የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት መግቢያ

 ምዕራፍ ሦስት ስለ ሁለተኛ ልደት ፣ ስለ ጥምቀትም ምሥጢር የተማርንበት ነው ፡፡ ሁለተኛ ልደትም ሆነ ምሥጢረ ጥምቀት መሠረቱ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው ፡፡ ይህንንም በናሱ እባብ ውስጥ አይተናል ፡፡ ጌታችን እኛን ሊያድን ወደ ዓለም መጥቶ አድኖናል ፡፡ የዳነው በዳነ ሕይወት ለመገለጥ እንጂ እገሌ የዳነ ፣ እገሌ ያልዳነ ብለን ክፍፍል ለማውጣትና ለመናናቅ አይደለም ፡፡ ነገረ ድኅነት በጥንታውያን አባቶቻችን አስተምህሮ ከነገረ ሥጋዌና ከነገረ ክርስትና ተለይቶ የሚታይ አይደለም ፡፡ ነገረ ሥጋዌ ለነገረ ድኅነት መነሻ ነው ፡፡ ነገረ ክርስትናም ለነገረ ድኅነት መድረሻ ነው ፡፡ የዳንበት መሠረት ክርስቶስ ሰው መሆኑ ነው ፡፡ የዳንበት ግብም በክርስትና ፍሬ ለመገለጥ ነው ፡፡ ነገረ ድኅነት የተቦጨቀ አሳብ ከሆነ ዛሬ የሚታየውን ግልብ ሕይወትና እውቀት እየወለደ ይመጣል ፡፡ የእስራኤል ልጆች በፋሲካው ደም መሠዋት በሙሴም መሪነት ከግብጽ ምድር ከፈርዖን ባርነት ነጻ ወጥተዋል ፡፡ የኤርትራን ባሕር አንድ ጊዜ ብቻ ተሻግረው እስከ ከነዓን ድረስ ግን መና ተመግበዋል ፡፡ እንዲሁም አንድ ጊዜ በተሠዋልን በክርስቶስ በመሥዋዕትነቱና በአዲስ ኪዳን ሙሴነቱ ከሰይጣን ባርነት ነጻ ወጥተናል ፡፡ የጥምቀትንም ባሕር አንድ ጊዜ ተሻግረን በበረሃው ዓለም ላይ የጌታን ሥጋና ደም እየበላን እስከ በረከት አገራችን እንጓዛለን ፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ መውጣታቸው በራሱ ግብ አልነበረም ፡፡ የመጨረሻው መጀመሪያ ነበረ ፡፡ እንዲሁም ዳግም ልደትን ማግኘታችን ሕይወት መካፈላችን እንጂ ሩጫውን መጨረሳችን አይደለም ፡፡ አንድ ልጅ የተወለደበት ቀን መጨረሻው ሳይሆን ለዕድገትና ለዘመን ቁጥሩ መነሻው ነው ፡፡
 የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ሲወጡ ታላላቅ ተአምራቶችና ድንቆች ተከናውነዋል ፡፡ እነዚህ ተአምራቶች ግን አልቀጠሉም ፡፡ ከፊት ለፊታቸው ውጊያ ነበረ ፣ የሕይወት ጥያቄና ፈተና ነበረ ፡፡ በዚህ ውስጥ መውደቅና መነሣት የሰው ክፋትና የእግዚአብሔር ምሕረት ታይቷል ፡፡ እንዲሁም ጌታችን ደሙን አፍስሶ ባሕረ እሳትን በበትሩ በመስቀሉ ከፍሎ ሲያሻግረን በበዓለ ሃምሳ ብዙ የመንፈስ ቅዱስ ተአምራት ታይቷል ፡፡ ከዚያ ዘመን በኋላ ግን ተአምራት እየደበዘዘ ትምህርትና ሕይወት ምሥጢራትና እረኝነት እየቀጠሉ መጥተዋል ፡፡ ይህ በብሉይ ኪዳኑ እንደ ታየው ነው ፡፡ እግዚአብሔር ተአምራትን ለመነሻ እንጂ ሁልጊዜ የምንጠብቀው አድርጎ አልሰጠንም ፡፡ ሁልጊዜ የሚቀጥለው መንፈሳዊ ሕይወት ነው ፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ ዘመነ ሐዋርያት ወደ ድንቅና ተአምራት አገልግሎት መመለስ አለብን ፡፡ አሁን ያለው አገልግሎት ሁሉ ደረቅና እግዚአብሔር ህልውናውን የማይገልጥበት ነው በማለት ቤተ ክርስቲያንን እያራከሱ ፣ ድኅነተ ነፍስን እያቃለሉ ይገኛሉ ፡፡ የዚህ ጠንቁ ሕዝቡን ተአምራት ናፋቂ በማድረግ መንፈሳዊ ዘማ አደረጉት ፡፡ ዘማ በአንድ እንደማይረጋ የተአምራት ናፋቂም በአንድ ጉባዔና እረኛ አይረጋም /ማቴ. 16፡4/ ፡፡ እንደ ሰፈር ምጣድ የሚዞረው ሕዝብ የመጨረሻ ዕጣው ምንድነው? ስንል ከሃዲ መሆን ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ የምዕራብ አገር አብያተ ክርስቲያናት ቋሚ ምስክር ናቸው ፡፡ የማይሠራና መናን ከሰማይ የሚጠብቅ ወይም የሀብታሞችን ኪስ የሚከጅል ትውልድ በማፍራትም አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ መንገድ ላይ ያለን ይመስላል ፡፡ ለቃለ እግዚአብሔር ክብር የሌለው ትውልድ ለመውደቅና ለመጮህ የሚሻ አንዳንዴም በክፉ መናፍስት በሚሠሩ ሰዎች እጅ ምርኮኛ የሆነ ትውልድ እያፈራን ነው፡፡ እነዚህ ተአምራትንና ድንቆችን ሰባኪ የሆኑት ፣ በሽታም ድህነትም የለም ነው የሚሉት ፡፡ በእውነት ከበሽታና ከድህነት ጋር ኪዳን ያለው ፍቅርም ያለው ማንም የለም ፡፡ እንደ አፋቸው ቢሆንልን ጥሩ ነበር ፡፡ እነዚህ ሰዎች የነፋስ ሠረገላ ናቸው ፡፡ ነፋስ ቀለል ያለውን ላስኪትና ቅጠል ከመሬት ላይ ያነሣና ይዞ ይሄዳል ፡፡ ሜዳው ላይ ተሸክሞ ሸለቆ ላይ ግን ጥሎ ይሄዳል ፡፡ ሕዝቡንም ያልቆሸሸ ልብሱን እያራገፉ ፣ የሌለ ችሎታውን እያበሰሩ ፣ አንተ እኮ አንቺ እኮ እያሉ የሚሸከሙ የነፋስ ሠረገላዎች ጥቂት ከተሸከሙ በኋላ ገደል ጨምረው መሄዳቸው የማይቀር ነው ፡፡ ከሚሸከመው መሬት ላይ አንሥቶ ጥሎ ይሄዳል የነፋስ ሠረገላ ፡፡ አየር ተሞልቶ በአየር ላይ የሚዘለውን ትውልድ መሬት ማስያዝና ተገቢውን የክርስትና ትምህርት ማስተማር የቤተ ክርስቲያን የዛሬው አንገብጋቢ ድርሻ ነው ፡፡ አሊያ ብዙ መበታተኖች እየመጡ ፣ ከሃዲ ትውልድም እያፈራን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ፡፡
