የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጌታ ሆይ፥… ውረድ

“ሹሙም፡- ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው” /ዮሐ.4፥49/ ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋ ደዌ የነፍስን ደዌ እንደሚያስቀድም በዚህ ሹም እያየን ነው ። ከባሕሩ ማዕበልም ለጥርጣሬ ማዕበል ቅድሚያ እንደሚሰጥ በደቀ መዛሙርቱ አይተናል ። በባሕሩ ላይ በማዕበል ሲጨነቁ ጌታ ግን ሰማያዊውን ሰላም ሊያስተምራቸው ተኝቶ ነበር ። በማዕበል ውስጥ በዕረፍት ያለውን ጌታ ቀሰቀሱት ። “ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፡- ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም፦ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ” /ማቴ. 8፥25-26/። ጌታችን ከማዕበሉ በፊት አለማመናቸውን ገሰጸ ። ከሥጋዊ ባርነትም ለነፍስ ባርነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ በእስራኤላውያን ተመልክተናል ። እርሱ ጭቆናን የማይወድ አምላክ ነው ። በሥጋ ሲመጣ እስራኤል በሮማውያን ቅኝ ተይዘው ነበር ። ጌታችን ከነፍስ ባርነት ነጻ ሊያወጣቸው መጣ ። ከሥጋ ባርነት ነጻ ወጥተው በነፍሳቸው ግን እስረኛ ከሆኑ ጥቅም የለውም ። እንዲሁም ይህንን የቅፍርናሆም ሹም ምልክትና ድንቅ ፈላጊ እንዳይሆን መከረው ። ከልጁ ሕመም ይልቅ የእርሱን ተአምር ፈላጊነት ብቻ ገሰጸ ። የሚቀድመው የቱ ይሆን ? የሚቀድመውን ካስቀደምን የሚከተለው ይከተላል ። ያውም በግዱ ይከተላል። የሚከተለው ከቀደመ ግን ፈረሱን እንደ ቀደመ ጋሪ መገፋፋት ይሆናል ። ጌታችን ፡- “ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል” አለ /ማር. 16፥17/። የእኛ ድርሻ ማመን ነው ። የምልክቶች ድርሻ እኛን መከተል ነው ። የሚከተለንን መከተል ጭራውን ለመንከስ እንደሚሽከረከር ውሻ መዞር ነው ። ጌታን ከመከተል ምልክት ወደ መከተል ሄደናል ። ውጤቱ ሁለቱም ማጣት ይሆናል ። ጌታንም ፣ ምልክቱንም ።
አዎ አንዳንድ ጭንቆቻችን የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ ተነሥ ያሰኙናል። ፍርድ ማጣት ፣ በሕመም መጎሳቆል ፣ ሁልጊዜ ጀማሪ መሆን ፣ የወዳጆቻችን በስቃይ ውስጥ ማለፍ ተአምራትን እንድንናፍቅ ያደርጉናል ። የተአምራት ግቡ ግን ተአምሩን ሳይሆን ተአምረኛውን ማሳየት አለበት ። ተአምራት ላይ ብቻ መቅረት ፣ በሥጋ መፍትሔ አግኝቶ ነፍስን ግን ከስሮ መቅረት ከባድ ጉዳት ነው ። ነፍስ ካልተፈወሰች የሥጋ ፈውሶች ግርሻት አላቸው ።
ጌታችን ምልክትና ድንቅ ካላያችሁ አታምኑም በማለት ሲናገር ያ ሹም መልስ አልሰጠም ። ምክንያቱም ችግሩ አደንቊሮት ፣ ከፍርሐቱ ውጭ ሌላ መስማት ተስኖት ነበር ። የጌታችንን ቃል መስማት አልቻለም ። የሚወደው ልጁ ታሞበታል ። ስለ ልጅ አደባባይ የሚቆሙ እናቶች ነበሩ ። ይህ አባት በጣም ልጁን እንደሚወደው እርግጠኛ ነን ። እናት ልጇን በጣም ስትወድ አባቶች ግዴለሽ ይሆናሉ ። አባትም ልጁን በጣም ሲወድ እናቶች ግድ የለሽ ይሆናሉ ። ሲጣሉ ደግሞ ሁለቱም ልጁን በጣም ይወዳሉ ። በሌላ አንጻርም አባት ልጆቹን የሚወደው ሚስቱን ሲወድ ብቻ ነው ። ሚስቱን ሲጠላ ልጆቹንም አብሮ ይተዋል ። ስለዚህ ይህ ሰው ሚስቱንም ልጁንም የሚወድ ነበር ።
እናቱም አባቱ አለለት ብላ ዕርፍ የምትልበት ሰው ነው ። ዛሬ ግን በቤት ውስጥ እናት የሚያጣጥረውን ልጇን ዓይን ዓይኑን ታያለች ። አባት ግን ስለ ልጁ በጌታችን ፊት ቆሟል ። እናት የልጇን ጣር ታያለች ። አባት ግን የኢየሱስን ብሩህ ፊት ያያል ። እናት የልጇን የመጨረሻ ድምፅ ትሰማለች ። አባት ደግሞ የኢየሱስን ከሞት መላሽ ድምፅ ይሰማል ። ከችግር ጋር ከመፋጠጥ ችግርን ለጌታ ማሳየት ፣ ችግርን በጌታችን ዓይኖች ማየት የተሻለ ነው ። ብዙዎች ስለሚወዱት ልጅ የሚወዱትን ጌታ አጥተዋል ። በልጃቸው ከመጣ እግዚአብሔርን አይፈልጉትም ። ልጃቸው ከእነርሱ ይልቅ የእግዚአብሔር መሆኑን ይዘነጋሉ ። አብርሃም ልጁን ለመሥዋዕት ይዞ ሄደ ሲባል እንደ ቀላል እንሰማዋለን ። አብርሃም እስከ ዛሬ ስሙ ባይሻር ድንቅ አይደለም ። የሚገባ ነው ። እንዲህ እግዚአብሔርን መውደድ የት ይገኛል ? እግዚአብሔር እንደሚወደን መስማት እንጂ እርሱን ለመውደድ ገና አናስብምና በጣም የተጎዳን ምስኪኖች ነን ። የእግዚአብሔር ፍቅር እንዳይነካው የሚጠነቀቅ እንዴት ያለ ፍጡር ነው ?
