የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድሆችን የረሳ አምልኮ

እግዚአብሔር የት ይገኛል ? እግዚአብሔር በእርግጠኝነት የሚገኝበት ቦታ የት ነው ? በቤተ መንግሥት ነው ? በቤተ መቅደስ ነው ? በሊቃውንት መካከል ነው ? እግዚአብሔር በእርግጠኝነት የሚገኘው በድሆች መካከል ነው። እርሱ ለልዑሉ ሳይሆን ለእረኛው ሙሴ ተገለጠ ። ልዑሉ ሙሴ ገደለ። እረኛው ሙሴ ግን ሕዝቤን ልቀቅ ይልሃል ብሎ በፈርዖን ፊት ቆመ ። ጌታችን በቤተ መቅደስ ሳይሆን በበረት  ተወለደ ። ለሊቃነ ካህናት ሳይሆን ለእረኞች ልደቱን አበሰረ ። ጌታችን ከድሆች ጋር ነው ። ባለጠጎች ታዲያ እግዚአብሔር የላቸውም ማለት ነው ? እነርሱም እርሱን ለማግኘት በመንፈስ ድሆች መሆን አለባቸው /ማቴ. 5፥3/ ። ማን ማለት ነው ? ያላቸውን ነገር እንደሌላቸው መቊጠር አለባቸው ። ታናናሾች ታላቅ አምላክ እንዳላቸው ጌታችን ተናገረ /ማቴ. 18፥10/ ። ከጠቢባን የተሰወረው በእውቀት ድሆች ለሆኑት ሕጻናት በመገለጡ ጌታችን ሐሴት አደረገ /ሉቃ. 10፥21/ ። ፍጹም ለመሆን የሚወድም ያለውን ሀብት ሽጦ ለድሆች ይመጽውት አለ /ማቴ. 19፥21/ ። የመጨረሻው ቀን ጥያቄም ድሆች ናቸው /ማቴ. 25፥35/ ። እግዚአብሔር መንፈሳዊነታችንን የሚመዝነው ለድሆች ባለን አመለካከት ነው። ራሱ ማጥገብ ሲችል እኛን ያዘዘን ድሆች የእኛ መለኪያ ሚዛን ፣ መታወቂያ ቱንቢ ስለሆኑ ነው ።
ሚዛን ቅለታችንን ወይም ክብደታችንን ይለካል ። ራሳችን ሚዛን የሚደፋልን ለራሳችን ባደረግነው ደግነት ሳይሆን ብድር መመለስ ለማይችሉ በተዘረጋው እጃችን ነው ። የእኩያ ጽዋ ያደከማችሁ “ሰው ማለት…” እያላችሁ የምትመረሩ ልብ በሉ ። “ሰው ማለት…” የሚል ትንታኔ ውስጥ ያስገቧችሁ በርግጠኝነት ድሆች አይደሉም ። እኩያዎቻችሁ ናቸው ። እኩያዎቻችሁ የሰፈራችሁላቸውን መልሰው ይሰፍራሉ ። ድሆች ግን የሚሰጡት ንብረት፣  የሚያቀርቡት እንጀራ ስለሌላቸው ራሳቸውን ይሰጣሉ ። እኩያዎቻችሁ ለእኔ ይህችን ታህል ለእገሌ ይህን ያህል ሰጠ ብለው ለሞት ይፈልጓችኋል ። ድሆች ግን በሣንቲም ምጽዋት ፈገግታ ያሳዩአችኋል ። እኩያዎቻችሁ ስታገኙ በቅንዓት ይታመማሉ ። ድሆች ግን ይጨምርለት ይላሉ ። እግዚአብሔር ድሆችን ስለረሳን በእኩዮቻችን እየቀጣን ይመስላል ።
ቱንቢ ሕንጻው ከመሠረቱ አፈንግጧል ? ወይስ በመሠረቱ ላይ ነው ? የሚለውን ያሳያል ። ድሆች ቱንቢ ናቸው ። ከጌታችን ትምህርት ፣ ከሐዋርያት ኑሮ ፣ ከሊቃውንት ስምሪት ፣ ከጻድቃን ምናኔ ፣ ከሰማዕታት መናኔ ንብረት ወክብር ፣ ከአባቶች ደግነት መጽናት ወይም መናወጣችንን የምናውቀው ለድሆች ባለን ልብ ነው ። እንጃ ልቤ ይሰጋል ። ድሆችን የሚያስቡ ምስጉኖች እየጠፉ ነው ። ስለዚህ ደስታ የሌለው ሕይወት እንገፋለን ።
