የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በዓላት

“ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ”
/ዮሐ. 5፡1/፡፡
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጣ ይነግረናል ፡፡ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ቁጥር አምባጓሮዎች ይነሣሉ ፡፡ ኢየሩሳሌም የሃይማኖት መዲና ናትና ፀሐፍት ፈሪሳውያን ፣ ካህናትና ሊቃነ ካህናት ከእነርሱ ውጭ ማንም እንዲረግጣትና እንዲያዝባት ፈቃደኛ አልነበሩም ፡፡ በሰማርያ ስለነበረው ውድቀት ፣ በገሊላ ስለነበረው ግዴለሽነት አይጨንቃቸውም ነበር ፡፡ ግዛታቸውን በኢየሩሳሌም ልክ አጥብበው ድንበሩን የተጠጋውን ለሞት ይፈልጉታል ፡፡ የሮማ መንግሥት የሞት ፍርድን ስለነጠቃቸው እንጂ ጌታችንን አስቀድመው ከመግደል አይመለሱም ነበር ፡፡ ሰዎችን ከመቀደስ ቦታን ቀድሰው መኖር ብቻ ይመርጡ ነበር ፡፡ ሰው ቦታን ፣ ቦታ ሰውን እንደሚቀድስ ዘንግተው በአንዱ ክንፍ ብቻ ለመብረር ይፈልጉ ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ግን ስለ ሰማርያም ስለ ገሊላም ግድ ይለው ነበር ፡፡ ከዚያም አልፎ ስለ መላው ዓለም ግድ ይለው ስለ ነበር አንድ ልጁን ቤዛ መድኃኒት ይሆን ዘንድ ላከው ፡፡ የኢየሩሳሌምን በሮች ቆልፈው ለመኖር ያቅዱ የነበሩ እነዚህ የካህናት ዘሮች ጌታችን ኢየሩሳሌምን አድራሻ አድርሆ ሲመጣ ሁለት ጊዜ ተቃወሙት ፡፡ እርሱ ቤተ መቅደሱን በባለቤትነት በማጽዳቱ እኛ እያለን እርሱ ምን አገባው በማለት ተቀየሙ ፡፤ እነርሱ የቤቱ አገልጋዮች ሳሉ እርሱ ግን የቤቱ ባለቤትና ልጅ መሆኑን ዘነጉ ፡፡ በሽተኞችን በመፈወሱም ደስተኛ አልነበሩም ፡፡ የሌሎች በሽታ ለእነርሱ የገቢ ምንጭ ነውና ፡፡ ዳግመኛም ሁሉም የድንጋይ ብርድ ልብስ ለብሰው በመተኛታቸው ለምን ከእንቅልፋችን ቀሰቀስከን የሚል ንዴት ውስጥ ገቡ ፡፡ አውቆ የተኛ የሚቀሰቅሰው ጠላቱ ነውና ፡፡ ደክሟቸው የተኙ ሲቀሰቀሱ ይነቃሉ ፡፡ አውቆ የተኛ ግን አይነቃም ፡፡

በምዕራፍ ሁለት ላይ ቤተ መቅደሱን እንዳጸዳ አይተናል ፡፡ ይህ በኢየሩሳሌም የተከናወነ ነው ፡፡ አሁንም በዚህ ምዕራፍ በኢየሩሳሌም ስለተከናወነ ታላቅ ፈውስ ይነግረናል ፡፡ ፈውሱ ግን ብዙ ጠላቶችን የቀሰቀሰ ነው ፡፡ ጌታችን በዚህ ፈዋሽነቱ ከራሱ ከተፈወሰው ሰው እንኳ ምንም ዓይነት ምስጋና ሲቀበል አናገኝም ፡፡ ምስጋና ሲቆም የእግዚአብሔር ሥራ ቢቆም ኑሮ ዛሬ ፀሐይ ወደ ዓለም አትመጣም ነበር ፡፡ ጌታችን ዝምታን ሳይሆን ብዙ ነቀፋዎችን አስተናግዷል ፡፡ ሰው ማመስገን ካልቻለ ምናለ  ባይራገም ! መስጠት ካልቻለ ምናለ ባይሳደብ ! እውነቱን መናገር ካልቻለ ምናለ ውሸት ባይናገር ! ዓለም እውነትን በሹክሹክታ ትናገራለች ፡፡ ተቃውሞዋን ግን በአደባባይ ታሰማለች ፡፡ ፈውስን በልብ ታደንቃለች ፡፡ ስድብን ግን በአዋጅ ትዘራለች ፡፡ ጌታችን እጆቹ ለፈውስ ሲዘረጉ ፈውስን በማይፈልጉ ትምክሕተኞች መከራ መጣበት ፡፡ የሥጋ ፈውሶች ፈቃድን ሊጠይቁም ላይጠይቁም ይችላሉ ፡፡ ደግሞም እምነትን ሊጠይቁም ላይጠይቁም ይችላሉ ፡፡ የልብ ፈውስ ግን ፈቃደኝነትን ይጠይቃል ፡፡ የልብ ፈውስ በቃለ እግዚአብሔር ሲሆን የሥጋ ፈውስ ግን በተአምራት ይከናወናል ፡፡ የልብ ጥመት በተአምራት አይላቀቅም ፡፡ ወርቅ አበድሮ ጠጠር ፣ እህል አበድሮ አፈር የተመለሰለት እንደ ጌታችን ማን አለ !
