የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ መጥምቅ የመጨረሻ ምስክርነት

የዮሐንስ መጥምቅ የመጨረሻ ምስክርነት
/ዮሐ. 3፡22-36/።
“ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥ እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና” /ዮሐ. 3፡22-24/።
በዱላ ቅብብሎሽ ጨዋታ አቀባዩ ካቀበለ በኋላ ጥቂት ርቀት ይሮጣል ። ተቀባዩ ሰው በትክክል መያዙን ለማወቅና በመጣበት ፍጥነት በአንድ ጊዜ መቆም ስለማይችል የተወሰነ ሮጦ ይመለሳል ። ዮሐንስ መጥምቅም የአገልግሎቱ መንገድ ጠራጊ ነበር ። ንጉሡ ከመጣ በኋላ መንገድ ጠራጊ ሥራውን ይፈጽማል ። ጌታችን ስብከት ከጀመረ በኋላ መጥምቁ ዮሐንስ ጥቂት ወራት አገለገለ ። ተልእኮው እንደ ቀጠለ ካረጋገጠ በኋላ ከቃል ሰማዕትነት ወደ አንገት ሰማዕትነት ይሄዳል ። ክርስቶስን የሚሰቅል ዓለም ምልክቱ አሁን ዮሐንስን መግደሉ ነው ። ዮሐንስን ያከበረ ፣ ክርስቶስን ያቃለለ ዓለም ቢሆንም ሁለቱንም ሞት ፈርዶባቸዋል ። የዓለም ክብሩም ንቀቱም ውጤቱ ሞት ነው ። ዓለም ዮሐንስን የውሸት አከበረች ፣ ጌታችንን የእውነት ናቀች ። መደምደሚያዋ ግን በሞት ማስወገድ ነበር ።
ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ እንደ ነበር ተገልጿል። በዮሐ. 4፡1-3 ላይ ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳላጠመቀ ተጽፏል ። በእርሱ እውቅናና ሥልጣን ያጠምቁ ስለነበር ኢየሱስ እንዳጠመቀ ተገልጿል ። በእርሱ እውቅናና ሥልጣን በሚደረገው ማንኛውም ተግባር ጌታችን ራሱን እንደ አንድ አባል ይገልጻል። እንደ እግዚአብሔር ቃል በሚወሰነው ውሳኔም ጌታችን አብሮ ያጸድቃል /ማቴ. 18፡19፤የሐዋ. 15፡29/። ስለ ስሙ የምንቀበለውን መከራም እንደ ራሱ መከራ ይሰማዋል ። ለዚህ ነው በክብር ዙፋኑ ያለው ጌታችን ጳውሎስን ለምን ታሳድደኛለህ? ያለው ። የደቀ መዛሙርቱን ስደት እንደ ራሱ ስደት ቆጥሮ ነው /የሐዋ. 9፡4/ ። በመከራችን የምንጽናናው የእርሱ አብሮነት ስለማይለየን ነው ። የጌታችንም ሆነ የዮሐንስ የስብከታቸው አክሊል መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ የሚል ነው ። ይህንን ንስሐ ተጨባጭ ለማድረግ ያጠምቁ ነበር ። ምክንያቱም ሰው የእግዚአብሔር ምሕረት ካልተሰማው ንስሐው ሙሉ አይደለም ። ዕረፍትም የለውም ። ውኃ እንደሚከድን እንዲሁ በእግዚአብሔር ምሕረት መከደኑን ከዚህ በኋላ እርሱ እንደማይታይ ምሕረቱ እንደሚታይለት ሊያምን ይገባዋልና ይህን ደካማ የሰው ተፈጥሮ ለማገዝ በውኃ ያጠምቁ ነበር ። ምክንያቱም ትልቁ በደል የእግዚአብሔርን ምሕረት አለማመን ነውና ። ንስሐው ንስሐ የሚያስፈልገው በምሕረቱ ካላመንን ነው ። ውኃ ያደፈውን ያጠራል ፣ የረከሰውን ይቀድሳል ፤ እንዲሁም ንስሐ የውስጥን ቆሻሻ ያስወግዳል ። ውኃ የተጠማውን ያረካል ፣ የተቃጠለውን ያበርዳል ፣ እንዲሁም ንስሐ እኔ አልድንም ላለ ተስፋን ፣ ጸጸት ለበላው ዕረፍትን ይሰጣል። ንስሐ የበረሃው ዓለም ጥላ ነው ። ከሠራነው ተቃራኒ የምንቀበልበት ነው ። ስለዚህ ጌታችን ምሕረቱን በተጨባጭ ለማስረዳት በውኃ ያጠምቅ ነበር ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በውኃ የሚፈጸሙ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎቶች አሉ።
