ኃጢአትን ባሕል ፣ ሥነ ልቡና ፣ ፍልስፍና ፣ ዘመናዊነት ፣ እውቀት የሚሰጠው ትርጉም አለ ። የኃጢአት ትክክለኛ ትርጉም ግን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚገኝ ነው ። ባሕል ኃጢአትን ሲደረግ የኖረ አይደለም ወይ ? የሚል ትርጉም ይሰጠዋል ። ሥነ ልቡና መብት ነው የሚል ትርጉም ይሰጠዋል ። ፍልስፍና ከተለመደው ውጭ ማሰብ ነው ብሎ ይፈታዋል ። ዘመናዊነት በራስ የማዘዝ ነጻነት ይለዋል ። እውቀት ልምምድ ነው ይለዋል። ኃጢአትን ከባሕል አንጻር የሚፈቱ ከማኅበረሰቡ ላለመገለል ብለው አክብረውት ይኖራሉ ። በኃጥአን ከተማ ጻድቁ ኃጥእ ነውና ። ኃጢአትን ከሥነ ልቡና አንጻር የሚተረጕሙት መብት ነው ። ዋናው ልውደደው ይላሉ። ከፍልስፍና አንጻር የሚፈቱት ከተለመደው ውጭ በመኖር አትኩሮትን መሳብ ይቻላል ይላሉ ። ከዘመናዊነት አንጻር የሚተረጕሙት ክልከላ አይስማማኝም ይላሉ ። ከእውቀት አንጻር የሚተጕሙት ራሴን ለመምራት በቂ ነኝና ማንም መንገዱን ሊያሳየኝ ብቁ አይደለም ይላሉ ። የኃጢአትን ትክክለኛ ፍቺ የሚሰጠን የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው ። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት አቅጣጫ ጠቋሚ ወይም ኮምፓስ ነውና ።
መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ ኃጢአት ማለት ዓላማ መሳት ማለት ነው ። የምን ዓላማ መሳት ? ብንል የሕይወት ዓላማን መሳት ማለት ነው ። አንድ ጠረጴዛን እንደ ወንበር ብንጠቀምበት ለራሱ ከብደዋል ፣ ለእኛም አይመቸንም ። ለምን ? ስንል የተሠራው ለመደገፊያ እንጂ ለመቀመጫ ስላልሆነ ነው ። እንዲሁም ሰው ለኃጢአት ሳይሆን ለጽድቅ ስለተፈጠረ ኃጢአትን ሲመርጥ ለራሱ መኖር ይከብደዋል ፣ ለአካባቢውም የማይመች ሰው ይሆናል ። የመጀመሪያው ሰው አዳም በኃጢአት ወድቆ የቅጠል ልብስ ባገለደመ ጊዜ ደግሞም በገነት ጫካዎች ውስጥ በተደበቀ ጊዜ የመጣው የእግዚአብሔር ድምፅ አዳም ወዴት ነህ ? የሚል ነው /ዘፍ. 3፥10/ ። አዳም ያለበት ቦታ ጠፍቶት አይደለም ። ከሕይወት ሐዲድ ስተሃል ወዴት እየሄድህ ነው ? የሚል ዓላማ የመሳት ጥያቄ ነው ። ይህ ድምፅም የመጀመሪያው የንስሐ ድምፅ ነው ። ብሉይ ኪዳንም በታወጀ ጊዜ “ብትስቱ” የሚል ቃል ተሰምቷል /ዘሌ. 4፥13/ ። ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፣ መሪዎች እንደ መሪዎች ፣ ሽማግሌዎች እንደ ሽማግሌዎች ሊስቱ ይችላሉ ። ስለዚህ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል ። የአዲስ ኪዳን መዛግብትን ስናገላብጥ ኃጢአትን የሚገልጠው ዓመፃ በማለት ነው ። “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና” /ሮሜ. 1፥18/ ። በዚህ ክፍል የተገለጠው ዓመፃ ተራ ዓመፃ ሳይሆን ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ አልገዛም የሚል አብዮታዊ ዓመፅ ነው ። አብዮታዊ ዓመፅ በማባበያ አይመለስም ። የዳቦ ወይም የቤንዚን ዋጋ በመቀነስም አይቀለበስም ። መንግሥቱ እስኪገለበጥ ድረስ የሚያምፅ ነው ። ኃጢአትም እንዲሁ በእግዚአብሔርና በመንግሥቱ ማመፅ እንጂ የግል ፍላጎትን መፈጸም አይደለም ። አንድ ሰው ፡- “በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት እስገጠምን ድረስ ከራሳችንና ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር አንችልም” ብሏል ። በዚህ ገለጻ መሠረት ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር መጋጠም ነው ። ቃሉ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ ይላልና መድቀቅ አለበት /1ሳሙ. 2፥10/ ። ዳግመኛም ከራሳችን ጋር እንዲሁም ከሰዎች ጋር ሰላም የምንሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ስንሆን ብቻ ነው ። የሰላም መሠረቱ እግዚአብሔር ነው ። የውጫዊ ጦርነቶች መነሻው ውስጣዊ ጦርነት ነው ይባላል ። የውስጣዊ ጦርነት መሠረትም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው ።
በአጭር ቃል ኃጢአት ማጣት ነው ። ኀጥእ ማለትም ያጣ ማለት ነው። ክብሩን ፣ ሰላሙን ፣ ጤናውን ያጣ ማለት ነው ። ጽድቅ ሠርቼ እንቅልፍ አጣሁ ፣ ኃጢአት ሠርቼ እንቅልፍ አገኘሁ የሚል ማንም የለም ። በርግጥ የማይሰማቸው ሰዎች በዓለም ላይ ታይተዋል ። ሕሊና ከኃጢአት ብዛት የተነሣ ይሞታል ። ሕሊና የሞት ዘመን ላይ ሲደርስ መጸጸት ያቆማል /ዕብ. 9፥14/ ። ጌታችን ከሞተ ሕሊናም ያድናል ። መንፈስ ቅዱስ ሊወቅሰን ከመጣ ክርስቲያን የሆንነው ክፉ ሠርተን ሕመም እንዲሰማን ነው ። በልጅነታችን ጭቃ አቡክተን እንጫወት ነበር ። በዚያም ደስ ይለን ነበር ። ካደግን በኋላ ግን ጭቃን እንኳን በእጃችን ልንነካው በእግራችን ልንረግጠው እንጸየፈዋለን። ምክንያቱም ማደግ ያስገኘልን እውቀት ከጭቃ ከመቆሸሽ በቀር ምንም አይገኝም የሚል ነው ። እንዲሁም በአእምሮ ሕጻን በነበርንበት ዘመን በኃጢአት ለመደሰት ሞክረናል ። ተደልለንም አልፈናል ። ለመንፈሳዊ አካለ መጠን ስንደርስ ግን ከኃጢአት ከመርከስ በቀር ምንም እንደማይገኝ ይገባናል ።
የንጉሡ ልጅ መንደር መጥቶ ኳስ ቢጫወት ሁሉ ይገረማል ። ልጅ ስላልሆነ ሳይሆን የንጉሥ ልጅ ሁኖ አልባሌ ቦታ በመዋሉ ነው ። እኛም የንጉሥ እግዚአብሔር ልጆች ነን ። ኃጢአትን ልንተው የሚገባን ክብሬ አይደለም ብለን ነው ። ዘፈን ቦታ ፣ መጠጥ ቦታ መገኘት ክብራችን አይደለም ። ኃጢአትን ልንተው የሚገባን ቅጣትን ፈርተን ሳይሆን ክብሬ አይደለም ብለን ነው ። አንድ ስብከት ትዝ ይለኛል ። በልጅነቴ የሰማሁት ነው ። “ኃጢአትን ልንተው የሚገባን በሥጋ እስር ቤትን ፣ በነፍስ ገሀነመ እሳትን ፈርተን ሳይሆን ክርስቶስ ወዶኛል ሞቶልኛል ብለን ነው።”
የሰው ልጆች ኃጢአትን የሚሠሩበትና በኃጢአት የሚቆዩበት የተለያየ ምክንያት አላቸው ።
1- ሰላምን ፍለጋ
