ጌታችን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት የጠባይን ግንብ ለማፍረስ ነው። ይህች ሳምራዊት ሴት በጣም የተናቀችና ሁሉ የተጸየፋት ሴት ነበረች። ይህንንም የምንረዳው በሦስት ነገሮች ነው ፡-
1- በቀትር ውኃ ለመቅዳት መምጣቷ
2- ጌታችን አምስት ባሎች ነበሩሽ ባለው ንግግሩ
3- እርሷም ፡- “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ” በማለቷ ነው።
ውኃ በማለዳ እንጂ በቀትር አይቀዳም ። ያውም ሰማርያን በሚያህል በረሃ ውኃ ለመቅዳት በቀትር ያመጣት መገለሏና መጠላቷ ነው ። ሳምራውያን ራሳቸው በአይሁዳውያን የተናቁ ናቸው ። ይህች ሴት ደግሞ በተናቁት የተናቀች ናት ። ፈረንጆቹ በሚመድቡት ደረጃ ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሆኑ አገሮች አሉ ይላሉ ። እነዚህ አገሮች መሥራት የሚጠበቅባቸው ገና ድሃ ለመሆን ነው ። ይህች ሴትም የተናቀች ብቻ ሳትሆን ከንቀት ወለል በታች ነበረች ። ገና ሳምራውያን ጋ ለመድረስ ብዙ ይቀራታል። ቢያንስ ሳምራውያን ሊቀበሏት ያስፈልጋል ። ሳምራውያን ይህች ሴት ባጠለቀችበት ጉድጓድ እኛ አናጠልቅም ብለው ይጸየፏት ነበር ። ጉድጓዱ ጥልቅ ነው ። በኅብረት ሁነው ጉድጓዱን የዘጋውን ትልቅ ድንጋይ ማንሣት ይጠበቅባቸዋል ። ቀድተው ሲጨርሱ ገጥመውት ይሄዳሉ ። ይህች ሴት ግን በዚያ ቀትር የመጣችው ከሰው አፍ በላይ በረሃው አያቃጥለኝም ብላ ነው ። አንድ ለማኝ እንዲህ ብለዋል፡-
የሰው ፊት ፣ የሰው ፊት ፣ የሰው ፊት እሳቱ
ፍምም አልወረደው እንደ መፋጀቱ
ይህች ሴትም ከሰው ፊት የቀትሩ ፊት ይሻለኛል ብላ ትገሰግስ ነበር ። ትንሹ ለማኝ ትልቁን ለማኝ አይወደውም እንደሚባለው ትንሹ ኃጢአተኛም ትልቁን ኃጢአተኛ አይወደውም ። እስር ቤቶችን ስንጎበኝ ከእስረኞች የምንሰማው ድምፅ አለ ። ሰርቆ የታሰረው የገደለውን በጣም ይጸየፋል ። የገደለው ደግሞ የሰረቀውን በጣም ይተቸዋል ። ያለው ውድድር የንጹሕነት ሳይሆን የኃጢአት ዓይነት ነው ። በንጹሕነት ሳይሆን በዓይነቱ ሲነቃቀፉ ይውላሉ ። ሳምራውያንም ይህችን ሴት ይንቋትና ይጸየፏት የነበሩት በንጹሕነት አልነበረም ። እውነተኛ ንጹሕ ፣ ንጹሕ ያደርጋል እንጂ አይገፋም። ማግኔት ተቃራኒውን እንደሚስብ ጻድቅም ኃጥኡን ይስበዋል ። ከቀትሩ ቀጥሎ የሚገጥማት ያን ድንጋይ ማንከባለል ነው ። የድንጋይ ሸክም ከባድ ነው ። እንኳን ሲሸከሙት ሲቀመጡበትም ድንጋይ አይደላም ። ቀጥሎ የሚገጥማት ጥልቅ ጉድጓድ ነው ። ጥልቅ ጉድጓድ እስከ ወገብ ድረስ ተንበርክኮ መግባትን ይጠይቃል ። ያንን ጉድጓድም እንደ ነበረ አድርጋ ዘግታ ካልሄደች በማግሥቱ ሲመጡ ለቀትር ዘብ ያቆሙበታል ። ይህች ሴት በቀትር መምጣቷ ይህን ያስተምረናል ።
ሳምራዊቷ ሴት ዕለታዊ ኑሮዋ ድካም የበዛበት ነው ። ያን ያህል ርቀት ተጉዛ ይዛ የምትመጣው አንድ እንስራ ውኃ ነው ። ደክማም የሚጠቅማትን ያህል ውኃ አታገኝም ነበር ። በነፍሷ ልዕልና እንዳትጽናና ሕይወቷ በኃጢአት ሰንሰለት የታሰረ ነበር ። የማትወዳቸውን ሰዎች በየዕለቱ የማቀፍ ግዴታ ነበረባት። ጌታችን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት የዚህች ሴት ሰቆቃ ስለተሰማው ነው ። ይህን ውስጣዊ ጩኸት ከእርሱ በቀር የሚሰማ፣ ከእርሱ በቀርም የሚመልስ አልነበረም ።