–    የፈውስ አገልግሎት በውኃ ይፈጸም ነበር።
–    የመንጻት ሥርዓቶች ለምሳሌ ከለምጽ የነጻ ሰው ፣ የቆሸሸ ሰው በውኃ በመታጠብ ይነጹ ነበር ።
–    ወደ ይሁዲ እምነት ለመግባት በውኃ ያጠምቁ ነበር ።
–    ንስሐ በመናዘዝና በውኃ ይፈጸም ነበር ።
–    ጥምቀትም ወደ ክርስትና ፣ ወደ ጸጋና ምሥጢራት ለመቀላቀል በውኃ ይፈጸማል ።
ጌታችን የዮሐንስን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እየተካው በሚበልጥ አገልግሎትም እየፈጸመው ነበርና በውኃ ያጠምቅ ነበር ። ሙሉ በሙሉ መተካቱ በማጥመቁ ሲገለጽ የሚበልጥ አገልግሎት መፈጸሙ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት በማጥመቁ ይታያል ። ለሚያምኑት የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ይሰጣል ። ለማያምኑት ደግሞ በእሳት በማጥመቅ ይፈርዳል ። መንፈስ ቅዱስንም ሆነ ፍርድ መስጠት የእርሱ ሥልጣን ነው ።
መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ወኅኒ ከመጨመሩ በፊት የሰጠው የመጨረሻው ምስክርነት በዚህ ክፍል ተጠቅሷል ። የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሰዎች የተለያየ ነገር ይናገራሉ ። ዮሐንስ መጥምቅ በመጨረሻው ሰዓትም የሚናገረው ስለ ክርስቶስ ትልቅነት ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ የሕይወት ዘመኑ አዋጅ ነበረ ። በኖረበት ዘመን ሁሉ አንደበቱ ስለ እርሱ ተናገረ ። በመጨረሻም በሰማዕትነት ዝምታው ተናገረ ። ዮሐንስ መጥምቅ ስለ ጌታችን በመመስከሩ እርሱ ዝም ባለ ጊዜ ጌታችን መሰከረለት ። “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” በማለት ተናገረ /ማቴ. 11፡11/። በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጠው በዚህ ምድር ላይ ከሁሉ ያነሰው ክርስቶስ ነው ። እርሱ የመንግሥተ ሰማያት ሠሪ የሰማይም አሳዳሪ ነውና ። በዚህ ምድር ላይ ግን ያለ ልክ ተዋረደ ፣ ስለ ሰው ፍቅር ዝቅ አለ ። መጥምቁ ዮሐንስ ትልቅ እንደሆነ ጌታችን ተናገረ ። በዚህ ዓለም ላይ የትልቅነት መለኪያዎች አሉ ። ዮሐንስ መጥምቅ ግን አንዱንም አያሟላም ነበር ። በዚህ ዓለም ላይ ትልቅ ለመባል ቢያንስ አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡-
