የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የናሱ እባብ

“ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” /ዮሐ. 3፡14-15/፡፡
ከላይ ሳይጎድል ከታች ሳይጨመር ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መታጣት ሳይኖርበት ወረደ የተባለለት ፣ በምድር እየታየ በሰማይ ይኖራል ተብሎ የተነገረለት ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው አማኑኤል ኒቆዲሞስን ሳይነቅፍ በብዙ ትዕግሥት አስተማረው ፡፡ እስኪያውቁት ሰዎችን የሚታገሥ ፣ አላወቁም አላገኙም ብሎ የማይንቅ በማስተማሩና በመስጠቱ ማንንም የማይተች ክርስቶስ ፣ የዳግም ልደትን ምሥጢር ለኒቆዲሞስ አብራራለት ፡፡ ኒቆዲሞስ ሳይገባውም ይሁን አልምጦ በጠየቃቸው ጥያቄዎች እኛ የተሟላ ትምህርት አግኝተናል ፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ባሕርይ ይህ ነው ፡፡ ጌታችን ለተቃዋሚዎችና እውነትን ለማይቀበሉ ወገኖች ለክርክራቸውና ለጥያቄአቸው በሰጠው መልስ የሥላሴና የሥጋዌ ምሥጢር ተብራርቷል ፡፡ “ድንጋይን ምን ያስጮኸዋል ቢሉ ውኃ” ይባላል ፡፡ እነዚህም ተሟጋቾች እነርሱ ለመቃወም ጠየቁ ። ጌታ ግን በፍቅር ስለ መለሰ ፤ ለእኛም ትልቅ ትምህርት ሆነ ፡፡ የጠየቁ ሁሉ ተጠቃሚዎች አይደሉም ፡፡ መልሱን ካልተቀበሉ ጥያቄው ጥያቄአቸው አልነበረም ማለት ነው ፡፡ ቢሆንም ጌታ አንዱን አስጠይቆ አንዱን ያጠግባል ፡፡ ዓለም ሁሉ እየኖረ ያለበት ሥርዓት ይህ ነው፡፡
ዳግም ልደት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር ጽኑ ኅብረት አለው ። ጌታችን የናሱን እባብ ምሳሌ ያመጣው ለዚህ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ስለ እኛ ባይሞት ኖሮ የዳግም ልደት ዕድልን ባላገኘን ነበር ። ዳግም ልደት ከእምነትና ከጥምቀት ጋር የተያያዘ ነው ። የምናምነው ምንድነው ? ስንል የክርስቶስ ፍጹም መድኃኒትነትን ነው ። ጥምቀት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር የምንተባበርበት ነው /ሮሜ. 6፡4/ ። ተምሳሌትነቱ ወደ ውኃው መጥለቅ ከክርስቶስ ጋር መቀበር ነው ። ከውኃው መውጣት ደግሞ ከክርስቶስ ጋር መነሣት ነው ። ይህንን ግዙፍ በሆነው ውኃ ሥርዓት ማሳየት ለምን አስፈለገ ? ስንል ሥጋም በክርስቶስ ሞት የተዋጀ ስለሆነ ነው ። ስለዚህ ግዙፍ ሥርዓት ግዙፉን ሥጋ አድራሻ አድርጎ ይፈጸማል ። ዳግም ልደት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር ጽኑ ቁርኝት አለው ። ጌታችን ለኒቆዲሞስ፡- “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ ?” በማለት ተናግሯል /ዮሐ. 3፡12/ ። 1ኛ ዮሐ. 5፡6-7 በአንዳንድ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ለየት ያለ ገለጻ አለው ። በአገራችንም በ1886 የታተመው የአባ አብርሃም ትርጉም እንዲህ ይላል፡- “በሰማይ የሚመሰክሩ < /i>ሦስት ናቸውና እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስም። እሌህ ሦስትም አንድ ናቸው ። በምድርም የሚመሰክሩ ሦስት ናቸው እርሳቸውም መንፈስ ውኃም ደምም። ሦስቱም ባንድ ይገድማሉ” ።
በዚህ ትርጉም መሠረት ከሄድን ጌታችን ስለምድራዊ ነገር ብነግራችሁ ያለው ስለ መንፈስ ውኃና ደም ነው ። ስለ ሰማያዊ ነገር ያለው ደግሞ ስለ ሦስትነትና ስለ አንድነት ምሥጢር ነው ። ምድራዊ መባላቸው በምድር ላይ የሚፈጸሙና ግዙፍ ሥርዓትም ስላላቸውነው ።
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ እስከ ከነዓን ብዙ ማጉረምረም አሰምተዋል ።። ማጉረምረም ብዙ ጊዜ በአራዊት ላይ የሚሰማ በቤት እንስሳም በውሻ ላይ የምንሰማው ድም ነው ። የማጉረምረም መነሻ ረሀብ የፈጠረው ውጫዊ ቁጣ ነው ። ማጉረምረም በሌላ ስፍራ ማንራጎር ተብሎ ተጠቅሷል ። ማንጎራጎር ዜማ ያለውና ሰውዬው ለመውጣት የሚቸገበት ሱስ ነው ። የሚያንጎራጉሩ ሰዎች በሌለበት ዘመን ስለ ሞቱ ሰዎች ያለቅሳሉ ፡፡ ለማልቀስ ምክንያት ስለሚፈልጉ ማንኛውም ክፉ ነገር ግብዓታቸው ይሆናል ። ካላለቀሱ ይታመማሉ ። ሲያለቅሱ የሚቀላቸው ይመስላቸዋል ። ነገር ግን በኀዘን ድባብ ውስጥ በልቅሶ ሸለቆ እንዲያፉ ያደርጋቸዋል እንጂ አይቀላቸውም ። ማጉረምረም ስሜት ከመሆን አልፎ ሕይወት ይሆናል፡፡ ምን ይከሰታል ስንል ሰበበኛነት ለሁሉም ነገር ጎዶሎን መፈለግ ያመጣል ፡፡ የእስራኤል ልጆች ያለፉቸውን ማጉረምረሞች ስናይ ንስኤውንና መገለጫውን ማየት እንችላለን ፡፡
1-  ከአዲሱ መልካም የኖረውን ክፉ ታርቆ ለመኖር መወሰን
       
       ይህ አስተሳሰብ ማጉረምረምን ያመጣል ፡፡ ዕድሌ ይህ ስለሆነ የሰጠኝን ተቀብዬ መኖር አለብኝ በሚል ስሜት የሚያልፉ ሰዎች ለጠላትና ለክፉ ገጠመኝ በመሸነፍ ስሜት እያጉረመረሙ ይኖራሉ ፡፡ እነዚህ ሰዎች ነጻ ለመውጣት አያስቡም ፡፡ ነጻ ላውጣችሁ የሚለውንም ወገን በጥላቻ ይመለከታሉ ፡፡ የበለጠ ቀንበርን ታጸናብኛለህ በሚል ስሜት ይሸሹታል ፡፡ ማጉረምረም ክፉ ገጠመኝን እንደ እግዚአብሔር ስጦታና እንደ ተፈጥሮ ዕድል የማየት ባሕርይ አለው ፡፡
2 አጣብቂኝ ቀኖች ማጉረምረምን ይፈጥራሉ ፡፡
         ወደ ኋላ ለመመለስ ጠላት ወደት ለማለት የእምነት ማነስ ሲገጥም ማጉረምረም ይከሰታል ፡፡ ይህን ጉዞ አልጀምርም ብዬ የነበረው እውነቴን ነበር በሚል ስሜት ማዘን ይጀመራል ፡፡ ነገር ግን የአሜሪካው መሪ የነበሩት ሰው እንደ ተናገሩት፡- ተንበርክኮ ከመኖር ቆሞ መሞት ይሻላል፡፡ ማጉረምረም ግን መከራውን በሚፈራበት መጠን የድል ትግልንም ይፈራል ፡፡
