የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአፍ አምልኮ

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ እውነተኛ አምልኮን ከሕዝቡ ፈልጓል ። ለእርሱ ቤትን ከመሥራታችን በፊት ቤት እንድንሆንለት ፣ መሥዋዕት ከማቅረባችን በፊት እንድንታዘዘው ፣ መባ ከማምጣታችን በፊት እርሱን እንድናውቀው ጠይቋል /ኢሳ. 66፥1-4፤ 1ሳሙ. 15፥22፤ ሆሴዕ. 6፥6/ ። ሳኦልን ከንጉሥነት የሻረው መታዘዝን ንቆ መሥዋዕት በማምጣቱ ነው ። መሥዋዕቱ የታየው እንደ መደለያ ነበር ። ይህ እግዚአብሔርን መናቅ ነውና እግዚአብሔርም በእስራኤል ንጉሥ እንዳይሆን ናቀው ። ሁላችንም ብንሆን የምንፈልገውን ነገር እንዲሰጡን እንጂ እንዲወረውሩልን አንፈልግም ። ከፍትፍቱ ፊቱ የምንለው በዚህ ምክንያት ነው ። ፊት ያልቀደመበት ፍትፍት ያንቀናል ። ለስላሳ ቢሆንም ከጉሮሮአችን አይወርድም ። እግዚአብሔር ትልቅ አምላክ ነው ። ልባችንን ደብቀን አፋችንን እንዳናጫውተው ሁሉን ያውቃል ። ራሳችንን ሰስተን ገንዘባችንን ብናቀርብለት ዓለምና ሞላዋ የእርሱ ፣ ያመጣነውም ገንዘብ የራሱ ነው ።
እግዚአብሔር ሕይወታችንን ፣ አገልግሎታችንን ፣ ገንዘባችንን ይፈልጋል ። ተራው መሳት የለበትም ። መጀመሪያ ሕይወታችንን ቀጥሎ አገልግሎታችንን ቀጥሎ ገንዘባችንን ልናቀርብለት ይገባል ። አንዱ ያንዱም ምትክ መሆን አይችልም ። ገንዘብ የአገልግሎት ፣ አገልግሎትም የሕይወት ምትክ መሆን አይችልም ።
አንዳንድ ሰዎች ሕይወታቸውን ሰጥተዋል ። አገልግሎታቸውንና ገንዘባቸውን ግን መስጠት አልቻሉም ። ከኃጢአት ርቀዋል ፣ ጊዜአቸውንና ገንዘባቸውን ለመስጠት ግን ይፈተናሉ ። ወይም ምክንያት ያቀርባሉ ።ሌሎችም አገልግሎታቸውን ሰጥተዋል ። ሕይወታቸው ግን ገና በዓለም ነው። ገንዘባቸውም አልተቀደሰም ። የተቀሩትም ገንዘባቸውን ሰጥተዋል ። ነገር ግን ሕይወታቸው በስርቆት ፣ ጊዜአቸው በብክነት ያልፋል ።
እግዚአብሔር አፋአዊ የሆነ አምልኮን አይፈልግም ። ጌታችን ነቢዩ ኢሳይያስን በመጥቀስ ፡- “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ”  ያለው ለዚህ ነው /ማቴ. 15፥8-9/ ። ቅጠል መበጠስ እየተጠነቀቁ ሰውን ግን ለመቊረጥ መድፈር ፣ ሥራ አልሠራም እያሉ ነገር ግን ሲካሰሱ መዋል ፣ ይህን አልበላም እያሉ ነገር ግን የሰውን ሥጋ በሐሜት ሲያወራርዱ መዋል ይህ ተውኔታዊ ጽድቅ ነው ። ጌታ ጌታ ማለት እግዚአብሔርን ማምለክ አይደለም ። ጌታ ጌታ ከማለት ለጌትነቱ መገዛት የተሻለ ነው ።
ጀርመን ውስጥ በሚገኝ በአንድ ካቴድራል ሕንጻ ውስጥ አንድ የጥንት ጽሑፍ አለ፡-
ክርስቶስም እንዲህ ሲል ተናገረ፡-
መምህር ትሉኛላችሁ ነገር ግን የምላችሁን አታደርጉም
ብርሃን ትሉኛላችሁ ግን አታዩኝም
መንገድ ትሉኛላችሁ ግን አትመላለሱብኝም
ሕይወት ትሉኛላችሁ ግን አትመኙኝም
ሊቅ ትሉኛላችሁ ግን አትከተሉኝም
ደስ የሚል ትሉኛላችሁ ግን አትወዱኝም
ሀብታም ትሉኛላችሁ ግን ምንም አትጠይቁኝም
ዘላለማዊ ትሉኛላችሁ ግን አትፈልጉኝም
ቸር ትሉኛላችሁ ግን አታምኑኝም
ጌታ ትሉኛላችሁ ግን አታገለግሉኝም
ኃያል ትሉኛላችሁ ግን አታከብሩኝም