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ብዙ ትምህርትን የያዘ ነው ፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ሙቶ ያዳነን ትሑት እንድንሆን ነው ፡፡ ኃጢአት እንቅፋት በሆነ ዘመን ጌታችን መልስ ሆነ ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ጥያቄው የሆነበት ግን መልስ የለውም ፡፡ መልሱ ጥያቄ ሆኖበታልና ፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እጅግ ትሑት ነበረ ፡፡ ድንቅ ምስክርነቱንም ይኸው ሰማን ፡፡ በምዕራፍ ሦስት ላይ የክርስትናን ጥምቀት በትምህርት ፣ የንስሐንም ጥምቀት በተግባር እናያለን ፡፡ መጠመቅ የአዲስ ሕይወት ማኅተም ነው ፡፡ ሰው ለመጠመቅ መጀመሪያ ልብሱን ያወልቃል ፡፡ ይህ ለእግዚአብሔር መራቆት ነው ፡፡ መራቆትንማ እብድስ ዘመናይስ ያደርገው የለም ወይ ቢሉ እብድ ቢያደርገው ሁሉን ንቆ ፣ ዘመናይ ቢያደርግ ፈላጊ አጥቶ ነው ፡፡ የሚጠመቀው ግን ቢራቆት ትሑት ሁኖ ነው ፡፡ የሚጠመቀው ሰው እየተናዘዘ ልብሱን ያወልቃል ፡፡ መናዘዝ ውስጥን መግለጥ ነው ፡፡ ውስጥን መግለጡን በቃል ብቻ ሳይሆን በሚታይ ሁኔታም ልብሱን በማውለቅ ጽኑ ያደርገዋል ፡፡ እግዚአብሔርም የማይታየውን ምሕረቱን በሚታየው ውኃ በማድረግ ተጨባጭ ያደርግለታል ፡፡ ወደ ባሕር የጠለቀው ሰው ዳግም ይወጣል ፡፡ የሚጠመቅም ለሚታየው ዓለም ሞቻለሁ በአዲስ ሕይወት ለክርስቶስ እኖራለሁ እያለ ነው ፡፡ ሞቶ ከጌታ ጋር መኖር ያልጀመረ ፣ ተነሥቶ ከራሱ ጋር ይሞታል ፡፡ መሞት ታላቅ ውሳኔ ይጠይቃል ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ካሉት ውሳኔዎች የሚልቀው ይህ ነው ፡፡ ከክርስቶስ ጋር መሞት ማለትም ትልቅ ውሳኔ ነው ፡፡ ከራሱ ጋር የሞተ ትንሣኤ የለውምና ፡፡ ብዙዎች ከራሳቸው ጋር በኃጢአትና በሱስ ሙተዋል ፡፡ ነገር ግን ትንሣኤ የላቸውም ፡፡ ሰው ሲመነኩስ የሚገነዘው ሞቻለሁ ለማለት ነው ፡፡ ደንበኛ ውሳኔ ሁሉ በውስጡ ሞት አለው ፡፡ ከአንዱ ጋር ለመሆን አንዱን መለየት እርሱ ሞት ይባላል ፡፡ እርሱ ውሳኔ ይባላል ፡፡ ለወሰንለት ነገር የምንኖረው ለተውነው ነገር ስንሞት ብቻ ነው ፡፡ ሞት በሌለበት ትንሣኤ የለምና  ፡፡ ሰዎች በመጨረሻ ላይ የሚያደርጉትን የሞት ሕግ ክርስትናው ግን በመጀመሪያው በጥምቀት ላይ ያስጀምረናል ፡፡ ጥምቀት የውሳኔ ምዕራፍ ፣ የክርስትና መሠረት ፣ የጸጋ በር ፣ ወደ አዲሱ ቤተሰብ መቀላቀያ ደብተር ነው ፡፡ የተጠመቀው ማደግ ይገባዋል እንጂ ላለማደጌ ምክንያቱ ጥምቀቱ በልቤ ስላልሰረጸ ነው እያለ መደጋገም አይገባውም ፡፡ ይህ ምሥጢርን ማፋለስ ነውና ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ጊዜ አልሞተምና ፡፡ ድሮ ሳናውቅ ነው የተጠመቅነው የሚሉ አሉ ፡፡ ለጥምቀት ግን የሚያስፈልገው እምነት ነውና አሁንም አላወቁም ማለት ነው ፡፡ ይቅርታ ያገኘነው በተናዘዝነው ዝርዝር መጠንና ባፈሰስነው የእንባ ጅረት ልክ አይደለም ፡፡ በእግዚአብሔር ምሕረት ነው ፡፡ እንዲሁም በጥምቀት ጸጋን የምናገኘው በልኩ ስለገባን ወይም እገሌና እገሌ ስላጠመቁን ሳይሆን የሥላሴ ጸጋ ብቁ ስለሆነ ነው ፡፡