1-  ቤት ፡- ቤት የትልቅነት መለኪያ ነው ። ቤቱን በማየት ይህ የትልቅ ሰው ቤት ነው ይባላል ። ዮሐንስ መጥምቅ ግን ቤቱ ምድረ በዳ ነበረ ።
2-  ልብስ ፡- ልብስ የትልቅነት መለኪያ ነው ። በቅጡ ያልለበሰ ሰው የማይገባባቸው ስፍራዎች በመላው ዓለም ላይ አሉ ። ለምሳሌ፡- ባንክ ቤት የሚሠሩ በቅጡ መልበስ አለባቸው ። ገንዘቡን ትቶ ለመሄድ ሰው ዋስትና የሚሰማው ባለባበሳቸው ነው ። ወደ ቤተ መንግሥት ሲገባም ስፍራው የሚጠይቀውን አለባበስ ካለበሱ መግባት ይከለከላል ። ልብስ የትልቅነት ማሳያ ነው ። ዮሐንስ ትልቅ ነው ። ልብሱ ግን የግመል ጠጉር ነበር ።
3-  ምግብ ፡- ምግብ የትልቅነት ማሳያ ነው ። አንድ ቁርስ ከአንድ ብር እስከ አሥር ሺህ ብር ሊበላ ይችላል ። ትልቅ የተባለው ዮሐንስ መጥምቅ ግን ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር ነበረ ።
4-  ንግግር ፡- ንግግር የትልቅነት ማሳያ ነው ። ዓለም ላይ ያሉ መሪዎች በንግግራቸው የተመረጡ ናቸው ። ንግግር የትልቅነት ማሳያ ነው ። ዮሐንስ መጥምቅ ትልቅ ሲባል ንግግሩ ግን ሰይፍ ነበረ ። እናንተ የእፉኝት ልጆች እያለ የሚገስጽ ነበር ። ዮሐንስ መጥምቅ እጅግ ትልቅ ነበር ። ጌታችን በልኩ ትልቅ ሲል ደግሞ በጣም ትልቅ እንደሆነ እንረዳለን ። ይህ ዮሐንስ የመረጠው ስፍራ የጌታችንን የጫማውን ጠፍር ልፈታ እንኳ አይገባኝም በማለት ከወለል ወለል የመረጠ ነው ። ጌታ ትሕትናውን አይቶ መጥምቀ መለኮት እንዲሆን አደረገው ።
 መጥምቁ ዮሐንስ በመጨረሻው የዕድሜ ዘመኑ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ባለው በሄኖን ምንጮች ያጠምቅ ነበር ። ከፍተኛ ሙቀት ባለበት በዚህ ስፍራ ሲያጠምቅ እርሱ ለአገልግሎት የከፈለውን ዋጋ ማየት እንችላለን ። ሰዎቹም ከበረሃውና ከጸጸቱ አምልጠው ሲመጡ ዕንባቸው ከውኃ ጋር ፣ ጸጸታቸው ከንስሐ ጋር ፣ ትሕትናቸው ከምሕረቱ ጋር ተቀላቅሎ ያርፉ ነበር ። ጌታችንና ዮሐንስ አንዱን ሰማያዊ መንግሥት በተለያየ አቅጣጫ አገልግለዋል ። ጌታችን ከተሜ ሁኖ ዮሐንስ መጥምቅ በረኸኛ ሁኖ አገለገሉ። ለምን? ስንል የሰውን ምክንያተኝነት ዝም ለማሰኘት ነው ። እንዴት ከእኛ ጋር እየኖረ አገለግላለሁ ይላል እንዳይሉ ዮሐንስ በምድረ በዳ ያገለግል ነበር። እንዴት ኑሮአችንን ሳያውቅ ያገለግለናል? እንዳይሉ ጌታችን በከተማ ያገለግል ነበር ። የሰውን ሰበበኛነት ዝም ለማሰኘት ጌታችን በከተማ ፣ ዮሐንስ በምድረ በዳ አገለገሉ ።
 ዮሐንስ በመጨረሻው ሰዓት ስለ ጌታችን ታላቅነት ተናገረ ። ጌታችንም በመጨረሻው ሰዓት ደቀ መዛሙርቱን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው /ዮሐ. 13፡1/ ። ወደ ታላቅ ከፍታ ሊመለስ በተቃረበበት ሰዓት ዝቅ ብሎ እግር አጠበ። በመጨረሻው ሰዓት ላይ ሞትም አሟሟትም ፣ ቀጣይ ታሪክም ያሳስብ ይሆናል። በጌታችንና በዮሐንስ ላይ የታየው ግን ይህ አይደለም ። የሕይወት ታሪኬ ይጻፍልኝ በሚባልበት ሰዓት ጌታችን እግር ያጥባል ። ዮሐንስም እኔ አንሳለሁ እርሱ ይልቃል በማለት ይናገራል።

ያጋሩ