የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሥርዓት ብቻ የሆነ አምልኮ

ሥርዓት ብቻም መሆንም ያለ ሥርዓት መሆንም ሁለቱም ተገቢ አይደሉም ። ሥርዓት ብቻ የሆነ አምልኮ ሕይወት የለውም ። ሥርዓት የለሽ አምልኮም ሰላም የለውም ። አምልኮ ሕይወትንና ሰላምን ማስቀጠል ዋነኛው ዓላማው ነው ። አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ሲቀጥል እርሱ ሕይወት ነው ፣ እርሱ ሰላም ነው ። ይህንን ሕይወትና ሰላም የምናገኘው በአምልኮተ እግዚአብሔር ነው ። በቤታችን ያለው አምፑል የሚያበራው በውበቱ አይደለም ። ከኃይል ምንጭ ጋር በመገናኘቱ ነው ። ክርስትናችንም የሚያበራው ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ሲኖረን ብቻ ነው ። ቃሉ ፣ ጸሎት፣ መንፈሳዊ ኅብረት ዕለታዊ ፍላጎት ናቸው ። እነዚህ ሦስት ነገሮች ከሌሉ ክርስቲያን ወደ ኋላ ለማለት ብሎም ለመካድ ይደርሳል ። ስለዚህ አምልኮ እውነተኛ እንዲሆን ሥርዓትም ሕይወትም ያስፈልገዋል ። ሐዋርያው በምክሩ እነዚህ ነገሮች የማይጓደሉ እስትንፋስ መሆናቸውን ይገልጣል ። ገለጣውንም ቀጥሎ ልብ በሉ ። “ሁልጊዜ” ፣ “ሳታቋርጡ” “አንተው” በሚሉት ነዋሪ አንቀጾች ያጸናዋል ።
“ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ”
                /ፊልጵ. 4፥4/ ።
“ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና”
               /1ተሰ. 5፥17-18/ ።
“በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ”
              /ዕብ. 10፥25/።
ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ትልልቅ የሃይማኖት ተቋማት ነበሩ ። ፈሪሳዊ ማለት ትርጉሙ የተለየ ማለት ነው ።  ራሳቸውን እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ያያሉ ። ሌላውን ደግሞ እንደ ርኩስ ይመለከታሉ ። አገር ወዳድነታቸው ፣ ለሃይማኖት ያላቸው ቀናዒነት ፣ ሕጉንም መድገማቸው ፣ ያለ ይሉኝታ በአደባባይ መንፈሳዊ ተግባራቸውን መፈጸማቸው ፣ ልጆቻቸውን ተተኪ አማኝ እንዲሆኑ ከኋላቸው ማስከተታቸው አስገራሚ ነው ። ይህንን ያህል ዋጋ የሚከፍሉት እነዚህ ፈሪሳውያን ጠብ የምትል ፍቅር ግን አልነበራቸውም ። ስለ ተራቡ ሰዎች ከማዘን በሰንበት እሸት ስለ ተቆረጠ ያዝናሉ ። ስለ ልብ ንጽሕና ከማሰብ ሳይታጠቡ መብላት ያረክሳል ይላሉ ። ልብን የሚሻውን አምልኮት በውጫዊ ሥርዓት ብቻ ተክተውት ነበር ። ይጾማሉ ነገር ግን የሌላውን አለመጾም ያያሉ ። ራሳቸውንም እንደ ጾም ፖሊስ ይቆጥራሉ ። ሰላም ሰንብተው ጾም ሲመጣ ለእነርሱ የሙግትና የመካሰሻ ሰሞን ነው ። ሕጉን ያነቡታል እንጂ አይፈጽሙትም ። የተሸከሙት ውጫዊ ምልክት ውስጣዊ እምነታቸውን ማብራራት ሲገባው ውስጣዊ ሽፍትነታቸውን ይደብቅ ነበር ። ተገርዘዋል ልባቸው ግን አልተገረዘም ። ቃሉን በጨርቃቸው ላይ ጽፈው አንጠልጥለዋል ። ልባቸውን እንዲያሸንፍ ግን አይፈቅዱለትም ።
በእነርሱ ጽንፍ የቆሙት ሰዱቃውያን ደግሞ ሁሉም ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሔርን ያገኛል ፣ የተደመደመ እውነት የለም ። ሁሉም ነገር ገና በመገለጥ ላይ ነው ። የምድሩን ሀብትና እውቀት መያዝ አለብን ። ከሁሉም ጋር በሰላም መኖር ያስፈልገናል ። ከዘመን ጋር ከመጋጨት ተመሳስለን መኖር ያስፈልገናል ። አማኝ ሊቸገር ሊታመም አይገባውም ። አገርና ድንበር ሰዎች ያሰመሩት ነው ። ድንበር የሌለው ግንኙነት መፍጠር አለብን። አገር እያሉ መቀመጥ ጠባብነት ነው ። ዘመኑን መዋጀት ያለብን ዘመኑ ያለበት ድረስ በመሄድ ነው የሚል የቅምጥልነት አስተሳሰብ ነበራቸው። ከቅዱሳት መጻሕፍትም ቆንጽለው አምስቱን ብሔረ ኦሪት ብቻ ይቀበላሉ ።እነዚህ ሁለት የሃይማኖት ጎራዎች ዛሬም አሉ ። ፍቅርን የጣለ እውነት የያዙና እውነትን የጣለ ፍቅር የያዙ ቡድኖች ዛሬም እየጎመሩ ነው ። ሐዋርያው ፡- እውነትን በፍቅር እንያዝ ማለቱ ከፍ ብሎ ሊሰቀል የሚገባው መመሪያ ነው /ኤፌ. 4፥15/ ።
ሥርዓት ብቻ የያዙት ፈሪሳውያን የሚደነቅላቸው ጠባይ ምንድነው ? ከእነርሱስ መማር ያለብን ምንድነው ? ካልን፡-
1-  እግዚአብሔር ከእኛና ከልጆቻችን ጋር ጉዳይ አለው ስለሚሉ ልጆቻቸውን መቅረጽ ይችላሉ ።
2-  አገርም የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ስለሚያምኑ በአገራቸው የሚኮሩና አገራቸውን የሚጠብቁ ናቸው ።
3-  ሃይማኖታቸውን በጋለ መንፈስ በመያዝ ቀዝቃዛነትን ይጸየፉ ነበር ።
4-  በቂ የሆነ የመጻሕፍት እውቀት ነበራቸው ።
5-  መጻሕፍትን ሳይቀናንሱ በሙሉነት ይቀበላሉ ።
6-  ለሃይማኖት መሥዋዕት ለመሆንም ዝግጁ ናቸው ።
7-  የእግዚአብሔር ሀልዎት ይሰማቸዋል ። በአደባባይም በመብት ሃይማኖታቸውን ይይዛሉ እንጂ አያፍሩበትም እንደ ተረትም አያዩትም ።
ችግራቸው ምን ነበር ?
1.  ሥርዓትን ሲያከብሩ ልባዊ ቅንነትን ጥለዋል ።
2.  እግዚአብሔርን በመንደራቸው ልክ አጥብበውት ለሌሎች ያለውን ዓላማ ዘንግተዋል ።
3.  ቀናዒነታቸውን ለማስተማር ሳይሆን ለመሳደብና ለመካሰስ አውለውታል ።
4.  የብርሃን ጻድቃን ፣ የጨለማ ኃጢአተኞች ናቸው ።
5.  የሰውን ሙገሳ ይፈልጋሉ ። የመበለቶችን ቦርሳ ያመናምናሉ ።
ጅረቱ ከወንዙ ፣ ቅርንጫፉ ከግንዱ መያያዝ እንዳለበት ሥርዓትም ከልብ ጋር ሊያያዝ ይገባዋል ። ሥርዓት መልካም የሚሆነው በልባችን ውስጥ ላለው እምነት መግለጫ ሲሆን ነው ። ሥርዓት ክፉ የሚሆነው በልባችን ውስጥ ላለው ክህደት መሸፈኛ ሲሆን ነው ። የተሳሳተ ምልክት ከዋናው ተቋም አያደርስም ። አንዳንድ ያልተነሡ መፈክሮች የሞት ያህል ይነበባሉ ። በአንዳንድ ከተሞች መግቢያ ላይ “ከጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አመራርረ ጋር ወደፊት” የሚል መፈክር እናነባለን ። ገለጻው ግን እውነትነት ስለሌለው የሞቱ ፊደሎች ይታያሉ ። ምክንያቱም መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሉም ። በየሆቴሉ ግድግዳ ላይ የተሳሉ የአንበሳ ሥዕሎች አሉ ። ግን ምንም ማድረግ አይችሉም ። መሥሪያ ቤቱ አድራሻ ቀይሮ አሁንም ግን ያልተነሡ የመሥሪያ ቤቱ የአድራሻ ምልክቶች አሉ ። አድራሻውን አይቶ የመጣውን ጊዜውን ፣ ምኞቱን ፣ ጉልበቱን ያደክማሉ ። ሕይወት የሌለው ሥርዓት ስንይዝ ላያችንን አይተው ሰዎች ይቀርቡንና እውነትነት ሲያጡብን የበለጠ ራሳቸውን እየጠሉ ይመጣሉ ። ዝናብ የሌለው ደመና ቀስ ብሎ የሚሄደውን ሰው ያሯሩጣል ። ገበያውን ያለ ሰዓቱ እንዲታጠፍ ያደርጋል ። አስገምግሞና ጠቊሮ ሲመለስ ግን ከንቱ ልፋት ያለፋል ። ዓለምን ስለ መናቅ አስተምረው ዓለም ላይ ሲራኮቱ ፣ የፈረንጅ አገርን ረግመው አስተምረው ሀገሬ አሜሪካ ነው ሲሉ ልብን ሊያዝሉ ይችላሉ ። እንዲህ ያለው ግብዝነት የሞላበት ፉከራ እንጂ ልባዊ ቅንዓት የሌለው አምልኮ አያርግም ።
