የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አትርሱ

“ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፡- እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው” /ዮሐ. 5፡14/፡፡
ደዌ ወደ ዓለም የገባው ኃጢአትን ተከትሎ ነው ፡፡ ሁሉም በሽታ ግን የኃጢአት ውጤት አይደለም ፡፡ አንዳንድ በሽታ ግን የኃጢአት ውጤት ነው ፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛው ኃጢአት ባመጣው በሽታ ነው ለማለት ፍንጭ የለንም ፡፡ ኃጢአት በአንድ ቅጽበት ተሠርቶ ውጤቱ ግን ለዘመናት ሊቆይ ይችላል ፡፡ ሃያም ሠላሳም ዓመት በእስር ቤት የሚሳልፉ በቅጽበት በሠሩት ስህተት ነው ፡፡ ለዘመናት በበሽታ የሚጎዱ ሰዎች ምናልባት በቅጽታዊ መተላለፍ ነው ፡፡ “ውሸት ጥሩ ነበር ጣጣው ባልነበር” እንደሚባለው ኃጢአት መዘዙ ረጅም ነው ፡፡ በሽታ ሁሉ ግን የበደል፣ ጤንነትም የጽድቅ ምልክት አይደለም ፡፡ መንፈሳዊነት መለኪያው ክርስቲያናዊ ፍሬ ነው ፡፡ ሀብትና ጤንነት መለኪያ አይደሉም ፡፡ ራሱ የሁሉ ጌታ የሕማም ሰው እንደነበር ማስታወስ አለብን ፡፡
ጌታችን ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደፊት ኃጢአት አትሥራ አለው ፡፡ ጽድቅ አጥር መሆኑን ነገረው ፡፡ በጽድቅ ስንኖር ኅሊናችን ፣ ቤታችን ፣ ኑሮአችን ክብር ያገኛል ፡፡ ዓለም በጽድቅ ስለመኖራችን ብትከሰንም በዚህ ዓለም ላይ ትልቁ ትርፍ እግዚአብሔርንና ኅሊናን ማትረፍ ነው ፡፡ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ያለው ምንድነው ? ስንል የነፍስ ሞት ነው ፡፡ ኃጢአት ያለው ምንድነው ? ስንል የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት ነው ፡፡ የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት ትልቅ በደል ነው ፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የመርሳት በሽታ የሚገጥማቸው ሰዎች አሉ ፡፡ ይህ በሽታ ፍልጠት ቁርጠት የለውም ፡፡ ነገር ግን ብርቱ በሽታና አሳዛኝም በሽታ ነው ፡፡ በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎች የትዳር ጓደኞቻቸውን ፣ ልጆቻቸውን የገዛ ቤታቸውን ይረሳሉ ፡፡ ከቤታቸው ወጥተው ለመመለስ ይቸገራሉ ፡፡ ምድርንና በምድር ላይ ያሉትን መርሳት ትልቅ በሽታ ከሆነ ያዳነንን አምላክ መርሳት ትልቅ ጉዳት ነው ፡፡
የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ጉዞአቸው እግዚአብሔርን በመርሳት ተፈተኑ ፡፡ አይተው እንዳላየ ለመኖር ፣ ያደረገላቸውን ድንቅ ለማቃለል ደፈሩ ፡፡ ይህ ማቆሚያ ለሌለው ማጉረምረም ፣ ደስታ ለራቀው ሕይወት ዳረጋቸው ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣሉ ከራሳቸው ጋር ተጣሉ ፡፡ ካዳናቸው እግዚአብሔርና ከመሪያቸው ከሙሴ ጋር ተጣሉ ፡፡ የምድር አራዊትም ጠላት ሆኑባቸው ፡፡ በእባቦች ተነድፈው አለቁ ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስንጣላ ተፈጥሮ ራሱ ይጣላናል ፡፡ ከእርሱ ጋር ከተጣላን የማይጣላን ምንም ነገር የለም ፡፡
