የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ስጦታ

“ኢየሱስ መልሶ፦ የእግዚአብሔርን ስጦታና፡- ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት” /ዮሐ. 4፥10/ ።
ጌታችን ብዙ ርቀት ተጉዞ በቀትር በሲካር ምንጭ አጠገብ ደረሰ ። ያችን ሳምራዊት ሴት ቀድሞ ጠበቃት ። ለራሷ ሳታስብ ጌታ ለነፍሷ አሰበላት። ምሥጢሯን እንዳይሰሙ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ገበያ ሰደዳቸው ። የነፍሷን ጉስቁልና ቢያውቅም ከዚያ አልጀመረም ። የሚያውቁት ሁሉ አይነገርም ብሎ ሊያስተምረን ይህን አደረገ ። በወቅቱ ሊያግባባ በሚችል፣ አጠገብ ባለውና አሳማኝ በሆነው በውኃ ጥያቄ ንግግሩን ጀመረ ። ውኃ አጠጪኝ ለሚለው ጥያቄ ሳምራዊቷ ሴት የሰጠችው ምላሽ በአይሁድና በሳምራውያን መካከል ያለውን የዘረኝነት ጉዳይ ነው ። ጌታችን ይህን ግንብ አፍርሶ ወደ እርስዋ እንደ መጣ አላወቀችም ። ይህች ሴት ነጻነቷ ብዙ ሰዎችን እንድታገኝ ስላደረጋት ስለ ሃይማኖትና ስለ ማኅበራዊ ጉዳዮች በቂ እውቀት ነበራት ። መላውን ከተማም የት ቦታ ሲጠሩት ሊመጣ እንደሚችል አውቃ ከኋላዋ አስከትላ መጥታለች ።
አንዳንድ ጊዜ ከትምህርት ቤት የሚባረሩ ልጆችን ስናይ ትምህርት ቤቱ አስተሳሰባቸውን ሊሸከም ስላልቻለ ነው ። ለዓለም መፍትሔ ያመጡ ተመራማሪዎች ከትምህርት ቤት አትችሉም ተብለው የተባረሩ ናቸው ። እውነቱ ግን ትምህርት ቤቱ እነርሱን አልቻላቸውም ። ማኅበረሰብም የሚያገልለው ሰዎቹ መጥፎ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባቸውን መሸከም ስለከበደው ነው ። ሰውን ወደ እውቀትና ብስለት ከሚያደርሱት ነገሮች ጥቂቱን ብንጠቅስ፡-
1-  መገለል፡- መገለል ራሱን የቻለ ሕመም አለው ። የሕይወት ልምዳቸው እንግዳ ለሆነ ሰዎች ጭልም ሊል ይችላል ። መገለል ግን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ፣ ግንድ ከሆነው ጌታ ጋር ቅርንጫፍ አድርጎ የሚያጣብቅ ነውና ብዙ ፍሬ አለው ። አዲስ አበባን ለማየት ከመሐል ፒያሳ ይልቅ ወጣ ብሎ እንጦጦ ላይ መቆም ይረዳል ። ዓለምም በዓለም ውስጥ ሆነን አትታየንም ። በአሳብ ወጣ ስንል ግን ትታየናለች ። መገለል ዓለምን ለማየት ከዓለም ወጣ የማለት አጋጣሚ ነው ። የተገለሉ ሰዎች ምክንያት የሌለው ጥላቻ ምን ማለት እንደሆነ ፣ ብዙዎች የተስማሙበት ውሸት እውነት ተብሎ እንደሚጠቀስ ያውቁታል ። ታላላቅ ቦታዎች ላይ የደረሱ ሰዎች እስር ቤትን የቀመሱ ፣ በበረሃ ትግል ያደረጉ ናቸው ። ይልቁንም መጠቃት ለተጠቁ የሚሆን የዘመናት ብርሃንን ለማውጣት ያነሣሣል። እግዚአብሔር የሌሎች ሕይወት እንዲሰማንና መፍትሔ እንድናፈላልግ በመገለል ውስጥ ያሳለፈናል ።