ሰዎች በኃጢአት ውስጥ የሚቆዩበት ምክንያት ሰላምን ፍለጋ ነው ። በኃጢአት የሚገኝ ጊዜያዊ ሰላም አለ ። ሰዎች በሱስ ፣ በዘፈን ፣ በመጠጥ ውስጥ ይደበቃሉ ። አንድ በሽተኛ ከማደንዘዣ ሲነቃ ሕመሙ እንደሚጀምረው እንዲሁም በኃጢአት የደነዘዙ ከማደንዘዣው ሲወጡ መታመም ይጀምራሉ ። ማደንዘዣ መፈወሻ አይደለምና ። አንድ ሰው ፡- “ሰዎች ሰላምን ዱርዬ መስላቸው ከየቡና ቤቱ ይፈልጓታል” ብሏል ። ሰላም የጽድቅ ፍሬ ነው ። ሰላም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ገንዘብ ነው ። ጌታችን ፡- “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” ብሏል /ዮሐ. 14፥27/ ። ጌታችን ሰላም መለኮታዊ ገንዘብ መሆኗን ተናግሯል ። ዓለም የምትሰጠው ሰላም እንዳለም አልሸሸገም ። የዓለም ሰላም ግን ጊዜያዊ ዋሻ ነው ።
2- ራሳቸው የራሳቸው ስለሚመስላቸው
ሰዎች ኃጢአት የሚሉት ጎረቤትን መጉዳት ነው ። በራሳቸው ላይ ግን ሥልጣን ያላቸው ይመስላቸዋል ። እኔ እጠጣለሁ ግን ሌላውን አልረብሽም ። ጠንቋይ ቤት እሄዳለሁ የምሄደው ግን ለዕድሌ ለግንባሬ እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደለም ይላሉ ። ኃጢአት ሦስት ወገኖችን ይነካል ፡-
– እግዚአብሔርን
– ሰዎችንና
– ባለቤቱን
አንዳንድ ኃጢአት ጎረቤትን አይነካም ። ማንኛውም ኃጢአት ግን እግዚአብሔርንና ባለቤቱን ሳይነካ አይቀርም ። እኛ ስንፈጠር የእግዚአብሔር ነን። በክርስቶስ ደም ስንገዛም አሁንም የእግዚአብሔር ነን ። እኛ የእኛ አይደለንም /1ቆሮ. 3፥17፤6፥19-20/። ሰዎች በኃጢአት የሚቆዩት ራሳቸው የራሳቸው ስለሚመስላቸው ነው ።
3- ኃጢአትን በስሙ ስለማይጠሩት ነው
ለኃጢአት የቅጽል ስም ፣ የብዕር ስም ፣ የዳቦ ስም ያወጡለታል ። መጠጡን መዝናናት ፣ ሱሱን ቀጭ ቀጭ ፣ ሌብነቱን ቢዝነስ ፣ … በማለት ይጠሩታል። ሰው ኃጢአትን የሚላቀቀው ኃጢአትን በስሙ ሲጠራው ብቻ ነው ።
4- ትልቅና ትንሽ ኃጢአት ብለው ሰንጠረዥ ስለሚያወጡ
ሰዎች በኃጢአት የሚቆዩበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የትልቁ ኃጢአት መነሻው ትንሹ ኃጢአት እንደሆነ ይናገራል ። ለወይኑ የሚያሰጋው ትልቁ አንበሳ ሳይሆን ጥቃቅን ቀበሮዎች ናቸው /መኃ. 2፥15/ ። የትልልቅ የቆሻሻ ተራራዎች መነሻው አንድ ቅርጫት ቆሻሻ ነው ። ግዙፉን መርከብ ለመስጠም የሚያደርሰው በወለሉ ላይ ያለች ትንሽ ቀዳዳ ናት። ሱዳንና ግብጽን አጠጥቶ ወደ ሜድትራንያን ባሕር የሚፈስሰው ዓባይ መነሻዎቹ ትንንሽ ምንጮች ናቸው ። የቢሊየን ቊጥር መነሻው አንድ ነው ። ትልቁ ፈረስ ላይ የምንወጣው በትንሿ እርካብ ነው ።
ጌታችን “ለቀደሙት፡- አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል” ብሏል /ማቴ. 5፥21-22/። ኦሪት ያወገዘችው መግደልን ነው ። ጌታችን ግን የመግደል መነሻ የሆኑትን ሦስት ነገሮችን አወገዘ ።
– ቊጣ
– ንቀት
– የማይረባ ብሎ ማሰብ
በቊጣ ምክንያት ግለሰቦች ተገድለዋል ። በንቀት ምክንያት ግን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል ። የማይረባ ብሎ በሰው ተስፋ መቊረጥም ከመግደል ያደርሳል ። አዎ የዝሙት መነሻ ማየት ፣ የስርቆት መነሻ ስስት ፣ የሱስ መነሻ ጓደኝነት ነው ።
5- ለድሆች ማሸከም
