የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግዚአብሔር ያሳድጋል

“በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን ፡- ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም” /ዮሐ. 4፥27/ ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማርያ ቀትር ትንገላታ የነበረችውን ያችን ሴት ፍለጋ በምትገኝበት ሰዓትና ቦታ ሄደ ። ሰው የሚገኝበትን ሰዓትና ቦታ የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ብቻ የት ቦታ ሲመቱ አቤት እንደሚሉ የት ቦታ ሲኮረኮሩ እንደሚስቁ ያውቃል ይባላል ። አዳምን በውድቀቱ ስፍራ ያነጋገረ ጌታ ይህችንም ሴት በድካሟ ስፍራ ሊያነጋግራት መጣ ። በመለኮቱ ድካም የሌለበት በለበሰው ሥጋ ግን ለመድከም ፈቃደኛ ሆነ። መለኮታዊ ብርታቱን ለሰዎች ጽናት ሲጠቀም እርሱ ግን በእውነት የዛለ። በሰውነቱ በጥማት ሲዝል በአምላክነቱ ደግሞ የሕይወትን ውኃ የሚያድል መሆኑን በዚህ ክፍል እናያለን ። የሚደንቀው መለኮት በሥጋ መጠማቱ ፣ ሥጋም በመለኮት ሕይወት አዳይ መሆኑ ነው ። መጠማትና የሕይወትን ውኃ መስጠት የአንዱ ክርስቶስ መገለጫ ነው ። የተጠማው እርሱ የሚያረካው ነው ። የሚያረካው እርሱ የተጠማው ነው ። ሰውነቱንና መለኮቱን መለያየት በፍጹም አይገባም።
ሳምራዊቷን ሴት ለማነጋገር መክፈቻ ያደረገው የውኃን ርእስ ነው ። ውኃ የሁሉ ፍላጎት ነው ። እግዚአብሔር እንደ ውኃ አብዝቶ የሰጠው ነገር የለም ። ውቅያኖሱ ከየብሱ ይሰፋል ። ዓለም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የዓባይ ወንዝ ይፈስሳል ። የዘላለም ሕይወት በውኃ መመሰሉ በእውነት ድንቅ ነው ። ውኃ የንግግር መክፈቻ ፣ ውኃ የሳምራዊቷ ሴት ዕለታዊ ፍላጎት ፣ ውኃ የማይሰፈረው የእግዚአብሔር ጸጋ ምሳሌ ሁኖ በዚህ ክፍል ተጠቅሷል ። ጌታችን የሳምራዊቷን ሴት እምነት አሳደገላት ። ውኃ ሲጠይቃት የይሁዳ ሰው አለችው ። ስለ ሕይወት ውኃ ሲናገር ጌታ ሆይ አለችው ። ስለ ማንነቷ ሲናገር ነቢይ አለችው ። ስለ መንፈሳዊ አምልኮ ሲናገር መሢሕ መሆኑን አመነች ። ጌታችን በብዙ ትዕግሥት አሳደጋት ። እነዚህ ሁሉ ዕድገት ናቸው፡-
1-  የይሁዳ ሰው /ተራ ሰው መስሎአት የተናገረችው/
2-  ጌታ ሆይ /ሰጪ ባለጠጋ እንደሆነ የተገነዘበችበት/
3-  ነቢይ /ጓዳዋን የሚያውቅ መንፈሳዊ መሆኑን የተረዳችበት/
4-  መሢሕ /ነጻ አውጪና አዳኝ አምላክ መሆኑን ያመነችበት ነው።/
