የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ያዳነንን እናውቅ ይሆን ?

“እርሱ ግን፦ ያዳነኝ ያ ሰው፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው” /ዮሐ. 5፡11/፡፡
በዚህ ሰው ሕይወት ውስጥ ሁለት ነገሮች ተከናውነዋል ፡፡ የመጀመሪያው መዳኑ ሲሆን ሁለተኛው አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ ኃይል ማግኘቱ ነው ፡፡ መዳኑን ሙሉና መለኮታዊ ፈውስ ያደረገው የተሸከመውን ለመሸከም መብቃቱ ነው ፡፡ ያገለገሉንን ማገልገል ፣ በጎ ያደረጉልንን ውለታቸውን ማሰብ ፣ ሳይከብዳቸው ጭንቀታችንን የሰሙትን በጭንቃቸው ሰዓት መገኘት ይህ መዳንን ሙሉ ያደርጋል ፡፡ ይህ ሰው ሁሉ ሲሸሸው አልጋው ግን ተሸክሞት ነበር ፡፡ አልጋውን ደግሞ የተሸከመች ምድር ነበረች ፡፡ የቻለውን አልጋ የቻለችው ምድር የእግዚአብሔር ምሳሌ ናት ፡፡ ሰዎች እግዚአብሔር ስለረዳቸው ጠባያችንን ፣ ሕመማችንን ፣ ችግራችንን ተሸክመዋል ፡፡ የተሸከሙንን የተሸከመ እርሱ ነው ፡፡ ጠባያችን ስለማይከብዳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ማመስገን አለብን ፡፡ እውነትን ለእኛ ለማሳወቅ ከእምቢታችን ጋር የታገሉትን ዋጋ ልንሰጣቸው ይገባል ፡፡ ለእኛ የከበደንን ጭንቀት ሳይከብዳቸው የሰሙትን እናንተስ እንዴት ናችሁ ማለት ይገባል ፡፡ አንገት የተፈጠረው ዞሮ ለማየትም ነው ይባላል ፡፡ የተሸከሙንን የተሸከመ እግዚአብሔር ለእኛም ሸክም ይሰጠናል ፡፡ እርሱም የሌሎችን ውለታ እንድንመልስ ነው ፡፡ ሸክምን አስጥሎ ሸክም እንደሚሰጥ ተናግሯል፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” /ማቴ. 11፡28-30/፡፡
ጌታችን የሚሰጠው ፈውስ  ከበሽታ ከመዳን በላይ ነው ፡፡ በተአምራት ወይን ጠጅ የሆነው የቃናው ውኃ ከማለቁ በፊት ከነበረው ወይን የበለጠ ነው፡፡ የጌታችን የሥልጣን ቃል እነዚህን ሁለት ነገሮች አከናውኗል፡፡ መዳንና መበርታት ፡፡ አልጋን መሸከም ጤነኛ እንኳ ላያደርገው ይችላል ፡፡ ጌታችን ይህን ሰው ወደ ጤንነት ሳይሆን የመለሰው ከጤንነት በላይ ወደሆነ ብርታት ነው ፡፡ በይቅርታው ውስጥም የምናየው ይህን ነው ፡፡ “ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች” ይላል /ኢሳ. 1፡18/፡፡ እንደ አለላ የሆነ ኃጢአት እንደ አመዳይ ሊነጻ የቻለው እንዴት ነው ? አለላ ቀለም የተነከረ በጣም ደማቅ ነገር ነው ፡፡ አለላ ከመሆኑ በፊት ወደ ነበረው መልኩ ቢመለስ ግራጫ ነው ፡፡ አሁን ግን እንደ አመዳይ ይነጻል ይላል ፡፡ አመዳይ በብርድ አገር ላይ ጥዋት ላይ የሚታይ ጤዛ ነው ፡፡ ይህ ጤዛ ነጭና ጠል ያረገዘ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ይቅርታ ከመበደላችን በፊት እንዳለው ሳይሆን ከዚያም በላይ ወደ ሆነው ጥራት ያደርሳል ፡፡ እግዚአብሔር ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ያከብራል ፡፡ አለላ እውነተኛ መልኩ ሳይሆን ሰው ሠራሽ ቀለም ነው፡፡ ኃጢአታችን አለላ መባሉ ኃጢአት የባሕርያችን እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ኃጢአት የምርጫ ውጤት እንጂ የተፈጥሮ አይደለም ፡፡ ቀጥሎ ኃጢአት ጉልበት የለሽ መሆኑን ሁሉንም ኃጢአት የሚሸፍን የእግዚአብሔር ምሕረት መሆኑን ይገልጣል ፡፡  “እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች” ይላል፡፡ እንዲሁም በአዳም ከመጣው በደል በክርስቶስ የሆነልን ጽድቅ የተትረፈረፈ ነው ፡፡ ከበደልነው በላይ የሚክሰን ይህ አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው ! ይህን መውደዱን በአደባባይ ፣ ደግሞም በበር አሊያም በመስኮት አይደለም ፡፡ ምነው በቀዳዳ ባየነው ! ምነው በውልብታ ባየነው !