2-  ነጻነት ፡- ከጭምቶች ይልቅ የቀልቃሎቹ አእምሮ ፈጣን ነው ። ማንኛውንም ነገር ለመስማትና ለመረዳት አይቸገሩም ። ሁሉም ነገር በጉልበት እንደማይፈጸም ስለሚያውቁ ብዙ ብልሃቶችን ይጠቀማሉ። ብዙ ነገሮችን ለማየት ስለቻሉ በማንም አይገረሙም ። አንዳንዴ ማኅበረሰቡ ወጣ ያለ አስተሳሰብ ስላላቸው ያርቃቸዋል ። የሚናገሩት ስለማይገባውም ይነቅፋቸዋል ። የዚህች ሴትን ነጻነት የወለደው ሰዎች ፍጹም አንቀበልሽም በማለታቸው ከይሉኝታ ሕይወት መፈታቷ ነው ።
3-  መስማት ፡- ተቋማት የእውቀት ሥነ ሥርዓትን እንጂ ሙሉ እውቀትን መስጠት አይችሉም ። በተቋማት ውስጥ ብዙ ጊዜ የተንጠለጠለ እውቀት እንጂ የረገጠ እውቀት አይሰጥም ። ሊሆን ይችላል ፣ ገና አልተደረሰበትም ፣ አይታወቅም የሚሉ ንግግሮች ይበዛሉ ። የእውቀት ገባሩ ሁሉን ሳይንቁ መስማት ነው ። ይህች ሴት የተለያዩ ሰዎች ወደ ቤቷ ይመጣሉና ስለ ብዙ ነገሮች እውቀት ነበራት ። እውቀት በሁለት መንገድ ይጠናል ። ሁለገብ እውቀትና ወጥ እውቀት በሚል ለሁለት መክፈል እንችላለን ። ሁለገብ እውቀት ያላቸው ሰዎች ብዙ ነገሮች ለመቅመስና እንደ ተሽከርካሪ ራዳር ወይም እንደ ወፍ እይታ ነገሮችን ሁሉ ማወቅ አለብን ብለው የሚያስቡ ናቸው ። ወጥ እውቀትን የሚያጠኑና የሚያሳድጉ ሰዎች ደግሞ ብዙ ነገሮችን በብቃት ማጥናት አንችልምና አንዱን በብቃት ማጥናት አለብን ብለው የሚያስቡ ናቸው ። እንደ ሳምራዊቷ ሴት ያሉ ሁለገብ እውቀትን ያዳበሩ ናቸው ።
ጌታችን ውኃ አጠጪኝ ለሚለው ጥያቄው ሳምራዊቷ ሴት የሰጠችው የዘረኝነት ምላሽ፡- “የእግዚአብሔርን ስጦታና፡- ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር” የሚል ነው /ዮሐ. 4፥10/ ። ውኃ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ተብሎ በዚያ ማኅበረሰብ ዘንድ ይታመናል ። ስለዚህ ላልለመነ ሰው እንኳ ደጃፍ ላይ ይቀመጣል ። ይህ በመካከለኛው ምሥራቅ የተለመደ ነው ። በአገራችንም የቆየው ባሕላችን ውኃ ለለመነ አይጨከንም ። እናቶቻችን ፡- “እኔ አፈር ልጠጣ” ብለው ቀድተው የሚሰጡት ነው ። ጌታችን ግን በምድር ላይ የቆየው አቀባበል በጣም ያልተለመደ ነው ። ለማንኛውም ሰው የሚሰጠውን ውኃ አሁን አላገኘም ። ፈሪሳዊው ስምዖንም እቤቱ በጋበዘው ጊዜ ለአንድ እንግዳ የሚደረገውን መስተንግዶ እንኳ አላቀረበለትም /ሉቃ. 7፥36-50/ ። አንድ እንግዳ በእስራኤላዊ ቤት ሲመጣ መጀመሪያ ለእግሩ ውኃ ይቀርብለታል ። ይህ ያቀዘቅዘዋል ፣ ያበረታዋል ። ቀጥሎ ጋደም እንዲል ይደረግና ሽቱ ካለ ይቀቡታል ። ሽቱ ከሌለም አበባ ያርከፈክፉለታል ። እንግዳው እያየ ምግቡን