የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ክርስቶስ ይበልጣል

“በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው”
                                              /ዮሐ. 4፥12/ ።
ሳምራዊቷ ሴት፡- “ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?” ካለችው በኋላ “በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን ?” አለችው ። በርግጥም ጕድጓዱ ጥልቅ ነው ። ወደ ጥልቁ ጕድጓድ ረጅም ገመድ ቢያንስ 32 ሜትር ገመድ መወርወር ይጠይቃል ። ገመዱ ጫፍ ላይ መጎተት እንደሚችለው ሰው አቅም መጠን መቅጃ ይታሰራል ። ገመዱ ባጠረ ቊጥር የሚቀዳው ሰው በርከክ ብሎ ግማሽ አካሉን ወይም እስከ ወገቡ ወደ ጕድጓዱ ገብቶ መቅዳት አለበት ። መቅጃው ሦስት ሊትር የሚይዝ ከሆነ ሃያ ሊትር ለሚይዘው እንስራ ሰባት ጊዜ መመላለስ ይጠይቃል ። ከዚያም የጕድጓዱን አፍ በትልቅ ድንጋይ ገጥሞ መሄድ ያስፈልጋል ። የጕድጓድ ውኃ አድካሚ ፣ አስፈሪ ነው ። ብዙ ጊዜ መቅጃው እዚያው ጕድጓዱ አጠገብ የሚቀመጥ የጋራ ንብረት ነው ። በኅብረት ከቀዱ በኋላ ይዘውት ሊሄዱም ይችላሉ ። ስለዚህ ሳምራዊቷ ሴት መቅጃ የለህም ስትለው ሳምራውያን ከሚጠቀሙበት ከዚህ መቅጃ ለመጠቀም እንዴት ትችላለህ ? ዘር የለየንን ውኃ እንዴት አንድ ያደርገናል ? የሚል አስተሳሰብ የያዘች ይመስላል ። መቅጃው የእርስዋ ከሆነ ደግሞ እኔ ሳምራዊ በመሆኔ ከአይሁዳውያን ፣ የተገፋሁ በመሆኑ ከሳምራውያን በእኔ ዕቃ የሚጠቀም የለም አንተ እንዴት ጠየቅከኝ ? የሚል አስተሳሰብ ሳትይዝ አልቀረችም ። ጌታችን ግን ከጕድጓዱ ውኃ ወደ ሕይወት ውኃ ፣ ከሆድ ውኃ ወደ ነፍስ ውኃ ፣ ከግዙፍ ውኃ ወደ መንፈሳዊ ውኃ ከፍ ሊያደርጋት ፈለገ ። የረካች ነፍስ ያልረካች ሥጋን መሸከም ትችላለችና ። እርሱ መቅጃ አያስፈልገውም ። ራሱ የሕይወት ውኃ ነው ። እርሱ ግን የጕድጓድ ውኃ ሳይሆን የምንጭ ውኃ ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ሰው የቆፈረው  ነው ፣ የምንጭ ውኃ ግን ራሱ የፈለቀ ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ካለበት ርቀት ድረስ ማጥለቅ ይፈልጋል ፣ የምንጭ ውኃ ግን ወደ ላይ ወጥቶ ይፈስሳል ።
–    የጕድጓድ ውኃ መቅጃ ይፈልጋል ፣ የምንጭ ውኃ ግን እጅን መዘርጋት ብቻ ይፈልጋል ።
–    የጕድጓድ ውኃ ደለል ይበክለዋል ፣ የምንጭ ውኃ በፈለቀ ቊጥር ራሱን የሚያነጻ ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ካልተከደነ ለሰው ለእንስሳ አደጋ ነው ፣ የምንጭ ውኃ ግን ባይከደንም አደጋ የለውም ።
–    የጕድጓድ ውኃ በቆፈሩት መጠን የሚገኝ ነው ፣ የምንጭ ውኃ ግን ሳይቆፈር የሚፈስ ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ወደ ላይ ኩፍ የሚል ነው ፣ የምንጭ ውኃ ግን ወደ ታች የሚፈስስ ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ዝም ከተባለ ይበሰብሳል ፣ የምንጭ ውኃ ግን እንደጠራ ይኖራል ።
