የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የበጎች በር

“በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት” /ዮሐ. 5፡2/፡፡
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል እንደ ወጣ በመናገር ክፍሉ ይጀምራል፡፡ በዓሉ ምን እንደሆነ ግን አይገልጽም ፡፡ የፋሲካ በዓል እንደሆነ የሚያስቡ መምህራን አሉ ፡፡ በርግጥ የፋሲካ በዓል ከሆነ ጌታችን አራት ፋሲካዎችን እንዳከበረ ወንጌላዊው በሙሉነት ዘግቦልናል ማለት ነው ፡፡ ይህ የጌታችንን ሦስት ዓመት ከሦስት ወር አገልግሎት ይገልጣል ማለት ነው ፡፡ ፋሲካ ግን ልዩ ዝግጅት ያለውና ለቀናትም የሚቆይ በመሆኑ ምንም ዓይነት ፍንጭ ወንጌላዊው አልሰጠም ፡፡ ሌሎቹን ሦስት ፋሲካዎች ሲጠቅስ ይህንን አይዘለውም ነበር ፡፡ በዚህ ክፍል ላይም የነበረው ክርክር ስለ ሰንበት ዕረፍት እንጂ ስለ ፋሲካ አይደለምና በዓሉ መለስተኛ በዓል እንደነበር እንረዳለን ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበጎች በር አጠገብ በኩል እንደመጣና ወደ መጠመቂያዋም እንደ ገባ ይነግረናል ፡፡
 ወንጌላዊው ጌታችን በበጎች በር እንደ ገባ አይገልጽም ፡፡ ነገር ግን ለመጠመቂያዋ ቅርብ በነበረው በር አጠገብ ስለገባ ይመስላል ወንጌላዊው የበጎችን በር ያነሣው ፡፡ ጌታችን በበጎች በር ከገባ ያልተለመደ ነው ፡፡ የኢየሩሳሌም በሮች ብዙ ናቸው ፡፡ የበሮቹ ዓላማ የከተማውን ክብር ለመጠበቅ ወይም ከጠላት ለመከላከል ፣ ግብር ለማስከፈልና በደጅ የሚያመሹትን ለመከልከል ወይም ሥነ ምግባርን ለመጠበቅ ነው ፡፡ በሮቹ ጥዋት ይከፈታሉ ፡፡ ማታ ይዘጋሉ ፡፡ በተለያዩ በሮች ላይ የተለያዩ ተግባራት ይፈጸማሉ ፡፡ ሽማግሌዎች ችሎት የሚያስችሉበት በር አለ /ሩት. 4፡11/ ፡፡ የቆሻሻ መጣያ በር አለ /ነህ. 2፡13/፡፡ በቤተ መቅደሱ የሚሠዉ በጎች የሚያልፉበት በር አለ /ዮሐ. 5፡2/ ፡፡ ይህ ሥርዓት መጋፋትን ያርቃል ፡፡ የሰውና የእንስሳት በሮችን ይለያል ፡፡ በዚህም አደጋን ይቀንሳል ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ የሚሠዉት በጎች በሚገቡበት በር ገባ ፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ያስታውሰናል ፡፡
1-  የእግዚአብሔር በግ ነውና በሚያርዱት በሰዎች በር ሳይሆን በሚታረዱት በበጎች በር ገባ ፡፡
2-  አንድ ቀን እነዚህን በጎች እንደሚያሳርፋቸው እያሰበ አንዱ በግ በበጎች በር ገባ ፡፡
3-  እውነተኛው የበጎች በር የሆነው ክርስቶስ በበጎች በር ገባ ፡፡
 በበጎች በር መግባት መልካም ነው ፡፡ መስቀል አሸካሚ ሳይሆን ተሸካሚ መሆን የክርስትናው ጥሪ ነው ፡፡ ሌሎችን በስድብ ፣ በስም ማጥፋት ፣ በሐሰት ምስክርነት ፣ በቅንዓት በምቀኝነት ማረድ ሳይሆን አስፈላጊ ከሆነ ስለ ፍቅር መታረድ አስፈላጊ ነው ፡፡ በሰው በር ሳይሆን በበጎች በር መግባት መልካም ነው፡፡ ተፈጥሮአችን የሰዎች ቢሆንም ጠባያችን ግን የበጎች ሊሆን ይገባዋል፡፡ በግ ከሆንን ክርስቶስ በር ይሆነናል /ዮሐ. 10፡7/ ፡፡ በር ያገኘ መግባት መሰማራት ይችላል ፡፡ ደግሞም እረኛችን ይሆናል ፡፡ አዎ ጌታችን የአራጆች ደጋፊ አይደለም ፡፡ እርሱ ሁልጊዜ ያለው ከተገፉትና ከተጠቁት ጋር ነው ፡፡
