የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰንበት ጌታ

“ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።” /ዮሐ. 5፡17/፡፡
ሰንበት ሰባተኛ ማለት ነው ፡፡ ሠሪው እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን የፈጸመበትና ያረፈበት ቀን ሰባተኛ ወይም ሰንበት ይባላል ፡፡ ምሥጢራዊ ፍችው ማረፍ ፣ መደሰት ማለት ነው ፡፡ የሰንበት ጀማሪው ሙሴ ተቀባዩም አይሁድ አይደሉም ፡፡ ሰንበት በጥንተ ፍጥረት የተሰጠች መለኮታዊ ስጦታ ናት ፡፡ የእስራኤል ልጆች ግን ያከብሯት ዘንድ የሕግ ከለላ አገኘች ፡፡ ሰንበት ከታላላቅ በዓላት አንዱና የመጀመሪያው ነው ፡፡ የሰንበትን ትርጉም በማዛባት ከመሠረታዊው የእግዚአብሔር ዓላማ ያፈነገጡትን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገስጾአል ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥንተ ፍጥረት በማረፍ ቀኑን እንደሰጠ ሁሉ በሞቱም በመቃብር በማረፍ የትንሣኤ መገኛ አድርጓታል ፡፡ ሰንበት ቀኑ የሚከበርበት ሳይሆን የሰንበት ጌታ የሆነውን የምናከብርበት ነው ፡፡ ጨርሶ የማይሠራበት ሳይሆን ተግባረ ነፍስ የሚተገበርበት ነው ፡፡ ቅዳሜና እሑድ የመሆኑ ጉዳይ ሳይሆን አሳቡ በእግዚአብሔር መደሰት ነው ፡፡ ሁለት ሰንበታት የተሰጡ ሳይሆን ሰንበት አንድ ነው ፡፡ ቀዳሚት ሰንበት የጥንተ ተፈጥሮ ሕግ ሲሆን ዕለተ እሁድ ግን ትንሣኤ የተገለጠባት ናት ፡፡ ዕለተ እሑድ የጌታ ቀን ተብላ ትታሰባለች /ራእ. 1፡10/ ፡፡ የጌታ ቀን መባሉ ለጥንት ክርስቲያኖች ትልቅ ትርጉም ነበረው ፡፡ ይህች ቀን “የቄሣር ቀን” ተብላ ትጠራ ነበርና የጌታ ቀን ማለታቸው በውስጡ ደስታና መሥዋዕትነት ነበረው ፡፡  በሰንበት ልናከናውናቸው የሚገቡ ተግባራትን ማሰብ አለብን ፡፡ በዓላት ዓላማቸው እግዚአብሔርን ለመጋበዝና በእግዚአብሔር ለመጋበዝ ነው ፡፡ ከሁሉ በላይም የሥራው ማስታወሻ ናቸው ፡፡ ሁሉ ቀን የጌታ ቢሆንም ሰንበት ግን በተለየ ሁኔታ የጌታን ሥራ እንሠራበታለን ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ስድስት ቀን ፍጥረታትን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፡- “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና” ብሏል /ዘፍ. 2፡2-3/፡፡ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን ማረፉ በሥጋዊ ተግባር ሳምንቱን ሙሉ ሲደክሙ የነበሩ እንዲያርፉ ምሳሌ ለመሆን ነው ፡፡ እግዚአብሔር ድካም የሌለበት ኃያል ፣ እንቅልፍ የሌለበት ትጉህ ነው ፡፡ እርሱ ዐረፈ ተብሎ መጻፉ እኛ ደካማዎቹ እንድናርፍ ሊያስገነዝበን ነው ፡፡ ሕይወት በአንድ ትንፋሽ የምትቋጭ የአንድ ሺህ ሜትር ሩጫ አይደለችም ፡፡ የዐሥር ሺህ ኪ.ሜ ሩጫ ናት ፡፡ ስለዚህ እያረፉ መጓዝ ያስፈልጋል ፡፡ ቀጣዩ ጉዞ የሚታየው በዕረፍት ነው ፡፡ ይህን ዓለም ጥለን ስንሄድ የምንሞተው ለአንዳንድ ጉዳዮች አይደለም፡፡ ለሁሉም ነገር እንሞታለን ፡፡ አንድ ቀን በግድ የምንለየውን ዓለም በፈቃዳችን ደግሞ ልናርፍበት ይገባል ፡፡ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ስናርፍ እንድንታደስ አድርጎ ነው ፡፡ ማረፍ ተፈጥሮ ነው ፡፡ የተፈጥሮም አካል ነው ፡፡ እንኳ ሰው መሬቱም ፣ እንስሳውም እንዲያርፉ ታዟል፡፡ ስድስት ዓመት የታረሰ መሬት በሰባተኛው ዓመት ሲያርፍ ያገግማል ፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት ብዙ ፍሬ ይሰጣል ፡፡ ዕረፍት ውስጥ ማገገም አለ ፡፡ አሊያ ሕይወት ሳይክል ወይም ዙረት ይሆናል ፡፡ እግዚአብሔር በስድስተኛው ዓመት በረከት እንደሚያኖረው በማመን በሰባተኛው ዓመት መሬቱን እንዲያሳርፍ እስራኤላዊ ሁሉ ታዝዟል ፡፡ የምድሪቱ ሰንበት ለእስራኤላዊው እምነትን ያስተምረዋል ፡፡ ሰው ማረፍ እንዳለበት በዘመናዊው ዓለምም ታምኗል ፡፡ ስድስት ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን ማረፍ አሊያም ሰባተኛውን ቀን በስድስት ቀናት ውስጥ ነስንሶ ማረፍ እንዳለበት አጥኚዎቹ ይናገራሉ ፡፡ ማረፍ ማለት ግን እንዴት ነው ? ሥራ በማቆም ነው ?