2-  መልካሙ ሲመርር ማጉረምረም ይከሰታል፡፡
         ማጉረምረም የማጣት ብሶት ብቻ አይደለም ፡፡ የፈለጉትን ነገር ጣዕሙ ትንሽ ሲሆንም የሚሰማ መከፋት ነው ፡፡ የእስራኤል ልጆች ውኃ ፈለጉ ውኃው ግን መራራ ስለነበር አጉረመረሙ ፡፡ መራራነቱ ገዳይ አልነበረም፡ ግን ለምኞታቸውና ለፍላጎታቸው አለቀሱ ፡፡ በአንድ ልቅሶ ላይ ለሰውዬው ሳይሆን ለምኞቱ ይለቀሳል፡፡ ትዳር አስቦ ሠርጉ እየተደገሰ ቢሞት ለምኞቱ ይለቀሳል ፡፡ ከሰውዬ ይልቅ ለምኞቱ እንደሚለቀስ እስራኤል ከሁነቱ ይልቅ በጋለ ስሜት ለመፈለጋቸው አለቀሱ ፡፡ እግዚአብሔር ግን ያደረገላቸው በሰባ ዘንባባ ዛፍ ሥር እንዲያርፉ አደረገ ፡፡ ከዚያ የተፈወሱ ምንጮችን አሳያቸው ፡፡ ለማጉረምረም ማረፍና ማሰላሰል ትልቅ መፍትሔ ነው ፡፡
4 የወደዱትን በመጥላት ማጉረምረም ውስጥ ገብተዋል ፡፡
         ፍቅርም ሆነ ጥላቻ እውነት ሳይሆኑ ስሜት የሚሆኑበት ጊዜ አለ ፡፡ የእስራኤል ልጆች መሪያቸው በነበረው በሙሴ ላይ ውኃን ሰበብ አድርገው ማጉረምረም ጀመሩ ፡፡ ሙሴ ዕዳው ምንድነው ማለት እንኳ አልቻሉም ፡፡ ማጉረምረማቸው ግን ሙሴን እንዲሰናከል አደረገው ፡፡ ተፈትነው ፈተኑት ፡፡ ስለዚህ ጣሉትና የተስፋይቱን ምድር ሳይወርስ ቀረ ፡፡ ማጉረምረም በአጠገብ ላሉ ሰዎችም መሰናክል ይሆናል ፡፡ ሁሉም ነገር ጨለማ ሁኖ እንዲታያቸውና ሕይወትን እንዲጠሉ ያደርጋል ፡፡ ማጉረምረም አካባቢውን ጨጋግ የማልበስ አቅም አለው ፡፡
5- መና ሰለቸን በማለት እግዚብሔርን አስቆጡት ፡፡
    
    የእስራኤል ልጆች እስካሁን ባለው ማጉረምረማቸው እግዚአብሔር ቢያዝንም ሕይወትን የሚጎዳ ቅጣት አላከባቸውም ፡፡ አሁን ግን የበረሃ እባብ ልኮ በሞት ቀጣቸው፡፡ የእርሱን በረከት ከሰማይ የወረደውን መና አቃለዋልና በዚህ ምክንያት ሞት ተሰደደባቸው ፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ሙሴ መጥተው እግዚአብሔርንም እርሱንም እንዳሳዘኑ ነገሩት፡፡ ሙሴም በሕዝቡ ጥያቄ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ፡፡    እግዚአብሔር የሰጠው መመሪያ ግን የናስ እባብ በዓላማ ላይ እንዲሰቅልና የተነደፈው እርሱን በማየት እንደሚድን ነገረው ፡፡ ሙሴም የነደፋቸውን እባብ የሚመስል የናስ እባብ ሠራ፡፡ የናሱ እባብ ጽሩይ ነው ፡፡ ያንን ጽሩይ እባብ በዓላማ ላይ ከፍ ባለ ማማ ላይ ሰቀለው ፡፡ በመርዙ የተነደፉ ግማሹ በቤት ግማሹ በአደባባይ ወድቀዋል ፡፡ በቤት ያለው ድንኳን ግለጡልኝ በማለት በአደባባይ ያለው ዓይኑን በማቅናት በቀላሉ ሲያየው በሕይወት ይኖር ነበር ፡፡
    