–    የጕድጓድ ውኃ ሰው በገመድ ወርዶ ያበጃጀዋል ፣ የምንጭ ውኃ ግን ጥገና አይፈልግም ።
–    የጕድጓድ ውኃ አገር አያቋርጥም ፣ የምንጭ ውኃ ግን የመጡትን ሲያረካ ያልመጡት ጋ የሚሄድ ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ሁልጊዜ ስጋት ነው ፣ የምንጭ ውኃ ግን ሕጻናት የሚጫወቱበት ነው ።
–    የጕድጓድ ውኃ ርቆ እንጂ እዚያው ለመታጠብ አይሆንም ፣ የምንጭ ውኃ ግን እዚያው ያነጻል ።
የጕድጓድ ውኃ የሰው መልካምነት ምሳሌ ነው ፣ የምንጩ ውኃ ግን የክርስቶስ ሕይወትነት ምሳሌ ነው ።
–    ሰው ከሰው የተገኘ ነው ፣ ክርስቶስ ግን የአብ ልጅ ነው ።
–    ሰው በፍለጋ የሚገኝ ነው ፣ ክርስቶስ ግን የፈለገን ነው ።
–    ሰው በጊዜ ፣ በቦታና በሁኔታ ይለወጣል ፣ ክርስቶስ ግን አይለወጥም ።
–    ሰው መተያያ ይፈልጋል ፣ ክርስቶስ ግን መሸነፍን ወይም መማረክን ብቻ ይፈልጋል ።
–    ሰው በምሕረቱ ካልተከደነ አደጋ ነው ፣ ክርስቶስ ግን ታውቆ የሚመለክ ነው ።
–    ሰው ደግነቱ እያደገ የሚመጣ ነው ፣ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወትን በመስጠት የሚጀምር ነው ።
–    ሰው ትንሽ ነገር ካለው አለኝ ብሎ ይኮራል ፣ ክርስቶስ ግን አለሁላችሁ ይላል ።
–    ሰው በየዕለቱ ካልጸዳ ይበከላል ፣ ክርስቶስ ግን የማይደፈርስ ምንጭ ሁኖ ይኖራል ።
–    ሰው ገና በመሠራት ላይ ነው ፣ ክርስቶስ ግን የዘላለም ቅዱስ ነው ።
–    ሰው በራሱ ዙሪያ የሚያስብ ነው ፣ ክርስቶስ ግን ሁሉን ሰብሳቢ ነው ።
–    ሰው ዛሬ ደግ ሁኖ እያለ ቢለወጥስ ? በማለት ያሰጋል ፣ ክርስቶስ ግን አላዋቂዎችን ይረዳል ።
–    ሰው ደግ ቢሆንም ይቅር ለማለት ይቸገራል ፣ ክርስቶስ ግን ሳይፈተን ይቅር ይላል ።
  አዎ እርሱ የምንጩ ውኃ ነው ። መቅጃ የማያስፈልገው ራሱ እርካታ ነው ። ሰው ባጠለቀው የማያጠልቅ የራሱ ፈቃድ ያለው አምላክ ነው ። የያዕቆብ ውኃ መልሶ ያስጠማልና ነገ በዚህ ሰዓት መመለስ ያሻል ፣ የአሮን መሥዋዕት ኃጢአትን ቢያዳፍን እንጂ አያጠፋምና ለሚቀጥለው ዓመትም ቀጠሮ ይያዛል ። ክርስቶስ ግን አንድ ጊዜ ለሁሌውም የሚበቃ ነው ። እርሱ አንድ የአብ ልጅ ፣ አንድ የማርያም ልጅ ፣ አንድ የነቢያት ተስፋ ፣ አንድ የሐዋርያት ስብከት ፣ አንድ የሰማዕታት መዓዛ ፣ አንድ የሕይወት ውኃ ፣ አንድ መሥዋዕት  ነው ።
 ሳምራዊቷ ሴት ፡- “በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው”                                     /ዮሐ. 4፥12/ ። ይህንን የመብለጥ ጥያቄ ያነሣችው ክርስቶስ እሰጣለሁ ያለው ውኃ የዘላለም የሕይወት ውኃ ስለነበረ ነው ። የዘላለም ሕይወት ውኃን ከጕድጓድ ውኃ ለይታ ተገንዝባለች ። በርግጥም ጌታችን ከያዕቆብ ይበልጣል። ያዕቆብ በተስፋ የተጽናናበት የዘላለሙ ጌታ ነው ። ይህች ሴት ክርስቶስን ከያዕቆብ ጋር አነጻጸረችው ። የሚነጻጻር በእኩያነት የሚቆም ነው። ክርስቶስ ግን ከሁሉ በላይ ነው ። ይህ አስተሳሰብ የገላትያ ክርስቲያኖችን እንዲሁም የዕብራውያን ክርስቲያኖችን ገጥሟቸው ነበር ። የገላትያ መልእክት ወንጌል ያለ ኦሪት ፣ ጥምቀት ያለ ግዝረት ፣ ክርስቶስ ያለ ሙሴ ሙሉ አይደለም ለሚሉ ወገኖች የተጻፈ ነው ። የዕብራውያን መልእክት ደግሞ ክርስቶስን ፡- ቃሉ ከመጣላቸው ከነቢያት ፣ ቃሉን ካገለገሉ ከመላእክት ፣ ቃሉን ከሰማ ከሙሴ ፣ ርስትን ካካፈለ ከኢያሱ ፣ መሥዋዕት ካቀረበ ከአሮን ጋር አነጻጽረው ነበርና ክርስቶስ የሁሉ የበላይ መሆኑን ለማስረዳት የተጻፈ ነው ። ብልጫነቱም፡-
–    ክርስቶስ ቃሉን የተናገረ ብቻ ሳይሆን ራሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
–    በአብ ፊት የቆመ ሳይሆን በእኩያነት በየማነ አብ የተቀመጠ ነው ።
–    ሰው ቢሆንም ፍጹም አምላክም ነው ።
–    እንደ ሙሴ የቤቱ አገልጋይ ሳይሆን የቤቱ ልጅ ነው ።
–    ምድራዊት ርስትን እንደ ኢያሱ ያካፈለ ሳይሆን በመንፈሳዊና በሰማያዊ በረከት የባረከን ነው ።
–    ለሕያው ነፍስ ዋጋ የማይሆነውን ደመ ነፍስ ፣ እንደ አሮን ያቀረበ ሳይሆን ራሱን የዘላለም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ ነው ።
–    ክህነቱም በጊዜ ተጀምሮ በጊዜ የሚፈጸም የአሮን ክህነት ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ የዘላለም ካህን ነው ።
–    ኪዳኑም ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው ።
–    ያገለገለበት መቅደስም ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነው ።
–    ያቀረበውም መሥዋዕት ተደጋጋሚ ሳይሆን ራሱን የዘላለም መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል ። በዚህ ምክንያት ክርስቶስ ይበልጣል በማለት የዕብራውያን ፀሐፊ ያትታል ።
 ሳምራዊቷ ሴት ክርስቶስን ከያዕቆብ ጋር አነጻጸረችው ። የገላትያ ሰዎች ክርስቶስ ብቻውን ሙሉ አይደለም አሉ ። የዕብራውያን ሰዎችም ከቃሉ አገልጋዮች ጋር አነጻጸሩት ። አዎ ክርስቶስ ይበልጣል ።
 ዛሬም የራሳቸው ትልቅ ፣ የራሳቸው ጀግና ፣ የራሳቸው የርእዮተ ዓለም አራማጅ … ያላቸው ክርስቶስን ያነጻጽሩታል ። ለእኔ ክርስቶስ ከቼኩቬራ አይበልጥም ብለው የተናገሩ ነበሩ ። በአፋቸው ያቃለሉት ፣ በልባቸውም የሚያቃልሉት አያሌ ቢሆኑም ሁሉን አሳልፎ ነዋሪ የሆነው እርሱ ግን ይበልጣል ።
 ጌታችን ሳምራዊቷ ሴት ትበልጣለህን ? ስትለው አዎን አላላትም ። አዎን ቢላት ምናልባት ዘራፍ ብላ ትሄድ ይሆናል ። መንገድ ላይ በብስጭት እየተናገረች ስትሄድም ለሚጠይቃት ሁሉ ከያዕቆብ እበልጣለሁ አለኝ በማለት ጉድ ባይ ሰዎች ታሰባስብ ነበር ። ጌታ ግን በሚቀጥለው ምላሽ ሸኛት ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