የቅን ፈራጅ ትሉኛላችሁ ግን አትፈሩኝም
ስለዚህ ብፈርድባችሁ በእኔ ማሳበብ አትችሉም ።
አንድ የተባረኩ ሊቀ ጳጳስ ናቸው ። ትሕትናቸውና መንፈሳዊነታቸው አሁንም ያብባል ። የአርምሞ ሕይወት እንዳላቸው አውቃለሁ ። ታዲያ በጣም የሚያስቸግራቸው መንፈሳዊነት ዕዳ የሆነበት አንድ ሥራ አስኪያጅ ገጠማቸው ። ወረዳ ገጠር እየወረደ ካህናትን ያስጨንቃል ሲባል ይሰማሉ ። ታዲያ አፍ መያዣ እያለ ማር ይዞላቸው ይመጣል ። አንድ ቀን ግን እኚህ ብፁዕ አባት ፡- “ልጄ ከዛሬ ጀምሮ ማር ይዘህ አትምጣልኝ ፣ ማር ሆነህ ናልኝ” አሉት ። ማር መሆን ማር ከማምጣት ይበልጣል ። እግዚአብሔርም ከስብከታችን በላይ ሕይወታችን እንዲሰብክ ፣ ከቃላችን በላይ ኑሮአችን እንዲዘምር ፣ ከቅኔአችን በላይ ሕይወታችን እንዲገዛ ይፈልጋል ።
ማመን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ልዩ መብት ነውና አምልኮአችን የውዴታና የእውነት ሊሆን ይገባዋል ። እግዚአብሔር የሚሰግዱለት በእውነት እንዲሰግዱለት ይፈልጋል ። በትዕቢት ከሚገላምጡን በላይ በሽርደዳ ጎንበስ የሚሉልን ያበሳጩናል ። እውነት የሌለበት እጅ መንሣት የስድብ ያህል ይሰማናል ። እግዚአብሔርም እውነተኛ ስግደትን ይፈልጋል ። እውነተኛን ስግደት ማቅረብ ካልቻልን እስክንችል መለመን ያስፈልጋል ። “ልቤን ወደ አንተ ሳብልኝ ፣ ውስጤም ውጬም ዝቅ እንዲልልህ እርዳኝ” ብለን መለመን ይገባናል ። አምልኮን እንደ ሥራ ሳይሆን እንደ ሕይወት ልንቀበለው ያስፈልጋል ። የአፍ አምልኮ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል ። ብዙ ሰው ለእግዚአብሔር ቀንቻለሁ ፣ እነ እገሌ ጌታዬን እያበሳጩት ስለሆነ ላጥፋለት የሚል ግብግብ ውስጥ የገባ ይመስላል ። እግዚአብሔር ግን ካንተ ይልቅ ያስቸገረኝ የለም ፣ እባክህ ተመለስ ሥራህን በፍቅር ፈጽም ብሎ ይመልስልናል።
የታይታ አምልኮ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ሦስት ነገሮችን ዳስሷል ። የከበረ ሕይወት ፣ የከበረ አምልኮና የከበረ ሃይማኖትን በሦስቱ ምዕራፎች ገልጿል ። የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት ስለ ከበረ አምልኮ የሚናገር ነው ። የከበረ አምልኮ ለታይታና ለሙገሳ የማይደረግ አምልኮ ነው ። የአምልኮን ዋጋ የሚከፍል እግዚአብሔር በመሆኑ ሰው የሚያየው ወይም ማስታወቂያ የሚሠራበት ስግደት ጌታችንን ያሳዝነዋል ። በዚህ ምዕራፍ የተጠቀሱት ዋና ዋና አምልኮዎች፡-
1-  ምጽዋት
2-  ጸሎት
3-  ጾም
4-  ኑሮዬ ይበቃኛል ማለት
5-  ጤናማ አመለካከት
6-  ለገንዘብ ያለን መንፈሳዊ እይታ
7-  የሚበልጠውን በማሰብ የሚያንሰውን መናቅ ናቸው ።