ጌታችን የዚህን ሰው ጭንቀት ተረዳው ። የምልህን አትሰማም ወይ ? ብሎት ሊቆጣው ፣ ጥሎትም ሊሄድ አልፈለገም ። በማንም ችግር ላይ ጨካኝ ፣ ተመጻዳቂ ፣ ቊጠኛ አይደለም የእኛ ጌታ ። እኛስ ? ችግሩ የሚያናግራቸውን ሰዎች ብዙ እንለፈልፍባቸዋለን ። የራባቸውን ሰዎች ዳቦ ለመስጠት እየተፈተንን ክርስቶስ ሞቶላችኋል እንላቸዋለን ። እንዴት ይመኑን ? ለዳቦ ሰስተን ሕይወቱን ሰጠ ስንል እንዴት ይቀበሉን ? በተዛባው ኑሮአችን ሰዎች ክርስቶስን ሊያዩት ተስኗቸዋል ። የቃል ሰባኪዎች ጸጋው ያላቸው ጥቂቶች ናቸው ። የሕይወት ስብከት ግን የክርስቲያኖች ሁሉ ነው ። የተለያየ ጸጋ ቢኖረንም አንድ ዓይነት ፍሬ ይጠበቅብናል ። በሰዎች ችግር መመጻደቅ ተገቢ አይደለም ። እኔ የሚሳካልኝ ልቤ ንጹሕ ስለሆነ ነው ማለት አይገባም። ራሳችንን ገና አናውቀውምና እግዚአብሔር ብቻ ስለ እኛ እንዲናገር እንፍቀድ።
 ይህ ሰው ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው ። ጌታችን በሽተኛ ፈዋሽ እንጂ ሙት አንሣ መሆኑን አያውቅም ነበር ። ቢሆንም ይህንን ያህልም ያመነው እርሱ ነው ። እርሱ ግን የአልዓዛር ጌታ ነው ። ጌታችን ባለበት ቦታ ሁኖ ቃል ቢናገር ልጁ እንደሚፈወስ አያውቅም ነበር ። ያ መቶ አለቃ ግን ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬ ይፈወሳል አለ /ማቴ. 8፥8/ ። ጌታችን ግን ሁሉንም እንደ እምነቱ መጠን ያግዘዋል ። እርሱ ለተሸከመ እኛ ሊከብደን አይገባም ።
ይህ ሹም ልጁ አንድ ጊዜ ካመለጠ እንደማይገኝ አሰበ ። ሞት ድንበር ላይ ሲደርስ አዝናለሁ ብሎ የሚመለስ ሐኪም ነው ። ጌታችን ግን የሞት መድኃኒት ነው ። ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለ ። ዛሬስ በጣር ላይ ያሉ ብላቴናዎች የሉንም ? ገና በጥዋቱ መታዘዝ እንደ እሬት የሚመራቸው ፣ ያለ ጉቦ አንዲት ዕቃ የማያነሡ ፣ ወላጆቻቸውን የሚያዋርዱ ፣ በግልጽነት ስም ያበዱ ፣ በአዋቂነት ስም የጠፉ ብላቴናዎች የሉንም ? ጌታን ውረድ የምንልበት ምክንያት ዛሬ ብዙ ነው ። ለቆዳው እንጂ ለቅንነቱ የማይጨነቅ ትውልድ ስናተርፍ ፣ ሃይማኖትን እንደ መዝናኛ ተቋም የሚቆጥር ወገን ስናፈራ ፣ በጥቁር ልብ የሚስቅ ብላቴናዎችን ስናይ ፣ ፖለቲካ ስፍራ አጥቶ በቤተሰብም ሲቀጥል ፣ ሽንገላ አድርቆ ሲያሰጣን ፣ እወድሃለሁ የሚል ቃል ላለመውደድ ሲጠቀስ ፣ እውነት እንዳይነካው ተጠንቅቆ የሚጓዝ ሲበዛ ጌታ ሆይ ውረድ መባል ያለበት ይመስላል ።
