የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የገበታ ወዳጆች

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት ወዳደረገበት ወደ ቃና ዘገሊላ እንደገና እንደ መጣ ሁለተኛም ምልክት እንዳደረገ ማየት ጀምረናል ። ታሪኩ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4፥46-54 ተጽፎልናል ። ከንጉሥ ቤት የሆነ ሹም ልጅ ታመመበት ። ይህ ሰው ጌታችን በቃና ዘገሊላ ያደረገውን ሳይሰማ አይቀርም ። የቃና ዘገሊላ ሰርገኞችን ከሐፍረት ያዳነ ጌታ እርሱንም ከሐፍረት አደባባይ ከመቆም ያድነው ዘንድ ለመነው ። ቢያጠፋም ባያጠፋም ሹም መሆን በራሱ ብዙ ጠላት ያመጣል ። እንዳለበት ከፍታ ጥቂት ስህተቱ ትጎላለች ። በዚህ ዓለም ላይ ተገዝቶ እንደ መኖር ያለ ሰላም የለም ።
የቃና ዘገሊላን ክስተትና ይህንን ክስተት አንድ የሚያደርገው ሁለቱም ክስተቶች ላይ ከጉዳዩ ባሻገር ያሉ የሚያቀርቡት ምልጃ አለ ። እመቤታችን ስለ ሰርገኞቹ ሐፍረት ትለምናለች ። ይህ ሹምም ስለ ልጁ መታመም ይለምናል። እግዚአብሔር ከሚወደው ነገር አንዱ ስለ ሌሎች የሚቀርበውን ልመና ነው ። በምልጃ ውስጥ ያለው ፍቅር ብቻ ነው ። የሰውዬው ችግር ካልተሰማን በቀር ወደ እግዚአብሔር አንጸልይም ። ምልጃ ሁለንተናው ፍቅር ነው ። አንድን ጸሎት ሙሉ የሚያደርገው በውስጡ ምልጃን ያዘለ ሲሆን ነው። እግዚአብሔር ስለ እኛ ጉዳይ እንዲሰማው ስለ ሌሎች ጉዳት ምን ያህል እንደ ተሰማን ማወቅ ይፈልጋል።
የልጅ ሕመም አደባባይ ያወጣል ። ይህንን በዚህ ሹም ብቻ ሳይሆን በዚያች በከነናዊት ሴትም አይተናል /ማቴ. 15፥21-28/ ። ጌታችንም በአደባባይ የተሰቀለው ልጁ አዳም በኃጢአት በሽታ ታሞበት ነው ። በኋላ የተወለደ ልጅ ቀድሞ ሊሄድ መቻኮሉ ቤተሰብን ያሳስባል ። ይልቁንም ከታማሚ ያስታማሚ በሽታው ይበረታልና ይህ ሰው እጅግ ተጨንቆ እንደ ነበር ፣ ከመንግሥታዊ ሥራ ጋር የልጅን ሕመም መሸከም ከብዶት ነበር ። የሚታወቀው በስፍራው ሁኖ ሲለመን ፣ ደጅ ሲጠኑት ነበር ። ዛሬ ደግሞ ለትልቁ ንጉሥ ለክርስቶስ እጅ ሲነሣና ደጅ ሲጠና ይታያል ። ክርስቶስም ለለመኑት ቸር ነውና ፣ ታሪክን ሳያገናዝብ ለጸሎት መልስ ይሰጣልና ተለመነው ።
ይህ ሰው ልጁ የሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር ። ጌታችንንም ልጄን መጥተህ ፈውስልኝ አለው ። በክርስቶስ ፈዋሽነት ፍጹም እምነት ነበረው ። ሹማምንት ሲያምኑ ብዙ ነገሮች ይለወጣሉ ። ጸሎታቸውም ተሰሚ ነው ። ብዙዎችን ወክለው ይኖራሉና እግዚአብሔር ድካማቸውንም በልዩ ያየዋል ። የሚቀጡትም ከተገዢው ሕዝብ ጋር ሳይሆን የሚዳኙበት