የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዴት ?

በሥጋዊው ልደትና በሥጋ ዓይን የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሁም የመንግሥቱን ባለቤት ማየት አይቻልም ፡፡ በሁለተኛው ልደት ግን ባለቤቱን እንዲሁም መንግሥቱን ማየት ይቻላል ፡፡ የሥጋ ወላጆቻችንን ያየነው በመወለድ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም መንፈሳዊ አባታችን የሆነውን እግዚአብሔርን የምናየው በመወለድ ነው ፡፡ እርሱ መልኩ ፍቅር፣ ቸርነትና ርኅራኄ ነው ፡፡ ይህን ማየት የምንችለው በመወለድ ነው ፡፡ አባ አባት ብለን በነጻነት ለመጥራት መወለድ ያስፈልጋል ፡፡ ያልተወለደ አባ አባት ሲል አፉ ላይ ይንቀዋለላል ፡፡ የተወለደ ግን ተሰምቶት ይጣራል፣ አባቱም በስስ ልብ ይሰማዋል ፡፡ ይህን ዓለም ከመውረሳችን በፊት ከወላጆቻችን ጋር ግንኙነት ነበረን ፡፡ እንዲሁም መንግሥተ ሰማያትን ከመውረሳችን በፊት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ያስፈልገናል ፡፡ ልደት የኅብረት ውጤት ነው ፡፡
ልደት በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ለዚህም የሚጠቀሰው የአዳም፣ የሔዋንና የአቤል መገኛ ነው ፡፡ አዳም ከመሬት ፣ ሔዋን ከአዳም ጎን፣ አቤል ከአዳምና ሔዋን ተገኝተዋል ፡፡ ስለዚህ ዳግም ልደት ቢባል ግር የሚያሰኝ ነገር የለውም፡፡
በአንዳንድ ባሕሎች ልጅ ከመወለዱ በፊት ለጀግንነቱ መሣሪያ፣ ለመተዳደሪያው ሀብት ይዘጋጅለታል ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር መንግሥቱን አዘጋጅቶልናል ፡፡ ምድርን የሥራ ቦታ ፣ ገነትን ግን የንጉሡ ቤተ መንግሥት እንድትሆን እግዚአብሔር ተክሏታል ፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ደግሞ ከሺህ ዘመን በኋላ እንዲወርሳት አሰናድቷል ፡፡ ለዚህም የመጀመሪያው ሰው ዕድሜ የሺህ ዘመን ድንበርን ይነካ ነበር ፡፡ እንደ ቀድሞ አሳብ ከሺህ ዘመን በኋላ በመታደስ መንግሥተ ሰማያት ይገባ ነበር፣ በኃጢአት ስለወደቀ ግን የሚሞትና ወደ ሲኦል የሚወርድ ሆነ ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሺህ ዓመት መንግሥትን ሲናገር ያ መንግሥት የአዳም መንግሥት ነበረ ፡፡ በኃጢአት ምክንያት ግን ለጊዜው ተሰናክሏል ፡፡ አሳቡ ከልካይ የሌለው ጌታ ግን አንድ ቀን ይፈጽመዋል ፡፡
ባለቤቱን ካላዩ መንግሥቱን ማየት አይቻልም ፡፡ ማየት ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው ፡፡ ማየት የብዙ ትርፎች መገኛ ነው ፡፡
    አጋር የሚያያትን በምድረ በዳ አየችው ፡፡ ስለዚህ ኤልሮኢ አለች /ዘፍ. 16፡13/፡፡ አጋር ሁለት ማየት ተፈጽሞላታል ፡፡ የመጀመሪያ በምድረ በዳ እግዚአብሔርን አየችው ፡፡ እግዚአብሔር የእልፍኝ አምላክ ብቻ ሳይሆን የምድረ በዳ አጽናኝም እንደሆነ ተረዳች ፡፡ ሁለተኛው እይታ ውኃ ፈልጋ ስታለቅስ ነው ፡፡ ነገር ግን የነበረችው በውኃ ዳር አጠገብ ነበር ፡፡ እግዚአብሔር የረዳት ውኃ በማፍለቅ ሳይሆን ዓይኗን በመክፈት ነው /ዘፍ. 21፡19/ ፡፡ የዓይን መከፈት የምናልፈውን ኑሮ እግዚአብሔር እንደሚያይ በማሰብ ያጽናናናል ፡፡ የዓይን መከፈት የምናለቅስበት ነገር ያላየነው በረከታችን እንደሆነ ያስረዳናል ፡፡ 