ከያዕቆብ መብለጡን ተጠራጥራለች ። ያንን የውኃ ጉድጓድ የቆፈረው ያዕቆብ ነው ። ጌታችን ግን የሕይወት ውኃ የሚሰጥ ነው ። እርሱ ግን በሚያግባባው ርእስ በውኃ ጀመረ ። ከያዕቆብ ትበልጣለህ ወይ? ስትለው መልስ ሳይሰጣት ንግግሩን ማብራራት ቀጠለ ። ለሰዎች ኋላ የምንነግራቸውን አሁን ማዘግየት ውሸት አለመሆኑን ጌታችን አስተማረን ። እበልጣለሁ ቢላት ኑሮ በዚያው ይለያዩ ነበር ። ጌታችን ግን መሄድ ለሚፈልጉ መንገድን አያሰፋም ። እርሱ አንድም ቀን “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል ፈሊጥ አላገለገለም ። ምግብ እንቢ እንዳለው በሽተኛ በማንኪያ ለማቅረብ ፈለገ ። ወላጆች ለተወለደው ሕጻን ዛሬ አጥንት ባለመስጠታቸው ንፉግ አይሰኙም ።
ሳምራዊቷ ሴት ወሳኝ የሆኑት ንስሐ ፣ እምነት ፣ ምስክርነት ፣ የሕይወት ፍሬ ታዩባት ። ያለ መሢሑ ከዘረኝነት ፣ ከኑሮ አሳብ ፣ ከሃይማኖት ክርክር መላቀቅ አልቻለችም ። እርሱ መሢሑ መሆኑን ስታውቅ ኃጢአቷንም አመነች ። ሰዎችን እውነተኛ ማንነታቸውን የሚያሳያቸው ወቀሳና ክስ አይደለም ። የክርስቶስ ብርሃናዊ ሕይወትና የቀራንዮ ፍቅር ብቻ ነው ። ንጹሕ መስተዋት ብቻ ራስን ያሳያል ። በንጹሕ ክርስቶስ ፊት ስንቆምም በፍቅር ማልቀስ ፣ በንስሐ መመለስ እንጀምራለን ። መድኃኒቱ ከሌለ ሰዎች ኃጢአታቸውን ማሰብ አይፈልጉም ። መድኃኒቱ ሲገኝ ግን በሳምራዊቷ ሴት የተከናወነው ነገር መከናወን ይጀምራል ።
1-  ያሳሰባትን ኑሮዋን ረሳችው ። እንስራዋን ጥላ ሄደች ።
2-  ያልፈለገችውን ኃጢአትን ማመን አሁን አመነች  ።
3- ሸሽታቸው በቀትር ትመጣ የነበሩትን የሰማርያ ሰዎችን በቀትር ልትሰብካቸው ወጣች ።
4-  በማንነቷ ማፈር አቆመችና ማንነቱን መተረክ ጀመረች ።
5-  በቀን አንድ ሰው የማታገኝ ሴት መላ ሰማርያን በኋላዋ እየነዳች መጣች
ይህች ሴት የነበረችበት ከተማ ሲካር የሚባል ነው ። በዕብራይስጡ ሺኮር ሰካራም የሚል ትርጉም አለው ። ስለዚህ ሲካር የሰካራሞች ከተማ የነበረች መሆኗን እንረዳለን ። ይህች ሴትም የነበረችበት ሕይወት ምን ይመስል እንደ ነበር መገመት እንችላለን ። ጌታችን ግን የኃጢአተኞች ወዳጅ ነውና ካለችበት ድረስ ፈለጋት ። ተስፋ ቆርጣ የዘጋችውን የሕይወት መዝገቧን እንደገና ከፈተላት ። አንድ ጊዜ ለመሄድ ይታክታት የነበረው ያ ምንጭ ዛሬ ግን ሁለት ጊዜ ተመላለሰችበት ። ደስታ ከድካም በላይ ነውና ። ውኃ ይዛ በገባችባቸው ዓመታት ደስታ አልነበራትም ። ዛሬ ግን ያለ ውኃ እቤቷ ስትገባ ደስታዋ ፍጹም ነበረ ። በተስፋ የምትጠብቀው መሢሕ እርሱ መሆኑን ሰማች ። መሢሕ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል በማለት የዛሬውን ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ስትፈልግ ሁለት ነገሮች ፍትው አሉ ።
1-  ለቀባሪው አረዱት እንደሚባለው ስለ መሢሑ ለመሢሑ ነገረችው ። በዚህም የኤማሁስ መንገደኞችን መስላለች /ሉቃ. 24፥18/ ።