ልዩ ችሎት አለ ። ያ ሹም ወደ ጌታችን ከፍና ዝቅ እያለ በአደባባይ ልመናውን እያሰማ መጣ ። ችግር ከመጠጥ በላይ ያሰክራል ። ይሉኝታን ያሳጣል ። እንዳበደ ሰው ያስጮኻል ። ጌታችን ግን የሰጠው ምላሽ የቊጣ ይመስላል ። በጣም ደግና ሩኅሩኅ የሆኑ ሰዎች አንድ ነገር ስንለምናቸው የቊጣ የሚመስል ድምፅ ያሰማሉ ። ልመናችን ሆዳቸውን እያራራው ስለሆነ ከዚያ ስሜት ለመውጣት ይቆጣሉ ። ሰከንዶች ስንታገሥ ያ ደግነት ይፈስሳል ። ጌታችንም በጣም ደግ ነውና ስንለምነው ከፍቅሩ የሚወጣ ቊጣ መሳይ ድምፅ ይሰማል ። እርሱ ጉዳያችንን ከመሥራቱ በፊት እኛን ለመሥራት ይፈልጋል ።
“ስለዚህም ኢየሱስ፦ ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው” /ዮሐ. 4፥48/ ። ጌታችን የቃሉን ወዳጆች እንጂ የተአምራት አፍቃሪዎችን አይፈልግም ። ተአምራት ስላዩ እግዚአብሔርን የሚከተሉ የበለጠ ካሳያቸው ሰይጣንን ይከተላሉ ። ተአምራት አፍቃሪዎች የበለጠ ካገኙ የያዙትን ለመተው በጨረታው አይገደዱም ። ጌታችን ከሰውዬው ልመና በላይ የሰውዬውን እምነት ሊጠግን ፈለገ ። የእምነት መሠረቱ እውነት ነው ። በጊዜውም ያለ ጊዜውም ለመጽናት እምነትን እውነት ላይ መመሥረት ይገባል ። በዓለም ላይ ትልቅ ውሸት ሁኖ የሚዘገበው ተአምራት ፈላጊዎች አንድ ቦታ ጸኑ ተብሎ ሲወራ ነው ። ብዙዎቹ ኑሮአቸው ይፈርሳል ። ተአምረኛ ነን ለሚሉ ሰዎችም አገልጋይ ሁነው ይቀራሉ ። የብዙ ባሕታውያን ተከታዮች ሰውን የተከተሉበትን መጠን ክርስቶስን መከተል አቅቷቸው በቤተ ክርስቲያን የስድብ መምህራን ሁነው ቀርተዋል ። አስተማሪ የሌለው ምእመን የሙት ልጅ ነው ። ለቤተ ክርስቲያን የጎን ውጋቶች ተአምር ፈላጊዎች ናቸው ። ተአምር አድራጊ መጣ ሲባል ዓመት ሙሉ ሲማሩት የነበረውን ገበታ በአንድ ቀን ለውጠው ፣ ያመኑትን ክደው ያድራሉ ። የከረሙትን አባቶች አንኳሰው አዲሱን ተአምረኛ አግንነው ይናገራሉ ። አዲሱን ባል በደንብ ሳያጣጥሙት ከቆየው ይፋታሉ ። “የወረት ውሻ ስሟ ወለተ ጴጥሮስ ነው” ይባላል ።
 የምዕራቡ ዓለም ለዛሬው ክህደት የተዳረገው አማኝ በሚመስሉ ተአምራት አድራጊዎች ነው ። ያ በሩቅ የታየው ቅርብ እየሆነ ነው ። ሳሙና ግዙ ፣ ብራችሁ ላይ ይጸለይ ዶላር ይሆንላችኋል የሚል ድምፅ እየተሰማ ነው። አሳሳቢው ከቤተ ክርስቲያን ሰዎች መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን ነገ ከሃዲ ሁነው የክርስትና ጠላት መሆናቸውም ነው ። የተጸለየበት መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት መቶ ሺህ ብር ጨረታ ሲሸጥ በቴሌቭዥን መስኮት እያየን ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይጸለያል ወይ ? የሚጸለየውስ ለምንድነው ? ይህ በሽታ ወደ ቤታችን እንዳይገባ ፍጹም ያሰጋል ። ብዙ የጓዳ ልምምዶች እንዳሉ የታወቀ ነው ።