እንደ ብላቴናው የሚያምሩ ፣ ልብን የሚሰርቁ ነገሮች አሁን ግን ጣር የያዛቸው አያሌ ናቸው ። ሳይሞቱ ጌታ ሆይ ውረድ ልንለው ይገባል ። የነበረን ፍቅር እየጠፋ ፣ አንድነታችን እየላላ ሲመጣ ፣ ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በዘሩ ስንመዝነው መልካም ነገሮቻችን በርግጥም ጣር ላይ ናቸው ። የማኅበረሰቡ ውድ የነበረው ልጅ ፣ የቤት ውድ ብቻ ሲሆን ፤ ጎረቤት ለጎረቤቱ ልጅ ግዴለሽ ሲሆን ፣ ጠባብነት ሲንሰራፋ ፣ ለእኔ ፣ ለእኔ የሚል ስግብግነት ትዝብት ላይ ሲጥለን ፣ የጥዋቱ ቃል ቀትር ላይ ሲታጠፍ…አዎ ብርቅ ነገሮቻችን ሳይሞቱ ውረድ ማለት ያስፈልገናል ። በደረስንበት ዕድሜ እንኳ ብዙ እሴቶቻችንን አጥተናል ። መከባበር ፣ መፋቀር በርግጥ ነበረ ። አሁን ግን እንደ ጉም እየተነነ ፣ ድሮ ለመባል ሁሉም ነገር እየቸኮለ ነው።
ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው ። ብላቴና ለልደቱ ብዙ ሩቅ አይደለም። ሞቱ ሲቃረብ በርግጥ ያሳዝናል ። ወጣት ሁኖ ሳይንጎማለል ፣ ጎልማሳ ሁኖ ሳይጠነክር ፣ ሽማግሌ ሁኖ ሳይዋብ ሊሞት እያለ ነው ። ሠርክ በጅምር ሁኖ ሊያስለቅስ ነው ። ብዙ ነገሮች ፣ ብዙ ራእዮች ፣ ብዙ ባለ ራእዮች ፣ ብዙ ተግባራት በአገራችን በጅምር ይቀራሉ ። ብቅ ሲሉ በብረት ዘነዘና ይመታሉ ። ያለቀ ነገር ማየት እስኪያቅተን በብላቴናነት ይቀጫሉ ። የራሱን የሚሠራ ተረኛ እየጠፋ ያለፈውን የሚያጠፋ ተረኛ ግን እየበዛ ዓመታትን ሀሁ ዘመናትን ዳዴ እንላለን ። ጌታ ሆይ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ ልንል ይገባናል ። እነዚያ ጎበዝ ሰባክያን ፣ እነዚያ ባለቅኔ ገጣምያን ፣ እነዚህ ድምፃዊ ዘማርያን ፣ እነዚያ አርቀው ያዩ ባለ ራእዮች የት አሉ ? የሞቱት ሳያሳዝኑን ያሉትንም እንዳንቀጭ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ብቅ የሚል ሰው ካለ ለመቅጨት ፣ ጭንቅላቱን ለመፈጥፈጥ የስድብ ናዳ ይዘው የሚጠብቁ ፣ የአገራችን መቃብር ጠባቂዎች ፣ የሕይወት ጠላቶች ብዙ ናቸው። ሁሉን የሚተቹ የማይተች ሥራ ግን ለመሥራት ያልታደሉ አያሌ ናቸው ። አዎ ብላቴና የሆኑት ነገሮቻችን ሳይሞቱ ጌታ ሆይ ውረድ ማለት ያስፈልጋል ። የሰርግ ዕቃ ሳይመለስ ጭቅጭቅ የጀመሩ ፣ መሐላው ሳይደርቅ መካካድ የፈለጉ ፣ ያጎረሳቸው እጅ ሳይመለስ መንከስ የከጀሉ አያሌ ናቸው ። አዎ ብዙ ብላቴና አለ ። ወጣትነት የናፈቀው ፣ ጎልማሳነት ብርቅ የሆነበት ፣ ሽምግልናን የማያስብ ብላቴናነት ብዙ ነው ። በሌላው ዓለም መቶ ዓመታቶች ያስቆጠሩ ንግዶች አሉ ። የእኛ ግን ነዶ አላቂ ነው ። ታይቶ እንደሚጠፋ የርችት ብርሃን ነው ። በአንድ ጊዜ ውበት ፣ ብርሃን ፣ ከፍታ ይታያል ። ለዘላለም ጨለማ ይወርሰዋል ።
እባክህ ጌታ ሆይ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ ። መውደድን ሳላጋምስ ጥላቻ ሲጀምረኝ ፣ ራእዬን ገና አጥርቼ ሳላይ አጉል መርካት ሲጀምረኝ ፣ መንገዴን ለመዝለቅ እሾህ ጋሬጣ ሲገጥመኝ ነገሮቼ በብላቴናነት እንዳይሞቱ ውረድ ፣ ውረድ ። ባደከመኝ ነገር ላይ ፍረድ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