ለድሆች የምንሰጠው ከራሳችን ሀብት አይደለም ። እግዚአብሔር እኛ ጋ ካስቀመጠላቸው ድርሻ ነው ። ድሆችን ማገልገል የራሳችንን የነገ መድረሻ ማገልገል ነው ። ባለጠግነት የስልት ጉዳይ ፣ የብልጠት ጉዳይ እንጂ የልዩ ጸጋ መንገድ አይደለም ። ዓለም የጋራ ቤታችን ከሆነች ከሚበቃን ውጭ የያዝነው የሌሎችን ድርሻ ነው ። ድሆችን የምናገለግለው ነገ ታማኝ እንዲሆኑልን ሳይሆን የሰብአዊነታችንና የመንፈሳዊነታችን ግዴታ ስለሆነ ነው። ድሆች ከምድሪቱ አያልቁም የሚለው የኦሪቱ አዋጅ እውን ሁኖ ዛሬም ድሆች አሉ ። ፈረንጆች ለድሃ አገሮች ቢረዱ ትላንት የወሰዱትን በትንሹ እየከፈሉ ነው ። አፍሪካ መሠረታዊ ድህነት ያለባት አህጉር አይደለችም ። በሌሎች ክፋት በብዙ መንገድ የታሰረች ናት ። ለምሳሌ ብንጠቅስ ቤልጄየም ኮንጎን ለቅቃ ስትወጣ የኮንጎ ሕዝብ ቊጥር 12 ሚሊየን ነበር ። ከዚያ ውስጥ የተማረ ሰው የተገኘው 16 ብቻ ነው ። ይህ የዛሬ ስድሳ ዓመት ታሪክ ነው ። በአገራችንም ሃይማኖትንና ዘመናዊ ትምህርትን ይዘው የገቡ ሚስዮናውያን የማይታዘዛቸውን ለማስተማር ፈቃደኛ አልነበሩም ። ወዳጄ የሆኑ አንድ ሐኪም “ከ4ኛ ክፍል በላይ መማር ኃጢአት ነው” ተብለው እንዳደጉ ብዙ ጊዜ ይነግሩኛል ። የሚስዮናዊው ልጅ ግን ስምንተኛ ክፍል ደርሶ ነበርና እኚህ ሰው ፡- “የሚስተር እገሌ ልጅ መንግሥተ ሰማያት አይገባም ማለት ነው?” ብለው ሲጠይቁ ከትምህርት ቤት ተባረሩ ። ወደ ሌላ ጣቢያ ለትምህርት ሲሄዱ እርስ በርሳቸው ተነጋግረው የትም አገር ባለ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት እንዳይማሩ ተጻጽፈውባቸው ነበር ። እነዚህ ሰዎች ግን ወንጌል ሰባኪ ነን የሚሉ ናቸው ። አለቃ አያሌው ታምሩም ሚስዮናውያኑ እንዳይማሩ ከልክለዋቸው እንደ ነበር ተናግረዋል ። እነዚህ ሚስዮናውያን አገሩን ይወዳል ብለው የሚያስቡትን ይገፉት ነበር ። ምክንያቱም ይዘው የመጡት የኢንዱስትሪ አብዮታቸውን ለማስተዋወቅና ሃይማኖትን በእነርሱ ባህል እንድንቀበል ለመጫን ነው ። ስለዚህ የድህነት ምንጫችን ድህነታችን የተደራጁ ጠባቂዎች ስላሉት ነው ። ዛሬም አፍሪካ እንዳታድግ የተማሩ ልጆቿ እንዲፈልሱ ይደረጋል ። ቅኝ ገዢዎች ሲወጡ ከወጡበት አገር ሁሉ እናንተ ልዩ ሕዝብ ናችሁ ብለው ለጦርነት የሚዳርግ ደረቅ ኩራት አስታጥቀው ወጥተዋል ። ዛሬም ሙያችንን የምንደብቅ የምናውቀውን ለማሳወቅ የማንጥር ከእነዚህ ቅኝ ገዢዎች በምንም የተሻልን አይደለንም ። እኛው ካልተዛዘንን የሌሎችን ኀዘኔታ መጠበቅ ሞኝነት ነው ። አፍሪካንም ስንረግም የምንውል ሰዎች አፍሪካ ፋታ ያጣች አህጉር መሆኗን በመገንዘብ ልንሠራላት ይገባናል ።