 አይሁድ ፣ ዮሐንስ መጥምቅ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያጠምቁ ነበር ፡፡ ጥምቀት እጅግ ክቡር ነው ፡፡ በጓዳ የማይፈጸም በአደባባይ የሚሰጥ ምስክርነት ነው ፡፡ ይህ የአደባባይ ምስክርነት በሠርግ ይመሰላል ፡፡ ሠርግ የሚደረግበት ምክንያቱ ያችን ልጅ ያንን ወጣት ይከጅሉ የነበሩ ካሉ ልባቸውን ተስፋ ለማስቆረጥ ነው ፡፡ ሠርግ ውስጥም ሞት አለ ፣ ውሳኔ ስላለ ነው ፡፡ ለዚህ ነው በዘፈኑም ሠርግና ሞት አንድ ነው የሚባለው ፡፡ ጥምቀትም ከክርስቶስ ጋር መተባበር ነውና በአደባባይ መፈጸም አለበት፡፡ ምእመኑን የሚከጅሉ ዓለምና ግብረ አበሮቿ ተስፋ ይቆርጣሉ ፡፡ የአደባባይ ምስክርነት የጓዳን ኃጢአት ባያስቀር የአደባባይን ኃጢአት ግን ያስቀራል ፡፡ ያ የተጠመቀው ሰውዬ አይደለም ወይ? ያ መድረክ ላይ የሚሰብከው አይደለም ወይ? ይባላል ፡፡ አንድ ሰባኪ መጠጥ ቤት ገብቶ በጨለማ ጣቱን እያጫወተ ሲተባበር አንዱ ጠጪ ያየውና “አንተ መምህር እገሌ አይደለህም?” ብሎ ሊያንቀው ሲል “አዎ” ይለዋል ፡፡ “ምን ትሠራለህ እዚህ?” ሲለው “እንደ እናንተ ያለውን ቀበዝባዛ እየፈለግን ነዋ” ሲለው አናቂው ሰውዬው በቃላት ታንቆ ቁጭ አለ ፡፡ አንዱ የቅድስና መንገድ አገልግሎት ነው ፡፡ ለሰው ሲጠነቀቅ ይቀደሳልና ፡፡ ቅድስና ከራስ ጋር በመፋጠጥ አይመጣም ፡፡ ብቻውን የሚኖር ሰው ጦሙን ያድራል ፡፡ እንግዳ ሲመጣበት ግን ሠርቶ አብሮ ይበላል ፡፡ ስናገለግልም ሌላውን ለማቅመስ ስንል ቃሉን እንቀምሳለን ፡፡ ማገልገል መገልገል ነው ፡፡ መንፈሳዊ ጸጋ መክሊት ነውና የሚበዛው በመቀመጥ ሳይሆን በመነገድ ነው ፡፡ መነገድ ማለት መለዋወጥ ማለት ነው ፡፡ መስጠት ብቻ ሳይሆን መቀበልም ነውና ፡፡ በባንክ ገንዘቡን ያስቀመጠ ኢኮኖሚው በወደቀ ቁጥር የእርሱም ገንዘብ አብሮ ይወድቃል፡፡ ነጋዴው ግን ያገላብጣልና ከስጋት ይድናል ፡፡ አዎ ጥምቀት ለዓለም ሞቶ ለክርስቶስ የመኖር ምሥጢር ነው ፡፡
 በምዕራፍ ሦስት ላይ ዮሐንስ ክርስቶስ በሌለበት ስለ ክርስቶስ ይናገራል ፣ ጌታችንም ዮሐንስ በሌለበት ያውም የዮሐንስ ደቀ መዛሙር እልፍ ሲሉ ስለ ዮሐንስ ይናገራል /ማቴ. 11፡7/ ፡፡ አገልግሎቶች መከባበር ካላቸው ምእመናን ነጻነትና ደስታ አላቸው ፡፡ እውነተኛ ምስክርነት ከኋላ የሚነገር ነው ፡፡ ስህተት የሚመለከተው ባለቤቱን ብቻ በመሆኑ ለራሱ ለባለቤቱ ፣ መልካምነቱ የሚያንጸው ሌሎችን በመሆኑ ለሌሎች መንገሩ መልካም ነው ፡፡ ለብዙ ሰው ኃጢአቱን ማመን ከባድ ነው ፡፡ ለሌሎችም ምሕረተ እግዚአብሔርን ማመን ችግር ነው ፡፡ ዮሐንስ እያናዘዘ የሚያጠምቀው ሁለቱንም ሙሉ ለማድረግ ነው፡፡ በእውነት በዚህ ምሕረት የሚያምን አለ ወይ? ሀብታም ለሰጠ ድሃ ይናደዳል እንዲሉ እግዚአብሔር ለማረ የሚበሳጭ ስንት አለ?