    ያዕቆብ እግዚአብሔርን በማየቱ ሰውነቱ ድና ቀረች ፡፡ ነገር ግን ያዕቆብ ያነክስ ነበር ፡፡ “ያዕቆብም፡- እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው።ጵኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር” /ዘፍ. 32፡30-31/፡፡ እያነከሱም ድኖ መቅረት አለ፡፡ እግዚአብሔርን በማየት ግርሻ የሌለው ፈውስ አለ ፡፡ ሁሉ ነገር ግን ሙሉ ነው ማለት ሳይሆን ማየቱ ከጉድለት በላይ ነው ፡፡
    የነቢዩ የኤልሳዕ አገልጋይ በዓይኑ የከበቧቸውን ሠራዊቶች አየ ፡፡ ኤልሳዕ ግን የከበቡትን የእግዚአብሔር ሠራዊት በእምነት ያይ ነበር ፡፡ በዓይኑ ያየው ብላቴናው ወዮልን አለ ፡፡ በእምነት ያየው ኤልሳዕ ግን “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ አለው” ብላቴናው ግን መረጋጋት አልቻለም ፡፡ ኤልሳዕም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ፡፡ “አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር” /2ነገሥ. 6፡15-17/፡፡ ኤልሳዕ በመጸለዩ የእግዚአብሔር ሠራዊት አልሠፈረም ፡፡ ኤልሳዕ ሠራዊት እንዲመጣ ሳይሆን የብላቴናው ዓይኖች እንዲከፈቱ ጸለየ ፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች የሚደፍሩት በወንድነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን የማይደፈር ቅጥር እያዩ ነው ፡፡ ዛሬም ከሚዋጉን የሚዋጋልን ፣ ከከበቡን የከበበን ይበልጣል ፡፡ የዓይን መከፈት በተከበበ ከተማ ዝማሬ ይሰጣል ፡፡
    ስምዖን አረጋዊ ጌታን በማየቱ መኖርን ጠገበ ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የበቃኝ ኑሮ ያለው እግዚአብሔርን በማየት ብቻ ነው ፡፡ የዓለም ደስታ ብዙ ሙከራ በመሆኑ ዘመንን ይጨርሳል ፡፡ እግዚአብሔርን ማየት ግን ያሳርፋል ፡፡ “ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና” /ሉቃ .2፡29-31/፡፡ ጌታ ገና የዐርባ ቀን ሕጻን ሳለ ስምዖን ታቀፈው ፡፡ ጌታ ምንም አላለውም ፡፡ ስምዖን ግን የንግግሩ መክፈቻ አሰናብተኝ አንተን አይቻለሁ የሚል ነበር ፡፡ ፊልጶስም፡- “አብን አሳየንና ይበቃናል” በማለት ጌታን ጠይቋል /ዮሐ. 14፡8/፡፡ በርግጥ ፊልጶስ ሌላ የሚበልጥ ክብር ናፍቆ ጠየቀ ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአብ ክብር ልክ እንዳለ አልተረዳም ነበር ፡፡ ይበቃናል የሚለው ልመናው ግን ግሩም ነው ፡፡ እግዚአብሔርን ካላዩ ይበቃኛል ማለት ከባድ ነው፡፡ አንድ እናት ደብረ ዘይት ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በእጃቸው ጨበጡ ፡፡ እጃቸውን በነጭ መሐረብ አስረው ሰው አልነካም ብለው ዋሉ ፡፡ ምነው ቢባሉ፡- “ንጉሥ በጨበጠ እጄ ሌላ አልጨብጥም” አሉ ይባላል ፡፡ ስምዖን አረጋዊም አንተን ባየ ዓይኔ ሌላ ማየት አልፈልግም ፡፡ አሁን አሰናብተኝ አለ ፡፡ አዎ ጌታን በሰበከ አፋችን ሌላ ሳናወራ ፣ ለእርሱ በዘመረ ምላሳችን ዓለምን ሳናወድስ ማለፍ ክብር ነው ፡፡
    ጌታችን ለኒቆዲሞስ ዳግም ልደት እግዚአብሔርንና መንግሥቱን የምናይበት ምሥጢር መሆኑን ነገረው ፡፡ ማየት ዋጋ አለው ፡፡ ያየ እንደ ቀድሞ አያስብም ፣ አይናገርም፣ አይኖርም ፡፡ የእስራኤል ልጆች የነሐሱን እባብ በማየት የሞት መንገድ እንደ ተሰበረላቸው በዚሁ ክፍል ለኒቆዲሞስ ተነግሯል /ዮሐ. 3፡14/ ፡፡ ማየት ማለት ማመን ማለት ነው ፡፡ ረቂቅ ነገርን የምናይበት መነጽር እምነት ይባላል ፡፡ 