ድሆች በዓለም ላይ የብዙ ነገሮች መነሻ ናቸው ። የግኝት መነሻዎች ድሆች ናቸው ። ማጣት የወለዳቸው ሥልጣኔዎች እንጂ ማግኘት የወለዳቸው ሥልጣኔዎች የሉም ። ማጣት የማግኘት መሠረት ነው ። ድሆች አገርን አገር አድርገው ያቆዩ ናቸው ። አገርና ንጉሥን የሚጠብቁ ወታደሮች ድሆች ናቸው ። ለአገራቸውና ለንጉሣቸው ታማኝ የሆኑ እነዚህ ድሆች በብዙ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ። ባለጠጋው ሁሉ ቪዛ አስመትቶ የተቀመጠ ነው ። አገሩ የእርሱ የምትሆነው ሰላም እስካለ ድረስ ነው ።
ድሆች ጥበበኞች ናቸው ። እግዚአብሔር ለድሆች የማይቆጠር ጥበብ አፍስሷል ። ብዙ ባለጠጎች ጥበብ ሳይሆን ገንዘብ ተሸክመዋል ። አብዛኛዎቹ የሚነጋገሩት ከሕጻናት ጨዋታ በጥቂት ከፍ ያለ ነው ። ብዙ ነጻ አውጪዎች ድሆች ናቸው ። መከራውን ስለቀመሱ ለመከረኞች ይታገላሉ ። ባለጠጎችን የሚጠብቁ ድሆች ናቸው ። ዘበኞች የምንላቸው ምስኪኖች ናቸው ። ልባቸው ግን ደፋርና ሙሉ ነው ። ሙሴ ድሃ ሁኖ ነጻ አውጪ ሆነ ። ነጻ ለማውጣት ነጻ መውጣት ያስፈልጋል ። ከኩራትና ከምቾት ያልተፈታ ራሱ ነጻ አውጪ ያሻዋል ።
ድሆችን ገሸሽ ያለ መንግሥት ዘመኑ አጭር ነው ። ድሆችን ያራቀች ቤተ ክርስቲያን ለመበታተን ቅርብ ናት ። ድሆችን የረሳ መንፈሳዊነት በክህደት የሚጠናቀቅ ነው ። ድሆችን የማያነሣ ስብከት መዶሻውን የጣለ አናጢነት ነው ። ቤተ ክርስቲያን በአካል ተመስላለች ። በአካል መመሰሏ ሥራ ስላላት ነው ። ከአካል ክፍሎች አንዱ እጅ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ለድሆች የማትሰጥ ከሆነ ዱሽ ናት ። አዎ ጸሎት ያለ ምጽዋት አይሆንም ። እግዚአብሔር በችግራችን የሚሰማን የጎረቤታችን ችግር በተሰማን መጠን ነውና ። ጾም ያለ ምጽዋት አይሆንም ። ብዙ የማይመጸውቱ ባለጠጎች የድሆች ላብ አልፎባቸዋል ፣ ነገር ግን ይጾማሉ ። እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ግን ይህ አይደለም /ኢሳ. 58፥1-12/ ። ምጽዋት የሌለበት አምልኮ ከንቱ ነው ። ክርስትናን ሕይወት ያለው ከምናደርግበት መንገድ አንዱ ምጽዋት ነው ። ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ ይላል ፡-
“ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” /ያዕ. 1፥27/ ። የሙት ልጆችን ፣ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን ቸል ያለ አምልኮ ንጹሕ አይደለም ተብሏል ። ስለ ተጣሉና በየጎዳናው ስለፈሰሱ ሕጻናት ፣ በምግብ እጦት በየትምህርት ቤቱ ስለሚወድቁ ምስኪን ልጆች እናስብ ።
ሕጻናት የዚህች ዓለም ትልቅ እንግዶች ናቸው ። እነዚህን እንግዶች በትጋትና በጥንቃቄ ከሁሉም በላይ በፍቅር እንድንቀበል አደራ የተጣለብን እኛ ነን ። ሕጻን ልጅ የአንድ ቤተሰብ አባል ብቻ ሳይሆን የመላው የሰው ዘር ወዳጅ ነው ። ሕጻን ልጅ ቋንቋው ፣ አገሩ ፣ ጎሣው ፍቅር ብቻ ነው ። ሕጻን ልጅ ፍቅርን ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ፍቅርን የሚሰጥ ነው ። ማንንም ሰው እንደ ወዳጁ ብቻ ስለሚያይ ደስተኛ ነው ። ሕይወትን እንደ አመጣጧ ይቀበላል እንጂ አስተያየት በመስጠት አይመረርም ። ሙቀቱ ሲበረታ ከመጨነቅ ውጭ “ምን መጣብን?” አይልም ። ይህችን ዓለም ከነማንነቷ ተቀብሎ እርዳታን ብቻ የሚፈልግ ነው ። በመንገድ ስናየው ፈገግ የምንልለት ፣ ከወላጆቹ ነጥቀን የምንስመው ፣ ሮጦ ሲመጣ የምናስጠጋው ሕጻን ልጅ የሁላችንም ልጅ ስለሆነ ነው ። እኩያችን የመሰሉንን ወላጆቹን መተዋወቅ ሳንፈልግ የሕጻኑን ስሙን የምንጠይቀው ወዳጅነቱን ስለምንፈልገው ነው ።
ሕጻንነት ለወደፊት ሕይወት መሠረት የሚጣልበት ዘመን ሲሆን መሠረቱን የምንጥለውም እኛ ነን ። ግንባታው በመሠረቱ ላይ እንደሚወጣ እንዲሁም የልጆች የወደፊት ማንነት ዛሬ በምንሰጣቸውና በምናሳያቸው ነገር ላይ ተወስኗል።
 ሕጻናት ሁለንተናዊ ዕድገትን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል ። የአካል ፣ የሥነ ልቡናና የመንፈስ ምግብን ሊያገኙ ያስፈልጋል ። የአካል የምንለው መብልና መጠጣቸውን ፣ የሥነ ልቡና የምንለው የተረጋጋ ቤተሰብና አገር ፣ የመንፈስ የምንለው ፈሪሃ እግዚአብሔርና ፍቅርን በማግኘት ማደግ ያስፈልጋቸዋል ። እነዚህ ሦስት ዕድገቶች ካልተሟሉ የወደፊት ዕጣቸው አስከፊ እየሆነ ይመጣል ። በአካል ብቻ ከተገነቡ የሥነ ልቡናና የመንፈስ ግንባታን ካላገኙ ራስ ወዳድ ፣ ማንንም የማያምኑ ፣ ጨካኞችና ተበቃይ ይሆናሉ ። ሥነ ልቡናቸው ብቻ ተገንብቶ የአካልና የመንፈስ ምግብ ካላገኙ ለጎዳና ሕይወት ይዳረጋሉ ፣ በለጋ ዕድሜአቸው የሱስ ተገዢ ይሆናሉ ፣ ለመላው የሰው ዘር የጥላቻን ልብ ይይዛሉ ። መንፈሳዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ፍላጎታቸው ካልተሟላ አቅመ ደካማ ፣ በበሽታ የተጎዱና ኀዘነተኞች ይሆናሉ። ስለዚህ ለልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ጠንክረን መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል።
