የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መሻገር

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” /ዮሐ. 5፡24/፡፡
ጌታችን ከሕይወት ጋር የተያያዘውን ነገር እውነት እውነት እላችኋለሁ በማለት አጽንዖት ይሰጣል ፡፡ ሰዎች እውነት እውነት ብለው የሚሰሙት ስለምድራዊ ነገር ሲነገራቸው ነው ፡፡ ስለ ሰማዩ ሲነገራቸው ግን “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ፣ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” በሚል ሂሳብ ነው የሚያዩት ፡፡ የሥጋ ሙላት ለነፍስ አይተርፍም ፤ የነፍስ ሙላት ግን ለሥጋ ይተርፋል ፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ያለው /ማቴ. 6፡33/፡፡ ዋናው መንግሥቱ የተባለው እምነት ጽድቁ የተባለው በጎ ኅሊና ነው፡፡ ሌላው ተጨማሪ ነው ፡፡ በግዱም የሚመጣ ነው ፡፡ ባናምንም ፀሐይ ይወጣል ፣ ካላመንን ግን የሕይወት ብርሃን አይመጣም ፡፡ በአገግሎትም ዋናው ማመን ነው ፣ ምልክት ግን ተከታይ ነው ፡፡ ወንጌላዊው ማርቆስ ፡- “ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” ብሏል /ማር. 16፡20/፡፡ እኛ እግዚአብሔርን እናምናለን ፣ ምልክት ደግሞ እኛን ይከተላል ፡፡ ዋናው ፈቃድን ለፈቃዱ ማስገዛት ወይም እግዚአብሔርን እረኛ ማደረግ ነው ፡፡ ከዚያ በኋላ ፡- “ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአብሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ” ብለን እንዘምራለን /መዝ. 22፡6/፡፡ እግዚአብሔርን ስንከተል ቸርነትና ምሕረት እኛን ይከተላሉ ፡፡ ቸርነትና ምሕረት ጸንተው እንዲኖሩ ደግሞ በእግዚአብሔር ቤት እንኖራለን ፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ ቃሉ ፣ ላኪው አብ ፣ ተላኪው ወልድ ፣ የዘላለም ሕይወት ፣ ሞትና ሕይወት ፣ ፍርድ ተጠቅሰዋል ፡፡ ጌታችን ቃሌ በማለት ተናገረ ፡፡ እኛ ቃሉ ብለን እንናገራለን ፡፡ እርሱ ግን የቃሉ ባለቤት ነውና ቃሌ አለ ፡፡ አይሁድ አምላክነቱን መቀበል አቅቷቸው ነበርና ቃሌ ብሎ ሲናገር እንደገና ይደነግጣሉ ፡፡ ቃሌ በማለቱ አምላክነቱን እየገለጠ ነውና ፡፡እርሱ እንደ ነቢያት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት የተነገረ አይደለም እኔ ግን እላችኋለሁ በማለት ያዘዘን ነው ፡፡ የእርሱ ቃል የሥልጣን ቃል መሆኑን የዕብራውያን ፀሐፊ ይናገራል /ዕብ. 1፡3/ ፡፡ ይህ የሥልጣን ቃል ሰማያትን ያጸና ፣ ምድርንም ያለ መሠረት ያቆመ ፣ ድውዮችን የፈወሰ ፣ ሙታንን የቀሰቀሰ ቃል ነው ፡፡ የቃሉ ባለቤት ክርስቶስ ነው፡፡ የእርሱ ቃል ወደ እውነት ይመራል ፡፡ በእርሱ ቃል የላከውን አብን የተላከውን ወልድን የዘላለም ሕይወትን እናገኛለን ፡፡ ይህ ቃልም ሕይወትና ሞትን እንዲሁም ፍርድንም ያመጣል ፡፡