 ጌታችን አንድ ቀን እንደሚያሳርፋቸው እያወቀ በበጎች በር መግባቱ ደግመን ልናስበው ይገባል ፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ በጎች በዚያ በር ገብተዋል ፡፡ ሺህዎች ያልቻሉትን ግን አንዱ በግ ክርስቶስ ፈጽሞታል ፡፡ እነዚያ ሁሉ የሰው በጎች ነበሩና ዋጋ ሊከፍሉ ፣ ግዳጅ ሊፈጽሙ አልቻሉም ፡፡ የእግዚአብሔር በግ ጌታችን ግን ዋጋ ሊከፍል ግዳጅ ሊፈጽም ተችሎታል ፡፡ እነዚያ በጎች ለራሳቸው ኃጢአት ሳይሆን ለሌሎች ኃጢአት በዚያ በር ይገቡ ነበር ፡፡ መሥዋዕት የማያስፈልገው መሥዋዕታችን ክርስቶስም በዚያ በር ገባ ፡፡ ዛሬ መሥዋዕትነት የሚከፍሉልንን ወላጆች ፣ ወዳጆች እንዲሁም አገልጋዮች አንድ ቀን እንደምናሳርፋቸው እያሰብን ይሆን ? እነዚያ በጎች በዚያ በር የሚገቡት ለመሥዋዕትነት ነበር ፡፡ በለምለም መስክ ለመሰማራት ፣ ለመጥገብና ተዘልለው ለመቀመጥ አልነበረም ፡፡ በየዋህነት ግን ይገቡ ነበር ፡፡ ጌታችንም በበጎች በር መግባቱ መሥዋዕታችን መሆኑን ለመግለጥ እንጂ ለምቾት አልነበረም ፡፡ የዋህነት አውቆ የመሥዋዕትነት ሕይወት መኖርና በዚያም መደሰት ነው ፡፡ ከእርሱ በፊት በእርሱ ስም የመጡ አያሌ ነበሩ ፡፡ የገቡት ግን በሰዎች በር ነው /የሐዋ. 5፡36/ ፡፡ ዓላማቸው መስቀል ሳይሆን ንጉሣዊ ሕለተ ወርቅ ነበር ፡፡ የእሾህ አክሊል ሳይሆን ዘውድ ነበር ፡፡ በጉ ክርስቶስ በበጎች በር ገባ ፡፡ ከዳንኤል መጽሐፍ እስከ ዮሐንስ ራእይ የምድር ነገሥታት በአራዊት ተመስለዋል ፡፡ ጨካኞችና በደም ምንጣፍ ላይ የሚደላደሉ ስለሆኑ ነው ፡፡ ንጉሥ ሁኖ በግ የተባለው ግን የእኛ ጌታ ክርስቶስ ነው ፡፡
 ክርስቶስ በግ ተብሎ በጎች አሰኝቶናል ፡፡ በር ተብሎም የበጎች በር ነኝ ብሏል ፡፡ በመጨረሻውም ቀን በጎችንና ፍየሎችን ሊለይ ይመጣል ፡፡ በግ የተባልነው በምን ምክንያት ነው ?
1-  በየዕለቱ መስቀሉን ስለምንሸከም ነው ፡፡ “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው” /ሮሜ. 8፡37/፡፡
2-  ክርስቶስ እረኛችን ስለሆነ ነው ፡፡ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል” /ዮሐ. 10፡11/፡፡ እርሱ የሚመራው ገራሞችን እንጂ ብልጦችን አይደለም ፡፡ እርሱ የበጎች እንጂ የተኩላዎች እረኛ አይደለም ፡፡ የዛሬው ዘመን ክርስትና ብልጠት እንዳይሆን ፣ ፋሽን እንዳይሆን ማሰብ ያስፈልጋል ፡፡ የክርስቲያን ማኅበር እየጠፋ የጦጣ ማኅበር እንዳይስፋፋ ያሰጋል፡፡ ሰውዬው እንዳሉት ይመስላል ይህ ዘመን ፡-
የጅብ በሬ
የአንበሳ ገበሬ
የእባብ ቀንበር
የዘንዶ ሞፈር
የዝንጀሮ ጎልጓይ
የጦጣ ዘር አቀባይ
ሁሉም እንብላ ባይ
አንድ እንኳ የለ ገላጋይ
መገን ኑሮ መገን ኑሮ
ከጦጣ ጋር ከዝንጀሮ
አዎ በጉ በበጎች በር ገባ ፡፡ ይህንን በር ሰዎች ፣ ተመጻዳቂዎች አይወዱትም፡፡ መገፋፋት አለበት ፣ መቆሸሽና መጉዳት ይበዛበታል ፡፡ ሰብአዊ ክብርን የሚሹ የክርስቶስ ሊሆኑ አይችሉም ፡፡ መገፋትን የማይወዱ ወደ መንግሥቱ አይጠጉም ፡፡ መቆሸሽን ማለት መሰደብን የሚፈሩ ምስክሮች ሊሆኑ ያቅታቸዋል ፡፡ መጉዳትን የሚሸሹ ምሉዕ ሕይወትን መኖር አይችሉም፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