ሁሉም ቀናት የእግዚአብሔር ናቸው ፡፡ በሁሉ ቀናትም እግዚአብሔር ሊመለክ ይገባዋል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ቀናት ለመስጠት ሰባተኛውን ቀን በመስጠት ሕዝቡን ማለማመድ ፈለገ ፡፡ ይህ ሰባተኛ ቀን የተፈጥሮ አካል ነውና ነገሥታት ሳይቀር አስከብረውልናል ፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ሁሉን ይገዛልና ፡፡ እግዚአብሔር ዐረፈ ተብሎ ሲነገር ከድካም ማረፍ አይደለም ፡፡ እፎይ ማለትና በሠራው ሥራ መደሰትን የሚያመለክት ነው ፡፡ በእግዚአብሔር ሥራ መደሰትና ማረፍ እርሱ እውነተኛ ሰንበት ነው ፡፡ ይልቁንም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነልን የማዳን ተግባር መደላደል እርሱ እውነተኛና የማያልፍ ሰንበት ነው ፡፡ ሰንበት ተግባረ ሥጋን ከመሥራት መታቀብ ቢኖርም ተግባረ ነፍስ ግን በይበልጥ የሚሠራበት ነው፡፡ ይልቁንም ዕረፍት የነጻነት ምልክት ነው ፡፡ የእስራኤል ልጆች በግብጽ ባሪያ በነበሩ ጊዜ ለ430 ዘመን አላረፉምና ሰንበት የነጻነታቸው ምልክት ነበረች ፡፡ እስራኤል ከግብጽ ባርነት እስኪወጡ ሰንበት እንደ ተከበረ የተጻፈ ነገር የለም ፡፡ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ ግን ሕዝቡ ፣ ባሮችና ምድሪቱም እንዲያርፉ ታዘዘ ፡፡ የእግዚአብሔር በዓላት የእግዚአብሔር ግብዣ ናቸውና ሊከበሩ ይገባቸዋል ፡፡ በእስራኤላውያን በዓላት እግዚአብሔርን የሚጋብዙበትና በእግዚአብሔር የሚጋበዙባቸው በዓላት ነበሩ ፡፡ በዓመት ሦስት በዓላትን በዓለ ፋሲካን ፣ በዓለ ሰዊትን /የእሸት በዓል/ ፣ በዓለ መጸለትን /የዳስ በዓል/ ኢየሩሳሌም ድረስ ተገኝተው ማክበር ነበረባቸው ፡፡ ይህ በእግዚአብሔር ግብዣ መገኘት ላይ ማለት ነው ፡፡ ሰንበትም በአቅራቢያቸው ባለው ምኩራብ የሚሄዱበት በመሆኑ የእግዚአብሔር ግብዣ ነው ፡፡ በቤታቸው የሚደረገው በዓል ግን እግዚአብሔርን የሚጋብዙበት ነው ፡፡ እርሱ ቀጥረውት ቀርቶ አያውቅምና በእግዚአብሔር ቀጠሮ ላይ መቅረትም አይገባም ፡፡
በጥንተ ተፈጥሮ ራሱ እግዚአብሔር አርአያ የሆነበት ሰንበት በሕገ ኦሪትም አጽንኦት ተሰጥቶታል ፡፡ “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።”/ዘጸ. 20፡8-11/፡፡ የሰንበትን ቀን ስለማክበር ሕግ አጽንኦት እንጂ መነሻ አልሰጠም ፡፡ በሰባተኛው ቀን እንግዚአብሔር ማረፉ ግን እስራኤላውያን እንዲያርፉ ትልቅ አርአያ ነው ፡፡ ዐሠርቱ ትእዛዛት የፍቅር ሕግ ነው ፡፡ ፍቅርም በሁለት ይከፈላል ፡፡ እርሱም ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ነው ፡፡ ሰንበትን ስለማክበር የሚናገረው ክፍል በፍቅረ እግዚአብሔር ውስጥ ያለ ነው ፡፡ ፍቅር ለሚወደው ጊዜ ይሰጣል ፡፡ ለእግዚአብሔር የአምልኮና የምስጋና ቀን መስጠት የፍቅር ጥያቄ እንጂ የሕግ ጥያቄ አይደለም ፡፡ ሰንበት ከሕግ በፊት ተሰጥታለችና ፡፡
