የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አምላከ ብርሃናት

 
 
 
 
“ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው” /ዮሐ. 3፡19/።
 
ፍርዱ ያለው በምርጫ ውስጥ ነው ። እግዚአብሔር በማንም አይፈርድም ። ሰውን የሚፈርድበት የገዛ ምርጫው ነው ። መንፈሳዊ ሕይወት ግር የምታሰኝ የፈላስፎች ትንታኔ የሚያስፈልጋት አይደለችም ። ብርሃንና ጨለማ ናት ። ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ግድ ነው ። ሦስተኛና ገለልተኛ ስፍራ የለም ። በብርሃን ውስጥ መሆን በጨለማ ውስጥ አለመሆን ነው ። በጨለማ ውስጥ ያለውም በብርሃን ውስጥ የለም ። ጌታችን ወደ ዓለም የመጣው ብርሃን ሁኖ ነው ። አብ ፀሐይ ነው ፣ ወልድ ብርሃን ነው ፤ መንፈስ ቅዱስ ሙቀት ነው ። የፀሐይ አካል በስፍራው እንዳለ አብም ከስፍራው አይናወጥም ። የፀሐይ ብርሃን ከፀሐይ አካል ወጥቶ ፣ ከፀሐይ አካል ሳይለይ ወደ ምድር እንደሚመጣ ወልድም ከአብ ወጥቶ ከአብ ሳይለይ ወደዚህ ዓለም መጥቷል ። የፀሐይ ብርሃን በዚህ ዓለም በመምጣቱ መልኩን እንደማይቀይር ፣ በቆሻሻ ቦታ በመውጣቱ እንደማይቆሽሽ ፤ ወልድም ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም በመምጣቱ ከክብሩ አልቀነሰም ፣ ከቅድስናው አልጎደፈም ። የፀሐይ ብርሃን በዚህ ዓለም ላይ ሲመጣ በራቸውን የዘጉ ዓይናቸውን የጨፈኑ እንደማያዩት እንዲሁም ወልድ በሥጋ ሲመጣ ያላመኑት አይሁድና መናፍቃን ሊያርፉበት ሊደሰቱበት አልቻሉም ።

 

ጌታችን ራስን የሚያሳይ ብርሃን ሁኖ ወደዚህ ዓለም መጥቷል ። ትሕትናን የምንማረው ራስን በክርስቶስ በማየት ነው ። ሌላውን ለማየትማ ፀሐይና ጨረቃ በቂ ነበሩ ፣ ክርስቶስ ግን ውስጣዊ ብርሃን ሁኖ መጥቷል ።
 
ንጹሕ መስተዋት እንጂ ቆሻሻ መስተዋት ፊትን እንደማያሳይ እንዲሁም ኃጢአታችንን አይተን ለንስሐ የምንበቃው በጌታችን የቅድስና ብርሃን ፊት ስንቆም ነው ። በቀራንዮ ፍቅር ፊት ካልቆምንም ለንስሐ አንበቃም ። የተዘረጉ እጆች ከሌሉ የበደለኛ እግሮች አይፈጥኑም ። ሌሎች ብርሃናት ያራቁታሉ ፣ እርሱ ግን ብርሃኑ ልብስ ነውና ይሸፍነናል ። ሰዎች ትልቁ ክፋታቸው ትሑት ሁኖ የመጣውን ጌታ መቀበል አለመቻላቸው ነው ። ትዕቢተኛውን ልባቸውን ፣ ትዕቢተኛውን ሰይጣንና አላውያን ነገሥታትን ሲታዘዙ ይህን ትሑት አምላክ ግን ገፍተውታል ። ሰዎች ክፉን ለማድረግ አጋዥ አይፈልጉም ፣ መልካም ለማድረግ ግን ረድኤተ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልጋቸዋል ። ያ ብርሃን በማለዳ ሲመጣ ጨለማውን ፈርቶ በሩን የቆለፈ እየደፈረ ይወጣል ። እንዲሁም እኔ አልችልም ብሎ በራሱ ተስፋ የቆረጠ ብርሃን ክርስቶስ መጥቷልና ሊወጣ ይገባዋል ።
 
