የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ አምልኮ

“ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና” /ዮሐ. 4፥23/ ።
በደብረ ገሪዛንም ሆነ በኢየሩሳሌም ይቀርብ የነበረው ስግደት እውነተኛነት ይጎድለው ነበር ። ለእግዚአብሔር ልባቸውን ደብቀው መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ፣ ፍቅርን ጥለው ወደ ፍቅር አምላክ የሚጸልዩበት ነበር ። አምልኮትን ከእውነት የሚለዩ ብዙ ነገሮች አሉ ። አምልኮ እውነተኛ ካልሆነ ለእውነተኛው አምላክ ሊቀርብ አይችልም ። እግዚአብሔር እውነተኛ ነውና እውነተኞችን ይወዳል ። እግዚአብሔር የሚወደው እውነት ኃጢአትን ያለመሥራት እውነት ብቻ ሳይሆን ኃጢአትን የማመን እውነትንም ነው ። እርሱ የሰውን ድካም የሚያውቅ አምላክ ነው ። ሰዎች ያለ እርሱ እርዳታ ደካሞች ፣ ሥጋቸውም ወደ ገዛ አገሩ ወደ ምድር የሚስባቸው እንደሆነ ያውቃል ። ኃጢአታቸውን አምነው የቅዱስ መንፈሱን እገዛ እንዲለምኑ ግን ይፈልጋል ። እውነትነት የሌለው አምልኮ ምን ዓይነት ነው ?
ያለ ፍቅር የሚደረግ አምልኮ
 እግዚአብሔር በፍቅራችን ደስ የሚለውን ያህል በመሥዋዕታችን ደስ አይለውም ። ፍቅርም ያለ እንቅፋት የሚጓዝ አይደለም ። መንገድን የሚያስረዝመው ድልድይ ነውና ፍቅርንም ቀጣይ የሚያደርገው ይቅርታ ነው። ስለዚህ ስንበድል ይቅርታ መጠየቅ ፣ ሲበድሉን ይቅርታ መስጠት ትልቅ አምልኮ ነው ። ሌሎች በእኛ ላይ ያላቸው ቅሬታ የአምልኮ መንገዳችንን ይዘጋል /ማቴ. 5፡23-25/ ። የምንጸልየውም ወደ ተዘጋ ሰማይ ነው ። ሰዎቹን ትንንሽ ብለን የምንንቃቸው ሊሆኑ ይችላሉ ። ትንንሾቹ ግን ትልቅ አምላክ እንዳላቸው ማወቅ አለብን ። እግዚአብሔር ለደካሞች ይዋጋል ፣ ለምስኪኖችም ይሟገታል ። ሰዎችን መንካት እግዚአብሔርን መንካት ነው።
ቅሬታውንም ትንሽ ነው ብለን ልንንቀው እንችላለን ። ሰዎቹን ካሳዘነ ግን ትልቅ ነው ። ቅሬታን መለካት ያለብን በእኛ ጥንካሬ መጠን ሳይሆን በሰዎቹ ጥንካሬ መጠን ነው ። ምናልባት የተናገርነውና ያደረግነው መልካም ነገር ክፉ መስሎአቸው ቅር ሊሰኙ ይችላሉ ። ያንንም አስረድተን ይቅርታ መጠየቅ ይገባል ። ለዓይንና ለፍቅር ትንሽ ይበቃዋል የሚባለውን ማሰብ አለብን ። ሰዎች ሲወዱን እንደ ፍጹም ሰው ያዩናል ። ስለዚህ መሳሳት አይችሉም ብለው ስለደመደሙ ትንሹ ስህተታችን ይጎላባቸዋል ። “አታስለምድ አታስቀር” ይባላል ። በአንዳንድ አገር ለሰዎቹ አንድ ነገር ካስለመድን ያንን የለመዱትን ሲያጡ ይጣሉናል ። ታዲያ ተጣላኝ ተብሎ ፖሊስ ጋ ሲኬድ ያስለመድከውን አድርግለት ብሎ ይመልሳል ። ምክንያቱም ያስለመድከውን በአንድ ጊዜ ስታቆም ጠብ ይመጣል ማለታቸው ነው ። ደግሞም በፈቃድህ ያስለመድከውን እንደ መብቱ ስላየው ነው የሚል ትርጉም ይሰጣሉ ። ወዳጅ ሲያረጅ በጓሮ ይሄዳል የሚባለው ለዚህ ነው ። ቅሬታን ከሚያስነሡ ነገሮች አንዱ ያስለመድነውን ማስቀረት ነው ። ደረጃ ያለው ግንኙነት ከጠብ ያድናል ።
