የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለምናውቀው እንሰግዳለን

“እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን” /ዮሐ. 4፥22/ ።
ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት ጥያቄ መልስ እየሰጠ ነው ። ስግደትን ብቁ የሚያደርገው ደብረ ገሪዛን ወይም ኢየሩሳሌም ሳይሆን አዳኙን በማወቅ ሲቀርብ ነው ። ጌታችን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ አላት ። ለባዕድ አምልኮ ትሰግዳላችሁ ማለቱ አይደለም ። የሰማይን አምላክ ልታውቁት በሚገባችሁ መጠን አላወቃችሁትም ማለቱ ነው ። ካላወቃችሁት ማን ብላችሁ ታመልኩታላችሁ ? ማለቱ ነው ። እነዚህ ሳምራውያን ብሉይ ኪዳንን በሙሉነት አይቀበሉም ። ስለዚህ ስለ እግዚአብሔርና ስለ መሢሑ ያላቸው እውቀት የተሟላ አይደለም ። ለአይሁዳውያን ጥላቻ ቢኖራቸውም መሢሑ ግን የሚመጣው ከአይሁድ ወገን ወይም ከይሁዳ ነገድ መሆኑን ነገራት ። ለአይሁዳውያን ያላቸው ጥላቻ መሢሑን እንዳይቀበሉ እንቅፋት እንዳይሆን አስጠነቀቃት ። ከአይሁድ ከሆነ ምንም አንቀበልም የሚል አሳብ ውስጥ ከገቡ መዳናቸውን እንደሚያጡ ነገራት ። ለመቀበል የተዘጋጀነው ከምንወዳቸው የሚመጣውን ብቻ ከሆነ የሚያመልጡን ብዙ ነገሮች አሉ ። ከምንጠላቸው ውስጥም ለእኛ የሚሆን ብዙ ክቡር ነገር አለ ። አንድን ሰው ማክበር እግዚአብሔር በእርሱ ውስጥ ያስቀመጠውን ጸጋ ማክበር ነው ። ከጸጋ የመከነ ባዶ ፣ ከቸርነትንም የነጠፈ ደረቅ የለም ። ሙሉ በሙሉ ደግ የለም መልአክ ካልሆነ ፣ ሙሉ በሙሉ ክፉ የለም ሰይጣን ካልሆነ ።
የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ ብቻ እናስተምራለን ማለት አይደለም ።የእግዚአብሔርን ቃል ከብሉይ ከአዲስ በሙሉነት ካላወቅን አስተማሪ መሆኑ ከባድ ሊሆን ይችላል ። አሊያ ቀጣይ ዘመናችንን የምናባክነው እኛው ያበላሸነውን ስናስተካከል ነው ። ለእርሱም ዕድሜአችን ከበቃን መልካም ነው። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ያስቀመጠውን ከግብ ሳናደርስ እንቀራለን ። ስንሳሳት የደገፈን ሕዝብ ስንታረም ሊጠላን ይችላል ። መሳሳታችንን የታገሠ ማወቃችንን መቃወም ይጀምራል ። የዚህ ችግሩ መሠረትን ሳያጠብቁ የአገልግሎትን ሕንጻ መገንባት ነው ። አስፈሪ ዘመን ማለት ሊቅ የበዛበትና ሁሉም ካልተናገረ የሚሞት የመሰለው ዘመን ነው ። ዘመነ ጆሮ ቀርቶ ዘመነ አፍ ብቻ ከሆነ ስህተት እየበዛ ይመጣል ። ምነው ሁላችንም ዝም ብለን እግዚአብሔር እንዲናገር ፣ አባቶች እንዲናገሩ ዕድል በሰጠን ። በዚሁ ከቀጠልን እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን ነጻ የትምህርት ዕድል እያበላሸን በክፍያ እንማራለን ። የሃይማኖት ነጻነት ባልነበረበት በደርግ ዘመን ሁለትና ሦስት እየሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ የነበሩ ሳያውቁት የየራሳቸውን ዶክትሪን በጓዳ መሥርተው ነበርና ነጻነት መጥቶ ሁሉም ወደ ደጅ ሲወጣ ይህ ሁሉ እምነት ተመሠረተ ። ቅዱስ ያዕቆብ ፡- “ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና” ያለው ለዚህ ነው /ያዕ. 3፥1/ ። ዛሬ ማረም እስኪከብድ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም ሐሰተኛ አሠራር እየሠለጠነ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው ። እንኳን ሃይማኖቱ ፖለቲካውና ባሕላዊ እሴቱ ኦርቶዶክሳዊ ቅኝት ያስፈልገዋል ። ኦርቶዶክሳዊ የእውቀት ጎዳና አንድን አሳብ ከብሉይ ከአዲስ ፣ ከታሪክ ከዓለም አቀፍ ጉባዔያት ፣ እንዲሁም ጌታችን ብሉይን ከተረጎመበት ከወንጌል ፣ የጌታችንን ቃል ካብራሩት ከሐዋርያት መልእክታት ፣ የሐዋርያትን መልእክታት ከተረዱበት ሐዋርያነ አበው አስተምሮ በመነሣት የሚተረጉም ነው ። በዚህም እያንዳንዱ ጥቅስ ነገረ መለኮታዊ ፋይዳና ጥበቃ ያገኛል ። ከእግዚአብሔር ህልውናና ክብር ጋር ይዛመዳል ። የአባቶችን ዐሠረ ፍኖት ይከተላል ። ኦርቶዶክሳዊ እውቀት ማለት የእግዚአብሔርን ቃል በቋንቋ ፣ በባሕል ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት መተርጎምና ማግዘፍ ነው ። በራሳቸው ሮጠው የደከማቸው ሁሉ ወደዚህ አስተሳሰብ እየመጡ እንደሆነ በመላው ዓለም እያየን ነው ። በእውነት ከመጠምጠም ትምህርት ይቅደም የተባለው ትክክል ነው ። አንድ አባትም ፡- “ላልተማረ ሰው ሥልጣን መስጠት ለእብድ ሰይፍ መስጠት ነው” ብለዋል ።
እግዚአብሔርን ለማምለክ እውቀት አስፈላጊ ነው ። እውቀት በመንፈሳዊ ዓለም መሠረት ነው ። በራሱ ፍጻሜ ባይሆንም የፍጻሜ መልካም መነሻ ነው ። እውቀት ለእምነት አስፈላጊ ነው ። ምክንያቱም እምነት የሚመጣው የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ ምላሽ በመስጠት ነውና /ሮሜ. 10፥17/ ። እውቀት ከዘላለም ሕይወት ጋርም የተያያዘ ነው /ዮሐ. 17፥3/ ። እውነተኛ አምላክ የሆነውን አብን የላከውንም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ እርሱ የዘላለም ሕይወት ነው ። ለእግዚአብሔር እውነተኛ ስግደትን ለማቅረብም እውቀት አስፈላጊ ነው /ዮሐ. 4፥22/ ። ለአምልኮ እውቀት አስፈላጊ ከሆነ ለመስበክና ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር የበለጠ እውቀት አስፈላጊ ነው ። ሰው በግሉ ለሚፈጽመው ስግደት እውቀት አስፈላጊ ከሆነ ሌሎችን ለመምራት የበለጠ ያስፈልገዋል ። እውቀትን በሚጠሉና እውቀትን መጨረሻ ባደረጉ ወገኖች ይህች ዓለም ተረብሻለች ። እንደ ጥንቱ ዛሬም በሰዱቃውያንና በፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት ትሞገታለች ። ፈሪሳውያን ሥርዓትን ያለ ፍቅር የያዙ ፣ ሰዱቃውያን ፍቅርን ያለ ሥርዓት የያዙ ናቸው ። ፈሪሳውያን ወግ አጥባቂ ናቸው ፣ ሰዱቃውያን ደግሞ ዘመናውያን ናቸው ። ፈሪሳውያን ንባብ ላይ ያተኩራሉ ፣ ሰዱቃውያን ሌሎችን መርዳት ላይ ጊዜ ይሰጣሉ ። ዓለም በአክራሪዎችና በንዝህላሎች ተጨንቃለች ። እውቀት ግን ከሁለቱም መልካሙን በመውሰድ ለእግዚአብሔር ክብር ያውለዋል ። የንጉሥ መንገድ ከመሐሉ ነውና።
አለቃ ለማ ኃይሉ ትልቅ ሊቅ ናቸው ። ትዝታቸውን ያሰፈረው ልጃቸው “ትዝታ ዘአለቃ ለማ” በሚለው መጽሐፍ የእውቀትን አስፈላጊነትና እውቀትን የሚጠሉ ሰዎችን ጉዳት እንዲህ ገልጸውታል ።
“ደጃች ኃይሉ የሸደሆ ገዥ ፣ ደጃች ወንዴ ደግሞ የመቄት ገዥ ነበሩ ። ደጃች ኃይሉ የተማሩ ሲሆኑ ደጃች ወንዴ ግን አልተማሩም ነበር ። ደጃሽ ከጣቢሽ የተባሉት ደግሞ ሁለቱንም ግዛቶች በአንድነት ይገዙ ስለነበር የሁለቱም ደጃቾች የበላይ ነበሩ ። ሁለቱ ደጃቾች ወደ ደጃች ከጣቢሽ ይሄዳሉ ። ቤተ ክርስቲያኑ ጊዮርጊስ ነው ። ሁለቱም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ይጸልያሉ ። ደጃች ኃይሉ ዳዊት አውጥተው ይደግማሉ ። መልኩንና ይህን የመሰለውን ሁሉ በመጽሐፍ ይደግማሉ። ደጃች ወንዴ ደግሞ ትምህርት የሌላቸው ናቸውና “ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቴ አምላክ ! ፈጥረህ የት ትጥለኛለህ? እያሉ ያለ መጽሐፍ በቃል ይጸልያሉ ። በኋላ ሁለቱም ተያይዘው ደጃች ከጣቢሽ ወዳሉበት ይወጣሉ ። ከዚያ ደጃች ወንዴ ፡- “ደጃች ኃይሉ፣ መማር ለምን ይበጃል? “አሉ ። ተንኮለኛ ነህ ለማለት ነው ። ደጃች ኃይሉም፡- “ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣሪዬ! ከማለት ያድናል” ሲሉ መለሱላቸው ይባላል።
