የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሥርዓት የለሽ አምልኮ

ጥቁር አሜሪካውያን ከለምለም አህጉራቸው ተግዘው ፣ የቅኝ ገዢዎችን መንገዶችና ከተሞች በላብም በደምም ገንብተዋል ። ጉልበታቸው ድንጋይ ሲጠርብ ወርቃቸው ደግሞ የነጮችን ምድር አበልጽጓል ። ሳምንቱን በሙሉ በአስገባሪዎቻቸው እየተገረፉ ይሠሩ የነበሩ እነዚህ መከረኞች የነጻነት ቀናቸው ሰንበት ፣ የነጻነት ቦታቸው ቤተ ክርስቲያን ነበረች ። ያን ሁሉ መከራ የሚያደርሱባቸው ነጮች በሰንበት ቀን ጥቁር ዝር ከማይልበት ቤተ ክርስቲያናቸው ያመልካሉ ። ጥቁሮችም አንድና ብቸኛ በሆነችው የነጻነት ስፍራቸው በቤተ ክርስቲያን ፈጣሪያቸውን ያመልካሉ ። ታዲያ እነዚህ ጥቁሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ነጻነታቸውን እንዴት እንደሚገልጡት ይጨነቃሉ ። ግማሹ እየዘለለ ፣ ግማሹ መሬት ላይ እየተንፈራፈረ ፣ ግማሹ ወንበር ላይ እየቆመ ለመጮህ ይሞክራል ። ስሜት የተቀላቀለውና መጨቆን የወለደው ይህ የአምልኮ አካሄድ ነጻነት መከበር ከጀመረ በኋላም ባህል እየሆነ መጣ ። እንደገና ከነጮቹ ጋር የሥርዓት ጠብ ጀመሩ ። ይህ መጨቆን የወለደው ፍንጠዛና ጩኸት ዛሬ በአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት እየተስፋፋ የእኛንም አገር እየወረሰ ይገኛል ። ሰላማዊ ስብከት ፣ ሰላማዊ ጸሎት እየጠፋ መዝሙሩ ከመልእክቱ ማጀቢያው እየደመቀ መጣ ። በአገሪቱ ያለው ሁሉም የዳንስ ዓይነት በመዝሙር ስም ይደነሳል ። ለእግዚአብሔር የተመረጠ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚቆጣ እንኳ ያለ አይመስልም ። እርስ በርሱ የሆነበት የወጣቶች አምልኮ ከእውነት ለስሜት ፣ ከፍቅር ለግዴለሽነት ፣ ከሥርዓት ለሁከት ያደላ ሁኗል ። ዕድሜአቸው ለዲቁና የሚበቃ የጳጳስን ቦታ ስለያዙ ወጣትነታቸው ያስገደዳቸውን በግድ ያደርጉታል ።
የብሉይ ኪዳን ክህነት አገልግሎት በ25 ዓመት ጀምሮ እስከ ሃምሳ ዓመት የሚቆይ ነው ። ዛሬ ያለውን ዘመናዊ የሥራ ሕግ በ25 ጀምሮ በ55 ዓመት የሚያበቃ ነው ። 25 ዓመት አንድ ወጣት የኮሌጅ ትምህርቱን ጨርሶ ለሥራ ብቁ የሚሆንበት ዕድሜ ነው ። በአይሁድ ልማድም እስከ 12 ዓመት ዕድሜ መደበኛ የንባብ ትምህርት ይሰጣል ። ከ12 ዓመት በኋላ የአንድ ልጅ የአካለ መጠን ዘመን ነውና ወደ ተግባረ ሥጋ ወይም ወደ ተግባረ ነፍስ ይሰማራል ። ወደ ተግባረ ነፍስ ከተሰማራ ብሉይ ኪዳንን እስከ 20 ዓመቱ ድረስ ያጠናል ። 5 ዓመት ከተራዳ በኋላ በ25 ዓመቱ ወደ ዘርዐ ክህነት ይመጣል ። ወጣቶች አባቶችን እየተራዱ ከቆዩ በኋላ ወደ ኃላፊነት ካልመጡ ዕድሜአቸው እንዳዘዛቸው መሆናቸው ግድ ነው ።
አንድ የፕሮቴስታንት መሪ በአደባባይ ቆሞ መዝሙር ሲዘመር እያየ ልቡ አዝኗል ። መዝሙሩ ላይ ግን እስክስታ መቅለጥ ጀመረ ። ወጣቶቹ ምንጃርኛውን መሬት ላይ እስከመውረድ አደረሱት ። ወንድና ሴት ሁነው አንገታቸውን አንዘረዘሩት ። መዝሙሩ እንዳበቃ መሪው በታላቅ ኀዘን ፡- “የእግዚአብሔር ፍቅር ነክቷችሁ ከሆነ ያደረጋችሁት የምለው የለኝም ። በዓለም ያልጨረሳችሁትን ጭፈራ በቤተ ክርስቲያን ለመጨረስ ከሆነ ግን ወዮላችሁ ። እግዚአብሔር አይዘበትበትም” ብሏል ። ይህንን ታሪክ ያጫወተችኝ ከእኛው ቤተ ክርስቲያን ወጥታ እዚያም ያልጣማት አንዲት እህት ናት ። አንድ የዚሁ የፕሮቴስታንት እምነት አስተዳዳሪም የጉባዔው አባላት ሲዘምሩና ሲጸልዩ ሁልጊዜ ወንበር ይሰብራሉ ። ይህ ሁኔታ አቅምን እየጎዳ ስለመጣ አንድ ቀን መሪው፡- “እነዚህ ወንበሮች የአንዱ ዋጋ 400 ብር ነው ። በየሳምንቱ ወንበር መቀየርና ማሠራት ሥራችን ሁኗል ። ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ወንበር የሰበረ 400 ብር ይከፍላል” አለ ። ከዚያ ቀን ጀምሮ ወንበር መስበር ቆመ ። ይህንንም በጆሮ የሰማች እህት ለወዳጆቿ ስትናገር የሰማሁት ነው ። በእግዚአብሔር ስም ወንበር መስበር ተገቢ አይደለም ። ይህ ስሜት እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ። 400 ብር ግን ጸጥታ አመጣች።
እነዚህ ሥርዓት ማጣቶች እየተስፋፉ በሥርዓቷ የተደነቀችውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አይነካም ብለን ልንተማመን አንችልም ። ጥንቃቄ ይጋርዳልና መጠንቀቅ በጣም ያስፈልጋል ። በየጓዳው ያሉ ልምምዶች አንድ ቀን አደባባይ ሲወጡ በሌላው ዓለም ያየነው እኛኑ ሊያስጨንቀን ይጀምራል ። አሁንም እየታዩ ያሉ ፈር የለቀቁ ነገሮች ቶሎ መታረም አለባቸው ። ችግኝ በጣት ይነቀላል ። ካደገ ግን በመጥረቢያም ያስቸግራል ። በጉባዔ ትምህርቶች ትምህርቱን ሳይሰሙ አሜን ማለት ፣ በጸሎቶች ሁሉም ሰው መንጫጫት ፣ በዝማሬዎች ሥጋዊነትን ማጉላት ፣ በስብከቶች መጮህና መፎከር እንዳይዙን ማሰብ ያስፈልጋል ። መንፈሳዊነት ጽሞና ከሌለው ተመስጦ ሊኖረው አይችልም ። ተመስጦ በሌለበትም አምልኮ ሊኖር አይችልም ። ለእግዚአብሔር ሆታና እልልታ ይገባዋል ። እርሱም ግን ሥርዓት ያለው ነው ።
1ኛ ቆሮንቶስ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ የቆሮንቶስ አማንያንን ለመገሰጽ ፣ ከጥፋት ለመመለስ የተጻፈ መልእክት ነው ። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የጸጋ ድህነት አልነበረም ። ጸጋውን ያድፋፉ ሦስት ችግሮች ግን በዋናነት ይጠቀሳሉ ፡-
1-  በኅብረት አንድነት ማጣት
2-  በግል ቅድስና ማጣት
3-  በአምልኮ ሥርዓት ማጣት
ሐዋርያው በእያንዳንዱ ምዕራፍ እየነቀሰ እንደ አባት ይመክር ፣ እንደ መምህር መንገድ ያሳይ ፣ እንደ መንፈሳዊ ሰው ይጸልይላቸው ፣ እንደ ባለሥልጣን ይቀጣቸው ነበር ። እነርሱም ምክሩን ፣ ትምህርቱን ፣ ተግሣጹንና ቅጣቱን ተቀበሉ ። ስለዚህ ሁለተኛ ቆሮንቶስን ለማጽናናት ጻፈላቸው ። አባት ልጁን ከቀጣ በኋላ መልሶ ያባብለዋልና ።
በአምልኮ ሥርዓት ስላጡበት ነገር ከምዕራፍ 10-14 ይመክራቸዋል ።
v ምዕራፍ 10 የአንድነትን ማዕድ ያለ አንድነት ስለ መውሰዳቸው
v ምዕራፍ 11 ወንዶችና ሴቶች በፀጉርና በአለባበስ የአምልኮን ሥርዓት ስለማፍረሳቸው እንዲሁም ሰንበቴና ቅዱስ ቊርባንን ስለማቃለላቸው
v ምዕራፍ 12 የጸጋ መቀባበል ስለማጣታቸው
v ምዕራፍ 13 በፍቅር አምልኮተ እግዚአብሔርን መፈጸም ስለሚገባቸው
v ምዕራፍ 14 የጸጋ ሥጦታዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው ይናገራል ።
