የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ፈቃድ

“ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” /ዮሐ. 4፥34/።
ደቀ መዛሙርቱ ያመጡትን ምግብ ጌታችን አልበላም ባላቸው ጊዜና በታላቅ ጥጋብ ውስጥ መሆኑን በነገራቸው ሰዓት ጉዳዩን ከምድራዊ እንጀራ ጋር አያያዙትና የሚበላ ምግብ አንድ ሰው አምጥቶለት ይሆናል ብለው አሰቡ ። ጌታችን የእርሱ መብል የአባቱን ፈቃድ መፈጸም መሆኑን ነገራቸው ። የአባቱ ፈቃድ ምንድነው? ስንል የሰዎች መዳን ነው ። አባቱ የላከው ሙትና አድን ብሎ ነው ። እንዲህ ብሎ ልጁን የላከ አባት ፣ ለሞት ለመታዘዝም እሺ ያለ ልጅ የለም ። ለበደለ ባሪያ አንድ ልጅን የሚሰጥ ጌታ በዓለም ቢዞሩ አይገኝም ። ለጠላቱ የሚሞትም ከክርስቶስ በቀር አይገኝም  በዚህች ሳምራዊት ሴት መዳንም አባቱ ደስ ይለዋል ። ምክንያቱም ፈቃዱ ይህ ነውና። በዚያ የምንጭ አጠገብ በሚፈጸመው መዳን ሰማይም በደስታ ይሞላል። ምክንያቱም ወልድ ሰው የሆነበት ዓላማ የእግዚአብሔር አብም ጽኑ ፈቃድ የሰዎች መዳን ነውና ። በራሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ስምረት መጣ ፣ ሰው ሁኖ አዳነን የምንለው ለዚህ ነው ።
በዚህች ሴት መመለስ ራሱ ጌታችንም ታላቅ ደስታ ተደሰተ ። እርሱ የተደሰተበት አንዱ ምክንያትም አባቱ ደስ ስለተሰኘ ነው ። ይህች ሴት የተናቀች ሴት ናት ። ወገኖቿ ሁሉ የጠሏት ብትሆንም ማንንም የማይንቀው እግዚአብሔር ግን በመመለሷ ይደሰታል ። እንዲህ ያለች ሴት ወደ ሃይማኖት ብትመለስ “ይሻላታል” ከማለት ውጭ ከልቡ የሚደሰት ሰው ላይኖር ይችላል። እግዚአብሔር ግን የነፍስ ዋጋ ያለው እርሱ ዘንድ ነውና ደስ ይለዋል ።
  የእግዚአብሔር ፈቃድና ሥራ ምንድነው ? በዋናነት ሰዎች እርሱን አውቀው እንዲያምኑት ፣ አምነው እንዲያመልኩት ነው ። ጌታችን ይህንን ፈቃድና ሥራ በምድር ላይ እንደ ፈጸመ በጌቴሴማኒ ጸሎቱ ገልጧል ። “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” /ዮሐ. 17፥4/። በዚህ ጸሎቱ ውስጥ የምንማራቸው ነገሮች አሉ ፡-
1-  እያንዳንዳችን ልናደርገው የተላክንበት መንፈሳዊ አደራ አለ ።
2-  ሥራችንን የምንፈጽመው በምድር ላይ ነው  ። በሰማይ ያለው የሥራ ዋጋ ነውና ።
3-  ሥራችንን መፈጸም የሚገባንም ለእግዚአብሔር ክብር ነው ።
4-  ያ ሥራም ሌሎችን ወደ እውነትና ወደ ሕይወት መምራት ነው ።
5-  የሥራችን ሪፖርትም ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ነው ።
ብዙ የተከፉ ፣ አንዲት የመጽናናት ቃል የራባቸው አያሌ ወገኖች አሉ። የእግዚአብሔርን መንገድ ማን ያሳየናል ? የሚሉ ፣ የሚያረጋጋቸው አጥተው በፍርሃት ቀኑን የሚገፉ ዕለት ዕለት እየበዙ ነው ። በቅምጥልነት ተይዞ የበደለውን ሕዝቡን በነቢያት የሚገስጽ እግዚአብሔር በኃጢአት ወድቆ የሚቀጣውን ሕዝብ ደግሞ አጽናኝ ነቢያትን ይልክለታል ። ከውድቀት በኋላ የማንሠራራት ፍርሃት አለና እንደገና የሚያበረታቱ ነቢያት ይላካሉ ። የዛሬውም ወገን ራሱን በኃጢአት ጦር ወግቶ የሚያቃስት ፣ ችግሩ በመጣበት መንገድ መፍትሔን የሚፈልግ ነውና አጽናኝ አገልጋዮች ያስፈልጉታል ።ስለዚህ ይህንን ሕዝብ በቊስሉ ከመነገድ ቊስሉን ልንጠርግለት ፣ ቀና ብሎ ይሄድ ዘንድ ተስፋን ልናበስረው ፣ የግላችንን ጠብ ከማውረስ ሰላምን ልናካፍለው ይገባል ። ለዓለም መፍትሔ እንድንሆን የተላክን አማንያን ተጨማሪ ችግር እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን ።