    ቅድም የነደፋቸውና ለሞት ያበቃቸውን እባብ ይመስላል ፡፡ ነገር ግን የናሱ እባብ ለመንደፍ የማይኖርና እባብ ተብሎም መርዝ የሌለው ነው ፡፡ ከሚታወቁት እባቦች ልዩ ነው ፡፡ በዓላማ ላይ የተሰቀለው ያ የነደፋቸው እባብ ቢሆን የት አባቱ በማለት የበቀል ስሜታቸው ይነሣሣል ፡፡ የሞቱበት እባብ ግን የሚድኑበት አይሆንምና ልባቸው መልሶ ይዝላል ፡፡ ቅድም ያልነደፋቸው መልኩ ግን ነዳፊውን እባብ የሚመስለውን ጽሩይ ንጹ እባብ ሲያዩ ግን በፍቅር ይሞላሉ ፡፡ ሳይገባው ያለ ጥፋቱ ለምን ተሰቀለ ብለው ሲጠይቁ ሞት የሚገባን እኛ እንድን ዘንድ ሞት የማይገባው ይህ የናስ እባብ ተሰቀለ በማለት የፍርድ ሚዛኑ በኅሊናቸው ይስተካከልላቸዋል ፡፡
ያን የናስ እባብ በማየት ብቻ በሕይወት መኖር አለ ፡፡ በማየት ውስጥ ተራ ማየት ሳይሆን ለምንና ለማን ተሰቀለ መንስኤውስ ምን ነበር የሚል ንስሐና መታዘዝ አለው ፡፡ የናሱ እባብ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር ፡፡ ይህንን የተናገረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ፊተኛውና መርዛሙ እባብ ግን የአዳም ምሳሌ ነው ፡፡ አዳም የኃጢአት መነሻ ምክንያት ነው ፡፡ አዳም ቢሰቀል በቀል እንጂ ቤዛ ሊሆን አይችልም ፡፡ የበደለ ቢሰቀል ጥቅም የለውም ፡፡ የራሱንም ስህተት ዋጋ አይከፍልም ፡፡ ፋተኛ ሲቀጣ እንዲታመም እንጂ ያጠፋው ነገር እንዲካስ አይደለም፡፡ እንደውም ሃያ ዓመት ታስሮ እርሱን መቀለብ ተጨማሪ ኪሣራ ነው ፡፡ ጌታችን በሚሰቀል ቀንም ሞት የተፈረደበትና ሞት የሚገባው አንድ እስረኛ ቀርቦ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሁነን ስናስው በርባን እንኳ አልሞተ ፡፡ በርባን ቢሞት ለእኛ ምንም ጥም አልነበረውም ፡፡ የገደላቸው ሰዎች እንኳ አይነሡም ፡፡ ክርስቶስ በመሞቱ ግን ይኸው ዓለም ዳነ ፡፡ የናሱ እባብ የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፡፡ የናሱ እባብ በአርአያ እባብ ቢገለጥም በዚህ ዓለም ላይ ሌላውን ለማጥቃት ኑሮ አያውቅም ፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ማንንም ለመበደል አልኖረም ፡፡ እባብ ተብሎ መርዝ የሌለበት የናሱ እባብ እንደሆነ ሰው ተብሎም እንከን ያልተገኘበት እርሱ ክርስቶስ ነው ፡፡ እንከን የሌለበት ክርስቶስም በዓላማ ላይ ወይም ከፍ ብሎ በእምነት መነጽር ለሚያዩት የሕይወት ምክንያት ሁኗል ፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባብ ሰቀለ ፡፡ ሙሴ ደግ ሳለ ያልበደለው እባብ እንዲሰቀል ጨከነ ፡፡ ደጉ አብም ያልበደለ ልጁ ቤዛ እንዲሆን ፈረደ ፡፡ የማይገባውን ሞት ካልተቀበለ የማይገባንን ሕይወት ማግኘት አንችልም ፡፡ ክርስቶስም የጽድቅ ምድረ በዳ በሆነችው ዓለም ላይ ስለ እኛ ተሰቀለ ፡፡ የሰው መዳን ከተፈለገ የክርስቶስ መሞት ግድ ነበረ ፡፡ ክርስቶስ ብቻ የመለኮትን ፍትሕ አርክቶ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለዓለም ይገልጣል፡፡ ምክንያቱም እርሱ ራሱ አምላክ ነውና ፡፡
        