ዜማው ሲሰበር ማዘናችን ትክክል ነው ። በሕይወታችን ግን ቃሉን ከሰበርነው ተገቢ አይደለም ። ቤታችን መኪናችን በጥቅስ አሸብርቆ ቃሉ ሲፈልገን መታጣት ግን ሐሰተኛነት ነው ። አዎ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነቡና መጽሐፍ ቅዱስ ያነበባቸው ሁለት ዓይነት ሰዎችን መለየት አለብን ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ፀሐፍት ፈሪሳውያን በማቴዎስ ወንጌል ምዕርፍ 23 ላይ በብርቱ ወቅሷቸዋል ። ወቀሳውን ሰብሰብ አድርገን ብንገልጠው ሥርዓት ብቻ መሆን ማለት ምን ማለት መሆኑ ይገባናል ።
1.  ለሌላው ኩንታል እያሸከሙ ለራሳቸው ግን በጣት አለመንካት
2.  ሃይማኖታዊ አልባሳትን ለብሶ በአደባባይ መታየት የዓለም የወሬ ማድመቂያ መሆን
3.  የአክብሮት ስምን ሲፈበርኩ መዋል
4.  ማስተማርን ጠልቶ አባት መባልን ፣ መማርን ጠልቶ ሊቅ መሰኘትን መፈለግ
5.  ስለ ሌሎች ማረፍና መዳን ግዴለሽ ሁኖ የእውነትን በር መዝጋት
6.  በኀዘን የተጎዱ ሴቶችን በጉድለታቸው በኩል ገብቶ የአጽናኝ አቊሳይ መሆን እጸልያለሁ እፈውሳለሁ እያሉ መዝረፍ
7.  አንድን ሰው ለማግኘት ብዙ መድከም የማግኘቱ ዓላማ ግን የሚመስላቸውን አድመኛ ማብዛት
8.  ከቤተ መቅደሱ ይልቅ ወርቁን ፣ ከመሠዊያው መሥዋዕቱን ማክበር ማለት ወርቁና መሥዋዕቱ የተረፈው ለእኛ ነው ብለው ማስላት
9.  ትንሽን እያጠሩ ግመልን መዋጥ
10.    ውጫዊ አደረጃጀትን ማሳመር የውስጡን ቅንነት ግን መጣል
11.    የሞቱትን ደጋግ እያዘከሩ ያሉትን ደጎች መግደል ይህ ፈሪሳውያውን የተወቀሱት ማንነት ነው ። እግዚአብሔር የሚሰግዱለት በእውነት እንዲሰግዱለት ይፈልጋል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ሥርዓት ብቻ የሆኑትን ወገኖች ሲወቅስ እንዲህ ይላል ፡- “አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን?” /ሮሜ.2፥22/ ። ዳግመኛም ፡- “ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል ። እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? … በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም” ይላል /ሮሜ. 2፥25-29/ ። ሥርዓት የእምነት መግለጫ ሲሆን የመገዛትም ምልክት ሲሆን እውነተኛ አምልኮ ነው ።
እግዚአብሔር በውስጣችንን ማንነት ይመዝነናል ። ዓለም ደግሞ ሥርዓታችንን በማየት ይማረካል ። እውነተኛ ሥርዓት ውበት ፣ ጸጥታና ተመስጦ ያመጣል ። ሥርዓት ዓለም እስከ ዛሬ የቆየችበት ምሥጢር ነው ። ተፈጥሮ በሥርዓት ውስጥ ነው ። ሌሊትና ቀን ፣ ክረምትና በጋ መፈራረቁ ሥርዓት ነው ። ሁሉም ቦታውን መያዙ ይህ ውበት ነው ። ሁሉም በሚያስፈልግበት ሰዓት መገኘቱ ይህ ጸጥታ ነው ። ፀሐይ ብርሃን ስታመነጭ የሚረብሽ ድምፅ የለም ። ነፋስም በዝግታ ይነፍሳል ። ዓለሙን ሁሉ ሙቀት ፣ ብርሃንና ነፋስ ሞልተውታል ። እነዚህ በአንድ ዓለም ላይ በምልአት ሲኖሩ መገፋፋት ግን የለባቸውም ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