አጠገቡ ይሠራሉ ። ምን ማለት ነው ስንል እያጫወቱት ምግብ ያቀርቡለታል። ጌታችን ለእንግዳ ከሚደረግ አንዱን እንኳ አላገኘም ። ያች ሴት ግን ከውኃ በላቀ በዕንባዋ እግሩን አጠበችው ። ሽቱን ለአንገቱ ሳይሆን ለእግሩ ቀባችው ። አዎ ጌታችን ለሰው ወይም ለእንግዳ የሚደረገውን ክብር እንኳ በምድር አላገኘም ። በፍርዳቸውም የሚሰቀል ሰው አይገረፍም ፣ የሚገረፍም አይሰቀልም ነበር ። ጌታችን ግን ተገርፎ ተሰቀለ ።
ጌታችን ስለ ዮሐንስ መጥምቅ ሲናገር ፡- “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” አለ /ማቴ. 11፥11/ ። ከሁሉ የሚያንሰው የተባለው ራሱ ጌታችን ነው ። በዚህ ምድር ላይ ያለ ልክ ዝቅ ብሏልና ። በመንግሥተ ሰማያት ግን ትልቅ ነው ። ወደር ከሌለው ክብር ወደር ወደሌለው ውርደት መጣ ። ዛሬም ክብሩን ሊረዱ ያልቻሉ ብዙዎች ናቸው ። አንዳንድ ጥቅሶችን በመያዝ እናቱን ድንግል ማርያምን አቃለለ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። ይህ ሰውነቱንም አምላክነቱንም አለመቀበል ነው ። ምክንያቱም ሰው ሁሉ እናቱን ያከብራልና ። አምላክም አባትና እናትህን አክብር ብሏልና ። እናቱን አቃለለ ብሎ መናገር ሰውም አምላክም አይደለም ብሎ ህልውናውን እንደ መካድ ነው ። ዛሬም ክብሩን መቀበል ብዙዎች ቢከብዳቸውም የመጨረሻው ዳኛ እርሱ ነው ።
በርግጥም ውኃን የሚያህል ቀላል ነገር ፣ ለማንም ሰው የምንሰጠውን ትንሽ ስጦታ የሚለምነን ማን መሆኑን ብናወቅ እንደነግጥ ነበር ። ውኃን የፈጠረው ጌታ ነው ። ለዜና የመደብነውን ፣ ለጨዋታ የምናባክነውን ጊዜ ለጌታችን መስጠት ሲያቅተን ፣ ጊዜን የሰጠን ማን መሆኑን ብናውቅ አናደርገውም ነበር ። ያች ሴት ለጣሳዋ ሰስታ ማን መሆኑን ስታወቅ ግን እንስራዋን ጥላ ሄደች ። የሚለምነን ማን መሆኑን ብናውቅ እንኳን ከሚጎዳን ኃጢአት ከሚጠቅመንም ሀብት በመነንን ነበር ። የሚጠየቀው ሲጠይቅ ፣ የሚለመነው ሲለምን እፁብ ከማለት ውጭ ምን ይባላል ! እልፍ አእላፋት መላእክት የከበቡት አንድ እኛን ሲፈልግ ፣ ያልበደሉ አገልጋዮች እያሉት ታጥቦ ጭቃ የሆነውን ወዴት ናችሁ ሲለን እፁብ የሚያሰኝ ነው ።
አለማወቅ የመጥፋት መሠረት ነው ። የማያውቅ ሰው ለብዙ ስህተቶች ይዳረጋል ። ትለምኚው ነበርሽ ብሏልና ለመጸለይም ማወቅ ያስፈልጋል ። ጌታችን የአቡነ ዘበሰማያትን ጸሎት ማስተማሩ ለዚህ ነው ። እምነትም ከመስማት ነው ተብሏል /ሮሜ. 10፥17/ ። ትክክለኛ እውቀት በሌለበት ትክክለኛ እምነት ሊኖር አይችልም ። እግዚአብሔር እናውቅ ዘንድ ብዙ አስተማሪዎችን ልኮልናል ። እነዚህ አስተማሪዎች፡-
1-  መጻሕፍት
2-  ተፈጥሮ
3-  ታሪክ
4-  መምህራን