“በቅሎ አትወልድም ፣ የሚወልድም አትወድም” እንዲሉ የማያገለግሉ የሚያገለግልም የማይወዱ አያሌ ናቸው ፡፡ ጌታችን ካህናትና ሊቃነ ካህናት የዘነጉትን  አገልግሎት እርሱ እየሠራ ፣ ያዝረከረኩትን እየሰበሰበ ቢሆንም እነርሱ ግን ደስተኛ አልነበሩም ፡፡ ያ ሕዝብ በሥጋ በነፍስ ወድቆ ነበር ፡፡ እነርሱ ግን ገና ሬሳን ለመግዛት ፈልገው ነበር ፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ፈርዖን የሚለውን ሲተረጉም ፡- “ፈርዖን ግፈኛ ፤ ግፍ ሠሪ፤ ሙት አስገባሪ ማለት ነው ፡፡ ላንድ ሰው መቃብር 2 መቶ ብር ይቀበል ነበር” ይላል ፡፡ /ገጽ. 733/፡፡ እነዚህ ፀሐፍት ፈሪሳውያንም ሙት አስገባሪ ነበሩ ፡፡ የተጨነቀን ሕዝብ ማስጨነቅ ፣ ድሆችን መበዝበዝ ፣ መጽናናት ለሚሹ የፍርድን ሰይፍ መምዘዝ ሙት ማስገበር ነው ፡፡ ፈርዖን ሙት አስገባሪ የተባለው ለሬሳ መቃብር 200 ብር ያስከፍል ስለነበረ ነው ፡፡ ዛሬ ለሬሳ በብዙ ሺህ ብሮች የሚያስከፍሉ ከፈርዖን ብሰው ይሆን ! ይህች ዓለም ከቆመውም ከሞተውም ጋር ትጣላለች ፡፡ ከድሀው ጉቦ የሚቀበሉ ዳኞች ፣ ከምስኪኑ በሽተኛ ገንዘብ የሚበዘብዙ ሐኪሞች ፣ ፍትሕ ካጣው ወገን የሚቦጠቡጡ ጠበቆች ሙት አስገባሪ አልሆንም ብንል እየዋሸን ነው ፡፡ ምንድነው ሬሳን መደብደብ ጀግና አያሰኝም ፡፡ በራብ ፣ በመከራ የወደቀን ወገን መርገጥ ትልቅነት አይደለም ፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ብዙ ምጽአቶች አድርጓል ፡፡ ዮሐንስ ወንጌላዊ ግን ሁለቱን እስካሁን ያሳየናል ፡፡ እነዚህ ሁለት ምጽአቶች የጌታችንን ሞት ያፋጥናሉ ፡፡ የእርሱ ቅዱስ ቀናዒነትና ፍቅር እነርሱን የበለጠ ነፍሰ ገዳይ እያደረጋቸው ይመጣል ፡፡ ፍቅር የተዘጋ ልብን ያንኳኳል እንጂ ሰብሮ አይገባም ፡፡ ፍቅር ፈቃድ ይፈልጋል ፡፡ ከጌታችን ፍቅር የበለጠ ኃያል የለም ፡፡ ፀሐፍት ፈሪሳውያን ግን ተቋቁመውታል ፡፡ የእኛን እፍኝ ፍቅር ሰዎች ቢገፉ ያን ያህል አይገርምም ፡፡ ፍቅር የታዳጊነት ሥራውን የሚሠራው ከሁለት ወገን ሲሆን ነው ፡፡ “የአንድ አሳቢ የአንድ በሬ ሳቢ” እንዲሉ የአንድ ወገን ፍቅር አይጠቅምም ፡፡ ምዕራፍ ሁለትንና ምዕራፍ አምስትን የሚያገናኛቸው ነገር አለ ፡፡ ጌታችን በምዕራፍ ሁለት በቤተ መቅደሱ ይሸጡ የነበሩትን በጎችና ከብቶች አስወጣ ፡፡ ምዕራፍ አምስት የሚጀምረው ወደ ቤተ መቅደሱ የሚቀርቡት በጎች ስለሚገቡበት በር በማንሣት ነው ፡፡ በምዕራፍ ሁለት ላይ ጌታችን በቤተ መቅደሱ ተገኝቷል ፡፡ በሽተኞችን ፈውሷል ፡፡ በምዕራፍ አምስት ላይም ፈውስን አድርጎ በቤተ መቅደስ ተገኝቷል ፡፡ መቅደሱና ፈውሱ አይለያዩም ነበር ፡፡ በመቅደሱ ፈውስ አለ ፡፡ በደጅ ፈውስ ካገኙም በመቅደሱ የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብ አለ፡፡ ምክንያቱም “የአምላኬ የንጉሥ መንገድ በመቅደሱ”ነውና /መዝ. 67፡24/፡፡