 ያለንበት ዘመን ለሕጻናት ምቾትን የሚሰጥ አይደለም ። ሕጻናት በባሕር ፣ በበረሃ ከወላጆቻቸው ጋር ስደተኞች ናቸው ። ገና በጠዋቱ ሠርክ ሆኖባቸው እያቃሰቱ ነው። የወላጆቻቸውን ፍቅር በሚፈልጉበት ዕድሜአቸው ትዳር እየፈረሰባቸው ፣ ወላጆቻቸው ሰላም እያጡባቸው ለአእምሮ ጭንቀት እየተዳረጉ ነው ። ከድህነት የተነሣ ከወንድማቸው ጋር በየተራ የሚመገቡ ሕጻናትን እየሰማን ነው ። በየትምህርት ቤቱ በረሀብ ምክንያት የሚወድቁ ሕጻናትን እናያለን ። እነዚህ ሕጻናት በተጎዱ ቊጥር የነገ አገርና ተስፋም እየተጎዳ መሆኑን ማሰብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው ። ዓለም ለእነዚህ ንጹሐን ሕጻናት ጨካኝ ሆናለች ። ያ ማለት እኛ ከዋናችን ሳይሆን ከቅንጦት ወጪዎቻችን እንኳ ቸር ባለመሆናችን ብዙ ሕጻናት እያለቁ ነው ። የምንበላው የማይጥመን ፣ የምንለብሰው የማያደምቀን ምናልባት የእነዚህ ሕጻናት ጩኸት ወደ ፈጣሪ እየተሰማ ቢሆንስ ብለን ማሰብ ያስፈልገናል ። እንዲህ ባሉ በተጎዱ ሕጻናት ፊት የምናደርገው ቅምጥልነት በሬሣ ላይ እንደ መኖር ነው ።
 ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ድህነት ምን ማለት መሆኑን ፣ ምን ዓይነት ጠባሳ ትቶ እንደሚሄድ የሚያውቅ ማን ነው ? ድህነት የብዙ ችግሮች መነሻ ነው ። ያሳለፍነውና ያደግንበት ዕድገትም የአንዱ ልጅ የአንዱ ሆኖ ነው ። በጎዳና ላይ የሚሳደብ ልጅ ካለ የሚያልፈው ሽማግሌ ይቀጣው ነበር። ልጅ የማኅበረሰቡ እንጂ የወላጆቹ ብቻ አልነበረም ። የአንዱን ልጅ አንዱ እያበላና እያቀፈ ያሳደገበት ምሳሌ የሚሆን ኑሮ አሳልፈናል ። እነዚያ መልካም ሀብቶቻችን ግን ዛሬ ወደ ታሪክነት እንዳይቀየሩ መትጋት አለብን ። ምግብ ያገኙ ሥነ ልቡናዊ ረሀብ ላይ ናቸው ። ሥነ ልቡናቸው ያገገመ የምግብ እጦት ላይ ናቸው ። የሕጻናት ጉዳይ ሁሉን ቤት የሚያንኳኳ ርእስና ጉዳይ እየሆነ ነው።
ነገር ግን ጊዜ የሚሰጥ ችግርና ጊዜ የማይሰጥ ችግር አለ ። ጊዜ የማይሰጠው ችግር የእነዚህ ረሀብተኛ ሕጻናት ጉዳይ ነው። ሆድ ቀጠሮ አያውቅምና ። ረሀብተኛን ነገ ና ማለት አንችልም ። ያለው ቀን ዛሬ ብቻ ነው ። በእውነት የሚሰግዱ ድሆችን ያስባሉ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