 እውቀት እንደሚያሳስት ተደርጎ ይታሰባል ። በርግጥ ያልተማሩ ማለት የማያነቡ የማይጽፉ ማለት አይደለም ። መሐይም የሚባሉ መማር የማይፈልጉና አለማወቃቸውን ሳያፍሩበት እንደ እውቀት የሚናገሩ ናቸው ። ሰው በትክክል ሲያውቅ ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጣል ። ብዙ ጊዜ እንደምናየው በጣም የተማሩ ሰዎች ዝቅ የሚሉ ትሑታን ናቸው ። ምክንያቱም በጣም ባወቁ ቊጥር የማያውቁት እየበዛባቸው ይመጣልና እውቀታቸው ሰበር ያደርጋቸዋል ። ፍሬ ያለው አገዳ ዘንበል ይላል ። ቀጥ ብሎ የሚቆመው ፍሬ የሌለው አገዳ ብቻ ነው ።
ጌታችን ፡- “እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን” አለ /ዮሐ. 4፥22/ ። እርሱ አዳኝ የማያስፈልገው አዳኝ ፣ ስግደት ተቀባይ የባሕርይ አምላክ ሳለ ራሱን ዝቅ አድርጎ በሚድኑት ሰልፍ ውስጥ ተቀላቅሎ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን አለ ። ራሱን በዚያች ሴት የእውቀት መጠን ዝቅ አድርጎ እያስተማራት ነው ። ሕጻናት ምንናገረውን በትክክል እንዲገነዘቡ ቀመን ልናወራቸው አይገባም ። ተንጠራርተው እያዩን መጨነቅ እንጂ ትምህርት አይዙም ። በርከክ ብለን በእነርሱ ቁመት ልክ ሆነን ስንነነግራቸው ግን ይሰሙናል ። በደረስንበት የእውቀት ቁመት ልክ ቆመን ብንናገር የሚሰማን የለም ። አድማጮቹ ባሉበት የእውቀት መጠን ዝቅ ማለት ያስፈልገናል ። ለምንናገረው ነገር ባዕድ ሳይሆን ተሳታፊ ስንሆን ንግግራችን ጽኑ ይሆናል ። የንግግር ማኅተሙ ተግባር ነውና ።
የብሉይና የአዲስ ትምህርት በምሳሌ ላይ የተመሠረተ ነው ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰዎች እንዲያውቁት በሰዎች ደረጃ ስለሚያስተምር ነው ። ተረቶችና ምሳሌዎችን ብዙ ሰዎች ይንቃሉ ። በዓለም ላይ ከባዱ ተረት ማዘጋጀት ነው ። በሕጻናት አእምሮ ወርዶ መሥራት ይጠይቃል ። ቅዱስ ማቴዎስ ፡- “በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም”ይላል /ማቴ. 13፥34/ ። ታዲያ እኛ ከጌታችን እንበልጣለን ወይ ?
በዓለም ላይ ብዙ እውቀቶች አሉ ። አዳኙን ማወቅ ግን ከፍ ያለ እውቀት ነው ። አዳኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ገድሎ ሳይሆን ሞቶ ፣ ብርና ወርቅ ከፍሎ ሳይሆን ወርቀ ደሙን አፍስሶ የታደገን እርሱ ነው ። በባሕር ላይ ዘራፊዎች ፣ በበረሃ ሽፍቶች የታገቱ ሰዎች ያለባቸው ሰቆቃ ከባድ ነው ። ሞትን አንድ ጊዜ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ያዩታል ። ታዲያ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች አሉ ። በመንግሥታቱና በሽፍቶቹ መካከል ገብተው የታገቱትን ሰዎች በክፍያ ያስለቅቃሉ ። በሕይወት መንገድ ላይ የታገትነውን ፣ ሽፍታው ሰይጣን የያዘንን ፤ የገዛ የጽድቅ ባሕርዩን አርክቶ ያዳነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እውነተኛ አምልኮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ይጀምራል ። ጸሎቱ ፣ ምስጋናው ፣ ምልጃው ሁሉ በአሐዱ ወልድከ ማለት በአንድ ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚል ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