   ይልቁንም በአንድነታችን የጋራ አምልኮ እናደርጋለን ። ቅዳሴ እናሳርጋለን ። ዝማሬ እናቀርባለን ። ምህላ እናደርሳለን ። ሥጋወደሙ እንቀበላለን ። እነዚህ ሁሉ ያለ ፍቅር ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርሱ አይደሉም ። የማይዋሸውን አምላክ ለመዋሸት የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው ። እግዚአብሔር ምን አደረጋችሁ ? ከማለት በፍቅር አደረጋችሁት ወይ ? ይለናል ። ይልቁንም የአዋጅ ጾም ስናደርግ ሦስት ነገሮችን ማድረግ ይገባናል።
1-  ርእስ መያዝ
2-  ይቅር መባባል
3-  ንስሐ መግባት
 ለአንድ አዋጅ ጾም ከሚያስፈልጉት ሦስት ነገሮች ሁለቱ ይቅርታ ናቸው ። ይልቁንም የማይቆጠረውን ኃጢአታችንን እግዚአብሔር ይቅር እያለ እኛ የሰዎችን የሚቆጠር ኃጢአት ይቅር ለማለት መቸገር የለብንም ። እግዚአብሔር በየቀኑ ይቅር እያለን እኛ ግን የሰዎችን ስህተት በሕይወት ዘመናችን አንድ ጊዜ ይቅር ለማለት እንቸገራለን ። ይቅርታ ማጣት ሰላማችንን ይጎዳል ። አምልኮአችንን ከንቱ ያደርገዋል ። በብዙ ችግር ውስጥ ሁነን መጸለይ እንችላለን ። በትንሽ ቅሬታ ውስጥ ሁነን ግን መጸለይ አንችልም ። ይቅርታ በማጣት በረከታችን ይያዛል ። የማገልገል ጉልበታችን ፣ የመስጠት እጃችን እየታሰረ ይመጣል ። ፍቅር የሌለው ማንኛውም መንፈሳዊ ተግባር ባዶ መሣሪያ እንደ መደገን ነው ። ባዶ መሣሪያ የደገነ ራሱም ይፈራል ። ምክንያቱም የደገነበት ሰው ቢይዘኝ የሚል ድንጋጤ አለው፤ የተደገነበትም ይፈራል ፣ ቢገድለኝስ የሚል ድንጋጤ ውስጥ ይገባል። ሁለቱም ግን ባዶ ናቸው ። ፍቅር የሌለበት የአገልግሎት ትጋት ፣ የጾም ጽናት ፣ የጸሎት ቁመት ዋጋው ያነሰ ነው ። እየጸለይን መልስ ፣ እየጾምን ምሕረት የማናገኘው በዚህ ችግር ነው ። በየቀኑ ስለ ዝሙትና ስርቆት አንወቀስም ። በየዕለቱ ይህ ስህተት አይገዛንምና ። በየዕለቱ ግን ከፍቅር ሳንጎድል አንቀርም ። አምልኮችንን ከመፈጸማችን በፊት ፍቅር እንዳለን ራሳችንን እንመርምር ። የበደልናቸውን ፣ ይጥፉ ብለን አዋጅ ያስነገርንባቸውን ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልገናል ። ምክንያቱም መንፈሳዊ ነገር በመንፈሳዊነት እንጂ በጉልበት የሚፈጸም አይደለምና ። እግዚአብሔር ሊምረን ተሰናድቷል ። የምሕረት ደጁን መጽፋት ሲገባን የእኛን ደንዳና ልብ እርሱ እየጸፋ ነው ። ሊምረን ደጃችንን የሚያንኳኳ ፣ ሊፈውሰን ክፈቱልኝ የሚለው አምላክ ቀርቦአልና በፍቅርና በይቅርታ ልናመልከው ይገባናል ። ፍቅር የሚለውን ቃል ፊደሉን እንኳ ብንተነትነው የፍቅርን ባሕርይ ያሳየናል።