በብሉይ ኪዳን ብዙ በዓላት ነበሩ ፡፡ የበዓላት ዓላማ እግዚአብሔርን ለማክበር ፣ ደግሞም ለመደሰት ነው ፡፡ አይሁዳውያን የትኛውም የቦታ ርቀት ላይ ቢሆኑ በኢየሩሳሌም ተገኝተው ሊያከብሯው የሚገቡ ሦስት በዓላት አሉ፡፡ እነርሱም፡- በዓለ ፋሲካ ፣ በዓለ ሰዊት /የእሸት በዓል/ ፣ በዓለ መጸለት /የዳስ በዓል/ ናቸው ፡፡ በዓለ ፋሲካ በሚያዝያ ወር ላይ ሲሆን ፋሲካ በዋለ በሃምሳኛው ቀን በዓለ ሰዊት ይውላል ፡፡ የዳስ በዓል በጥቅምት ወር የሚውል ነው ፡፡ የበዓላት ዓላማ የእግዚአብሔርን ውለታ ለማስታወስ ፣ ለትውልድ ለማስተማርና በእግዚአብሔር ለመደሰት ነው ፡፡ የእልልታ ድምፅ የሚሰማው በበዓላት ላይ ነው ፡፡ እልል የሚለው ይደሰታል ፡፡ የሚሰማው ምንድነው ይላል ፡፡ የእግዚአብሔርን ውለታ ለመመስከር ጥያቄ የሚፈጥር ነገር ቢኖር በዓል ነው ፡፡ ጌታችን በዓል ነበርና ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ ፡፡ ድሮም ዛሬም በዓልን ኢየሩሳሌም ማክበር ድምቀት አለው ፡፡
በአገራችንም የቀናትና የወራት ስያሜ ምስጋናንና የሥራ ፕሮግራምን የሚያሳይ ነው ፡፡ ለምሳሌ ያህል የወራቱን ስያሜ እንኳ ብናስታውስ ፡-
1.  መስከረም ማለት መክረሚያ
2.  ጥቅምት ማለት መጠቀሚያ “በጥቅምት አንድ አጥንት” እንዲሉ
3.  ኅዳር ማለት ማደሪያ
4.  ታኅሣሥ ማለት መሰብሰቢያ
5.  ጥር ማለት ጠራራማ
6.  የካቲት ማለት መክተቻ
7.  መጋቢት ማለት መመገቢያ
8.  ሚያዝያ ማለት መጀመሪያ  /የአቢብ ወር ለእስራኤል መጀመሪያ ነው ፡፡ የአቢብ ወር የሚውለው በሚያዝያ ነውና/
9.  ግንቦት ማለት መገንቢያ
10.          ሰኔ ማለት ውኃማ
11.          ሐምሌ ማለት መለምለሚያ
12.          ነሐሴ ማለት መገንቢያ ማለት ነው ፡፡
እነዚህ ስያሜዎች መልካም ምኞትን ይዘዋል ፡፡ መስከረም ማለት መክረሚያ ማለት ነውና ፡፡ የግንባታ ጊዜዎችን ይገልጻሉ ፡፡ ጥቅምት ፣ ግንቦትና ነሐሴ የግንባታ ወቅት እንደሆኑ ያሳያሉ ፡፡ እስራኤል ከግብፅ ባርነት የወጡበትን የመጀመሪያውን ወር አቢብን ያስታውሳል ፡፡ እርሱም ሚያዝያ ነው ፡፡ የአዝመራውን መሰብሰቢያ ፣ ወደ ጎተራ መክተቻውን ያወሳል ፡፡ እርሱም ከታኅሣሥ እስከ የካቲት ነው ፡፡
በዓላት መገናኛ ናቸው ፡፡ የአንድነት መቀነት ናቸው ፡፡ ድሆች ይታሰቡባቸዋል ፡፡ ሃይማኖት በአደባባይ በነጻነት ይሰበካል ፡፡ ይልቁንም በአገራችን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ነጻትን የሚያውጁ ናቸው ፡፡ ነጻነት ያለው ሕዝብ በእግዚአብሔርም የሚኮራ ወገን ብቻ እንዲህ እየዘመረ በአደባባይ ይታያል ፡፡ የአፍሪካ የነጻነት እንቅስቃሴም የተወለደው በእነዚህ በዓላት ላይ ነው ፡፡ ቅኝ ገዥዎች በዓሉን ለማየት የሚገዙአቸውን አፍሪካውያን ይዘው ሲመጡ አፍሪካውያን ገዥዎቻቸውን ካስተኙ በኋላ እኛም እንደ ኢትዮጵያውያን በነጻነት የምንኖረው ፣ ሃይማኖታችንን በድፍረት የምንገልጠው እንዴት ነው ይሉ ነበር ፡፡ በዓላት የነጻነት ንቅናቄ ናቸው ፡፡ ነጻነት ያለው ሕዝብ ብቻ ይህን ያደርጋል ፡፡ ሃይማኖት ማስታወሻ ያስፈልገዋል ፡፡ አሊያ የመዘንጋት አደጋ ይገጥመዋል ፡፡

ያጋሩ