አልጋን የሚያሸክም አምላክ ድንቅ ነው ፡፡ ለምስኪኑ ሞገስ የሚሰጥ ፣ ራብተኛን የሚያጠግብ ፣ መካኒቱን ደስ የተሰኘች የልጆች እናት የሚያደርግ ፣ ስደተኞችን ባለ አገር የሚያደርግ ፣ ችግረኛውን ከመሬት የሚያነሣ ፣ እረኛውን ንጉሥ የሚያደርግ ፣ ትንሽ የተመኘውን በብዙ የሚባርክ አምላክ በእውነት ድንቅ ነው ፡፡
“እነርሱም፦ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት።” በዚህ ሰው መዳን ልባቸው አልተነካም ፡፡ ምንም እንኳን ምልክት ናፋቂዎች ቢሆኑም እውነተኛውን ምልክት ግን አያምኑም ነበር ፡፡ ከእርሱ አልፈው ያዳነውን ለመግደል ማሰብ ጀመሩ ፡፡ ሔዋን እባብ በሰው ቋንቋ ሲያናግራት አልደነገጠችም ፡፡ ውይይቷን ቀጠለች ፡፡ በለዓም አህያ አፍ አውጥታ ስታናግረው መመለስ ጀመረ እንጂ አልተገረመም ፡፡ እነዚህ ሰዎችም የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ አልጋ ተሸክሞ ሲሄድ አልተገረሙም ፡፡ በምስጋናው ባይካፈሉ እንኳ ዝም አላሉም ፡፡ ከዚያ አልፈው ያዳነውን ለመግደል ፈለጉ ፡፡
“ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም።”  ጌታችን ተአምራትን ካደረገ በኋላ ፈቀቅ ይል ነበር ፡፡ ሰዎች ተአምራቱ ካመጣባቸው መገረም የተነሣ የስሜት አምልኮ እንዲሰጡት አይወድም ነበር ፡፡ እርሱ ፈውስን የሚያደርገው በሽተኛውን ለማሳረፍ እንጂ ጤነኞችን ለማስገረም አልነበረም ፡፡ የእርሱ ፈውስ ርኅራኄ እንጂ ማስታወቂያ አይደለም ፡፡ ጌታችን ሰዎች በቃሉ ላይ ብቻ እንዲመሠረቱ ተአምራት አድርጎ ፈቀቅ ይላል ፡፡ አሊያ ለማንም እንዳይናገሩ ያዝዛል ፡፡ ጌታችን ተአምራትን ያደረገው በራሱ ኃይልና ሥልጣን ነው ፡፡ በሥልጣኑ ተአምራት ያደረገው እርሱ ፈቀቅ አለ ተብሎ ተጽፎ ሳለ በእርሱ ስም ተአምራት እናደርጋለን የሚሉ ግን ድርቅ ብለው ቆመዋል ፡፡ ተናገሩልን እያሉ በሽተኞችን ያስጨንቃሉ ፡፡ ቪድዮ እያሰራጩ ደንበኛ ያሰባስባሉ ፡፡ በሰዎች መዳን ተደስተው ሳይሆን ብዙ ሕዝብ ለመሰብሰብ እዩልን ስሙልን ይላሉ ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተአምራት ለግለሰቦች ተሰጥቶ እገሌ ተብሎ ተነግሮ አያውቅም ፡፡ በየጠበሉ የሚድኑ ሕመምተኞች አንድም ቀን የሰው ስም ሲያነሡ አይታዩም ፡፡ የፈውሱን ባለቤት ብቻ ያመሰግናሉ ፡፡ የእገሌ ጠበል እንጂ እገሌ ተብሎ የሰው ስም አይጠራም ፡፡ ተአምራት አንዱ የቤተ ክርስቲያን ሀብት እንጂ የግለሰቦች አይደለም ፡፡ ተአምራት እናደርጋለን እያሉ የሚያውጁ ተአምራቱ ከገረማቸው እግዚአብሔር እንደሚያደርግ ተጠራጥረው ነበር ማለት ነው ፡፡ የእጁን ሥራ ለማየት ቀና ብሎ ሰማይን ማየት ይበቃል ፡፡
