የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዘላለም ሕይወት መንገድ

“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ” /ዮሐ. 3፡1/፡፡
ፈሪሳውያንየታወቁ የሃይማኖት ቡድን ናቸው ፡፡ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍትንና የነቢያት መጻሕፍትን የሚቀበሉ ናቸው ፡፡ ከሰዱቃውያን የሚለዩት በመላእክትና በትንሣኤ ሙታን የሚያምኑ በመሆናቸው ነው ፡፡ እንዲሁም ሰዱቃውያን አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ሲቀበሉ ፈሪሳውያን ግን ብሉይ ኪዳንን በሙሉ ይቀበላሉ ፡፡ ፈሪሳውያን የስማቸው ትርጉም የተለዩ የሚል ሲሆን ራሳቸውንም እንደ እግዚአብሔር ምርጥና የጠራ እስራኤል አድርገው ይቆጥሩ ነበር ፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሕግ ላለመቅረብና ላለመጣስ ብዙ አጥሮችን አርቀው አጥረው ነበር ፡፡ ይህም የሽማግሌዎች ወግ ተብሎ የሚጠራ ነው ፡፡ ያመጣው ችግር ከእውነተኛው ሕግ በላይ የሚከበር ሲሆን ተለዋጭ ሕግም ሁኖ ዋናውን አስረሳ ፡፡ ፈሪሳውያን በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት የነበራቸውና ብሔራዊ ስሜት አላቸው ተብለው የሚታመኑ ራስን በመጨቆንና በሜዳዊ ሥርዓት የዋሃንን የሚማርኩ ናቸው ፡፡ ሀብታምነትና ድህነት የኑሮ መልክአ ምድር እንጂ የጽድቅና የኩነኔ መገለጫ አይደለም፡፡  ኒቆዲሞስም የዚህ የሃይማኖት ቡድን አባል ነበረ ፡፡ የአይሁድም አለቃና ማኅበረሰባዊ ሥልጣን የነበረው ሰውም ነው ፡፡ ሰባ አባላትን የሚያቅፈው የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበር ፡፡ ይህ ሸንጎ በአገር ጸጥታና ሰላም ላይ መወሰን የሚችል እንደ ሕዝብ ተወካዮች የሚታይ ነው ፡፡ ኒቆዲሞስ በዚያ ዘመን ኩሩ የነበሩት የፈሪሳውያን ወገን የሆነ ፣ ባለሥልጣንና ባለጠጋ ሰው ነው ፡፡ ይህ ሁሉ ክብርና ሥልጣን ያልመለሰው የሕይወት ጥያቄ ነበረው ፡፡ በሌሊት እንዲገሰግስ ያደረገውም ይህ ጥማት ነው፡፡
ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ የመጣው ጌታችን ከአንድ ቀን በፊት በመቅደሱ ተገኝቶ ነጋዴዎችን በሥልጣን እንዳስወጣና ብዙ ተአምራትን እንዳደረገ ባየ ጊዜ ነው ፡፡ የጌታችን አድራጎቱ ለአክራሪ አይሁዳውያን ከንቀት የዘለለ ትርጉም አልሰጣቸውም ፡፡ ስለ አምላክነቱ ከማሰብ በናዝሬት ስለማደጉ ያስባሉ ፡፡ ኒቆዲሞስ የእግዚአብሔር ቤት የንግድ ቤት በመሆኑ የሚያዝን ቢሆንም ያንን ለመናገር ግን ያልደፈረ ሰው ነበር ፡፡ ጌታችን በሥልጣን በማድረጉ አድናቆቱን ለመግለጥ ፣ ፈሪሳዊ ክብሩን ጠብቆ ለመነጋገር ወደ ጌታችን መጣ ፡፡  
“እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፡- መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው” /ዮሐ. 3፡2/ ፡፡
ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ ጥማቱ አላስተኛህ ቢለው ነው ፡፡ ጌታ ግን እርሱን በሌሊት ማስተናገዱ ትጉህ መምህር መሆኑ ነው ፡፡ ኒቆዲሞስ በቀን ቢመጣ አይሁድ ሊቃወሙት ይችላሉ ፡፡ ፈጽሞም በጌታችን ስላላመነ ለተራው ሕዝብ አርአያ እንዳይሆን በሌሊት መጣ ፡፡ ጌታችን ግን እንዴት ትፈራለህ? በሚል ነቀፋ አልተቀበለውም ፡፡ ባወቀ መጠን ከፍርሃት እንደሚድን ተስፋ አድርጎ እስከዚያ ድረስ በትምህርት አነጸው ፡፡ አንድ ነገር እንዲፈስስ ከተፈለገ ሕጉ መሙላት ብቻ ነው ፡፡ የሞላ በግድ ይፈስሳል፡፡ ጌታችን ስለመሞላት ብቻ ያስብ ነበር ፡፡ ትምህርቱም ሠርቶ ዓርብ ዕለት ወዳጅ ጠፍቶ ኒቆዲሞስ ተገኘ ፡፡ ጌታን ከመስቀል አወረደ ፡፡ ከመስቀል ማውረድ ብዙ ዋጋ አለው ፡፡ ጌታችን እንደ ብራና ከተወጠረበት ሰሌዳ ላይ ማላቀቅ ነው ፡፡ ስለ እኛ ኃጢአት እርቃኑን ከዋለበት አደባባይ ገለል ማድረግ ነው ፡፡ ለኑሮው ቤት ላልነበረው ጌታ መቃብር መስጠት ነው፡፡ ያን ቀን ሁሉ አወቀው ፡፡ ሰዎች በጊዜው እንዲያድጉና እንዲገለጡ ዛሬ ማስተማር ተገቢ ነው ፡፡ ጌታችን ብዙ ተአምራት ያደረገላቸውንና ሲደረግ ያዩትን ደቀ መዛሙርት ለማንም እንዳይናገሩ ያዝዛቸው ነበር ፡፡ ለምን ስንል የተለያየ ምክንያት አለው ፡-
1-  ያዩትን ተአምር መጀመሪያ ለራሳቸው እንዲያጣጥሙት ነው ፡፡ የተደረገለትን በቅጡ ያላጣጣመ እንደሚገባው ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ምስጋና አይደርስም ፡፡ በዘመኑ ሁሉ የሰማውን ሳያጣራ የሚለቅቅ ይሆናል ፡፡ አዲስ ነገር በሰማ ቁጥር አዲስ እውነት የሰማ ይመስለዋል እንጂ በቃላት የተሸፈኑ ስህተቶችን መረዳት አይችልም ፡፡ ስህተትን ከሚፈበርኩት ይልቅ ሳይገባው የሚለፈልፍ ይበልጥ ያዳርሰዋል ፡፡ ቆሻሻ አንድ ቦታ ነው ያለው የምታዳርሰው ግን በከንቱ የምትለፋዋ ዝንብ ናት ፡፡
2-  የምስክርነትን ዋጋ ለመክፈል ብቁ እስኪሆኑ ድረስ ነው ፡፡ ምስክርነት ዋጋ ያስከፍላል ፡፡ ጌታችን ወደ ዓለም ሁሉ ቢልከንም ዓለሙ ሁሉ የሚያምን አይደለም ፡፡ የማያምነው ደግሞ በቃልም በኃይልም ይዋጋል ፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ያልተጎናጸፈ በስድብና በተቃውሞ ይደነብራል ፡፡ ስለዚህ ጌታችን የምስክርነት ዋጋን ለመክፈል ብቁ እስኪሆኑ ለማንንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው ፡፡
3-  የጌታችንን ሞት እንዳያፋጥኑ ነው ፡፡ በገለጡት ቁጥር መስቀሉ እየቀረበ ይመጣል ፡፡ ጌታችን ደግሞ በጊዜው ለመሞት ተጠንቅቋል፡፡ ስለዚህ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው ፡፡
