የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውኃ አጠጪኝ

“ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም፦ ውኃ አጠጪኝ አላት” /ዮሐ. 4፥7/ ።
በጌታችን ሰው መሆን ከሚያስደንቁ ነገሮች አንዱ ሰጪው ለማኝ መሆኑ ነው። ከእናቱ ድንግልናዊ ወተትን እየለመነ ያደገው ጌታችን አሁን ደግሞ ውኃ አጠጪኝ በማለት ሳምራዊቷን ሴት ለመነ ። በዚህ ዓለም ላይ ውኃ ርካሽ ነገር ነው ። እግዚአብሔር እንደ ውኃ ያበዛው ነገር የለም ። ውኃን አብዝቶ የሰጠን ለመታጠብ እንዳንሰስት ነው ። በመካከለኛው ምሥራቅ ውኃ ተለምኖ የሚጨክን ሰው የለም ። እንደውም ሰው ሊጠማው ይችላል ተብሎ ቀዝቃዛ ውኃ ከነመጠጫው ደጅ ላይ ይቀመጣል ። መንገደኛውም ቀድቶ እየጠጣ ያልፋል ። እነዚያ ሕዝቦች የሚያስቡት ውኃ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ብለው ነው ። ጌታችንም ይህን ቃል ደግሞታል፡- “የእግዚአብሔርን ስጦታና፡- ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት” /ዮሐ. 4፥10/ ። ውኃ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። በአገራችንም ውኃ የሬሣ ማጠቢያ ነው ይባላል ። እንኳን ለቆመ ለሞተም አይከለከልም ማለት ነው ። የጎንደር ሰው “ለውኃ ለውኃ ምን አደረገኝ ቀሃ” ይላል ። የቀሃ ወንዝን እያስታወሰ የሚናገረው ነው ። ጌታችን በሕይወት ዘመኑ ሁለት ጊዜ ውኃ እንደ ለመነ ተጽፏል ። የመጀመሪያው በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ሲሆን ሁለተኛው በመስቀል ላይ “ተጠማሁ” በሚለው ጩኸቱ ነው ። ሁለት ጊዜም ውኃ አላገኘም ። ውኃ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ብሎ የሚያስበው ማኅበረሰብ ጌታችን ሲለምነው ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም ። ጌታችን እንኳን የአምላክነቱን አይደለም የሰው ልጅን ያህል እንኳ አቀባበል አላገኘም ። ትንሽ የሚመስለውን ነገር ለተነፈጉ ቤዛ ሊሆናቸው ትንሹንም ትልቁንም ጥቅም አጣ ።
ሁለቱንም ጊዜ ከውኃው በላይ የተጠማው የሰዎቹን መልካምነት ነው ። ሳምራዊቷ ሴት ካመነች በኋላም ውኃውን አልጠጣም ። በመስቀል ላይም በውኃው ፈንታ ሆምጣጤ ቢያቀርቡለት አልጠጣውም ። ውኃን ለመስጠት ዘርን ጎሣን የሚያስጠይቅ ማንነት በሳምራዊቷ ሴት ነበረ ። ውኃን ለለመነ ሆምጣጤ የሚያቀርብ ማንነት በሰቃዮች ውስጥ ነበረ ። ከስጦታው በላይ ስጦታው የሚወጣበት ልብ እንዲቀደስ ጌታችን ፈለገ ። ልባቸው ቢቀደስ ለውኃ ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን ለመስጠትም አይሰስቱም ። የመጨረሻውን ስጦታ የዘላለም ሕይወትን የሚሰጠው ጌታችን የመጨረሻውን ትንሽ ስጦታ ውኃን ለመነ ። ውኃን የለመነባቸው ሰዓቶች በሰማርያ ደክሞ ፣ በመስቀል ላይ ታሞ ነው ። ከግለሰብ እስከ ሕዝብ ፣ ከሳምራውያን እስከ አይሁዳውያን ውኃን ነፈጉት ። ራሱ የፈጠረውን ውኃ ተነፈገ ። ያልፈጠርነውን ቢነፍጉን ታዲያ ለምን ደነቀን ?