ሰዋዊ ጽድቅ ከእግዚአብሔር ጽድቅ ይለያል ። ሰዋዊ ጽድቅ በብልሃት የተጠለፈ እንዲመስል ተብሎ የተደከመበት ነው ። ውጤቱም ማኅበራዊ ከበሬታን ፈላጊነት ነው ። የእግዚአብሔር ጽድቅ ግን ልብን በመለወጥ የሚጀምር በውስጣችን የሚበራ መንፈሳዊ ብርሃን ነው ። ሰዋዊ ጽድቅ ከላይ በካባ በነጠላ ይሸፈናል ፣ ውስጡ ግን ሽፍታ ይሆናል ። ይህንን በምን እንለያለን ? ስንል በቃሉ ነው ። የዕብራውያን ፀሐፊ ፡- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል” ይላል /ዕብ. 4፡12/ ። የእግዚአብሔር ቃል የመለየት ሥራ ይሠራል ። የሚለየውም ነፍስና መንፈስን ነው ። ነፍስ የእኛ አዋቂ ማንነት ነው ። መንፈስ ደግሞ እግዚአብሔር ነው ። የእኛን እውቀት ከእግዚአብሔር ምሪት የሚለይልን ቃሉ ነው ። ሰዎች ክፋታቸውንም ከእግዚአብሔር ጋር ለማያያዝ ይፈልጋሉ ። የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ ሲል እግዚአብሔርን የሐሰት ተባባሪ አታድርገው ማለቱ ነው ። ሰዎች የራሳቸውንም እውቀትና ስሜት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይቀላቅላሉና ቃሉ ነፍስና መንፈስን ይለያል ። ነፍስና መንፈስን መለየት አለመቻል ለሐሰተኛ ሕልም፣ ራእይን ትንቢት ሁሉ ያጋልጣል። የምናስበውን መንፈስ ቅዱስ ያሳሰበን እየመሰለን መጥፋት እንጀምራለን ። መንፈስ ቅዱስ ግን ቃሉን ሊያፀና እንጂ ሊቃረን አይመጣምና በቃሉ መመዘን ያስፈልገናል ። ዛሬ በምዕራባውያን ቅኝት ወንጌልን እንሰብካለን የሚሉ ወገኖች መጽሐፍ ቅዱሱን በማንጠልጠል ፡- “ከዚህ ከወረቀቱ እንንገራችሁ ወይስ እንደ ወረደ እንንገራችሁ” በማለት በአደባባይ ይናገራሉ ። ጌታችን መንፈስ ቅዱስ እንደሚመጣ ሲናገር ከራሱ ምንም እንደማይነግረን የክርስቶስን ቃላት ግን እንደሚያሳስበን ተናግሯል ። ደግሞም ጌታችን የመገለጥ መጨረሻ ሁኖ መጥቷል ። ከዚህ የሚበልጥ ምን ዓይነት አዲስ ነገር ልንሰማ እንችላለን ? የጌታን ቃላት መንፈስ ቅዱስ የሚያሳስበን ከሆነ እኛ እንዴት ከቃሉ በላይ እንሆናለን ?
 
የእኛም የጽድቅ መለኪያ በጣም የሚያሳዝን ነው ። እገሌ ጻድቅ ነው ምግብም አይበላም እንላለን ። ይህን ከማድነቅ በሥርዓቱ እንዲመገብ መምከር አለብን ። በቀጣይ ዘመናት ፀንቶ እንዲያገለግል ራሱን በተገቢው መንገድ መንከባከብ አለበት ። አገልጋይ በጸጋ የከበረ እንጂ ሰውነቱን የለቀቀ አይደለም ። እንደ ሰው መመገብ መልበስ አለበት ። በፊት ለፊታችን የሚበሉትን አባቶች እየናቅን በጓዳ እየበሉ በፊታችን ግን ትሕርምት የሚያበዙትን እናከብራለን ። የተውኔት ጽድቅ አጃቢና የማስታወቂያ ሠራተኛ ይፈልጋል ። ማስታወቂያ ግን የጥራት ማረጋገጫ ሳይሆን ማሟያም ሆኖ ያገለግላል ። የምናደርገውን ስለ እግዚአብሔር ብለን እንደምናደርገው ለማረጋገጥ ወደ ብርሃን ጌታ መምጣት አለብን ። ሐኪም ጋ የታመመ ብቻ ሳይሆን ያለበትን ደረጃ ለማወቅም የሚመጣ አለ ። ሁሉንም የሚመረምር ጌታ አለ ። እርሱ ደግሞ የፈጠረን ስለሆነ በትክክል በሽታችንን ያውቀዋል ። በውስጣችን ሕመም ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ የተስማሙን በሽታዎችም አሉ ። የሕመም ስሜት ካለ ፈጥኖ መዳን ይቻላል ። ሕመም አልባ የሆኑት ግን ራሳችንን ካላስፈተሽን የጣሉን ቀን መነሻ የለንም ። ከሚያመን ስህተት ይልቅ ጥቅስ ያለው ስህተት የበለጠ ይጎዳናል ። ነቢዩ እግዚአብሔርን ሐኪሙ አድርጎ ፡- “አቤቱ፥ ፍተነኝ መርምረኝም ኵላሊቴንና ልቤን ፍተን” ይላል /መዝ. 25፡2/። ዳግመኛም፡- “አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ” ይላል /መዝ. 138፡1-3/ ። ይህ መመርመር ፖሊስ ወንጀለኛን እንደሚመረምረው ዓይነት መመርመር ሳይሆን ሐኪም እንደሚመረምረው ያለ መመርመር ነው ። ፍተነኝ ይላል ። ሐኪም መታ መታ እያደረገ የሰውነት ክፍሎችን እንደሚፈትን የሚሠራና የማይሠራ ነገሬን ፍተን እያለ እየጸለየ ሙሉ ፈቃዱን እየሰጠ ነው ።
 
“ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” /ዮሐ. 3፡20-21/።
 
ጨለማ ሌቦችንና ዓመጸኞችን እጅግ ይረዳቸዋል ። የተፈጥሮ ብርሃን እንኳ ወንጀልን ይከላከላል ። ብዙ ስርቆቶችና ግድያዎች የሚፈጸሙት ጨለማን ተገን ተደርጎ ነው ። የተፈጥሮ ብርሃን ወይም የቀኑ ፀሐይ ወንጀልን ከተከላከለ እውነተኛውና ፈጣሪ የሆነው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት ማዳኑ እርግጥ ነው ። የፀሐዩ ብርሃን ወንጀልን የሚከላከለው በማስፈራራት ወይም ሰው ያይሃል በማለት ነው ። አምላከ ብርሃናት ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ውስጥን በመለወጥ ከኃጢአት ያድነናል ። የፍቅር ሠራተኛም ያደርጋል ። ዓለሙ ወደዚህ ብርሃን የማይመጣው ብርሃኑ ክፉ ስለሆነ አይደለም ። የብርሃን ክፉ የለውምና ። አንዱን ብርሃን ሌቦች ይሸሹታል ፣ ንጹሐን ይፈልጉታል ። አንዱን ብርሃን አራዊት ይፈሩታል ፣ ሰዎች ይሰማሩበታል ። ከእውነት ጋር ላለመገናኘት ተጠንቅቀው የሚጓዙ ሰዎች ይህን ብርሃን ይሸሹታል ። ብርሃኑ ጽድቅና ክብር የተሞላ ነው ።
 
ክፉ የሚያደርጉ ከብርሃን ሲሸሹ መልካም የሚያደርጉ ደግሞ የሚያደርጉት መልካም በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ለማረጋገጥ ወደ ብርሃን ይመጣሉ ። ከክፉ በላይ መልካም የመሰለው ክፉ የመጉዳት አቅም አለው ። ዕድሜንም የሚበላ ብል ነው ። በሳጥን ውስጥ ያለ ብል የበላው ልብስ በቁመቱ ልክ ፣ በጥለቱ ድምቀት ተዘርግቶ ይታያል ። ሊያነሡት ሲሉ ግን ይበታተናል ። ብል የበላው ዕድሜም እንዲሁ ነው ። ያለ ይመስላል የሞተበት ዘመን አይታወቅም ፣ አንድ ቀን ግን መቆም ሲያቅተው ፣ ሌላውን ማልበስና ማስጌጥ ሲሳነው ወንድሙን እህቱን መከለል አልችል ሲል እንደነተበ ይታወቃል ። እንዲሁም የወየበ ልብስ በጥንካሬው አለ ፣ በመልኩ ግን የለም ። የወየበ ዕድሜም መንፈሳዊ አገልግሎቱና ሩጫው አለ ። ደስታውና ሰላሙ መንፈሳዊ ክብሩ ግን የለም ። ወደ ብርሃኑ የሚመጡ መንፈሳውያን ሽልማትን ፈልገው ሳይሆን የማደርገው መልካም ነገር ባንተና ላንተ የተደረገ ነው ወይ ? ብለው ሊጠይቁ ይገባቸዋል ። ነቢዩ መርምረኝ ያለው ለዚህ ነው ። የሕክምና ምርመራ ልምድ ያላቸው ሰዎች በዕለት  አንዳንዶች በወር ሌሎችም በመንፈቅ የቀሩትም በዓመት አንድ ጊዜ ያደርጋሉ ። በሰለጠነው ዓለምም ተቋማት ሠራተኞቻቸውን ያስመረምራሉ ። የምናደርገውን መልካም ነገር ፡-
 
1-  በእግዚአብሔር የተደረገ ነው ወይስ በጉልበት የተደረገ ነው ? ብሎ መመዘን ያስፈልጋል ።
2-  ያደግሁት ለእግዚአብሔር ክብር ነው ? ወይስ የሰዎችን ሙገሳ በመፈለግ ለተጨማሪ ዘረፋ ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ። የቀበሮ ባሐሕተታወዊሐሕሕታዊ ፣ የድመት መነኩሴ መሆን አይገባም ። “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ ።
3-  የማደርገው መልካም ነገር የሰዎችን ምላሽ ካጣ ይቆማል ወይስ እግዚአብሔርን ብቻ እያየ ይቀጥላል ? ለወደዱኝ ማር ነኝ ፣ ለጠሉኝ እሬት ነኝ የሚለው የሰው ጽድቅ ነው ።
 