 ኒቆዲሞስንም በጊዜው እንዲገለጥ ተወዉ እንጂ እንዴት በእኔ ታፍራለህ ? ብሎ የሌሊት ግስጋሴውን አልነቀፈም ፡፡ እንደውም በትጋት አስተማረው ፡፡ ኒቆዲሞስ የሌሊት ተማሪ ነው ፡፡ የሌሊት ትምህርት ዋጋ እየከፈሉ መማር ነው ፡፡ እግዚአብሔር በቀኑ በተፈጥሮው ሌሊት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ሌሊትም ያስተምራል ፡፡ የሌሊት ዝማሬን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ፡፡ የሚታይ ተስፋ ፣ የሚጨበጥ መልካም በሌለበት ሌሊት እግዚአብሔርን ብቻ እያዩ ማመስገን መልካም ነው ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ፡- እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው”ይላል /መዝ. 41፡8/ ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስና ሲላስ በመንፈቀ ሌሊት ዝማሬን ያቀረቡት በጌጠኛ መቅደስ ሳይሆን በወኅኒ ቤት ነው ፡፡ የወርቅ ዕቃ ይዘው ሳይሆን በሰንሰለት ታስረው ነው ፡፡ በበቂ ብርሃን ሳይሆን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሁነው ነው ፡፡ እግዚአብሔር በተፈጥሮም ሆነ በሕይወት ሌሊት ያስተምራል ፡፡ ይህ ኒቆዲሞስ ፡-  
“መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው” /ዮሐ. 3፡2/ ፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ መምህር እንጂ እንደ እግዚአብሔር አልተቀበለውም ፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ እንጂ ራሱ እግዚአብሔር እንደ ሆነ አማኑኤል ወይም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የተባለለት መሆኑን አልተረዳም ፡፡ ጌታችን ለኒቆዲሞስ ጥማት መሠረታዊ መልስ ለመስጠት በማሰብ ሳይነቅፍ አስተማረው ፡-
“ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው” /ዮሐ. 3፡3/፡፡ ኒቆዲሞስ እንደ አንድ ረቢ ወይም መምህር ጌታችንን ተቀብሎታል ፡፡ ጌታችን ግን ከልጅነት ሊጀምርለት ፈለገ ፡፡ ይህ ብዙ ፍቺዎች አሉት ፡፡
1-  እግዚአብሔርን ለማወቅ አስፈላጊው ነገር የአእምሮ ብስለት ሳይሆን የእምነት ልብ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የማይታይ በመሆኑ ደግሞም የማይወሰን በመሆኑ በእምነት ካልሆነ ልንረዳው አንችልም ፡፡ በአገራችን አንድ ምሳሌ አለ ፡- ልጅ አባቱን “አባባ እምነት ምንድነው? እውነትስ ምንድነው? በማለት ጠየቀው ፡፡ አባትም ሲመልስ ፡- “እምነት እኔ አንተን መውለዴ ሲሆን እውነት ግን እናትህ አንተን መውለዷ ነው” አለው ይባላል ፡፡ በርግጥም እናቲቱ እናት መሆኗን አዋላጆችም ይመሰክራሉ ፡፡ አባትነት ግን በእምነት የሚቀበሉት ነው ፡፡ እንዲሁም ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ምሥጢርና ልጅነታችንን ተቀብለን የምንኖርበት ነገር እምነት ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ስለ ክርስቶስ ለመረዳት ከእምነት መጀመር አለበት ፡፡ ብዙ እውቀቱ ያላረካው ኒቆዲሞስ ለመርካት አሁንም የእውቀት አሰሳ ላይ ያለ ይመስላል ፡፡ ከብዙ እውቀት ጥቂት እምነት ሥራ ትሠራለች ፣ ታሠራለች ፡፡