– ፍትሕ
– ቅንነት
– ርኅራኄ
ፍቅር ፍትሕ አላት ። ፍትሕ በራስም መፍረድ ነው ። እገሌን በድያለሁ ፣ ለጥቅሜ አድልቼ ወይም ይህን ላጣ እችላለሁ ብዬ ባልተጨበጠ ስህተት የተጨበጠ በቀል አድርሻለሁ ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ ማለት ነው ። ለበረታ ጎበዝ ፣ ጊዜ ለሰጠው ደፋር ሳይሆን ለተጎዳ መፍረድም ከክርስቲያን የሚጠበቅ ነው ። እውነትን እውነት በማለት ብቻ ምድርን ከስቃይ እናተርፋለን ።
ፍቅር ቅንነት አላት ። ቅንነት ማለት አክሞ መስማት ፣ ነገሮችን በበጎ ማየት ፣ ከችግሩ ወራጅ ችግሩን የወለደውን ምንጭ ማጥናትና መፍትሔ ማፈላለግ ነው ። ሰውዬው ያንን ክፉ ነገር ለማድረግ አስተዳደጉ ፣ ትምህርቱ ፣ ሃይማኖቱ ፣ ልማዱ ያደረሱበት ተጽእኖ ምንድነው ? ብሎ ማሰብ እርሱ ቅንነት ነው ። ምክንያቱም ሰው ብቻውን በጎ ነገር ብቻውን ክፉ ነገር አይሠራምና ። አብረውት አስተዳደጉ ፣ ትምህርቱ ፣ ሃይማኖቱ ፣ ልማዱ አንዳንዴም ቅዱስ መንፈስና ርኩስ መንፈስ አብረውት አሉ ። ፍቅር ይህንን ታከናውናለች ።
ፍቅር ርኅራኄ አላት ። ሌሎችን ይቅር ለማለት ትፈልጋለች ። መንፈሳቸው በጠኔ የተያዙ ወይም ይቅርታ የተነፈጋቸው ራሳቸውንም የሚቀጡ አያሌ ወገኖች አሉ ። ፍቅር ታዝናለችና እነዚህን ሰዎች ይቅር ትላለች ፣ ይቅር ታስብላለች ። ፍቅር ጠባይዋ ማዋረድ ሳይሆን መሸፈን ነው። ፍቅር የኃጢአትን ብዛት የምትሸፍነው በፍትሕ ፣ በቅንነትና በርኅራኄ ነው /1ጴጥ. 4፥8/ ። ይኸው ስለ ፍቅር ስንናገር እንኳ ውስጣችን ደስ ይለዋል ። ፍቅር ሲያደርጉት ብቻ ሳይሆን ሲሰሙትም ደስ ያሰኛል ። የጎደለን ፍቅር ነው ። ቅዱስ አውግስጢኖስ ፡- “ፍቅር ልብህን ይግዛው ከዚያ በኋላ የወደድከውን ማድረግ ትችላለህ” ይላል ። እውነተኛ ፍቅር በውስጣችን ካለ ሐሰተኛ ተግባር ሊኖረን አይችልም ። ያለ ሕግጋት ዝርዝር ፍቅር ሕግጋትን ትጠብቃለች ። እውነተኛ ፍቅር እስከሌለን አምልኮአችን ልባዊና ሙሉ መሆን አይችልም ። ጸሎታችንን ቆም ፣ ምህላችንን ገታ አድርገን እስቲ አሁን ይቅር እንባባል ። ያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ምሕረት ማየት እንችላለን።
