅር ወረተኛ የሆነ በሁሉም ነገር ወረተኛ መሆኑ ግድ ነው ፡፡
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት በቃና ዘገሊላ ተአምርና ጌታችን ቤተ መቅደሱን እንዳጸዳ በመናገር ይደመድማል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