፡ ምሕረት የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የማያስፈልገው በሰማይና በምድር ሥልጣን የጸና ነው ፡፡ አንድና ሰፊ እርሻ የሚያጭዱ እያዜሙ ግጥም እየተቀባበሉ ያጭዳሉ ፡፡ እንዲሁም ዮሐንስና ጌታችን የዛሬውን አገልግሎት ለማስተማር ዜማ ይቀባበሉ ነበር ፡፡ በዜማ ሕግ የራስ አይባልም ፡፡ የእኛን ስም ሌላው ፣ እኛ የሌላውን ስም በጣዕም እናነሣለን ፡፡
ጌታችን እየጎመራ ሲመጣ ዮሐንስ ስፍራ እየለቀቀ መጣ ፡፡ አገልግሎት ተረኛ መሥዋዕት መሆን እንጂ ተረኛ በላተኛ መሆን አይደለም ፡፡ አንድ ወቅት አንድ አገልጋይ ያማከረኝን አልረሳም ፡፡ “እስካሁን አንተ ተጠቅመሃል አሁን ደግሞ ለእኛ ስፍራ ልቀቅልን” አለኝ ፡፡ በጣም የደነገጥኩበትና አዲሱ ትውልድ ምንኛ ደፋር እንደሆነ ያስተዋልኩበት ቃል ነው ፡፡ እርሱ እንደሚያስበው ብኖር ጥሩ ነበር ፡፡ በካባ ውስጥ ያለውን መስቀል የሚያውቅ መንፈሳዊ ሰው ብቻ ነው ፡፡ አገልግሎት እንዲህ የሚታይ ከሆነ አሳዛኝ ነው ፡፡ አለመጋደላችን ሕግን ፈርተን እንጂ እግዚአብሔርን ፈርተን አይመስለኝም ፡፡ ገና ምን እበላለሁ ? ብሎ የሚጨነቅ ሰው ማገልገል አይችልም ፡፡ ስለዚህ ምእመናንም የድርሻቸውን አባቶችም የድርሻውን መወጣት ያስፈልጋቸዋል ፡፡ ከላይ ያነሣሁት ያ አገልጋይ ኋላ ላይ የተደራጀ እርሱን መሰሎች ይዞ ለብዙ አደጋ መጣ ፡፡ አገልጋዮች ሰብሳቢ አባቶች ከሌሉአቸው ይህ ችግር እየሰፋ ይመጣል ፡፡ ሕዝቡም በተረኛና ባልደከመው ገራፊ ሲገረፍና ሲጋጥ ይኖራል ፡፡ የካደውን ለማሳመን የጀመርነው አገልግሎት ያመነውን እንዳያስክድ መጠንቀቅ አለብን ፡፡ ድንኳን እየሰፋንም ቢሆን ማገልገል እንችላለን ብለን ማሰብ መልካም ነው ፡፡ አገልግሎት የጠራንን ጌታ እያየን የምንቀጥለው ነው ፡፡ አትኩረን ጌታን ማየት አለብን ፡፡ ወደ ሴት ያየ እንደሚለው የምናየው ፈተና እንደሚሆን ሁሉ የምናየው ጌታም መልስ ይሆናል ፡፡ አትኩረው ሲያዩት ውብ ክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡ ሰውን በአንድ ዓይን ጌታችንን በሁለት ዓይን ማየት ይገባናል ፡፡ ሰውን በአንድ ጆሮ ጌታችንን በሁለት ጆሮ መስማት ያስፈልገናል ፡፡ በሁለት ዓይን እያየን ከማንም ጋር መኖር አንችልም ፡፡ አንዱ ስህተት ሲያይ አንዱ መጨፈን አለበት ፡፡ አንዱ ጆሮ ክፉ ሲሰማ አንዱ ማፍሰስ አለበት ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