5-  ኑሮ … አዘጋጅቶልናል ። ስለ አንዱ እግዚአብሔር ከተለያየ አቅጣጫ የምናይባቸው ብዙ ሰሌዳዎች ተዘርግተዋል ። እግዚአብሔር የማወቂያ መሣሪያ የሆነውን አእምሮን መስጠቱም እውቀትን እንዳከበረ ያሳያል ። ጠቢቡ ሰሎሞን፡- “ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም” ብሏል /ምሳ. 19፥2/ ።
ማንኛውም ነገር ህልውናውን የሚያስጠብቀው ለተሠራበት ነገር ሲውል ነው ። መኪና ለመሄድ ስለ ተሠራ ሲንቀሳቀስ ብቻ ዕድሜ አለው ። አውሮፕላንም በበረረ ቊጥር እየታደሰ ይሄዳል ። አእምሮም እውቀት ባገኘ ቊጥር እየጠነከረ ይመጣል ። ምክንያቱም የተሠራው ለማወቅ ነውና ። ጌታ ሳምራዊቷን ሴት “ብታውቂ” አላት ።
በምድር ላይ እንደ ውኃ ብዙ የለም ። ውኃ ሲጠጡት ያረካል ፣ ውኃ ሲታጠቡበት ያነጻል ፣ ውኃ ሲተክሉ ያበቅላል ፣ ውኃ መርከብን የሚያህል ትንሽ ቀበሌ ተሸክሞ ይሄዳል ። ውኃ መንገድም ሁኖ ያገለግላል ። ታላቅ በረከት የሆነው ውኃ መዓት ሁኖ ሲመጣ በኖኅ ዘመን እንደ ታየው ዓለምን ያሳልፋል ። ከውኃ አደጋ የእሳት አደጋ ይሻላል ። እሳት ጊዜ ይሰጣል ። ውኃ ጠርጎ ይወስዳል ። ሰውዬው ሃምሳ ዓመት ያጠራቀመውን ንብረት ጎርፍ ወሰደበት ። ቆም ብሎ በመገረም፡- “ሊያልፍ ውኃ አደረገኝ ድሃ” አለ ይባላል። ውኃ ርካሽ ነው ። ሲጠፋ ግን እንደ ውኃ ውድ የለም ። ንጉሡ አክአብ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ ሲፈልግ የነበረው ውኃን ነው /1ነገሥ.18፥5/። ውኃ ቤዛም ነው ። ንጹሕ ውኃ የእኛን ቆሻሻ ይወስድና እኛን ንጹሕ ያደርገናል ። በዕቃ የነበረው ውኃ የእኛን ቆሻሻ ሲወስድ ይደፋል ። በቤት የነበረው ወደ ውጭ ይረጫል ። እኛ ከነጻን በኋላ አደባባይ እንወጣለን ። ውኃው ግን የእኛን ቆሻሻ ተሸክሟልና ከአጥር ውጭ ይደፋል ። ውኃ ንጹሕ ባይሆን ምትክ መሆን አይችልም ። ውኃ የጌታችን ምሳሌ ነው ። እርሱ ንጹሕ ሳለ የእኛን ኃጢአት ተሸከመ ። እኛን ሊያነጻ እርሱ ኃጢአተኛ ተባለ። ከሰፈር ውጭም በቀራንዮ ተወገደ /ዕብ. 13፥12/ ።
ጌታችን ውኃን እንዲህ በገፍ ሰጠ ። ርካሹን ውኃ ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሕይወትንም በውኃ መጠን ለሰዎች ለቀቀ ። ለእርሱ ምድራዊ ውኃንም ዘላለማዊ ሕይወትም መስጠት ሁለቱም ያው ነው ። ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት ከምድራዊ ውኃ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት እንድታስብ እየረዳት ነው ። ውኃን በነጻ የሰጠው እርሱ የዘላለም ሕይወትንም ይሰጣል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