ለአምልኮተ እግዚአብሔር ከሚያስፈልጉ ጉልህ ሥርዓቶች ውስጥ ውስኑን በቆሮንቶስ መልእክት ተመሥርተን እንመልከት ፡-
     አለባበስ ፡- የልብስ ዓላማው ሰውነትን ከራቁትነት ለመሰወር ፣ የሰውነት ቅርጽ እንዳይታይ ለማድረግ ነው ። ሰውነትን ከራቁትነት ሸፍኖ ቅርጽ ማሳየት እርሱም መራቆት ነው ። አለባበስ አንዱ የቅድስና ሕግ ነው ። ቅድስና ማለት ለእግዚአብሔር መኖርና እግዚአብሔርን በኑሮ ማሳየት ነው ። አለባበሳችን ግን ራሳችንን የምናጎላበት ከሆነ ቅድስናና አምልኮትን ሰርቀናል ማለት ነው ። አለባበስ ተፈጥሮንም ያመለክታል። ወንዶችና ሴቶች በአለባበስ ይለያሉ ። በአምልኮት ሰዓት አለባበስን ማስተካከል ይገባል ። ወደ ቤተ መንግሥት ተጠርታችሁ ታውቁ ከሆነ ከጥሪው መጨረሻ ላይ ሁለት ማስጠንቀቂያ ይሰፍራል ።
–    ወንዶች ሙሉ ልብስ ፣ ሴቶች ቀሚስና የአገር ልብስ መልበስ ግዴታ ነው ።
–    የማይገኙ ከሆነ አስቀድሞ ማሳወቅ ግዴታ ነው ።
አምልኮተ እግዚአብሔር የንጉሥ ግብዣ በመሆኑ የአለባበስ ክብርን መጠበቅ ይገባዋል ። አለመገኘትም ያስቀጣል ። ለመንግሥቱ ግብር ያልከፈለ እንዲቀጣ አምልኮም ግብር ነውና አለመክፈል ያስቀጣል ። ሳጥናኤልን ሰይጣን ያሰኘው ከልዕልና ወደ እንጦሮጦስ ያወረደው ፣ አዳምን ገነት ያሳጣው የአምልኮ በደል ነው ። ሌላው በደል ሁሉ የባሕርይ ድካም ሊሆን ይችላል ፣ አምልኮትን መስረቅ ግን ዓመጽ ነው ። አለባበስ የቅድስናና የአምልኮ ድንጋጌ ከሆነ አምልኮ የማያቋርጥ አገልግሎት ነውና በጸሎት ሰዓት ብቻ ሳይሆን በሥራችንም በኑሮአችንም አለባበሳችን ክርስቲያናዊ መሆን ይገባዋል ።
ይልቁንም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ስንገናኝ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ልብስ ዋጋው ቀለል ያለ ነጠላ ይለብሳል ። በቤተ ክርስቲያንም ማንም ድሃና ባለጠጋ መሆኑ አይታወቅም ። በትምህርት ቤቶች ዩኒፎርም በመጀመሩ የተማሪዎች ሥነ ልቡና እንደ ተጠበቀ እናውቃለን ። በአንድ ልብ ሁነውም ትምህርታቸውን ለመማር እንደሚያስችላቸው ይነገራል ። አእምሮን ባካና ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የሰዎችን ልብስ ሲያዩና ሲተቹ መዋል ነው ። በቤተ ክርስቲያን ግን ይህ ዕድል እንዳይኖር ተደርጎ ተዘግቷል ። ይህ ብቻ አይደለም ወንዶችና ሴቶች በየአቅጣጫቸው መቀመጣቸው አርቆ ማጠርና ለቅድስና ትልቅ ዋጋ መስጠት ነው ። ዛሬ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ወደዚህ ኦርቶዶክሳዊ ባህል ለመመለስ በብርቱ ይናፍቃሉ ። ተቀምጦ የሰቀሉትን ቁሞ ማውረድ እንደማይቻል እያዩት ነው ።
የአለባበስን ሁኔታ በሚመለከት የሠራን እግዚአብሔር ቢመርጥልን የተሻለ ነው ። እርሱ ሲሠራን ወንድ ልጅ በመሸፈን ሳይሆን በመገለጥ ሴት ልጅ በመሸፋፈን እንዲያምሩና እንዲከብሩ አድርጎ ነው ። ስለምንጠቀምበት አንድ ዕቃ የሠራው ድርጅት አጠቃቀሙን ቢነግረን ከራሳችንም ከሌሎችም በላይ የድርጅቱን መመሪያ እናከብራለን ። የሠራን እግዚአብሔር ስለ እኛ የሚናገረውን ማክበር እንጂ ዘመንና ሥልጣኔ የሚያወራውን መከተል ተገቢ አይደለም ።