ይህች ሴት በቀትር መምጣቷ ኑሮዋን የሚያሳይ ነው ። ጌታችን በንግግሩ መሐል ፡- “አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት” /ዮሐ. 4፥18/። አምስት ባሎች ላይ የደረሰች ከሆነች ይህች ሴት ምን ዓይነት ኑሮ እንደምትኖር የታወቀ ነው። ሳምራውያን የሚያገልሏት በዚህ ምክንያት ነው ። ምእመኑ ለቄሱ ፡- “አራት ሚስቶች አሉኝ” ቢላቸው “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቤን ልቀቅ ይልሃል” ብለውታል ። ይህች ሴትም ሕዝቤን ልቀቂ የምትባል ነበረች ።
ለምስክርነት በወጣች ጊዜ ሳምራዊቷ ሴት ፡- “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ” ብላለች ። ፍጹም ንስሐ እንደ ገባች የሚያሳይ ነው ። ጌታችን ግን ያደረገችውን ሁሉ አልነገራትም ። ኅሊናዋንና የሰውነት አቅሟን ጠብቆ አናገራት ። በእነዚህ ምክንያቶች ሳምራዊቷ ሴት በወገኖቿ የተናቀች እንደሆነች መረዳት ይቻላል ። ከእርሷ ጋር በአንድ ጉድጓድ ውኃ ለማጥለቅ ያቆሙት ግንብ የጠባይ ግንብ ነበረ ። ጌታችን ኃጢአትን ይጠላል ፣ ኃጢአተኛን ግን ይወዳልና ሊረዳት መጣ ። እርሱ በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት ይህንን የጠባይ ግንብ ለማፍረስ ነው ። መንፈሳዊነት ይቀበላል እንጂ አይገፋም ። ለንስሐ ይጋብዛል እንጂ አሳልፎ አይሰጥም ። የሰዎች ጠባዬኝነት ግን እኔ ጨዋ ነኝ እገሌ ባለጌ ነው በማለት ሌሎችን ያርቃል ። ጌታችን ይህን የጠባይ ግንብ አፈረሰ ። ዛሬ ሰዎች ወደ ንስሐ ሲመጡ አይታዩም ። ምክንያቱ ምንድነው ? ስንል ስለ ኃጢአታቸው ብዛት እንጂ ስለ ጌታ ምሕረት ስለማንነግራቸው ነው ። ሰውን ለንስሐ የሚያበቃው በር ከፍቶ የሚጠብቀው አምላክ ፣ የሚምረው ጌታ እንዳለ ሲያውቅ ብቻ ነው ። የእግዚአብሔርን ምሕረት በመንፈሳዊ ድምፅ ብንናገር ለንስሐ የሚጋፉ ወገኖችን እናይ ነበር ።
የመዐርግ ግንብ
ጌታችን በዓይን ለሚያየው እንኳ መምህር መሆኑ የታወቀ ነው ። በእምነት የሚያዩት ደግሞ አምላክነቱን ይረዳሉ ። የአይሁድ መምህራን ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ርቀትን የጠበቀ ነው ። በመካከላቸው የማያገናኝ የመዐርግ ግንብ ነበረ ። ጌታችን ግን ይህን ግንብ አፍርሶ ያችን ሳምራዊት ሴት ለማነጋገር ወደ ሰማርያ ሄደ ። በዳዊት መዝሙር ውስጥ ከመዝሙር 119-133 ያሉት የመዐርግ መዝሙራት ይባላሉ። ካህናቱ የቤተ መቅደሱን ደረጃዎች ሲወጡ የሚዘምሩአቸው ዝማሬዎች ናቸው። መዐርግ ያራርቃል ። ወደ ከፍታ ሲወጣ ከሥር ያሉት ትንሽ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋል ። በፍቅር ይገናኙ የነበሩ በክብር ብቻ እንዲገናኙ ያደርጋል ። መዐርግ ግንብ ሁኖ ብዙ አብሮ አደጎችን ብዙ ወዳጆችን ለይቷል። መዐርግ እንደ ዘማ በአንድ ወዳጅ እንዳይረጉ ያደርጋል ። ሁሉን ተጠራጣሪና ለወንበሩ ሲል መግደልን