አንድ እናት ከልጆቻቸው ጋር በሀብት ምክንያት ትልቅ ረብሻ ተፈጠረባቸው ። ልጆቻቸውም እናትነታቸውን ለመካድ ትንሽ ቀራቸው ። እናቲቱም ብቸኛ ሆነው ቆሙ ። ነገር ግን ከመጀመሪያ ልጅ ጀምሮ መንፈቅ ባልሞላ ጊዜ ሦስት ልጆች ሞቱ ። በአራተኛዋ ልጅ ልቅሶ ላይ በአደባባይ ቆመው ፡- “ወገኖቼ አታልቅሱብኝ ። እኛ የሞትነው ከፍቅር ገንዘብን ያስቀደምን ቀን ነው ። ለሚያልፍ ንብረት ይኸው ከልጆቼ ጋር እንጣላለን ። አራት ልጆች ሸኘሁ” አሉና ወደ ቀሩትና ልባቸውን ወዳደነደኑት ልጆቻቸው ዘወር ብለው ፡- “የቆመው ሳይዋደድ ለሞተው መናደድ ከንቱ ነው ። እኛ እንስማማ” ብለው እግር ላይ ሲወድቁ ልጆቹ በልቅሶ ተመለሱ ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ሞትም ሰይፉን ወደ ሰገባው እስከ ጊዜው አስገባ ። ዛሬም ላለፈው ትተን ቀጣዩን ለመዋጀት ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል ። በአገር በቤተ ክርስቲያን የመጣውን ክፉ ነገር የምንመልሰው በፍቅር ብቻ ነው ። የመጣብን ባዕድ የለም ። እርስ በርሳችን መጨቋቆናችን ይገርማል ።
ሐዋርያው ፡- “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም” ብሏል /1ቆሮ. 13፥1-3/ ።
ሐዋርያው በዚህ ክፍል ላይ ትልልቅ ዋጋ የሚሰጣቸውን ነገሮች ያነሣል፡-
1-  የንግግር ችሎታ
2-  ስለወደፊቱ መተንበይ
3-  እውቀት
4-  ሃይማኖት
5-  በጎ አድራጎት
6-  ሰማዕትነት
እነዚህ ነገሮች በዓለም ላይ ትልቅ ዋጋ አላቸው ። እነዚህ ነገሮች ግን ያለ ፍቅር ከንቱ ናቸው ። ፍቅር የሌለው የንግግር ብቃት ይማርካል እንጂ አያሳርፍም ። ዛሬ ማድረግ ያለብንን ጥለን ስለ ነገ ትንቢት መናገርም ከንቱ ነው ። ነቢይነት ለዘመኑ ሰፊውን አገልግሎት ይሰጣል ። ሌሎችን የማያስብ እውቀትም ጨለማ ነው ። ለዓለም መፍትሔ መሆን ሲገባው ስጋት የሆነ ሃይማኖትም ጥቅም የለውም ። ፍቅር የሌለበት ምጽዋትም ከስድብ አይተናነስም ። ከሰማዕትነትም ፍቅር ይበልጣል ። እውነተኛ ሰማዕትነት ጥላቻንና ራስ ወዳድነትን መጣል ነው ። በየቀኑ ሰማዕት የምንሆነውም ፍቅርን ስንመርጥ ነው ። ፍቅር አቀበት ነው ። አንዳንዴ እየዳሁ የሚወጡበት ተራራ ነው ። የነፍስ ግን ቀለቧ ነው ። አምልኮ እውነተኛ የሚሆነው በፍቅር ነው ።
ጌታችን በእውነት የሚሰግዱ በማለት ተናገረ ። በእውነት መስገድ ከቻልን ከቦታና ከጊዜ በላይ ሁነን እንሰግዳለን ። አንተ ሳምራዊ ፣ አንተ አይሁዳዊ መባባል ያለበት ፤ የዘር ጽዋ ስካር የወለደበት አምልኮ ቅድመ እግዚአብሔር አይደርስም ። እኛስ ፍቅር አለን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