አዎ ጌታችን ማስተማር ከጀመረ ብዙ ጊዜ ነው ። ይህ ሹም አንድም ቀን ጌታን አልፈለገውም ። ዛሬም ቢሆን ለልጁ እንጂ ለራሱ እግዚአብሔርን አልፈለገም ። ብዙ ወላጆች ለልጆቻውም ጨዋነት መንፈሳዊ ሕይወትን ይመርጣሉ ። ለራሳቸው ግን አይፈልጉትም ። ክርስትናን እንደ ጠባይ ማረሚያ ማየት የቆየ ልማድ ይመስላል ። ልጆች ወላጆቻቸው ሲከተሉ ያዩትን እንጂ ወላጆቻቸው የመረጡላቸውን ብዙ ጊዜ አይከተሉም ። ልጆች ከደጅ መምህራን በቃል ይማራሉ ። ከወላጆቻቸው ደግሞ በተግባር ይማራሉ።
“ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” የሚለው ቃል እግዚአብሔርን ለመከተል ተአምራትን እንደ ቅድመ ሁኔታ የማያስቀምጡ አማንያንን ይመለከታል ። በተጨባጭ ነገር ላይ የሚመሠረት እምነት አይደለም ። እምነት ማለት የማያዩትን ከሚያዩት በላይ ማመንና በዚያም መደሰት ነው ። ተአምራት የሌለበት አገልግሎት ሙሉ አይደለም የሚል አስተሳሰብ እየተዛመተ ነው ። ተአምራት ግን የአሕዛብን ልብ ወከክ ለማድረግ እንጂ ለአማኝ አይደለም /1ቆሮ. 14፥22/። ጌታችን ያዳነን በተአምራት ሳይሆን ፍትሕና ፍቅርን ባሟላው ሞቱ ነው ። ለመዳን ተአምራት ሳይሆን ፍትሕና ቤዛነት አስፈላጊ ሁኗል ። ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ሊያተኩሩ የሚገባው መስቀሉ ላይ ነው ። ስለ ድኅነተ ነፍስ ሲያስቡ እንኳ መዳንን ከነገረ ሥጋዌና ከነገረ መስቀሉ ለይተው ማየት አይገባቸውም ። ከነገረ መስቀሉ የተለየ ነገረ ድኅነት ዋጋው ቀላል ሁኖ ይታያል ። ተአምራት የማያደርጉ አገልጋዮች ሙሉ አይደሉም የሚሉ ትምህርቶች እየተስፋፉ ይገኛሉ ። ይህ ግን መጽሐፋዊ አይደለም ። ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት ። ተአምራት ማድረግ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ከሆነ ሁሉ ተአምራት ያደርጋሉን ? ሐዋርያው ፡- “ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?” ብሏል /1ቆሮ. 12፥30/። ሐዋርያው እንደውም ሰዎች ሊያስሱት የሚገባውን በአንድ ጊዜ ጸጋና ፍሬ የሆነውን ፍቅርን መፈለግ እንዳለባቸው ሲጠቅስ እንዲህ ይላል፡- “ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ” /1ቆሮ. 12፥31/።