እንደ ጽድቅ የሚያይ ነው ። ጌታችን ግን ይህን ግንብ አፍርሶ ሰዎቹ ወዳሉበት ድረስ ሄደ ። እየዞረ ያከመ ሐኪም አናውቅም ፣ ክርስቶስ ግን በየቤቱ እየሄደ ይፈውስ ነበር ። ወደ እኔ ኑ የሚል ሹም እንጂ ሰዎቹ ወዳሉበት ሂዶ ችግር የሚፈታ አላየንም ። ጌታችን ግን እስከ ሰማርያ ያውም በቀትር ይሄድ ነበር ። እርሱ የሥጋን ሳይሆን የነፍስን ፣ የጊዜውን ሳይሆን የዘላለሙን እንቆቅልሽ የሚፈታ ሳለ ነገር ግን ትሑት ነው። እስኪፈልጉት አይጠብቅም ፣ ፈልጎ ያድናል ።
ሹሞች በስፍራቸው ሁነው የሕዝባቸውን ችግር መፍታት አይችሉም ። ሕዝባቸው እንዴት እንደሚኖር ወርደው ማየት ያስፈልጋቸዋል ። በተቀመሙ ሪፖርቶች ተደልለው የተቀመጡ ነገሥታት ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ይነቃሉ። የሚያስተዳድሩት ሕዝብ እንዴት እንደሚኖር ለማወቅ ዝቅ ማለት ያስፈልጋቸዋል። አሊያ በባለጠጎች ተከብበው የባለጠጎች ዘበኛ ሁነው ያበቃሉ። አገር ግን በዋናነት የድሆች ነው ። ባለጠጎች በአንድ እግራቸው በአገር ቤት የሚኖሩ አንድ እግራቸውን ደጅ ያወጡ ናቸው ። ለአገሩ የሚሞት ድሃው ትልቅ ክብር ሊሰጠው ይገባል ። ጌታችን ከሰማይ ወደ ምድር የወረደው የማኖረውን ሕዝብ ኑሮውን ልካፈለው ብሎ ነው ። ይህ ትልቅ አርአያነት ነው ።
ጌታችን ወደ ሰማርያ ሲሄድ ዋጋ ከፍሏል ። በዚያ ቀትር በብርቱ ደክሟል። ሄዶም ያገኘው አንዲት ሴትን ነው ። ያውም የተናቀችና ሁሉ የገፋት ሴት ናት ። ጌታችን ግን ለአንድ ሰው ዋጋ አለውና አገለገላት ። ታላላቅ የሃይማኖት ምሥጢራትን ገለጠላት ። ለአንዲት ተራ ሴት ይህን መግለጥ ምሥጢር ማባከን ይመስላል ። ነገር ግን ይህች ሴት መላ ሰማርያን በምስክርነት ወደ ክርስቶስ አምጥታለች ። የሰማርያ ሕዝብም አምኖ ከዳነ በኋላ እንዲህ ብሏታል፡- “አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር” /ዮሐ. 4፥42/ ። መድኃኔዓለም የሚለው የሚለው ስያሜም በዚህ ጊዜ ተሰማ ። እውነታቸውን ነው ። አይሁድ ከእናንተ ጋር በአንድ መቅደስ አናመልክም ብለው የገፉአቸውን ሳምራውያን ከተቀበለ እርሱ በርግጥም መድኃኔዓለም ነው ። ከዚህች ሴት ይህን ያህል ትርፍ ይገኛል ብሎ ማን ያስባል ? “በቆሎ ከጤፍ ማኅጸን ዱቄት የሚወጣ አይመስለውም”ይባላል ። በትልቅነታቸው የሚመኩ ይህችን ሴት ተስፋ ማድረግ አይችሉም ። ጌታችን ግን ምንም የሚመኩበት የሌላቸውን ድሆችን በማክበር ይጠቀምባቸዋል ። ዛሬም በምድራችን ሊያልፍ ግድ ነው ፡-
– ብዙ የተገለሉ ፣ የሰውነት ክብራቸው የተረገጠባቸው ፣ ፍትሕ አጥተው የሚባዝኑ አሉ ።
– በዘረኝነት ጦስ ሕይወታቸውን ያጡ ፣ ከስደት ወደ ስደት የሚጓዙ አያሌ ናቸው ።
– ጾታቸው የመጠቃት ምክንያት የሆነባቸው እንደ ተንቀሳቃሽ ዕቃ የተቆጠሩ ብዙ ምስኪን ወገኖች አሉ ።
– በኃጢአታቸው የተገለሉ ፣ የምሕረት አምላክ እንዳለ የማያውቁ ፣ ራሳቸውን መቀበል ያቃታቸው ደግሞም ነጻ አውጪ ክርስቶስ እንደ መጣ ያልሰማ ብዙ አሉ ።
– የተሾሙ ሰዎች ዘንድ መድረስ ያልቻሉና አቤቱታቸው ሰሚ ያጣባቸው አያሌ ሰዎች አሉ ። ጌታችን በእኛም ዘመንና ምድር ሊያልፍ ግድ ነው።
እርሱ ሲያልፍ ብዙ ነገር ያልፋል ።