ጌታችን በተራ ቊጥር ከ1 – 3 ያሉት ለታይታ የመደረግ አደጋ እንዳለባቸው ጠቊሟል ። በጣም ጠቃሚ የሆኑ ምግቦች በቀላሉ የመበከል አደጋ እንዳለባቸው እነዚህም ነገሮች በትንሽ ነገር ሊበላሹ ይችላሉ ። ምጽዋት ለማስታወቂያ ፣ ጸሎትም የሌሎችን ልብና ኪስ ለመበዝበዝ ፣ ጾምም በማይጾሙት ላይ ለመመጻደቅ ይውላል ። በእውነት ሰዎች የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው ብለው ወደ እኛ ሲደውሉ ስልኩን ካላነሣን ጸሎት ላይ ይሆናሉ ብለው የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል ። እንዳሰቡን እንድንገኝ ሁልጊዜ መትጋት ይኖርብናል ። በአዋጅ የምናደርጋቸው ምጽዋት ፣ ጸሎትና ጾም አሉ ። የግል በሚሆንበት ጊዜ ግን በሚቻለን አቅም መሰወር ይገባናል ።
“በዚህ ኮሌጅ የተማረ ፣ ይህን ያህል መጽሐፍ የጻፈ ፣ ይህን ያህል ካሴት ያሳተመ ፣ ይህን ያህል ዘመን ያገለገለ ፣ በቤተ ክርስቲያን በእንዲህ ያለ ሹመት የሚሠራ …” ብላችሁ አስተዋውቁኝ የሚሉ ለአሙቁልኝ ሠራተኞች የሚከፍሉ አያሌ ናቸው ። ቃሉ ካገለገላችሁ በኋላ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ በሉ እያለ እኛ ግን ከማገልገላችን በፊት ትዕቢት መንገዱን እንዲጠርግልን እንፈልጋለን /ሉቃ. 17፥10/ ። የቱንም ያህል ብናገለግል መንፈስ ቅዱስ ልብን ካልማረከ ጆሮን እንጂ ልብን መማረክ አንችልም ። “ጌታ ሆይ በሰብአዊ ሩጫ ያንተን ሥራ ስለ ሠራን እባክህ ይቅር በለን ። ከቃልህም ፣ ከኪሣራችንም ልንማር አልቻልንምና እባክህ ወዳንተ መልሰን ። ለሚሠራው መንፈስህ ቦታ እንድንለቅ እርዳን ። በጸሎት የታሸ አገልግሎት ስጠን ። እያዳመጥንህ እንድንናገር እርዳን ። ከራሳችን የምንናገር አፈ ንጉሥ ከመሆን አድነን።”
አንድ ድምፃቸው የማያምር ሽማግሌ ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” የሚለውን ዝማሬ ሲዘምሩ ብዙዎች በዕንባ ይታጠባሉ ። ይህንን ዝማሬ በልዩ ድምፅና ቅላጼ ፣ በልዩ ቄንጥ ይዘምር የነበረ አንድ ወጣት መጣና እርስዎ ሲዘምሩ ብዙዎች ይነካሉ ፤ እኔ ግን ያንኑ ዝማሬ ስዘምር ሰዎች አይነኩም ። ምሥጢሩ ምንድነው ?” አላቸው ። እርሳቸው ግን ፡- “እኔ የምዘምረው እረኛዬን እያየሁት ነው ። አንተ የምትዘምረው ለድምፅህ ማማር እየተጨነቅህ ፣ የሰዎችንም ደስታ እያየህ ነው፤ ልዩነቱ ይህ ነው” አሉት ይባላል ። እግዚአብሔርን እያየን ስናገለግል እግዚአብሔርን የሚፈልግ ይፈወሳል ። ልቡን ያጸናም ይመለሳል ። የሰዎችን ሙገሳና ደስታ በመፈለግ ማገልገል ግን ድካሙ ብዙ ነው ።
አገልግሎትን በጸጋና በትሕትና ከማድረግ በደላላዎች ሰብሳቢነት ማድረግ እየተለመደ ነው ። ድሮ ጮሌ ባሕታውያን ሲሰብኩ ከአድማጮች መሐል ሁኖ ደህና የለበሰውን የሚያግባባ “ቤት ቢኖረኝ እኚህን አባት አንድ ሳምንት ማስቀመጥ ለዘር የሚተርፍ በረከት ያመጣል ። የበቁ እኮ ናቸው” የሚል ደላላ ነበር ። ትምህርቱን ሲጨርሱ መኪናው ቀረብ ብሎላቸው ወደ ቦሌ ይሄዱ ነበር ። ለመስረቅም ይጨነቁ ነበር ። ዛሬ ደግሞ ደረቅ ዘረፋ በዛ። ዛሬም ባለጠጎችን እያሳመኑ በሚያመጡ አገናኞች ብዙ አገልግሎቶች ተለክፈዋል ። በአገልግሎት ስፍራ የጋራ ተጠቃሚነትን ማዳበር ይገባል የሚል ውይይቶች መሰማት ከጀመሩ ቆየት አላሉምን ? ዘማሪ ሲዘምር ሰባኪ ወጥቶ ኳስ የሚያይባቸው ፣ ሰባኪ ሲሰብክ ዘማሪ ካርታ የሚጫወትባቸው አገልግሎቶች ላይ ደርሰን ይሆን ? እንደ ሱቅ በደረቴ ቤተ ክርስቲያን መክፈት ታክስ የማይከፍል ንግድ እንደ ማቋቋም አልተቆጠረምን ? ታይታን መውደድ የሚከተን እዚህ ውስጥ መሆኑን ፣ የተሸጡ ምጽዋቶች ጸሎቶችና ጾሞች ይህንን እንደሚወልዱ ማቴዎስ 6 በቅጡ ሲጠና ይገባናል ።