የእስራኤል ልጆች ስድስት ቀን መና እንዲለቅሙ በሰባተኛውም ቀን እንዲያርፉ ታዘዋል ፡፡ ሰስተው በሰባተኛው ቀን ቢወጡ መጣ አላገኙም ፡፡ ትዝብትን አተረፉ እንጂ /ዘጸ. 16፡29/፡፡ እንዲሁም በረከታችን ያለው እግዚአብሔር ከፈቀደው ነገር ውስጥ እንጂ ከመሻችን ውስጥ አይደለምና ለእግዚአብሔር ጊዜን መስጠት ይገባል ፡፡ ለማይሞላው ኑሮ ሁልጊዜ ማሰብ ተገቢ አይደለም ፡፡ ዛሬ የምንሮጠው ትላንት እንዳልሮጥን አድርገን ነው ፡፡ ዕረፍት ውሳኔ ነው፡፡ የሚሞላውም ሞላ ስንለው እንጂ ቋቱ ጠብ እንደማይል መረዳት አለብን ፡፡
በዚህ ቀን ተግባረ ሥጋን እንዳያከናውኑ ታዘዋል ፡፡ አሁን ነጻ ሕዝቦች ናቸውና ማረፍ ይችላሉ ፡፡ የነጻነታቸውን ጌታ ማምለክም እርሱ እውነተኛ ሰንበት ነው ፡፡ በዚህ የሰንበት ቀን እንጨት መልቀም ፣ እሳት መጫር አይችሉም ነበር /ዘኁ . 15፡32-35፤ ዘጸ. 35፡3/፡፡ ሰንበት በዘመናት ሦስት ነገሮችን ታሳስባለች ፡፡ የመጀመሪያው እግዚአብሔር የፍጥረቱ ባለቤት መሆኑን ፣ ሁለተኛ ፡- እግዚአብሔር የባርነትን ቀንበር የሚሰብር የነጻነት ንጉሥ መሆኑን፣ ሦስተኛ ፡- በጌታችን ትንሣኤ የሞት ዕዳ መነሣቱን ታሳስበናለች ፡፡ ይልቁንም ክርስቲያኖች ጌታችን ሞትን አሸንፎ በተነሣባት ፣ ፍጥረት መፈጠር በጀመረባት ፣ የተፈጠረው ፍጥረት እንደገና በትንሣኤ በታደሰባት ቀን በዕለተ እሑድ መሰብሰብ የጥንት ልማዳቸው ነው ፡፡ በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ቁርባንን ይቀበሉ ነበር /የሐዋ. 20፡7/፡፡ በዚህ ቀንም ክርስቲያኖች ሁሉ ይሰባሰቡ ስለነበር ለድሆች መዋጮ ይደረግ ነበር /1ቆሮ. 16፡1-2/፡፡ በዚህ ቀን ጌታችን ዳግመኛ ሲመጣ የሚጠይቀን ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በተለየ ሁኔታ የሚተገበሩበት ቀን ነው ፡፡
ሰንበት ቀኑን ሳይሆን የቀኑን ባለቤት እግዚአብሔርን የምናከብርበት ቀን ነው ፡፡ በሰንበትም በጎ መሥራት ተፈቅዷል ፡፡ የታመሙትን መጠየቅ ፣ ችግረኞችን መርዳት ፣ ያዘኑትን መጎብኘት ፣ ለታሰሩት ዋስ መሆን በሰንበት የሚሠራ ዋነኛ ሥራ ነው ፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርም ይፈጸማል ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጥረታትን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ያረፈው እርሱ ፣ በደብረ ሲናም መመሪያ አድርጎ የሰጠ እርሱ ነው ፡፡ በአዲስ ኪዳንም በሥጋ ተገልጾ የሰንበት አከባበር ሥራ በመፍታት ሳይሆን በበጎ ተግባራት መፈጸም እንዳለበት አሳስቧል /ማር. 3፡1-6፤ ሉቃ. 13፡10-17፤ ዮሐ. 5፡1-9፤9፡1-14/፡፡