 መልካም ተግባሮችን ብቻ ሳይሆን የምናስተምረውን ትምህርትና የተገለጥንበትን ጸጋ በእምነት ለቀደሙን አባቶች ፣ በእውቀት ለበረቱ መምህራኖች ማስገምገም ይገባናል ። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚያስተምረውን ትምህርት ይገመግሙለት ዘንድ ወደ ዋነኞቹ ሐዋርያት ይዞ ሲመጣ በ14 ዓመት የአገልግሎት ልምዱ አልተመካም ። “ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው” ይላል /ገላ. 2፡1-2/። ጳውሎስ የማስተማሪያ ደብተሩን ወይም የስልጠና ቁሳቁሱን እያስፈተሸ ነው ። እኛ ከጳውሎስ የተሻለ ጸጋም ቅድስናም የለንም ። ትሑታን ሆነን ወደ ቀደሙት አባቶች መምጣት አለብን ። አሊያ አገልግሎታችን ከንቱ ሩጫ እየሆነ ይመጣል ። ዛሬ ተዋረድ ያለው አገልግሎት እየጠፋ ሁሉም ራስ ገዝ ሆኖ ተቀምጧል ። ወደ ብርሃን እውቀታችንን ፣ ምግባራችንን ፣ ትንቢታችንን ፣ የፈውስ ጸጋችንን ይዘን መምጣት ይገባናል እንጂ ደጋፊዎችን እያከማቸን የጎበዝ አለቃ መሆን አይጠቅመንም ። ለቤተ ክርስቲያን እንቆረቆራለን እያሉ በአካልና በመንፈስ ሲሳደቡ የሚውሉ ፣ አባቶችን እንደ ቤት ሠራተኛ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያኖሩ ፣ የበላይ ለመሆን የሚፈልጉ ምእመናን እንደ ገና ማሰብ ያስፈልጋቸዋል ። የምናደርገው ምንድነው ? እግዚአብሔር ይወደዋል ወይ ? ማለት ያስፈልጋቸዋል ። አሊያ አባቶችን በቤተ ክርስቲያን ሲያዋርዱ የሚያዋርዱ ልጆችን በቤታቸው ያመርታሉ ። አባቶችን ሲያባርሩ ከቤት የሚያባርሩ ልጆችን ያፈራሉ ። በሁሉም አቅጣጫ የምናደርገው ከእግዚአብሔር ነው ? የቤተ ክርስቲያንን ውስጥ ልብስ ለዓለም እገልጣለሁ ብለን ስንነሣ ፣ መልካም እሴቷን ስናፈራርስ ፣ የቅጥር ተሳዳቢዎች ሆነን ሰድበን ለሰዳቢ ስንሰጣት በእውነት ከእግዚአብሔር ተልከን ነው ? በኦሪት ራሱን የላከ ነቢይ ወይም ነቢየ ሐሰት እንዲሞት ተነግሯል ። በእግዚአብሔር ስም ወንጀል የሚሠራም ከቅጣት አያመልጥም ። የምናደርገውን በምን ስሜትና መንፈስ እንደምናደርገው የሚነግረን አምላከ ብርናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። መርምረኝ እንበለው ደም ሳንሰጥ ውጤቱን ይሰጠናል ፣ መድኃኒት ያዝልናል ። ላለፈው ተግሣጽ ፣ ለሚመጣው ምክር ያጎናጽፈናል ። መድኃኒት የሚፈውሰው በእኛ እምነት በራሱ ጉልበት ነው ። እንዲሁም መድኃኒት የሆነውን ጌታ ስናምን ከራሳችን ማንነትም ያድነናል ። ይህ ለእኛ ከባድና ብዙ ዘመን ሞክረነው ያቃተን ነው ። ለእርሱ ግን ቀላል ነው ። መድኃኒት ሁሉ በዓለም ላይ ተዘዋዋሪ ጉዳት አለው ። ጠባሳ የሌለው መድኃኒት ክርስቶስ ብቻ ነው ። ወደዚህ አጋላጭ ሳይሆን ሸፋን ብርሃን እንምጣ ። በጓዳ ይቅር እያለን በአደባባይ በጸጋ ያከብረናል ። ዛሬም እጆቹ ተዘርግተው ይጠብቁናል። እስከዚህ ያለው ለኒቆዲሞስ ተሰጠው ትምህርት ነው።
 
 
 
 

 

 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