2-  እኔ ነኝ ባላት ጊዜም በፍጹም አመነች ።
ይህች ሴት ፍጹም ባመነችበት ቅጽበት ደቀ መዛሙርቱ መጡ ። ደቀ መዛሙርቱ ሴት እንደሆነች እንጂ ማን እንደሆነች አላወቁም ። ምክንያቱም ጌታ በስውር ለንስሐ አብቅቷታልና ። ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው ያለ ጌታ ለሰው ይህንን አዝዞ ራሱ አያፈርሰውም። ስለዚህ ለብቻዋ ወቀሳት ። በአደባባይም ሲሰበክ ሰባኪው ያፈስሰዋል ። መንፈስ ቅዱስ ግን በየእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ይህ ምክር ላንተ ነው እያለ ለብቻ ይወቅሳል ። በጉባዔም እየተሰበከ በግል የሚያስተምር እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው ። ከጉባዔው ሲወጡ ተሰባኪያኑ እግዚአብሔር የተናገረው ለእኔ ነው ይላሉ ። ሳምራዊቷም ሴት ጌታችን ካነጋገራት በኋላ ለከተማው ሕዝብ ያደረግሁትን የነገረኝ እያለች መናገር ጀመረች ።
ደቀ መዛሙርቱን የደነቃቸው ጌታችን ሴት ማነጋገሩ እንጂ የሳምራዊቷ ሴት ማንነት አይደለም ። ታሪኳን አያውቁም ። ያሉበት ደረጃ የእርስዋን መዳን ብቻ ማወቅ ነው ። ከእነዚህ ምዕራፎች በኋላ እንኳ ዓይነ ስውር አይተው በማን ኃጢአት ነው ዓይነ ስውር ሁኖ የተወለደው? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል /ዮሐ. 9፥2/ ። የሥጋ ጉድለትን የኃጢአት ውጤት ብለው የሚያምኑ ደቀ መዛሙርት ይህች ሴት የሠራችውን ቢያውቁ ምን ይሉ ነበር? ጌታችን ግን እርስዋንም እነርሱንም ያሳድግ ነበር ። እርስዋን ለታማኝ ምእመንነት እነርሱን ለታማኝ አገልጋይነት ያሳድግ ነበር ። አንድ ቀን ግን እንዲህ የሚል ሥልጣን ይሰጣቸዋል ። “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው” /ዮሐ. 20፥23/ ። የእግዚአብሔር ቤት የመንግሥት ሥራ ነውና የራሱ የሆነ ምሥጢር ያሻዋል። ደቀ መዛሙርት እንኳ የማይሰሙት ምሥጢር ሊኖር ይገባዋል ።
አንድ የአይሁድ መምህር ሴትን በአደባባይ ሲያነጋግር ማየት የተለመደ አይደለም ። ዓይኖቹ ሴትን እንዳያዩ ፊቱን ሸፍኖ ያልፋል ። ይህ አታመንዝር ከሚለው ሕግ ጋር ከመታገል አስቀድሞ ማጠር እንደሆነ ያስባል። አንድን ነገር በጣም በፈሩትና በተሰቀቁት ቊጥር ፈተና የመሆን አቅሙ ይጨምራል ። ነገሮችን በልካቸውና በመጠናቸው አለማየት የብዙ ችግር መነሻ ነው ።  ደቀ መዛሙርቱ ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ እንጂ ምን ትፈልጊያለሽ ወይም ምን ታደርጊያለሽ? ሊላት የደፈረ አልነበረም ። ጉንጮችዋ በእንባ ርሰው ደስታ እንደ እሳተ ጎሞራ ከውስጧ ሊፈነዳ ሲተናነቃት ታላቅ ንስሐና ታላቅ እምነት እንደ ተፈጸመ መገመት ይችላሉ ።
