የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ነቢይ በአገሩ አይከበርም

“ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ ። ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና ። ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት” /ዮሐ. 4፥43-45/ ።
ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴትና ለሰማርያ ሰዎች ድኅነትን ከፈጸመ በኋላ ወደ አደገበት ወደ ገሊላ መጣ ። ወደ አደጉበት አገር ተልእኮ ይዞ መሄድ ከባድ ነው ። ምክንያቱም አብሮ አደጎች የተለያየ ጠባይ አላቸው ። ነቢይ ወደ ትውልድ አገሩ ሲሄድ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ ፡-
1-  ሲያስተምር የሚያዩት አብሮ አደጎች ይህንን እውቀትና ጥበብ ከየት አመጣው ? በማለት ከመስማት ይልቅ የትመጡን መመርመር ይቀናቸዋል።
2-  እኛ እዚህ ተቀምጠን ምን አገኘን ። እርሱ ጎበዝ ነው ፣ ይህን ሕዝብ ይንገሥበት በማለት ሥጋዊ ትርጉም ይሰጡታል ።
3-  ትልልቆቹም እገሌ አድጎ ማስተማር ጀመረ በማለት ከትምህርቱ ይልቅ የልጅነት ረብሻውን ማስታወስ ይጀምራሉ ።
ጌታችን ነቢይ በገዛ አገሩ አይከብርም ማለቱ ለዚህ ነው ። የተፈተነ ቃል ነው። በሌላው አገር አባ ፣ መምህር የሚባሉ ወዳጉበት ሲሄዱ በድሮ የጠባይ ስማቸው ሲጠሯቸውና ቀልል አድርገው ሲያዩአቸው አብረዋቸው የሄዱ ተከታዮቻቸው ይደነግጣሉ ፣ ይቆጣሉ ። አብሮ አደጎች ነቢይን የማያከብሩበት ምክንያት ምንድነው ?
1-  ስለዚያ ሰው ያላቸው ውስን እውቀት ይይዛቸዋል ። እነርሱ የሚያውቁት የዚያን ሰው ማንነት ነው ። እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያለውን ዓላማ ግን አያውቁም ።
2-  እኛ እያለን በየት በኩል አልፎ ጥበብ ነካው ? በማለት መቀበል ይከብዳቸዋል።
3-  ቅንዓትም ፈተና ስለሚሆንባቸው ማጣጣል ብሎም ስም ማጥፋት ይጀምራሉ ። ያ ሰው የያዘው የማይሰረቅ ሀብት መሆኑን አይረዱም ። ገንዘብ ፣ ሹመት ፣ ሥልጣን ፣ ዝና ሊወሰድ ይችላል ። ጸጋ እግዚአብሔር ግን አይሰረቅም ። የማያውቅ ሲያከብር የሚያውቀው የሚንቀው በቅንዓትም ነው ። ቅንዓት ስሙን መጥራት እንፈራዋለን እንጂ የብዙ ሰው ፈተና ነው ። ከዘወትር ጸሎታችን ሊለይ የማይገባው ነገር፡- ጌታ ሆይ በወንድሜ መልካም ዕድል እንዳልበሳጭ እርዳኝ የሚል ሊሆን ይገባዋል ።
በገዛ አገራቸው ያልተከበሩ ስንት አሉ ? ሰውዬው መጋቢት 5 ቀን አቡዬን ለማክበር ከሩቅ ቦታ መጥቷል ። በአቅራቢያው ያለው አንድ ገበሬ ደግሞ በዓሉን ትቶ ያርሳል ። ይህ የሩቅ ሰውም ተገርሞ፡- “አቦን የሩቅ ያከብራቸዋል ፣ የቅርብ ይሽራቸዋል” አለ ይባላል ። የሩቁን ማክበር የቅርቡ መሻር የተለመደ ነው ። የሩቁ የሚሰማቸውን ሰዎች ትዳራቸው ግን የማይሰማቸው አያሌ ናቸው ። አገርን የገዙ ሚስታቸውን መግዛት ግን አልቻሉም ። ሕዝብን የሚያስተምሩ ልጆቻቸው ግን እንቢ ሲሏቸው ማየት የተለመደ ነው ። ብዙ ፀሐፍት የራሳቸውን ቢጽፉ አንባቢ ስለሌላቸው የሌሎችን ሥራ ይተረጉማሉ ። የራሱን ፀሐፊ የሚንቀው ወገን የፈረንጅን ትርጉም ይሻማበታል ። በዚህም ስንት ፀሐፊያንን ፣ ደግሞም አገር በቀል እውቀትን ገድለናል ። ያለ ልካችን የተሰፋውን የፈረንጅ ሥነ ጽሑፍ ግን ተሸክመናል ። እገሌ የሚያነበው የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን ነው እንዲባል የአማርኛ መጽሐፍ ይዘው የማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ ። የአማርኛ መጽሐፍ ሲያነቡ ይህ የተከለከለ ነው ፣ የመናፍቅ ነው እያሉ ከእጅ የሚያስጥሉ ሰዎች ፣ የእንግሊዝኛ ከሆነ የሌሎች ሃይማኖቶችን መያዝ ብቻ አይደለም እየጠቀሱ ያስተምራሉ ። መናፍቁ ቋንቋው ነው ወይስ አሳቡ ? የሚለው ገና መልስ አላገኘም ። ከውጭ አገር ለሚመጡ መምህራን ከፍተኛ ደመወዝ ሲከፈል ለአገር ውስጥ መምህራን ግን የወደቀ ገንዘብ መክፈል የተለመደና ያልተፈወስንበት ነው ። በቤተ ክህነት ኬንያ ደርሶ የመጣ ሰው ካለ አባ ኬንያ ተብሎ አንድ ደብር ይሰጠው ይባላል ። ለማንኛውም አንድ አገር ደርሶ መምጣት ክብር ያሰጣል ። ሱዳንም ፣ ሩዋንዳም ብቻ ወጣ ብሎ መግባት ለመከበር ወሳኝ ነው ። ስለ አገሩ የሚያውቅ ግን በየሀብታም ቤት ዘበኛ ሁኗል ። ብዙ የቅኔና የመጻሕፍት መምህራን የሀብታም ቤት ዘበኛ ሁነው አይቻለሁ ። ማንበብ እንኳ የማይችሉ መስሎን ስንንቃቸው የምንሠራውን ሁሉ ይታዘቡ ነበር ።
አዎ ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም ። ይህ ቃል ከእኛ አገር በላይ የት ይሠራል ? የራሳችን ሊቃውንት ቢሰድቡን እንኳ አንቀን ይዘን መጠቀም ሲገባን የሚያማክሩንና የሚተቹልን ፈረንጆችን ግን በሚሊየን ብሮች እያስመጣን እንዳክራለን ። በአገሩ በሬ ካልሆነ የአገሩ እርሻ አይዘለቅም ። የገዛ አባባላቸውን ሰው ስለማይሰማላቸው ሪቻርድ የተባለ ኢማኑኤል የተባለ ፈረንጅ እንደ ተናገረው እያሉ የሚጽፉ ተወዳጅ የሆኑ አያሌ ናቸው ። በሕይወት ካለው የአገር ልጅ የሌለው ሪቻርድ ሲከበር ማየት በጣም ይገርማል። ስማቸውን ዮሐንስ ከማለት ጆን ፣ ማርቆስ ከማለት ማርክ፣ ጳውሎስ ከማለት ፖል የሚሉ የአገራችን ልጆች ብዙ ናቸው ። አካላችን ቅኝ ባይገዛም የመንፈስ ቅኝ ግዛት ውስጥ ገብተናል ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገሪቱን ለፈረንጆች ክፍት በማድረጋቸው መሳፍንቱና መኳንንቱ “ተፈሪ የፈረንጅን ጎረምሳ ከነንፍጡ ሳመው” እያሉ ይተቹ ነበር ። አዎ ከሌሎች የሚወሰደውንና የሚቀረውን አለመለየት ትልቅ ድንቁርና ነው ።
“የቅርብ ጠበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል” ይባላል ። የቅርብ አገልጋይ ይናቃል ። ቢያውቅም የሚያውቅ አይመስለንም ። የምናጣውና የሚያጎድለንም አይመስለንም ። ነገር ግን አንድን አምባሳደር መናቅ መንግሥቱን መናቅ እንደሆነ አገልጋዩንም መናቅ እግዚአብሔርን መናቅ ነው። በቤታቸው ያሉትን አገልጋዮች እየናቁ ሌላ ቦታ ሄደው የሚሰሙ ብዙ ናቸው። የእነርሱ የሥጋ አባት የሆነው ያስተማረውን ሰው የሚሰሙ ፣ አባታቸውን ግን የማይሰሙ ብዙ ገጥመውኛል ። የቄስና የፓስተር ልጅ ጨዋነት ብዙ ጊዜ የሚያንሰው ለምንድነው ? የመጀመሪያው ታሰድበኛለህ እያሉ ለልጁ ሳይሆን ለክብራቸው ስለሚያስተምሩት ነው ። ሁለተኛው ግን ነቢይ በገዛ አገሩ ስለማይከብር ነው ።