2-  ካለን ነገር በመጀመር ሳይሆን እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ያስጀምራል፡፡ ኒቆዲሞስ ባለሥልጣን ፣ ባለጠጋ ፣ አዋቂ ፣ ፈሪሳዊም ነው፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ ግን ከመንፈሳዊ ድህነት የሚጀመር ነው ፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን ሥራ መሥራት ሲጀመር በማፍረስ ይጀምራል ፡፡ በእኛ መሠረት ላይ አያንጽም ፡፡ አንዳንዴ ትምክሕታችንን ሌላ ጊዜም በዙሪያችን ያሉትን የከበቡንን ይበትናል፡፡ እርሱ ብቻችንን ሲያገኘን የዘላለምን ምሥጢር ያጫውተናል ፡፡ ጌታችን ለኒቆዲሞስ ከልጅነት ጀመረለት ፡፡ ልጅነት መነሻ ነው ፡፡ በማንኛውም ጊዜ ከጌታ ጋር መጀመር ይቻላል ፡፡ ያለ እርሱ ለዓመታት ከገነባነው ከእርሱ ጋር ዛሬ የጀመርነው ለፍጻሜ ይበቃል ፡፡ መጀመር እንፈራለን ፡፡ ክፉውን ሳይቀር ተላምደን ለመኖር ኪዳን እናደርጋለን ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሲያስጀምረን ያባከነውን ዘመን በሚክስ ጸጋ ያፈጥነናል ፡፡
ኒቆዲሞስ የራሱን ግንዛቤ ወስዷል ፡፡ ጌታችን ተአምር ማድረጉን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለም ተረድቷል ፡፡ ጌታችን ግን እንደገና ከልጅነት አስጀመረው ፡፡ የትኛውም የኑሮ ልምድ መንፈሳዊ ትምህርትን አይተካም ፡፡ በኑሮ ልምድም እግዚአብሔርን መከተል አይቻልም ፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ከዳግመኛ መወለድ ጋር ተያያዛለች ፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ በቁጥር 3 እና 5 ላይ እንደተገለጠው ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት መጀመሪያ አያይም ፣ ሁለተኛ አይገባም ፡፡ ማየት ዛሬ ያለን መንፈሳዊ ሕይወት ፣ በቃሉ ጥላ ሥር ማረፍ ነው ፡፡ መግባት በፍጻሜ የሚሆነው ብይን ነው ፡፡ ያላየ አይገባም ፡፡ ያየ ይገባል ፡፡ የዘላለም ሕይወት ሲባል ዘላለም ከአሁን አንሥቶ ነው ፡፡ ኒቆዲሞስ ዛሬ መንግሥቱን እንዲያይ ተጋበዘ ፡፡ ይህንን ዓለም ያየነው በመወለድ ነው ፡፡ የሚመጣውንም ዓለም የምናየው በመወለድ ነው ፡፡ ልደት ዓለምን መውረሻ ነው ፡፡ ይህ አሳብ ኒቆዲሞስን ግራ አጋብቶታል ፡፡ በሊቅነት እግዚአብሔርን መረዳት አይቻልም ፡፡ ለመቻል አልችልም ማለት ተገቢ ነው ፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ባለን ነገር ላይ ታሳቢ ሳይሆን ከመጀመሪያው መሆን ይኖርበታል ፡፡ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ይጀምራል፡፡ ካለመኖር ወደ መኖር በተጠራ ነገር ተጀመረ ፡፡ እግዚአብሔር የሌለን ነገር እንኳ በመጥራት ይጀምራል ፡፡ በቃና ዘገሊላ የሰው ድግስ ፍጹም ማለቁን ካየ በኋላ መሥራት ጀመረ ፡፡ ጌታችን ሂደት ሳያግደው ይሠራል ፡፡ ዳግመኛ መወለድም እግዚአብሔር ከአዲስ እንደሚጀምር የሚያሳይ ነው ፡፡ በመገረዝ ውስጥ ማነስ አለ ፡፡ በማነስ ውስጥ ግን ጥራትና ብዛት ይወጣሉ ፡፡ ግዝረት ሁለቱንም ያመጣል ፡፡ ዛፍ አንድ ግንድ ነው ፡፡ ሲቆረጥ ግን ቁጥቋጦው ብዙ ነው ፡፡ በብዙ ዘለላዎች ያቆጠቁጣል ፡፡ ስለዚህ ዳግም መወለድ ከእግዚአብሔር ጋር ለመጓዝ “ሀ” ብሎ መጀመርን የሚያሳይ ነው ፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ደግሞም ፈሪሳዊ ነው ፡፡ አሁን የተወለደ ልጅ ግን እነዚህ ሁሉ ሊኖሩት አይችሉም ፡፡ ዳግመኛ መወለድ እንደ ገና “ሀ” ማለትን የሚያሳዩ ናቸው ፡፡ እንደገና ካልጀመርን በተሳሳተ መንገድ ተጉዘን የተራራው ጫፍ ላይ መድረስ አንችልም ፡፡ አንድ ረጅም ተራራ የሚወጣ ሰው መንገድ ጠፍቶት መዳከር ጀመረ ፡፡ አንድ ሰው አገኘውና ሲመክረው “የዚህ ተራራን ጫፍ ለማግኘት እንደገና ከሥር መጀመር አለብህ” አለው ፡፡ ያ ሰው ከሥር መጀመርን ስላላሰበ ብዙ ጉልበቱንና ተስፋውን ከሰረ ፡፡ መንፈሳዊ ሕይወትም ከሥር መጀመር ያስፈልገዋል ፡፡ ከሥር ወይም ከምንጩ ካልተፈወሰ ወራጁን ንጹሕ ማድረግ አይቻልም ፡፡ በተናጋ መሠረት ላይ ማነጽ ለማፍረስ ነው ፡፡ በመራራው ግንድ በአዳም ላይ ማሻሻያ ማድረግ ፍሬውን አያጣፍጥም ፡፡ አዲሱ ግንድ ክርስቶስ ላይ ተቆርጦ መተከል ግን ጣዕም ያለው ሕይወት ያመጣል ፡፡
የእስራኤል ልጆች የተስፋይቱ ምድር መግቢያ ላይ ቆመው መገረዝ ያስፈልጋቸው ነበር /ኢያሱ 5፡2/፡፡ ያን ሁሉ ተጉዘው ርስቱን ለመውረስ ግን መገረዝ አስፈላጊ ነበር ፡፡ ለሚያምም ሥርዓት መታዘዝ ያስፈልጋቸዋል ፡፡ ሸለፈት ተፈጥሮ ነው ፡፡ በመገረዝ ውስጥ አብሮ የሚወድ ነገር አለ እርሱም የግብጽ ነውር ነው ፡፡ የላይ ምልክቱ ለውስጥ እምነት ማጽኛ ነው፡፡ በሕይወት ውስጥም አንዳንድ ነገሮች እንዲወድቁልን በሚያም ሥርዓት ውስጥ እናልፋለን ፡፡ ስለቱ ግን ያለው በቆሰለልን በክርስቶስ እጅ ላይ ነው ፡፡ ስለዚህ ቁስለቱ ለሞታችን ሳይሆን ለበረከታችን ነው ፡፡ ያማል ግን ውበት አለው ፡፡ ሴቶች ሁሉ የሚዋቡት በሚያም መንገድ ነው ፡፡ ፍጻሜው ውበት ነውና ይችሉታል ፡፡ ዳግም መወለድም ሕመም አለው ፡፡ ከዓለም ፣ ከአሮጌው ቤተሰብና አስተሳሰብ መለየት ነውና ፡፡ መወለድ መጀመር ነው ፡፡ በብዙ ሕይወታችን መጀመርን በመፍራት እየተጎዳን እንኖራለን ፡፡ ይሉኝታ ፣ የሰውን ወዳጅነት የማጣት ስጋት ብዙ ጊዜ ይጎዳናል ፡፡ እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገርን ይሰጣል ፡፡ መገረዝ በረከትን ለመውረስ ቅድመ ሁኔታ ነበር ፡፡ እንዲሁም ዳግም መወለድ ወደ ምድረ በረከት ለመግባት የመጨረሻ መጀመሪያ ነው ፡፡ ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነውና በደንብ ይናበባል ፡፡ አካል እዚያ ጋ ባይቆም ብሉይ ኪዳን ላይ ጥላው አይታይም ነበር ፡፡ ጥላው ግዝረት ነው ፡፡ 

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።