ዳግመኛም ከሴቶች ከተወለዱ ከዮሐንስ መጥምቅ የሚበልጥ የለም በማለት ጌታችን የተናገረለት ዮሐንስ በዘመኑ አንድ ተአምራት በእጁ አልተደረገም ። “ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፡- ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ” /ዮሐ. 10፥41/። ዮሐንስ አንድ ስንኳ ምልክት አላደረገም ፣ ዮሐንስ ግን በሕዝብና በመንግሥት የተፈራ ፣ በአይሁድ ቤተ ክህነትም ገናና ስም የነበረው ከሁሉ በላይ ጌታችን የመሰከረለት ክቡር ሰው ነው ። ስለዚህ አገልጋዮች ለመክበር ያልተሰጣችሁን አደርጋለሁ ብትሉ ውጤቱ ውርደት ነው። መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን እንዳሻው ይሰጣል እንጂ ማንም እጅ ጠምዝዞ አይወስድበትም ። ጸጋም ጸጋ እንጂ ልምምድ አይደለም ። ዛሬ በተአምራት ስም ንግድ ሲካሄድ ማታወቂያ ሲሠራ እያየን ነው ። አጋንንትም ስበኩ እየተባሉ ንግግር ሲያደርጉ ፣ የሐሰት አባት ከተባለው ሰይጣንም እውነትን ሲፈልጉ ማየት ምን ያህል እንደ ተቀጨን ማሳያ ነው ። አጋንንት ስለ እኔ እንዲህ ብሎ መስክሯል በማለት በትዕቢት የሚንጠራሩ ፣ ጉባዔ በጩኸት ካልተናጋ እግዚአብሔር አልተገኘም ብለው የሚያስቡ ሰዎችን እያፈራን ይመስላል ። በዚያ ጉባዔ እግዚአብሔር እንዳለ ምልክቱ አጋንንትን ቅጥሩን አልፎ አለመግባቱ ነው ። በዚህ የኑሮ ጭንቀት በበዛበት አገር ላይ የሚጮኸው ሁሉ በአጋንንት ነውን ? አንዱ አንተ የሐሰት አባት እያለ ሰይጣንን ስርየት የሌለው ማናዘዝ ያናዝዘዋል ። ሰይጣኑም፡- “ታዲያ እናንተን ሁሉ ወልጄ አባት መሆን አይገባኝም ወይ?” አለው ሲሉ ሰምቻለሁ። አዎ ለቃሉ የሚተኙ ለተአምራት ግን የሚነቁ እንደገና ክርስትናቸውን መመርመር ይገባቸዋል ። በዛር ውላጅ ቤት ያደጉ ሰዎች ሲሰሙ የኖሩት ይደረግልሃል የሚል ድምፅ ነውና ይህንን በቤተ ክርስቲያን ይናፍቃሉ ። የኖሩበትን ሲያጡ አባቶችን ይነቅፋሉ ። የስማቸውን ትርጉም በትክክል የማያውቁ ሰዎች አባቶችንና ቤተ ክርስቲያንን ሲነቅፉ መስማት ይገርማል ።
ጌታችን ያንን ሹም መከረው ። ሹሙ ለልጁ ያስባል ፣ ጌታ ደግሞ ለእርሱ ያስብለታል ። “ልጄ ለልጅዋ ታስብ” ይባላል ። እኔ ለልጄ አስባለሁ ማለት ነው ። ጌታ አሰበለት ። ልጁ በሥጋ ታሟል ፣ ያ ሹም ደግሞ በነፍሱ ዕረፍት ያስፈልገዋል ። ልጄን አሞብኛል ሲለው አንተስ መች ጤንነትህ ተሟላ እያለው ይመስላል ። ከሥጋ በሽታ የነፍስ በሽታ ይልቃልና ። አዎ ጌታችን መስቀል ሲመጣ የሚሸሹት ብዙ የተአምራት ወዳጆች አሉት ። ተአምራት በሌለበትም ያመኑ ብቻ እነርሱ የመስቀል ወዳጆች ናቸው ። የገበታ ወዳጅ ሞልቷል ። መከራውን የሚካፈል ግን ጠፍቷል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