ዐጼ ቴዎድሮስ እቴጌ ተዋበች ከሞቱ በኋላ ያገቡአቸው ሁለተኛ ሚስታቸው እቴጌ ጥሩ ወርቅ ነበሩ ። እቴጌ ጥሩ ወርቅ የሰሜኑ ገዥ የደጃች ውቤ ልጅ ናቸው ። ንጉሡ እቴጌ ጥሩ ወርቅን ያገቡት አባታቸውንና ሁለት ወንድሞቻቸውን አስረው ነው። በቤተሰባቸው ላይ በወረደው መከራ ዓለምን ንቀው መመነን የሚፈልጉት እቴጌ ጥሩ ወርቅ በግድ የዐጼ ቴዎድሮስ ሚስት ሆኑ ። እቴጌም ደስተኛ ስላልነበሩ ለንጉሡ ደስታን መስጠት አልቻሉም ። ንጉሡንም ከማክበር ወደ መናቅ ደርሰው ነበር ። አንድ ቀን ከደጅ ሲመጡ እቴጌ ዳዊታቸውን ይዘው እንደሚያነብ በመምሰል ከመቀመጫቸው ሳይነሡ ቀሩ ። ንጉሡም እንዴት አትቀበይኝም  ? ቢሏቸው “እርስዎ ከሚበልጥ ንጉሥና ከሚሻል ሰው ጋር ጉዳይ ይዣለሁ” በማለት መልሰዋል ። የንግሥቲቱ ሁኔታ ዕለት ዕለት እየጨመረ መጣ ። አንድ ቀን ባለሟላቸው ተከፍቶ ሲጠይቅ ንጉሡ ፈገግ ብለው ፡- “አንተ የምታውቀኝ ታጥቄ ፣ እርስዋ የምታውቀኝ አውልቄ ነው” በማለት የክብሩንና የንቀቱን ምክንያት ተናግረዋል።
ነቢይ በገዛ አገሩ ቢከበር ነገሥታት ለክፉ ውሳኔ አይዳረጉም ነበር ። ከነገሥታት ውሳኔ ጀርባ እቴጌዎች አሉ ። አገልጋዮችም በዘበት አያገለግሉም ነበር ። ጳጳሳትም የእልህ ሥራ ሠርተው አይሄዱም ነበር ። አለማክበር አለመከበርን ይወልዳል ። የተላኩልን ነቢያት ነገሥታት ይሁኑ ጳጳሳት ፣ ቀሳውስት ይሁኑ ምሁራን ከምንሰጣቸው ክብር የሚሰጡን ክብር ይበልጣል ። የተላኩልንን መልእክተኞች በክብር ስንቀበል ከላኪው አካል ሌላ በረከት ይላካል ። አሊያ መልእክተኛው ሲታሠር ንጉሡ ጦር ይልካል ። የእግዚአብሔር ቃል አይለወጥም፡- “የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ” /መዝ. 104፥14-15/።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገዛ አገሩ ወደ ገሊላ በሄደ ጊዜ ብዙ ጊዜ የንቀት ድምፅ አሰምተውበታል ። “ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ። ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው?…” /ማቴ. 13፥53-58/። ቢሆንም ጌታችን እነርሱን ለማስተማር አልታከተም ። ዛሬ ከአገር ርቃችሁ ያላችሁ ፣ ክብሬ ተደፈረ ፣ ሞገሴ ተገፈፈ ብላችሁ ያኮረፋችሁ የምታስፈልጉት ለተላካችሁበት አገር ነውና መለስ በሉ ። እግዚአብሔር እናንተን በዚህች ምድር ላይ ሲፈጥር ፣ኢትዮጵያዊ አባትና እናት ሲሰጣችሁ አልተሳሳተም ። የሰው አገር በቁም ቢያከብር ሲሞቱ ይረሳል ። አገር ግን በቁም ቢያዋርድም የሞቱ ቀን ሲያስብ ይኖራል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