ሲካር የሰካራሞች ከተማ ከሆነ ሰዎች በማለዳ መጠጥ ላይ የሚሰየሙበት ከተማ ነው ። ያች ከተማ ለኃጢአት ራሷን ራስ ገዝ ያደረገች ፣ ዛሬ የቁማር ከተሞች የዝሙት ከተሞች እንደምንላቸው መሆኗ ጥርጥር የለውም ። እዚህች ከተማ መግባት ይቻላል ። መውጣት ግን አስቸጋሪ ነው ። የዓመፅ ድንበር ናትና ከጣሱ በኋላ ለመውጣት አስቸጋሪ ናት ። ሰካራሞች ሰክረው ፍጹም ወደ አእምሮአቸው አልመለስ ሲሉ ሰዎች በቁማቸው ውኃ ያፈሱላቸዋል ። ወዲያው ነቅተው ይቀመጣሉ ። ይህች ሴት ለእነዚህ ሰዎች የሕይወትን ውኃ ይዛላቸው ስትሄድ ከስካራቸው ነቅተው መድኃኔዓለም ነው አሉ ። ሴቲቱ ከተማዬን ያድናል ስትል እነርሱ ግን የበለጠ አመኑና መድኃኔዓለም ነው አሉ። ከእኛ በላይ እኛ የምናመጣቸው ያምናሉ ።  ሴቲቱ በክርስቶስ ካመነች በኋላ ፡-
1-  “ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች”
2-  “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤”
3-  “እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች።”
ልብ አድርጉ ለብርጭቆ ውኃ የተከራከረች አሁን እንስራዋን ትታ ሄደች። ለብቻዋ ንስሐዋን ማመን ያልፈለገች አሁን ለከተማው በሙሉ ያደረግሁትን የነገረኝን በማለት መሰከረች ። ክርስቶስ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል ያለችው አሁን እርሱ ይሆንን ? በማለት ልባቸውን በናፍቆት ሞላች ። ትንቢት እያጠኑ በመቅደስ ይጠብቁት የነበሩት ቀርተው ራሳቸውን ለመርሳት የሚጠጡት ሰዎች ክርስቶስን አገኙ ። በቅርብ ጊዜ አንድ የአይሁድ ረቢ ሲናገር ሰማሁት በማለት አንድ ወዳጄ ነገረኝ ። ይህ ረቢ እንዲህ አለ ፡- “በዓለም ላይ ሦስት ከባድ ነገሮች አሉ ። አንደኛው፣ መንግሥተ ሰማያት መግባት ነው ። ሁለተኛው ፣ ቶራህን /ሕጉንና ማብራሪያ መጻሕፍቱን/ አንብቦ መፈጸም ነው ። ሦስተኛ፣ በኢየሩሳሌም ውስጥ በዐረቦች ስጋት መኖር ነው።” እነዚህ ሦስት ነገሮች ግን ለሳምራውያን ከባድ  አልሆኑም ። ጌታችን በመገኘቱ አቀለለላቸው ። አንድ አጥባቂ አይሁዳዊ መንግሥተ ሰማያት መግባትና መጻሕፍትን በጥልቀት ማወቅ ከባድ ነው ካለ ሳምራዊማ ምን ቢል ምን ይታመናል ። በክርስቶስ ግን መላው ኦሪት የተናገረለትን መሢሕ ማወቅና መንግሥቱን መውረስ ቀለለ ። ሲካር ከቴሌአቪቭ አቅራቢያ ካሉ ከተሞች አንዷ ናት ። ዛሬ በቴሌአቪቭ ወንጌል መስበክና እንደ ወንጌል አሳብ መኖር የሚቻል አይመስልም ። ከተማዋ የስካርና የዝሙት ከተማ ሁናለች ። ጌታችን ግን መድኃኔዓለም ነውና ሁሉን ማዳን ይችላል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