 ይህን መንግሥትለማየት ዳግም መወለድ ያስፈልጋል ፡፡ ይህ ልደት እንዴት የማይባል በእግዚአብሔር አሠራር የሚከናወን ነው ፡፡ እንዴት የግል አቅምን ከእግዚአብሔር አቅም ጋር በማነጻጸር የሚመጣ ጥያቄ ነው ፡፡ እንዴት የፍልስፍና አስተሳሰብ ነው ፡፡ ከተፈጥሮ በላይ የሆነውን የእግዚአብሔርን አቅም አለመገንዘብና የእምነት ዓለም ክንውንን አለመቀበል ነው ፡፡ እንዴት የጥርጣሬና የኑፋቄ መነሻ ነው ፡፡ እውቀት ሁሉ እምነት ላይ ካልደረሰ አለማወቅና ድንበር የለሽ ይሆናል ፡፡ እግዚአብሔር ሁለት ነገር አይባልም  ፡፡ እንዴትና ለምን አይባልም ፡፡ እንዴት ችሎታውን መጠራጠር ነው ፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያደርግ እንጂ እንዴት እንደሚያደርግ መንገድ መሪ ፣ ምክር አበዳሪ መሆን አንችልም ፡፡ ለእግዚአብሔር ድንጋይ ሎሌው ባሕር አሽከሩ ነው ፡፡ ደመና መንኮራኩሩ ፣ ሰማያት ጎዳናው ነው ፡፡ እርሱ ይነሣ እንጂ የሚሳነው አንዳች ነገር የለም ፡፡ እግዚአብሔር “ለምን?” አይባልም ስንል “ለምን?” ማለት ይግባኝ መጠየቅ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የመጨረሻው ዳኝነት ደግሞም ሥራውን በጽድቅ የሚያከናውን ነውና ለምን? አይባልም ፡፡
 ኒቆዲሞስ ስለ ዳግም ልደት እንዴት? የሚል ጥያቄ አነሣ ፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህንን ሲመልስ ፡-
“እንዴት?” ማለት መሬታዊ የሆኑ ሰዎች ጥያቄ ነው፤እምነት የጎደላቸው ሰዎች የሚያነሡት የጥርጣሬ ጥያቄ ነው፡፡ ሳራም ሳቀች፣እንዴት? ብላ! እንዴት ተወለደ? እንዴት ሥጋ ሆነ? የሚሉ፣ እንዴት እንደሆነ ወደ ማወቅ ከፍታ ሳይወጡ፤በእምነት ጉዳይ የተጣሉ ሆነው በምንፍቅና ኖረዋል፡፡
ከሰው አፍ የሰው ቃል ሊሰማ  የመጣው ኒቆዲሞስ፤ከሰው አፍ ያልተሰማ ከፍ ያለውን ቃል ቢሰማ፡- እንዴት? አለ፡፡
ኒቆዲሞስ ደግም ካልተወለድህ ስለተባለ ዳግመኛ መወለድ እንደማይቻል ለማስረዳት ጣረ ­ከሸመገለ በኋላ ሰው ሁለተኛ ወደ እናት ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?
ስለመንፈሳዊ ልደት ሰማ፤ መንፈሳዊነቱን ግን አልደረሰበትም – ከፍ ያለው ይህንን ልደት እርሱ ወደ ሥጋ ዝቅታ አወረደው፡፡ጳውሎስ እንዳለ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነው ፡፡ /1ኛቆሮ 2፡14/፡፡
ዳግም ልደትና የእግዚአብሔር መንግሥት ለአይሁድ ጆሮ እንግዳ ትምህርት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር መንግሥት አሳብ ይልቅ፤ ዳግም ልደት የኒቆዲሞስን ቀልብ ሰርቆበታል፡፡
…እንዴት ከውኃ? የሚለኝ ካለ፤ እንዴት ከአፈር ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ ወጥ ከሆነው ከአንድ አፈር ምንያህል የተለያዩ ነገሮች እንደ ተሠራ ልብ በል … አጥንት፣ጅማት፤ አርተሪ የተባለ የደም ሥር፤ቬይን የተባለ የደም ሥር፣ጉበት፣ ጣፊያ፣ልብ፣ቆዳ ደም ኧረ ስንቱ! ይህ ሁሉ የተፈጠረበት ኃይል ከየት የተገኘ ይመስልሃል? … ከአፈር?… አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር እንጂ!