ነቢዩ ይህንን መርሳት የተባለውን መንፈሳዊ በሽታ ሲገልጥ ፡- “ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ” ብሏል /መዝ. 105፡21-22/፡፡ እነዚህ ክስተቶች የማይረሱ ናቸው ፡፡ ታላቅ ነገር በግብጽ የተደረገው ምንድነው ? ስንል በአሥር መቅሰፍቶች ገናና የነበረውን ንጉሥ አዋርዶ በአሥራ አንደኛው መቅሰፍት ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር መጣሉ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን በግብጽ አድርጎ ቢያድናቸውም ረሱት ፡፡ በካራን ምድር ጠላቶቻቸውን ድል ነሥቶ ምድራቸውን ርስት አድርጎ ሰጣቸው ፡፡ በኤርትራ ባሕርም በእውን እስከማይመስል ድረስ የውኃ ግድግዳን እየዳሰሱ ተሻገሩ ፡፡ ይህ የማይረሳ ቢሆንም እስራኤል ግን ረሱ ፡፡ እኛስ በበረቱብን ላይ በታላቅነቱ የተገለጠውን ፣ የጠላትን መንደር ያወረሰንን ፣ ያለ መርከብ ባሕሩን ያስረገጠንን እግዚአብሔርን ረስተን ይሆን ?
ጌታ ከዚህ የሚብስ እንዳይገጥምህ ደግመህ ኃጢአት አትሥራ አለው ፡፡ ያዳነህን እንዳትረሳ ! ከረሳህ የሚጠብቅህ ብርቱ ጉዳት ነው ማለቱ ነው ፡፡ በእግዚአብሔር ደጅ ላይ ለዘመናት ወድቀው ፣ የምሕረቱን ስጦታ ናፍቀው የነበሩ ዛሬ ግን ማዳኑን የረሱ ፣ ስጦታውን ነጥቀው የሮጡ አያሌ ናቸው ፡፡ ነገር ግን የባሰ እንደሚገጥማቸው አልተረዱም ፡፡ የፊት ችግራቸው የጤናና የበረከት እጦት ነው ፡፡ አሁን ግን የሚገጥማቸው እግዚአብሔርን ማጣት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት ትልቅ በደል ነው ፡፡ የወጡበት መሰላል ለመውረድም ያስፈልጋል ፡፡ አሊያ እየተቁለጨለጩ ገደሉን ወደ ታች እያዩ በስጋት መኖር ነው ፡፡ ሰው በእጁ ሲጨብጠው የነበረውን መሰላል ጫፍ ላይ ሲደርስ በእግሩ ይረግጠዋል ፡፡ እንዲሁም የከፍተኛነታችንን ምሥጢር እግዚአብሔርን መርሳት ከባድ ነው ፡፡ በኀዘን ቀን የምንጽናናበት ፣ በሽንፈት ቀን እንደገና የምንበረታበት ነው ፡፡ ለመውጣት በእጅ የጨበጡትን ከወጡ በኋላ በእግር መርገጥ ተገቢ አይደለም ፡፡ ዛሬ ተማርን ብለው ሰው የሚንቁ ያስተማራቸው ያን ምስኪን ሕዝብ ረስተዋል ፡፡ በእጃቸው የጨበጡትን በእግራቸው ረግጠዋል ፡፡ ወደ ሥልጣንን ማማ የወጡ የደገፋቸውን ሕዝብ ረስተዋል ፡፡ መሰላሉን በእግራቸው ገፍተው ጥለዋል ፡፡ ቢወርዱ ማረፊያ ስለሌላቸው እዚያው እየተፋጁ ለመኖር ወስነዋል ፡፡ መሰላሉን የጣለ አጥፍቶ ጠፊ ይሆናል ፡፡ ቃል የገቡለትን ወገን የረሱ ለብዙዎች የልብ ሕመም ሁነዋል ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያምናቸውና የሚፈልጋቸው ያለ ስለማይመስላቸው ሥራ ትተው በቀል ፣ ፍቅር ትተው ጥላቻ ይፈጽማሉ ፡፡ ግፍን አውግዘው ወጥተው ግፈኞች ይሆናሉ ፡፡ የታገሉለትን ነገር መልሰው ይፈጽማሉ ፡፡ “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር” እንዲሉ ሌሎችን የታዘቡበት ሀብት ሲመጣ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል ፡፡ የሰው ጨዋነት ቦታው ላይ እስኪደርስ ነው ፡፡ ሁሉም በቦታው ላይ አዳም ነው ፡፡ ሁሉም በቦታው ላይ ነፍሰ ገዳይ ቃየን ነው ፡፡ “ታሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ” እንዲሉ ያዳነንን መርሳት ትልቅ በደል ነው ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ “አትርሱ” የሚለን ብዙ ነገሮችን ነው ፡፡ የመጀመሪያው የእግዚብሔርን ማዳን ነው ፡፡ እኛ የዳነው እንደ እስራኤል ከፈርዖን ሳይሆን ከዲያብሎስ አገዛዝ ነው ፡፡ እኛ የወጣነው እንደ ያዕቆብ ልጆች ከግብጽ ሳይሆን ከሲኦል ነው ፡፡ እኛ የተሻገርነው የኤርትራን ባሕር ሳይሆን ባሕረ እሳትን ነው ፡፡ የወልድ ሰው መሆንን ፣ በመስቀል ላይ የከፈለውን ውለታ እንዴት እንረሳለን ? አዲስ አበባ የሚገኘው በ1915 ዓ.ም በልዑል ራስ ካሣ የተመሠረተው ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንም ቤተ ክርስቲያን በውስጡ አለ ፡፡ አንዲት እናት ሁለት ጥላ ይዘው ስእለት ለማቅረብ ይመጣሉ ፡፡ አለቃው አቡነ ዘበሰማያት ሰጥተው ፡- “አንዱ ለኢየሱስ ፣ አንዱ ለማርያም ነው ?” ቢሏቸው ፡- “እኔ ለጴንጤ አልሰጥም ለማርያም ነው ሁለቱም” ብለዋል ፡፡ በእውነት ሰማዕታት በደም የመሰከሩለትን ፣ ጻድቃን የመነኑለትን ፣ ነገሥታት ጣዕመ ዓለምን ትተው ዘውዳቸውን ያወለቁለትን ጌታ የማያውቁ ብዙዎች ናቸው ፡፡ ገና አላስተማርንም ፡፡ በእውነት ያዳነንን ጌታ እንዳንረሳ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡ ዛሬ የእልህ መልስ እንሰጥ ይሆናል ፡፡ ነገ ግን በጌትነት ዙፋኑ ፊት ዲዳ እንዳንሆን ማሰብ ያስፈልጋል ፡፡ የክርስቶስ ነገረ መስቀል በጣም እየተረሳ ነው ፡፡ በመንፈሳዊ ስም የሚነገረው ሥጋዊ ስኬት ነው ፡፡ በክርስቶስ ፍቅር የምትቃጠል ነፍስ እያጣን ነው ፡፡ አገልግሎታችን ሁሉ ከማን አንሼ ፣ የእልህ እንጂ የፍቅር አይደለም ፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ሕዝብን ከማዳን የአድማ ሠራዊት እያበዛን ያለነው ፡፡
“ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ” ይላል /2ነገሥ. 17፡38/፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መርሳት ከባድ ነው ፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት ካልተማርን ብዙ ነገሮች እያስፈሩን ይመጣሉ ፡፡ ፍርሃት የሚነቀለው በፍርሃት ነው ፡፡ እግዚአብሔርን ስንፈራ ክፉ አጋንንት አያስፈሩንም ፡፡ እግዚአብሔርንም መፍራት የምንለማመደው በቃሉ ነው ፡፡ ዛሬ ብዙ ሰዎች በአማልክት ፍርሃት ተይዘዋል ፡፡ የጸኑትን መላእክት ለማክበር እያቃታቸው የወደቀውን ሰይጣን ግን ያከባብራሉ ፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ከራቀ ብዙ ፍርሃት ይነግሥብናል ፡፡ እንዳንፈራ ከፈለግን እግዚአብሔርን መፍራት አለብን ፡፡
“እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና” ይላል /ዕብ. 13፡1/፡፡ በጣም እየተዘነጋ ያለ ነገር ቢኖር እንግዶችን መቀበል ነው ፡፡ ግለኝነት በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ሰው ሰውን ፈርቶ ተቀምጧል ፡፡ ጌታችን በመጨረሻው ቀን ከሚጠይቀን ጥያቄዎች አንዱ ወይም ሰጥቶን የሄደው የቤት ሥራ እንግዶችን መቀበል ነው፡፡ ከእንግዶች ጋር እንግዳ ሁኖ የሚመጣ ጌታ ነው ፡፡ ስደተኞች እንግዶች ናቸው ፡፡ ለአገሩ እንግዳ ፣ ለሰዉ ባዳ የሆኑ እነዚህ እንግዶች ናቸው ፡፡ እነዚህን መቀበል ግለሰቦችና አገራት እየረሱ ነው ፡፡ ሰዎች በራብተኞች ላይ ሰማይ ጠቀስ አጥር እያጠሩ ነው ፡፡ በቅርብ በሰማነው ዜና በፈረንሳይ ገጠር ውስጥ የሚኖር አንድ ገበሬ ስደተኞች በደጁ ሲያልፉ እህል ውኃ እየሰጠ ያስተናግዳቸዋል ፡፡ የደከማቸውንም ለሳምንታት ያሳርፋል ፡፡ ይህ ሰው በፈረንሳይ ፍርድ ቤት ተከስሶ አንድ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተፈርዶበታል ፡፡ ይህንንም ድርጊት እንዲያቆም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ፡፡ ሰውዬው ግን የመገረም ሳቅ ሲስቅ ታይቷል ፡፡ በሚመሰገንበት ተግባር እየተከሰሰ ፣ በሚያሸልመው ሥራ እየተቀጣ ነው ፡፡
“ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” ይላል /ዕብ. 13፡16/፡፡ ሁሉ ለአፌ የሚል የመንፈቅ ልጅ ነው ፡፡ ያደገ ሰው ለወገኔም ይላል ፡፡ እግዚአብሔር ከሰጠን ላይ ለሌሎች ማካፈልን መርሳት የለብንም ፡፡ አንድ ሊቀ ጳጳስ አስታውሳለሁ ፡፡ አሁንም በሕይወት አሉ ፡፡ ገንዘብ ሲያገኙ የስም ዝርዝር መዝገብ አላቸው ፖስታ ውስጥ እየተከተተ ለወዳጆቻቸው ያከፋፍላሉ ፡፡ ለራሳቸው የሚበቃቸውን ከያዙ በኋላ የጥንት ወዳጆቻቸውን ያስባሉ ፡፡ የሚላላኩአቸው አንድ መነኩሴ ሲነግሩኝ እኚህ አባት ይሰጣሉና አጥተው አያውቁም ብለውኛል ፡፡ ወገኖቼ አትርሱ ወዳጆቻችሁን ፣ አትርሱ ድሆችን !
“እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ”  ይላል /2ጴጥ. 3፡8/፡፡ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት ነው ፡፡ ምን ማለት ነው ? በአንድ ቀን የሺህ ዓመት ሥራ ይሠራል ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ ዘመኔ አለፈ አትበሉ ፡፡ እርሱ በዘላለማዊነት ሲኖርም ሺህ ዓመትን እንደ አንድ ቀን እየኖረ ነው፡፡ ያለፈውን ሺህ ዓመት ለማስታወስ እግዚአብሔር ቆይ ላስታውስ አይልም ፡፡ እርሱ በዘላለም አሁን የሚኖር ነው ፡፡ ተስፋ የቆረጣችሁ ፣ ጊዜው ነጎደ የምትሉ አትርሱ ! በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት ነው ፡፡ ምስጋና እናቀርብልሃለን፡፡   

ያጋሩ