 ዳግም ልደትም በእምነት ላይ ይመሠረታል ፡፡ ይህ እምነትም በተሰቀለው ጌታ ማመን ነው ፡፡ ይህ ነገር ለዓለም ሞኝነት ነው ፡፡ ምልክት የሚሹ አይሁድ ጥበብ የሚፈልጉ አሕዛብ ሊቀበሉት የሚቸግራቸው ነገር ነው ፡፡ በሚገድል ጌታ ማመን እንጂ በተሰቀለ ጌታ ማመን ሞነት ነው፡፡ በዚህ ሞኝነት የሚያምኑ በሕይወት ይኖራሉ ፡፡ ማመን ማለት ለእግዚአብሔር ሞኝ መሆን ማለት ነውና ፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ውስጥም የእግዚአብሔር የፍርዱ ጽኑነት ታይቷ ፡፡  እግዚአብሔር ፍቅርን የሚገልጠው ራሱን አክብሮ ጻድነቱን ጠብቆ ነው ፡፡ የጻድነቱን ፍርድ ደግሞ ሰው ሊከፍልና ሊቋቋም አይችልም ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አንድ ልጁን በባሪያ መልክ ላከ ፡፡ የናሱን እባብ በእባብ መልክ እንዲሠራ እንደ አዘዘ ማለት ነው ፡፡ አንድ ትልቅ ምግብ ቤት ያለውን ሰው እናስብ፡፡ በምግብ ቤቱ ውስጥ ያገኘውን እንግዳ ከፍሎ ይጋብዛል፡፡ ለሚያየው ሞኝነት ይመስላል ፡፡ እንዲያ ማድረጉ የሠራተኞቹን ኅሊና የሒሳብ ዝውሩን ጤናማ ያደርገዋል ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር ሰው ሁኖ ስለ እኛ ተሰቀለ ማለት ለአንዳንድ ሰው ሞኝነት ይመስለዋል ፡፡ ይህን ማድረጉ ግን መላእክትንም የሚያስገርም ራሱንም የሚያከብር ነው ፡፡ ያ ባለጠጋ መልሶ የሚያገኘውን ገንዘብ አሁን መክፈሉ ሒሳቡን ትክክል ያደርገዋል ፡፡ ወዲህ ደግሞ እንግዳውን ማፍቀሩን ይገልጣል ፡፡ እንዲሁም ጌታችን በመሞቱ የሰው መዳን ሕጋዊ ይሆናል ፡፡ የእግዚአብሔርም ፍቅር ለዓለም ይገለጣል ፡፡ ለዚህ ነው ክርስቶስ በመሞቱ እግዚአብሔር ዓለምን አፈቀረ የተባለው ፡፡
የፍርዱን ተአምር አየነው
ልጁን በመስቀል አገኘነው
የተባለው ለዚህ ነው ፡፡ የሌላውን ደረት እየመቱ ኀዘናውን ቢገልጡ እውነተኛ አፍቃሪ አይባሉም ፡፡ የገዛ ደረታቸውን እየመቱ ቢያለቅሱ ግን እውነተኛ አፍቃሪ ይባላሉ ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር መልአክን ሥጋ አስለብሶ እንዲሞት ቢያደርግ ነቢይን አሰይፎ ላድናችሁ ቢለን ፍቅር ነው ለማለት እንቸገር ነበር ፡፡ በአንድ ልጁ ቤዛ መድኃኒትነት የፍቅሩን ታላቅነት አየነው ፡፡  
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