   ጌታችን ይህችን ሴት ብዙ መንገድ ተጉዞ ፣ በሐሩር ተቃጥሎ ፣ በብርቱ ደክሞ ሊያገኛት መጣ ። ምሥጢሯን እንዳይሰሙ ደቀ መዛሙርቱን የማይበላውን ምግብ እንዲገዙ ወደ ከተማ ላካቸው ። ደቀ መዛሙርቱ የመጡት ይህች ሴት አምና ለምስክርነት ልትሰማራ ስትል ነው ። ምን ያህል ሰዓት እንደሚያናግራት ያውቅ ነበር ። ይህን ሁሉ የሕሊና ጥበቃ ካደረገላት በኋላ አሁን ደግሞ እንዳትደናገር ውኃ አጠጪኝ አላት ። በውኃ ጉድጓድ አጠገብ የውኃ ጥያቄ ማንሣት የሚያግባባ ርእስ ነው ። ጌታችን ትልቅ የስብከት ዘዴ እንደ ተጠቀመ እንረዳለን ። የስብከት ዘዴ ማለት ከሚያግባባው ርእስ መነሣት ማለት ነው ። የሰውን ሕሊናና ክብር ጠብቆ ለንስሐ ማብቃት ፣ በመራራት ሰዎችን ማከም ማለት ነው ። ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመለከት ርእስን አይወዱም ። ይህን ርእስ በሚመለከት እንኳን ከሰባኪ ከራሳቸውም እየሸሹ ነው የሚኖሩት ። የሚወዱትም ትምህርት ሕይወትን የማይመለከት በገንዘባቸው ብቻ መልስ የሚሰጡበትን ሙገሳና ድለላ ያለበትን ነው ። እንደ ነቢይ ፣ እንደ ፈዋሽ የሚያደርጋቸው ሰዎች ብዙ ተከታይ ሲኖራቸው ፣ ወንጌል የሚሰብኩት ግን ሌጣ የሚሆኑት ለዚህ ነው ። ሰይፍ እንደ ያዘ እብድ የሚያስፈራራ ሰባኪም ዘዴን ከጌታችን መማር አለበት። ሰው ማለት ነጻ ፈቃድ ያለው ፤ ለባዊት ፣ ነባቢትና ሕያዊት ነፍስን የተቀዳጀ ፣ በአምላክ የፍርድ ዙፋን ፊትም ራሱን ችሎ የሚቆም ክቡር ፍጥረት ነው ። ይህንን ሰው  እንደ እንስሳ ንቆ ፣ እንደ ጣዖት ፈርቶ ሳይሆን እንደ ሰው አክብሮ ማነጋገር ይገባል ። ስብከት ማለት ሰውን በፈቃዱ የምንማርክበት መለኮታዊ መሣሪያ ነው ። እንኳን በግልጽ አዋርደናቸው ይቅርና የሌላውን ንስሐ ለትምህርት ማጣፈጫ ስንጠቀም ሰሚዎቹ ይሰጉናል። ይልቁንም ያለንበት ዘመን የሰዎች አእምሮ በብዙ የሕሊና ትግል ውስጥ የሚያልፍበት ፣ በሕመምና በጭንቀት የተጎዱበት በመሆኑ በጥንቃቄና በፍቅር ልናክማቸው ይገባል እንጂ በጭካኔ ቊስላቸውን ልንነካቸው አይገባም ። “እናትና ልጅ ሲጣሉ ሞኝ እውነት ይመስለዋል” ይባላል ። እግዚአብሔርና ሰውም በጣም ይዋደዳሉና ሲጣሉ እንደ ሞኝ ልናስብ አይገባም ። ነቢዩ ዮናስ የእግዚአብሔርን ምሕረቱን ብቻ ማሰቡ ፍርዱን እንዳስረሳው ፣ እኛም ፍርዱን ብቻ ማሰብ ምሕረቱን እንዳያስረሳን መጠንቀቅ አለብን ። “ካነጋገር ይፈረዳል ካያያዝ ይቀደዳል” የሚባለው ለዚህ ነው ። ንግግር ራሱን የቻለ ጥበብ ይፈልጋል ። ጥበብ ውሸት አይደለም ። ለማን ምን መናገር ፣ እንዴት መናገር እንዳለብን የምናውቅበት ነው። ቀጥሎ ያለውን ንግግር እስቲ ምረጡ ፡-
–    ጫማው ትንሽ ስለሆነ አይበቃዎትም ።