 አፈር ዘር ተቀብሎ ያበቅላል፤ከአፈር የተሠራው ሥጋ ግን ያጠፋዋል፤ አፈር ያስቀመጡበትን ይመግባል፤ሥጋ ግን ይመገባል፡፡ አፈር ውሃን ተቀብሎ ወይን፤ ሥጋ ወይን ተቀብሎ ውሃ ይመልስልሃል፡፡
ሰው ከምድር አፈር መበጀቱን በምርምር አልደረስንበትም በእምነት ግን ተቀብለናል፡፡ የአፈር ባሕርይ ከሥጋ ምን ያህል እንደተለየ ግን አስተውለሃል?
በየለቱ የምናያቸው፤ በየቀኑ የምንዳስሳቸውን ነገሮች ለመቀበል እምነት ካስፈለገን፤ ከዚህ ከፍ ያለውን እንዴታ! እንዴት?  አትበሉ፡፡
 ነፍስ አልባ ፣ እንቅስቃሴ አልባ የሆነው አፈር፣በእግዚአብሔር ኃይል ይህንን ያህል ታምራት ከተሠራበት የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከውኃ ጋር( በውኃው ላይ) ምን ሊያደርግ እንደሚችል አስብ!ነፍስ እንዳለን እናምናለን፣ ነፍሳችን ከሥጋ የተለየች እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ነፍስን የት አያችኋት? ግን አመናችሁ!
ሰው ከአፈር ቢበጅም የተበጀው በእግዚአብሔር ነው፤ አሁንም እንዲሁ ነው፤ከውኃ ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
ያኔ ሰው ሕያው ነፍስ ሆነ /ዘፍ 2፡7/፡፡ አሁን ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ … በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ነው /1ኛቆሮ 15፡45/፡፡
ያኔ የፍጥረት መካተቻ ሆነ፤ አሁን ግን ቀደምን፤ያኔ ረዳት እንፍጠርለት /ዘፍ 2፡18/ ብሎ ነበር፤ አሁን ግን እንዲህ አይደለም ፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከተቀበልን ምን ረዳት ያስፈልገናል! ለክርስቶስ አካል ብልት የሆንን ምን አጋዥ ያስፈልገናል?ያኔ፤ በእግዚአብሔር ምሳሌ አበጀው፤ አሁን ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ አደረገን፡፡  ያኔ በእንስሳቶች እና በአራዊት ላይ እንዲገዛ አደረገው፤ አሁን ከሰማያት በላይ አወጣን! ያኔ፤ ገነትን መኖሪያ አድርጎ ሰጠው፤ አሁን ሰማይን ከፈተልን፡፡የሆነልን ያለገደብ የተሻለ እንደሆነ አስተውል፡፡
 ኒቆዲሞስ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው”/ዮሐ. 3፡4/ ፡፡ እንዴት የሚል ጥያቄ በዘመናት ተነሥቷል ፡፡
    ሳራ በዘጠና ዓመቷ እንደምትወልድ ሲነገርላት እንዴት በማለት የዘበት ሳቅ ሳቀች ፡፡ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ሳቅን ይሰጣልና የልጁ ስም ይስሐቅ ተባለ /ዘፍ .18፡12-15/ ፡፡
    በሰማርያ በተነሣው ራብ የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ ነገ ጥጋብ እንደሚሆን ሲናገር የንጉሥ ሎሌ እንዴት የሚል ጥያቄ አነሣ ፡፡ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም፦ እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ”/2ነገሥ. 7፡2/፡፡
    እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደምትጸንስ መልአኩ ሲነግራት፡- “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው”/ሉቃ. 1፡34/፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ሲላት ግን አረፈች ፡፡ “እንዴት” የሚለው ጥያቄዋን የእግዚአብሔር ቻይነት መለሰው ፡፡ እግዚአብሔር እንዴት እንደማይባል ታውቃለች ፡፡ ሁሉን ማድረግ ይችላል ፡፡
    ኒቆዲሞስም፡- “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?”አለ ፡፡ እንዴት ዛሬም ያላባራ ጥያቄ ነው ፡፡ ግን እንዴት ማለት የማንችልባቸው ተፈጥሮን ተሸክመናል ፡፡ እንኳን መንፈሳዊውን ዓለም ግዙፉን ዓለምም በእምነት መቀበል ያስፈልገናል ፡፡

ያጋሩ