በራሱ መደሰት ያቃተው ፣ በሰዎች ወጥመድ ተሰናክሎ የወደቀው ፣ ከፈራጆች ፍርድ ያጣው ፣ የበላዮች ያላዘኑለት ፣ ትዳሩ የእሾህ ጉዝጓዝ የሆነበት ፣ ልጆቹ የካዱት ፣ ሰንሰለታማ ችግር ያሰቃየው ፣ የዘመናት ቀንበር የከበደው ፣ ምን ሠርቼ ይሆን ? ይህ ሁሉ የሆነብኝ የሚለው ፣ አልፎ ማውራትን የተጠራጠረው ፣ ስንዴ ዘርቶ እንክርዳድ ያጨደው ፣ በገዛ አገሩ የባዕድ ያህል የተገፋው ፣ ካህን ምሥጢሩን ያወጣበት ፣ መቃብር የተፋው ፣ ቤቱ ጎዳና የሆነበት ፣ ነግቶ የምሽት ያህል መውጣት ያቃተው ፣ ሞትን ፈርቶ ወደ ሞት የሚሰደደው ፣ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ያዛሉት ፣ በተስፋ ዳቦ ዘመኑን የጨረሰው ፣ መንከራተት ወጥ ቀማሽ ያደረገው ፣ ከሃይማኖት ወደ ሃይማኖት የሚቀላውጠው ፣ በጥዋት አቋሙ መዋል ያቃተው ፣ ወዳጁ ያላዘነለት ፣ ፀሐይ ቃጠሎ ፣ ዝናብ ጎርፍ የሆነበት ፣ ጨረቃ ያቃጠለው ፣ ሌሊቱን በመንገድ የሚጨርሰው ፣ የሚፈልገውን የማያውቀው ፣ መልሱ ጥያቄ የሆነበት ፣ በደል ቤቱን የሠራበት ፣ ቀቢፀ ተስፋ ምላሱን መራራ ያደረገበት ፣ ፍቅረ ንዋይ ያሰከራቸው ያደከሙት ፣ እንብላ ባዮች መቃብር የሆኑበት ፣ አምላኩን ለማየት ረጃጅሞች የጋረዱት … አዎ ለዚህ ከርታታ ፣ አዎ ለዚህ የመከራን ጽዋ ከእጁ ነጥቆ የሚያሳርፈው ላጣ ወገን የክርስቶስን ፍቅር መንገር ይገባል ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነው ።
አንድ ወዳጄ የነገረኝ ትዝ አለኝ ። አንድ አፍሪካዊ ድሃ በቊስል ተወርሮ ዝንቦች ደሙን መጠው ፣ ጠግበው ላዩ ላይ ተኝተዋል ። ይህንን ክስተት ያየ አንድ ደግ ሰው ዝንቦቹን ሊያባርርለት ጠጋ ሲል ተው በማለት ከለከለው ። ያም ደግ ሰው “ላንተ አዝኜ ዝንቦቹን ላባርርልህ ነው” አለው ። ያ ምስኪን ለማኝ ግን ፡- “እነዚህ ዝንቦች ደሜን መጠው ጠግበው ተኝተዋል ። እነዚህን ካባረርካቸው ገና ያልጠገቡ መጥተው ያቆስሉኛል ስለዚህ ተዋቸው” አለው ። አዎ ካለመዱት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል ማለት ጭንቀት የወለደው እንጂ እውነት የወለደው ሐቅ አይደለም ። እንዲህ ላለው ወገን በመራራት ማጽናናት የእግዚአብሔር ፈቃድ ፣ እኛ የምንኖርበት ዓላማ ነው ። “አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ” /ኢሳ. 40፥1/ ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመቀጠል፡- “እናንተ፡- ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል ፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል ። አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና ። እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ” በማለት ተናገረ /ዮሐ. 4፥35-38/ ።
የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሻ መመሰሏ ከጥንት ጀምሮ የታወቀ ነው /መዝ. 79፥8-19፤ ኢሳ. 5፥1-7፤ ማቴ. 21፥33-41፤ ሉቃ. 13፥6-9፤ 1ቆሮ. 3፥9/።  ጌታችንም የወንጌሉን ሥራ በእርሻ መስሎ ተናገረ ። እርሻው ምእመናን ናቸው ። ገበሬዎቹ ነቢያትና ሐዋርያት ናቸው ። ዘሩ ቃሉ ነው ። እርሻው እንደ ነጣና ለአጨዳ እንደ ቀረበ ምልክቱ ምንድነው ? ስንል ጥዋት ኃጢአተኛ የነበረች ሴት ከሰዓት በኋላ ሰባኪ ሁና መላውን ሰማርያ አስከትታ መምጣቷ ነው ። ሐዋርያት በለማ መንገድና ዝግጁ በሆነ ትውልድ መካከል እንደ ተላኩ በመግለጥ ልባቸውን ያነሣሣዋል ። መስከረም ላይ የበቀለውን በማየት ትሣሥ ላይ ይታጨዳል ጥሩ ይዟል ይባላል ። ልክ እንደዚሁ ዓይናችሁን አንሥታችሁ ተመልከቱ አለ ። በትንሽ ንግግር ብዙ ምርኮ ከመጣ ፣ በሳምራዊቷ ሴት ምስክርነት ይህ ሁሉ ሰው ካመነ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ብትወጡ ብዙ ትርፍ ታገኛላችሁ ማለቱ ነው ። አንድ ሰባኪ መጣ ሲባል የሚጎርፈውን ሕዝብ ስናይ ምን ያህል የተሰናዳ ልብ እየጠበቀን እንደሆነ እንረዳለን ። ወንጌል በሰው ብርታት የሚሰበክ ሳይሆን በራሱ ብርቱ ነው ። ቃሉን በአፋችን ያዘጋጀ ጌታም የተዘጋጀ ልብም ያመጣልናል ። አባት ቢያገኝ ስንት ልጅ ፣ መምህር ቢያገኝ ስንት ደቀ መዝሙር ይገኝ ነበር። የወንጌል ሥራ የደቦ ሥራ ነው ። ነቢያት መደመዱ ሐዋርያት ገደገዱ እንደተባለው ምንጠራውን የመነጠሩ ፣ መዐዘኑን ያቆሙ አሉ ። ጀማሪው ለሚጨርሰው መሠረት ነው ። የጨረሰውም በመሠረተው ላይ ቆሞ ነው ። ወንጌልን እኔ ጀምሬ እኔ ጨረስኩት የሚል ሊኖር አይችልም ። ክብሩ የጋራ ነው ። እኛ ስንሰብክ ስብከት የጀመረ ከመሰለን በእውነት ሞኞች ነን ። ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች እንደሚባል አባቶችን ለማስተማር የምናስብ ፣ የምናውቀውን የማያውቁ ከመሰለን ሞኞች ነን ። አዎ ነቢያት ዘሩ ሐዋርያት አጨዱ ። የዛሬ አገልጋዮች ክብርና በረከት የቀደሙት ልፋትና መከራ ነው። የወንጌሉ ሥራ ዛሬ በቀላል መንገድ ስናካሂደው ዕድሜ ለዘመናዊነት እንል ይሆናል ። የደከሙና ዋጋ የከፈሉ አባቶች ግን አሉ ። አባት የሌለውና የቀደሙትን የማያከብር አገልግሎት የትም አይደርስም ። አባቱን የማያከብር የሚያከብሩት ልጆች አይወልድም ።
ዛሬም እርሻው ነጥቷል ። ለአጨዳ ተዘጋጅቷል ። የሐሰት አስተማሪና መናፍቃን እንኳ የእያግበሰበሱት ነው ። እውነትን የያዙ ፣ ክርስቶስን ኃይላቸው ያደረጉ ሊበረቱ ይገባል ። የማይሻሻለውን ሃይማኖት በተሻለ ቋንቋ ለትውልድ ማቅረብ ይገባል ። እውነተኞች ዘወር ሲሉ ሐሰተኞች አደባባዩን ይሞሉታል ። ለማያፍሩት ከምናፍርላቸው የማያሳፍረውን እውነት ልናስተምር ይገባናል ።
የዚያን ያህልም ብዙ ወጥ የቀመሰ ትውልድም አለ ። ብዙ ድስት የለመደ ምንም አይጥመውም ። መተቸት እንጂ በደስታ መመገብ አይሆንለትም ። እንደ ሰፈር ምጣድ ሲዞር በሚኖረው ትውልድ  ሁሉን መለካት አይገባም ። አንድ አባት እረኛ ጠፋ ስላቸው “በግ ራሱ የት አለና” ብለውኛል ። እውነት በጎች ነን ? በግ እረኛ ይፈልጋል ። ተኩላ ግን እረኛ አይፈልግም ። ራሱን ማሰማራት የሚፈልግ በግ አይደለም ። በማመንና በአገልግሎት የቀደሙትን የማያከብር በግ አይደለም ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