የክርስቶስን ቃል መስማት ማለት ምን ማለት ነው ስንል የላከውን አብን የተላከውን ወልድን መቀበል ማለት ነው ፡፡ የዘላለም ሕይወት በእምነት ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡ በግላችን እምነት ላይ ሳይሆን በሚታመነው ጌታ እውነትነት ላይ ነው ፡፡ የዘላለም ሕይወትን የሚያሰጥ እምነት የዘላለሙ አምላክ ነው ፡፡ ሰዎች በጠፊ ነገሮች በማመን ጊዜያዊ ዕረፍት ለማግኘት ይሞክራሉ ፡፡ በዘላለሙ ጌታ በማመን ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ፡፡ የሚታመነው ነገር ባለው ዕድሜ መጠን አማኙ ዕረፍቱ ያን ያህል ነው ፡፡አብን የላከ ብሎ ማመን ወልድን የተላከ ብሎ ማመን ነው ፡፡ ተላኪ በሌለበት ላኪ የለምና ፡፡ የሥላሴን አንድነት መበታተን ፣ ሦስትነትን መጠቅለል ከሃይማኖት መሠረት የሚጥል ነው ፡፡ አብን ያለ ወልድ የሚያምን ወልድንም ያለ አብ የሚያምን ድኅነት የለውም ፡፡ በእግዚአብሔር ማመን መሻገር ነው ፡፡ ይህ መሻገርም ከሞት ወደ ሕይወት መፍለስ ነው ፡፡ ትልቁ መሻገር በእግዚአብሔር ማመን ነው ፡፡ ከድህነት ወደ ባለጠግነት ፣ ከእስር ቤት ወደ ቤተ መንግሥት መሻገር ይህ ትንሽ ነገር ነው ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ግን ትልቅ ነገር ነው ፡፡ እንዲህ ያለው አዲስ ልደት የሚገኘው በእግዚአብሔር በማመን ነው ፡፡ አንድ ሰው በክርስቶስ ብቻ አምኖም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ካላመነ አይድንም ፡፡ ምክንያቱም ቤዛነት ወልድ በለበሰው ሥጋ የራሱ ግብር ሲሆን ማዳን ግን የመለኮት አንድ ግብር ነው ፡፡ ሃይማኖት ሚዛን በመሆኑ ትክክል እስኪመጣ ድረስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡
እግዚአብሔር አብ በነቢያት ስለ ልጁ መምጣት ማናገሩ ፣ እግዚአብሔር ወልድ በዘመነ ሥጋዌ ስለ አብና ስለ መንፈስ ቅዱስ መናገሩ ፣ መንፈስ ቅዱስም በቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ መናገሩ ለዚህ ነው ፡፡ መዳን ሥላሴያዊ ስለ ሆነ ነው ፡፡ ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ሲኖረን ስለ እግዚአብሔር አብና ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ትክክለኛ እውቀት ይኖረናል ፡፡ ጌታችን ቃሌን የሚሰማ የሚለው ስለ ራሱና ስለ አባቱ የሚናገረውን የሃይማኖት ቃል ነው ፡፡
ጌታችን አብ ላከኝ ብዬ የነገርኳችሁን ቃል ብትሰሙ የዘላለም ሕይወት አላችሁ እያለ ነው ፡፡ በዮሐ. 17፡3 ላይም ይህን የሚያጸና ንግግር ተናግሯል ፡፡ ጌታችን ስለ ማመንና ስለ አለማመን ሦስት ንግግሮችን ተናግሯል፡፡ ፍርድ፣ ሕይወትና ሞት ፡፡ ትልቁ ፍርድ ፣ ትልቁ ሞት ከእግዚአብሔር ኅብረት መለየት ነው ፡፡ በራሳችን ያልጀመርነውን እስትንፋስ በራሳችን ለማስቀጠል መሞከር ትልቁ ፍርድ ነው ፡፡ ፍርድ ሁለት ዓይነት ክፍሎች አሉት ፡፡ የመጀመሪያው የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሆን ሁለተኛው የቅጣት ውሳኔ ነው ፡፡ የጥፋተኝነት ውሳኔ ትልቁን ጊዜ የሚወስድ ሲሆን የቅጣት ውሳኔ ግን የታወቀ ነው ፡፡ ከጥፋተኝነት ውሳኔ በፊት ዐቃቤ ሕግ ፣ ምስክሮች ፣ ጠበቃ … ይቆማሉ ፡፡  በመጨረሻ ሦስቱ ዳኞች ይወስናሉ ፡፡ እንዲሁም ፈጣሪውን የካደውን ሰው ሥላሴ ዐቃቤ ሕግ በተባለው በሕጉ ፣ ምስክሮች በተባሉ ወንጌላውያን ፣ ጠበቃ በተባለው የምሕረት ደም መመለሱን ያያል ፡፡ እንቢ ካለ የጥፋተኝነት ውሳኔ ይሰጠዋል ፡፡ የቅጣት ውሳኔው በሲኦል የሚከናወን ነው ፡፡ ቢሆንም የጥፋተኝነት ውሳኔ የሰማ የተቀጣ ያህል ይሰማዋል ፡፡ እንዲሁም በሕይወት ጥላና በሞት ጥላ ውስጥ መኖር የራሱ የሆነ ስሜት አለው ፡፡ አብን ላኪ ወልድን ተላኪ መንፈስ ቅዱስን መሪ አድርጎ ያልተቀበለ አፈጻጸሙ ቢዘገይም ያለው በፍርድ ክልል ውስጥ ነው ፡፡