አይሁዳውያን ከዓርብ ፀሐይ መጥለቅ እስከ ቅዳሜ ፀሐይ መጥለቅ ወይም እስከ ቅዳሜ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ለ25 ሰዓታት ሰንበትን ያከብራሉ ፡፡ 39 ዓይነት ተግባራትን መሥራት በፍጹም የተከለከሉ ናቸው ፡፡ በምኩራብም ተገኝተው ከቶራ ከነቢያትና ከመዝሙራት ያነባሉ ፡፡ ስብከት ይሰማሉ ፡፡ ዝማሬ ያቀርባሉ ፡፡ እነዚህ አይሁዳውያን ግን እግዚአብሔር ለዕረፍትና ለደስታ የሰጠውን ቀን አስጨናቂ ቀን አደረጉት  ፡፡ ጌታችን በሰንበት ድውይ ሲፈውስ እንኳ እንደ ሥራ ቆጠሩትና ተቃወሙ ፡፡ በሰንበት ዋና ዋና ተግባራት ሲገጥሙ መፈጸም እንዳለባቸው መጻሕፍትን አላስተዋሉም፡፡ ከካህናት በቀር ማንም የማይመገበውን ኅብስት ዳዊትና ተከታዮቹ በረሀብ ጊዜ እንደበሉና እንደ በደልም እንዳልተቆጠረባቸው አላሰቡም /ማቴ. 12፡3-4/ ፡፡ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሁለት ጊዜ ጾሟል ፡፡ በሰማንያ ቀናት ውስጥ ብዙ ሰንበቶችን እንደሻረ አላሰቡም ፡፡ በሰንበት መጾም አይቻልምና ፡፡ እስራኤል ኢያሪኮን ሰባት ቀን ሲዞሩ ሰንበት እንደ ሻሩ አልተቆጠረባቸውም ፡፡  ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅም ለአሥር ቀናት በጥሬ ሲጾሙ ሰንበትን እንደ ሻሩ አልተጻፈም ፡፡ ካህናትም በሰንበት ለተግባረ አምልኮ ሲፋጠኑ ሰንበትን እንደ መሻር አልተቆጠረባቸውም ፡፡ አይሁዳውያን ግን እግዚአብሔርን አስጨናቂ አምላክ ሰንበትንም የጭንቀት ቀን አደረጓት ፡፡
      በሁሉ ቀን እግዚአብሔር ማሰብ ይገባናል ፡፡ ሰንበትም ልዩ ቀን ናትና የተፈጠሮና የነጻነትም ቀን ናትና በዚህች ቀን በእግዚአብሔር ቃል ማረፍ ይገባል ፡፡ ክርስቲያኖችንም የምናገኘው በዚህ ቀን ነውና መሰባሰብ ካለ መሰባሰቢያ ቀን ማስፈለጉን መርሳት የለብንም ፡፡ ሰንበት ከቀኑ በላይ አሳቡና ዓላማው ዋጋ አለው ፡፡ ሰንበት አንድ ነው ፡፡ ቅዳሜ ነው እሑድ እያልን መጣላት ተገቢ አይደለም ፡፡ ሁለቱንም ቀን ለጌታ ብንቀድስ ያንስበታል ወይ?  ሁሉ ቀን የእግዚአብሔር መሆኑን እናምናለን ፡፡ ሁሉን ቀን መስጠት ግን ለጥቂቶች እንጂ ለሁሉም የሚቻል አይደለም ፡፡ ከሁሉ በላይ ሰንበት ያለ ሰንበት ተግባር ከንቱ ነው ፡፡ አንዱ ቀን ከአንዱ ቀን ይበልጣል የሚል አሳብ ሳይሆን ሰንበት የኅብረት ቀን የነፍስ ቀጠሮ ነው ፡፡ አይሁድ ግን በሰንበት ቀን የሰንበትን ጌታ ተቃወሙ ፡፡ የሰንበትን ሥራ ሻሩ ፡፡ እርሱም የሌሎች መፈወስ ነው ፡፡ አይሁድ ራሱ ባወጣው ሕግ ጌታችንን ከተቃወሙ አንዳንዶች ጥቅስ እየጠቀሱ ቢቃወሙን ምንም አይደንቅም ፡፡ መጻጉዕ በተፈወሰ ጊዜ ፈውስን እንደ ሥራ በመቁጠር ፈዋሹን ጌታ ተቃወሙ ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