ሰዎች ኃጢአትን የሚሠሩበትና በኃጢአት የሚቆዩበት ምክንያት ኃጢአታቸውን ለድሆች በማሸከም ነው ። ድሆች በዓለም ላይ የባለጠጎች ቤዛ ከሆኑ ሰንብቷል ። ወንጀለኛው በከተማ ይንጎማለላል ። ንጹሑ ግን በሐሰት ምስክር ተፈርዶበት እስር ቤት ይማቅቃል ። ስላልታሰሩ ያልበደሉ ይመስላቸዋል ። የተከበሩ የተባሉ ሰዎች ከሠራተኞቻቸው ይወልዳሉ ። ልጁ ግን የአሽከር ነው ይባላል ። ዳዊት የኦርዮን ሚስት ወስዶ ማርገዟን በሰማ ጊዜ ኦሪዮንን ከጦር ሜዳ አምጥቶ ወደ ቤትህ ሂድ ብሎ አባብሎታል ። ልጁ የኦርዮ ነው እንዲባል ሞክሯል 2ሳሙ. 11፥6-9/ ።
6- ከራሱ ከኃጢአት ጋር ስለሚታገሉ
ኃጢአት ማለት እንደ ነብር ዘሎ የሚያንቅ አይደለም ። ኃጢአት ሂደት ነው። ራሳችንን ካልደለልን በቀር ምን ስናይ ምን እንደምናደርግ እናውቃለን። ከነማን ጋር ስንውል ምን ዓይነት ስህተት ውስጥ እንደምንገባ እናውቃለን ። ከራሱ ከኃጢአት ጋር መታገል ባለ ድል አያደርግም ። ወደ ኃጢአት ከሚያደርሱ ሁኔታዎች ፣ ቦታዎች ፣ ጊዜዎች ፣ ሰዎች ፣ ጽሑፎች ፣ ፊልሞች መራቅ ይገባል ። ሐዋርያው ፡- “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም” ይላል /ዕብ. 12፥4/ ። ይህ የእኛ መልእክት ነው ።
7- ኃጢአትን በኃጢአት ለማጥራት ስለሚፈልጉ
አፍሪካውያን ፡- “ደም በደም አይጠራም ይላሉ ። ደም የሚጠራው በውኃ ነው ። የሰረቀ በጉቦ ፣ ያመነዘረ ጽንስን በማስወገድ ፣ ወንጀል የሠራ ያየውን ሰው በማስወገድ ኃጢአትን ለመሸፈን ይሞክራል ። ዳዊት ኃጢአትን በኃጢአት ለመሸፈን ሞከረ ። ዝሙትን በመግደል ለመሸፈን ሲፈልግ የበለጠ ወደቀ ። ኃጢአት የሚሸፈነው በንስሐ ፣ በይቅርታ ፣ በክርስቶስ ደም ነው ።
ኃጢአት ሁለንተናዊ ጥፋትን የሚያስከትል ነው ። የሕሊና ቊስለትን ያመጣል ። ሰው ኃጢአት በሠራ ቅጽበት ጸጋው አይገፈፍም ፣ ፀሐይ አትጠልቅም ። ከሕሊናው ጋር ግን ይጣላል ። እግዚአብሔር ኃጢአት በሠራን ቅጽበት ሰላማችንን የሚወስደው ቆም እንድንል ነው ። ኃጢአት ጤናን ይጎዳል ። በመጠጥ ፣ በዝሙት ብዙ ዓይነት በሽታዎች ይመጣሉ ። ኃጢአት ኢኮኖሚን ያናጋል ። ሱሰኞች ቁማርተኞች ገንዘብ አይበቃቸውም ። የሀገርም ሀብት የሚባክነው ለደኅንነት ሥራ ነው ። ኃጢአት ማኅበራዊ ተቀባይነትን ያሳጣል ። ሌቦችን ማንም አያምናቸውም ። ሰካራሞችን ማንም ለሽምግልና አይጠራቸውም።
ኃጢአት ዘር ነውና የአጨዳ ዘመን አለው ። ገበሬ የሚያጭደው የዘራበት መሬት ላይ ነው ። መዝራትና ማጨድም በምድር ላይ ነው ። ከዚህ ሁሉ በላይ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ለይቶ ለዘላለም በገሀነም ይጥላል ። ጌታችን ያችን ሳምራዊት ሴት ለንስሐ መጋበዙ ከዚህ ሁሉ ጥፋት ሊያድናት ነው ። በኃጢአት የቆየችበትን ምክንያት ስላወቀ መፍትሔውን በመንገር ለንስሐ ጋበዛት ። መድኃኒት ሲገኝ በሽተኞች ይሰለፋሉ ። የእግዚአብሔር ምሕረትም ሲነገር ብዙዎች ለንስሐ ይበቃሉ ። ጌታችን ጸጋውን በውኃ ነው የመሰለው ። ድንቅ ምሳሌ ነው ። እግዚአብሔር እንደ ውኃ አብዝቶ የሰጠን ምን ነገር አለ ? የምድር ሦስት አራተኛው ውኃ ነው ። አባቶች የእግዚአብሔርን የምሕረት ስፋት ለመግለጥ ፡- “የእግዚአብሔር ምሕረት እንደ ውቅያኖስ ነው ። የሰው በደልም እንደ ቤት ጥራጊ ነው ። የቤት ውስጥ ጥራጊ በውቅያኖስ ላይ ቢበተን ውቅያኖሱ እንደማይቆሽሽ እንዲሁም የሰውም ኃጢአት የእግዚአብሔርን ምሕረት አያሸንፈውም” ይላሉ ።