–    እግርዎት ትልቅ ስለሆነ ጫማው አይበቃዎትም ።
 አንድ ጫማ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ገብታችሁ የሰማችሁት ድምፅ ነው ። የሁለቱም አሳብ አንድ ዓይነት ነው ። የምትቀበሉት ግን የቱን ንግግር ነው ? አነጋገር ወሳኝ ነው ።
 ይልቁንም ስብከት ማለት ሰውና እግዚአብሔርን ማስታረቅ ማለት ነው ። ሰው የበዳይ አኩራፊ ሁኖ ተቀምጧል ። እግዚአብሔር ደግሞ ከልጄ አስታርቁኝ ብሏል ። አስታራቂ ሰው ሽማግሌ ነውና ጠንቃቃ ፣ ንግግር አዋቂ መሆን አለበት። አሊያ አባትና ልጅን አለያይቶ ሊቀር ይችላል ። በስብከት ያመኑትን ያህል የካዱም አይጠፉም ። ጌታችን ጸሎትን በአቡነ ዘበሰማያት ካስተማረ ስብከትንማ በጣም መማር ይገባናል ። “ከመጠምጠም ትምህርት ይቅደም” የሚባለው ለዚህ ነው ። ትምህርት ለምን ይፈራል ? የቀደሙትን አገልጋዮች መጠየቅ ለምን ይሸሻል ? ልብ አድርጉ የስብከት ዘዴ ማለት የኑሮ ዘዴ ማለት አይደለም ። ካልደፈረሰ አይጠራም የሚል ንግግር ትክክል አይደለም ። ሰው ያደፈረሰው አይጠራምና ።
   ጌታችን በወቅቱ ከሚያግባባው ርእስ ከውኃ በመነሣት ትልቅ የስብከት ጎዳናን አሳየን ። ይህች ሴት ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው ፣ የአለባበሱ ሁኔታ አይሁዳዊ የሚመስል ሰው በማየቷ መደንገጧ እርግጥ ነው ። የንግግሩ መክፈቻ ግን የሚያግባባ በመሆኑ ድንጋጤዋ ወደ መገረም ተለወጠ ። ወገኖቼ ሳምራውያን እንኳ እኔ ባጠለቅሁበት አይቀዱም ፣ እርሱ አይሁዳዊው እንዴት በእኔ ማጥለቂያ ውኃ ይጠጣል ? ወደሚል አግራሞት ተሻገረች ። ሕሊናን የፈጠረው የሕሊናን ምቾት ይጠብቃል ። ጌታም በብዙ ትዕግሥት እምነትዋን አሳደገላት ።
የሚፈለገው ጌታ በመፈለግ መጣ ። የሚጠየቀው ጌታ ጥያቄዋንና መልሷን ይዞ ተገለጠ ። የሚሰጠው ጌታ በልመና ጀመረ ። ፍጻሜው ምን ሆነ?
–    በልመና የጀመረው ግንኙነት የዘላለምን ሕይወት በመስጠት ተደመደመ።
–    በውኃ የጀመረው ርእስ መሢሕና መድኃኔዓለም በማለት ተፈጸመ ።
–    አንዲትን ሴት በመማረክ መላው ከተማ ተማረከ ።
–    በሚያስጠማው ውኃ የሸሿት ሳምራውያን በሕይወት ውኃ ግን ተከተሏት።
–    አንድ ጽዋ ውኃ ለመስጠት የተከራከረች እንስራዋን ጥላ ሄደች ።
ትንንሽ የሚመስሉ ግንኙነቶች ትልቅ በረከት ይወጣቸዋል ። ትንንሽ የሚመስሉ ርእሶች የዘመናትን እንቆቅልሽ ይፈታሉ ። ትንንሽ የሚመስሉ ሰዎች ለብዙዎች መዳን ምክንያት ይሆናሉ ። ትልቅነታችን የማያግዘው ፣ ትንሽነታችን የማይመልሰው ጌታ ስሙ ይመስገን !!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