የእስራኤል ልጆች ቀይ ባሕርን መሻገራቸው ከሞት ወደ ሕይወት መፍለሳቸው ነው ፡፡ ራሳቸውን ለባርነት ፣ ልጆቻቸውን ለሞት ፣ ንብረታቸውን ለብክነት ፣ ሰላማቸውን ለፍርሃት ከሰጡበት ከግብጽ መውጣት ከሞት ወደ ሕይወት መሻር ነው ፡፡ በላከው በአብና በተላከው በወልድ ማመንም እንዲህ ያለ የሕይወት ፍልሰት የሚያመጣ ነው ፡፡ የእስራኤል ልጆች በተሻገሩ ጊዜ እነርሱም ልጆቻቸውም ከብቶቻቸውም ተሻግረዋል ፡፡ በእግዚአብሔር የዳነም እርሱና ቤተሰቡ እንዲሁም ንብረቱ ይድናሉ ፡፡ ካልተሻገርን ልጆቻችን ባለ ማመንና በሞት ቀጠና ውስጥ ይኖራሉ ፡፡ አለመሻገር ልጆችን ለሲኦል ግብር መውለድ ነው ፡፡ አለመሻገር ንብረትን ለሱስና ለበሽታ ማባከን ነው ፡፡ እግዚአብሔር ያለ እኛ ነበረ ፤ ይኖራል ፡፡ እኛ ግን እግዚአብሔርን ካላመንን ሁሉም ነገራችን የሞት ቀጠና ውስጥ ነው፡
የእስራኤል ልጆች ቀይ ባሕርን አንድ ጊዜ ተሻገሩ ፡፡ ቢመኙም ግን መመለስ አልቻሉም ፡፡ በምድረ በዳ ረግፈው ቀሩ ፡፡ አንድ ጊዜ በእግዚአብሔር ማመን ይገባል ፡፡ ሕይወት አንድ ጊዜ በማኅፀን ይፀነሳል ፡፡ ያ እስትንፋስም ባለ ጊዜ ሁሉ ዕድገት የማያቋርጥ ይሆናል ፡፡ አንድ ጊዜ በእግዚአብሔር እናምናለን ፣ ዕድገት ግን ይቀጥላል ፡፡ በእግዚአብሔር ያገኘነውን ሕይወት መጣል ማለት ራስን በጦር መውጋት ማለት ነው ፡፡ የትኛውም ጠላት ወደ ሲኦል ሊያወርደን አይችልም ፡፡ ንብረትን ፣ ክብራችንን ሊሳጣን ይችል ይሆናል ፡፡ ሕይወትን የምናጣው ግን በገዛ ምርጫችን ነው ፡፡ የሰው ልጅ ትልቅ ጠላቱ ክፉ ምርጫው ነው ፡፡
እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ከወደደን መጥላት ፣ ከታመነልን መክዳት የለበትም ፡፡ እግዚአብሔርን ማግኘት በዘላለም እቅፍ ውስጥ መግባት ነው ፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ ፍርድን ይፈራል ፡፡ እንኳን ፍርድን ፍርድ ቤትንም አይወድም ፡፡ የምድር ፍርድ ግን ጊዜያዊ ነው ፡፡ ከዘላለም ፍርድ የምናመልጠው በእግዚአብሔር በማመን ነው ፡፡
   እግዚአብሔር አምላክ እስራኤልን ስለ ታገሠበት ትዕግሥት ሲናገር መዝሙረኛው ፡- “እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም። ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ”  ይላል /መዝ. 77፡38-39/፡፡ አንድ ጊዜ ከገደላቸው ተመልሰው መኖር አይችሉም ፡፡ የሞት ዕድል አንድ ጊዜ ነው ፡፡ ስለዚህ ታገሣቸው ፡፡ እንዲሁም ዛሬም የሚታገሠን የኋላ ፍርዱ የማይቀለበስ ስለሆነ ነው ፡፡ በዚህ ቅዱስ ፍርሃት ወደ እርሱ እንመለስ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት እንሻገር ፡፡

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።