አለባበስን በሚመለከት ከወንዶች ይልቅ ለሴቶች ብዙ ትምህርት ተሰጥቷል። በልብስ ያውም በተሻለው ውበት መታዘዝ ካልቻልን በሌላ መታዘዝ እንዴት ይቀለናል ? ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ፡- “እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው ። ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ ። እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና” ብሏል /1ጴጥ. 3፥1-3/ ። በተለይ 1ቆሮ. ምዕራፍ 11፥1-16 አለባበስ ለኅብረት አምልኮ ለቅዳሴና ለጉባዔ አስፈላጊ መሆኑን ይነግረናል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንዶች ፀጉራቸውን እንዲያሳጥሩ ሴቶችም እንዲያስረዝሙ ይናገራል ። ወንዶች ማሳጠራቸው መሸፋፈን እንደማይገባቸው ገና በተፈጥሮ የታቀደ መሆኑን ያሳያል ። ሴቶች ፀጉራቸው መርዘሙ ገና በተፈጥሮ መሸፋፈን እንደሚገባቸው ያሳያል ። እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው ። ሴቶች ይላጫሉ ። ወንዶች ሹሩባ ይሠራሉ ። አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በአለባበስ አንድ ዓይነት መልክ እንደ ነበራቸው ሐዋርያው ይናገራል /1ቆሮ. 11፥16/ ።
 የአምልኮተ እግዚአብሔር መሪዎች ፡- የኅብረት አምልኮ መሪ ያስፈልገዋል ። ሊመሩ የሚገባቸውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው ። “የወፍ ዘፈን አውራጁ አይታወቅም” እንዲሉ መንጫጫት ተገቢ አይደለም ። የአደባባይን ጸሎት እንዲመሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንዶችም ሴቶችም ሳይሆኑ ቀሳውስትና ዲያቆናት ናቸው ። ስብከትን በሚመለከት ግን ሴቶች አልተፈቀደላቸውም ። “ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና” /1ቆሮ. 14፥34/ ። ይህ ሴቶችን የሚያቃልል ሳይሆን ድርሻን የሚያመለክት ነው ። ይህ ቃል የተነገረው ለዚያ ዘመን ነው በማለት ሴቶች ሊቃነ ጳጳሳትን የሾሙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ ። አሁን ሽረዋል ። ማስታወስ ያለብን የእግዚአብሔር ቃል ቋሚ መሆኑን ነው ። ሁለተኛ ሁሉም ወንዶች ጳጳሳት ይሆናሉ ወይ ? የተሰጣቸው ጥቂቶች ናቸው ። ሐዋርያው ለዚያ ዘመን ነው የተናገረው የሚለው ስህተት ነው ። ምክንያቱም ሐዋርያው አሁንም የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ለነበረው ለልጁ ለጢሞቴዎስ የቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደር መመሪያ ሲሰጠው ፡- “ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር ፤ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም ። አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፥ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች ። የተታለለም አዳም አይደለም፥ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች” ብሏል /1ጢሞ. 2፥11-14/ ። ሐዋርያው ማጣቀሻ ያደረገው ጥንተ ተፈጥሮንና ጥንተ አብሶን /የመጀመሪያውን ውድቀት/ ነው ።