ጌታችን ፈሪሳውያንን ግብዞች በማለት ብዙ ጊዜ ጠርቷቸዋል ። ግብዝ ማለት ጭምብል ያጠለቀ ማለት ነው ይላሉ በአዲስ ኪዳን መሠረታዊ ቋንቋ በግሪክ የሚተረጉሙ መምህራን ። ጭምብል ያጠለቀ እውነተኛው ማንነቱ ከመድረክ ሲወርድ ይገለጣል ። ፈሪሳውያን የተወቀሱት ባለ መጸለይ ፣ ባለ መጾም አስራት በኩራት ባለ ማውጣት አይደለም ። ለእግዚአብሔር ክብር የሚደረገውን ለራስ ክብር በመዋላቸው ነው ። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በልብሳቸው ላይ ጽፈው ይሄዳሉ ። የእግዚአብሔር ቃል ከልባቸው ሞልቶ በልብሳቸው ላይ ፈስሷል እንዲባል ይህን ያደርጋሉ ። ቀን በሥርዓታቸው የሚማርኩ ምሽት ላይ በውድቀታቸው ያሳዝናሉ ። ዛሬም አይሁዳውያን ሰንበት ከገባ እሳት አይጭሩም ። መንገድ ላይ የገጠማቸውን ሰው ለምነው ሲጋራ አውጥተው ለኩስልኝ ይላሉ ። የሚበልጠው የቱ ነው ? እግዚአብሔርን የሚያከብረው ከእሳት መጫር ይልቅ ጤናችንን መጠበቃችን አይደለምን ? ፈሪሳዊነት ዘር ሳይሆን ባሕርይ ነው ። በየመንገዱ እየጸለዩ የሚሄዱ ፣ ሰው ሲመጣ ድምፃቸውን በማሰማት ጸሎት ላይ ናቸው መባል የሚፈልጉ አያሌ ናቸው ። ለሚቀጥሉት ወራት ስልኬ ላይሠራ ይችላል ጽሞና ላይ እሆናለሁ እያሉ የየዋሃንን ልብ የሚበሉ ፈሪሳውያን ዛሬም አሉ ።
 የሰሎሞን መቅደስ ሲሠራ ከሚያስደንቁ ነገሮች አንዱ እንዲህ ተጠቅሷል ፡-  “ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም” /1ነገሥ. 6፥7/ ። ሰሎሞን ምን ያህል ጠራቢዎች ነበሩት ? ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው ። “ሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት ። ይኸውም በሠራተኛው ሕዝብ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ሌላ ነው” ይላል /1 ነገሥ. 5፥15-16/ ። የእግዚአብሔር ቤት ሲሠራ ግን መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም ።
 እንኳን የእግዚአብሔር አገልግሎት ባለሙያ ሴት ስትደግስ ድግሷ የተሰጣ እህል ፣ የሚለቀም ምስር ፣ የሚሸት ወጥ የለውም ። የድግሱ ቀን ስትገልጠው ፣ ገበታ ሙሉ አድርጋ ስታቀርበው የሚያዩ ሁሉ “ምንም ሳይሰማ እንዴት ብቻሽን ደገስሽው ?” በማለት ያደንቋታል ። የሰነፍ ድግስ ግን ማኅበር አለብኝ ፣ ሠርግ አለብኝ እያለች ታውጃለች እንጂ የሚሠራ ምንም ነገር የለም ። አገልግሎት እንዲህ ሊከወን ይገባዋል እንጂ ታይታ የሚያስፈልገው አይደለም ። አዎ እግዚአብሔር በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል ። በእውነት ስንልም በፍቅር ፣ ከልብ ፣ ታይታን በመናቅ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻል /ዮሐ. 4፥23/
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