የተፈወሰው ሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አላወቀውም ፡፡ ጌታ ግን ያውቀዋል ፡፡ የፈውሱ መሠረት በሽተኛው ጌታን ማወቁ አይደለም ፡፡ ጌታ በሽተኛውን ማወቁ ነው ፡፡ ከሰው እምነት በላይ የእግዚአብሔር ታማኝነት ፣ ከሰው እውቀት የእግዚአብሔር ማስተዋል ፣ ከሰው አገልግሎት የእግዚአብሔር በረከት ባይበዛ ኖሮ አማኒ ነኝ ለማለት አንበቃም ነበር ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ቆመን ክፋት የምናስብ ፣ እርስ በርስ የምንፋጅ ፣ እየተጠላለፍን የምንወድቅ ነን ፡፡ እግዚአብሔርን ገና አላወቅነውም ፡፡ እርሱ ግን አውቆ አልካደንም ፡፡
ያ ሰው ፈውሱን ያውቃል ፣ የፈወሰውን ግን አያውቅም ፡፡ ከግርግሩ ውስጥ ያዳነውን ማወቅና መለየት አልቻለም ፡፡ ብዙ ግርግሮች ያዳነንን እንዳናውቅ ያደርጉናል ፡፡ ግርግር አንዱ ጭንቀት ነው ፡፡ ግርግር በብዙ ሕዝብ መካከል መሆን ብቻ አይደለም ፡፡ በብዙ አሳብ ውስጥ መዋተትም ግርግር ነው ፡፡ ራሳችንን ከመጠን በላይ ማየት ግርግር ነው ፡፡ ከሳሁ ጠቆርኩ እያልን ለራሳችን ማልቀስ የመስቀሉን ዋጋ እንድንረሳ ያደርገናል ፡፡ ግርግር ዘመን ባመጣቸው መገናኛዎችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች መጠመድ ነው ፡፡ ከልባችን የሰዎችን ነውር የምናነብበትን ከልባችን የጌታን ቃል ለመስማት ግን አልቻልንም ፡፡ ከልባችን የምንከራከርበትን ከልባችን ፍቅራችንን መግለጥ አልቻልንም ፡፡ ግርግር በወዳጆች ተከብቦ ጌታን መርሳት ብቻ አይደለም ፡፡ በጠላቶች አሳብ ተይዞም የጌታን ኃይል መርሳትም ነው ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብናስብ ጠላቶቻችን ያንሱብን ነበር ፡፡ ግርግር ገበያ መካከል መገኘት ብቻ አይደለም ፡፡ ግርግር በብዙ እቅዶች መያዝና ሁልጊዜ እቅድ አውጪ መሆንንም ነው ፡፡ ግርግር በሰርግ ቤት መገኘት ብቻ አይደለም ፡፡ ጀምረን የምንተዋቸው ብዙ መጻሕፍትን ዘርግቶ ማስቀመጥም ነው ፡፡ ግርግር አንዱን ሳይጨርሱ ሌላ ሥራ መጀመርም ነው ፡፡ ትጋት የሚመስለው መክነፍ እርሱ ግርግር ነው ፡፡ ያዳነንን እንዳናይ ያደረገን ምን ይሆን ?
የበሽታውን ዘመን የሚያውቀው ፣ ከበሽታው ፍጹም ተፈውሶ መበርታቱን የሚገነዘበው ያ ሰው ያዳነውን አያውቅም ፡፡ ዛሬስ ትውልዳችን ያዳነውን ያውቅ ይሆን ?
 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