 ሰላማዊ መሆን አለበት ፡- ከአምልኮ ሥርዓቶች አንዱ ፀጥታና መደማመጥ ነው ። ይልቁንም የቆሮንቶስ ምእመናን በልሳን ጸጋቸው ጉባዔውን በመንጫጫት ያውኩ ነበር ። የእነርሱ ልሳን የተረጋገጠ ነበር ። አጠቃቀሙ ግን ትክክለኛ አልነበረም ። ትክክለኛውን ልሳን እንኳ በሥርዓት ለዓላማውና ለግቡ መጠቀም ይገባል እንጂ ከማን አንሼ እንደ ሽጉጥ የሚመዘዝ አይደለም ። በጉባዔ ሊነገር የሚገባው ግልጽ ቋንቋ ነው ። ሌላ ቋንቋ ከተጠቀሰ በግድ መተርጎም አለበት ። ከሁሉ በላይ ሰላማዊ ሊሆን ይገባዋል ። ዛሬ በመዝሙርና በስብከት ሰዓት ፉጨት  እንዳለ ፣ ጩኸት የሌለበት ጉባዔ የፈዘዘ እንደሚባል እየሰማን ነው ። በመግቢያችን ላይ ይዘሉ ይጮኹ የነበሩት ጥቁር አሜሪካውያን ከደረሰባቸው ተጽእኖ በመነሣት ነው ። እኛ ያልተገዛን ሕዝቦች ግን ይህን መቀላወጥ አይገባንም ። ሕጻናት የሚጠናገር ሰው ካዩ እንደ እርሱ ለመሆን ይኮርጃሉ ። ሕጻን ናቸውና የቱ እንደሚኮረጅ አያውቁም ። ታዲያ ወላጆች በመግረፍ ያስጥሏቸዋል ።  እንኳን ክፉው ደጉንም መኮረጅ ተገቢ አይደለም ። የራሳችን ባህልና ማንነት አለን ። በራሳችን ባህልና ማንነት እግዚአብሔርን ማምለክ አለብን ። የሚታየው ግን የባህል ወረራ ከመሆን የሚያልፍ አይመስልም ።
የአማርኛ መዝሙሮች በእንግሊዝኛ ዜማ ሲዘመር ለዓመታት ተሰምቷል። ይህ የራሷ ዜማ ባላት አገር ላይ ወረራ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል ? አብዛኛዎቹ አብያተ ክርስቲያናት በቴሌቪዥን መስኮት ስናያቸው ኢትዮጵያዊነትን ከስረዋል ። ከባህል እስራት መፈታት አለብን የሚል ግሳጼም ሲሰጡ ይሰማል ። ባህል ሁሉ ክፉ ነው ወይ ? አንድ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሰባኪ ፡- “ይህን አማርኛ ጌታ ይገስጸው አልገልጥልኝ አለ” ብሎ እንግሊዝኛ እንደሚገልጥለት በአደባባይ ሲናገር ተሰምቷል ። በአገራችን ባሉ ትምህርት ቤቶችም ፡- “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው” የሚል ጽሑፍ የተለጠፈባቸውም ነበሩ ። የአካልን ቅን ግዛት ስናመልጥ የባሰው የኅሊና ቅን ግዛት በሃይማኖትና በትምህርት ታክኮ እንዳይገባብን መጠንቀቅ ያስፈልገናል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው። …ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን” /1ቆሮ. 14፥33 እና 40/። አዎ አምልኮን እውነተኛ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ መንፈሳዊ ሥርዓታችን ነው ። የራሳችንን ቤት ሥርዓት እየጠበቅን የእግዚአብሔርን ቤት ሥርዓት ማፍረስ ተገቢ አይደለም ። በቤታችን የድምፅ ብከላ ሕግን ሳይቀር እናከብራለን ። የምንጣፍ አረጋገጥ ሕግ አለን ። ምግብ የሚቀርብበት የተወሰነ ሰዓት አለን ። አባት የሚሠራው እናት የምታከናውነው ድርሻ አለ ። በቤታችን የምናደርገውን በእግዚአብሔር ቤት ለምን እንቀይረዋለን ? የእግዚአብሔር ቤት ከእኛ ቤት ምንኛ ይልቅ ይሆን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