የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ማጠቃለያ

በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አምስት ውስጥ አካሉ በደዌ የሞተና ኅሊናቸው በድንቁርና ነፍሳቸው ባለማመን የሞተች ሁለት ዓይነት ወገኖችን እናያለን ። ሙታነ ሥጋና ሙታነ ኅሊና ልዩነታቸው ምንድነው ? ብሎ የሚጠይቅ ካለ ቀጥሎ እናያለን ። ሙታነ ሥጋ ያለ ፈቃዳቸው በደዌ የደቀቁ ናቸው ፤ ሙታነ ኅሊና ግን ማወቅ ባለመፈለግ በድንቁርና ፣ ማመን ባለመ ፈለግ በክህደት የጸኑ ናቸው ። ሙታነ ሥጋ ፈውስ ካገኙ ነግ ዛሬ ሳይሉ ይወስናሉ ። ሙታነ ኅሊና ግን በሽታቸውን ተላምደው ለመኖር ይፈልጋሉ ። እንደውም “ካልለመዱት መንፈስ ቅዱስ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል” ይላሉ ። ሙታነ ሥጋ ያስነሽው ሥልጣን እንጂ የእነርሱ እምነት አስፈላጊ አይደለም። ሙታነ ኅሊና ግን የእነርሱ ፈቃድና የእግዚአብሔር ሥልጣን ሲገናኙ ነጻ የሚወጡ ናቸው ። ሙታነ ሥጋ ከደዌ ቢድኑ ተመልሰው በሌላ በሽታ ይታመማሉ ፣ በማይቀረው ሞት ይወሰዳሉ ። ሙታነ ኅሊና ግን አንድ ጊዜ ሲያምኑ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ። ጌታችን ለሁለቱም ወገኖች መልስ አለው ። ሙታነ ሥጋን በተአምራት ፣ ሙታነ ኅሊናን በትምህርት ያድናል ። ምዕራፍ አምስት ይህንን ያስገነዝበናል ።
በሽተኛ ፣ ታካሚ ፣ ሐኪምና መድኃኒት የሚባሉትን አስታውሱ ። ሁለት ሁለት ስናደርጋቸው በሽተኛና ታካሚ ፣ ሐኪምና መድኃኒት ብለን መመደብ እንችላለን ። በሽተኛው የታመመው ነው ። ታካሚ መፍትሔ የሚፈልግ ነው ። ሐኪሙ አዋቂው ነው፣ መድኃኒቱ መፈወሻው ነው ። ሐኪሙና መድኃኒቱ ራሱ ክርስቶስ ነው ። ሰዎች ግን በሁለት ምድብ ላይ ናቸው ። ሁሉም በሽተኛ በመሆናቸው አንድ ሲሆኑ ታካሚ የሆኑት ወይም አዳኝ የሚፈልጉት ግን ጥቂት ናቸው ። ዛሬም በአማኒና በኢአማኒ መካከል ያለው ልዩነት በሽተኛ አለመሆን ሳይሆን አንዱ በሽተኛ አንዱ ታካሚ መሆን ነው ። ምእመናን ተመላላሽ ታካሚ ናቸው ። እኛ አገልጋዮች ደግሞ በሽታው ስለጠናብንና ከሐኪሙ መለየት ስለማንችል የአዳሪ ታካሚ ነን ። ዛሬም ሰዎች ከጌታ ሥጋዊ ፈውስን በሙሉ ፈቃድ ይፈልጋሉ ። መንፈሳዊ ፈውስን ግን አይፈልጉም ። ስለዚህ ለማወቅ እውነትን ፣ ለመዳን እምነትን ገፍተው ይኖራሉ ። ሥጋዊ ሞት ፈርተው ፈውስ ይፈልጋሉ ። መንፈሳዊ ሞትን ፈርተው ግን ማወቅና ማመን አይፈልጉም ። በምዕራፍ አምስት ላይ ያሉ ሁለት ታማሚዎች አንዱ የሚያቃስት አንዱ የማያቃስት ነው ። ሕመም ያለው በሽታ መፍትሔ ለማፈላለግ ይረዳል ። ሕመም የሌለው በሽታ ግን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ ይታወቃል ። በምዕራፍ አምስት ላይ ሁለቱም ታማሚዎች በሕይወት አሉ ። አንዱ አልጋ ይዞ አለ ፣ አንዱ እየተወዘወዘ አለ ። አንዱ አሞኛል ይላል ፣ አንዱ አያመኝም ጤነኛ ነኝ ይላል ። አንዱ ፈውስን ይፈልጋል ፣ አንዱ ፈውስ አያስፈልገኝም ብሎ ይናገራል ። ዳግመኛም ምዕራፍ አምስት ጌታ ለሙታን ቃል እንዳለው ይናገራል ። የእኛ ድምፅ አቅሙ የተኛን መቀስቀስ ይሆናል ። የሞተን የሚቀሰቅስ ድምፅ ግን የመድኃኔዓለም ነው ። ጌታ የሚፈልገው ለችግራችን ደጋግሞ መምጣት ሳይሆን በአንድ ጊዜ ቃሉ የዘላለም ችግራችንን መፍታት ነው ። የእግዚአብሔር ቃል ውጤቱ ከፍ ያለ ነው ። በቀትር ለጨለመበት የሚያበራ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ቃል ያድናል ፤ ቃል ይገድላል ። በየቀኑ ጥይት ላንተኩስ እንችላለን ። በየቀኑ ግን ቃል ይተኮሳል ። የቃል ኃይል ያለው ተናጋሪው ጋ ሳይሆን ተቀባዩ ጋ ነው ። “ምክርና ቡጢ ለሚሰነዝረው ቀላል ነው” ይባላል ። የእግዚአብሔር ቃል አይሻርም የምንለው የሚሻር ቃል ስላለ ነው ። የምንሽረውም በእግዚአብሔር ቃል ነው ። ዛሬ ሰዎች አስደንብሮ ለመግዛትና ሰላምን ለመስጠት ቃልን በሁለት መንገድ ይጠቀማሉ ። ሰዎች እንፈልጋችኋለን ሲሉን የምንደነብርበት ሁኔታ አለ ። የፈራነው ጥይት አይደለም ። ክፉ ቃል ነው ። በእውነት የሚያልፈው እንዲያሳልፋችሁ አትፍቀዱ ። የእግዚአብሔር ቃሉ ትንሣኤ ነው ።
ሽማግሌዎች ዋሽተው ያስታርቁናል ፣ ሸንጋዮችም ዋሽተው ያስደስቱናል። በእኛ ስፍራ ሁነን ሰዎችን ስንናገር በቊስላቸው ላይ ሚጥሚጣ እንነሰንሳለን ። በእግዚአብሔር ስፍራ ሁነን ስንናገር ግን ዘይት እናፈስሳለን። በእግዚአብሔር ቃል ከቆምን በሰው ቃል አንፈርስም ። ሰማይ ፍረስ ብንለው አይፈርስም ፣ የቆመው በእግዚአብሔር ቃል ነውና ። ምዕራፍ አምስት እውነተኛው ፋሲካ ፣ በፋሲካ በዓል ላይ እንደ ቆመ በመናገር ይጀምራል ። በበጎች በርም እውነተኛው በግ ክርስቶስ ሲገባ እናነባለን ። በምድር ላይ ያሉ ነገሥታት የተጠቀሱት “አውሬ” በሚል ስያሜ ነው ። ያለ ደም ስለማይኖሩ ። አንድ አባት ጓድ መንግሥቱ ባሉበት ስብሰባ ላይ ሲናገሩ “መንጌ አገር ይወዳሉ ፣ ነጻነት ይወዳሉ ፤ ደምም ይወዳሉ” ብለው ተናግረዋል ። የምድር ነገሥታት በደም ምንጣፍ ላይ ዙፋናቸውን ዘርግተዋል ። ጌታችን ግን በግ የተባለው ራሱን አሳልፎ ስለ ሰጠን ነው ። እርሱ በመምጣቱ እንኳን ሰዉ የሚሠዉት እንስሳትም አርፈዋል ። ሌላውን እያስገደለ ሊኖር አልመጣም ። እርሱ በግ ነው ሌላው እንዲኖር መጥቷል ። በግ የማትጎዳ ናት ። ለመሥዋዕት የምትፈለገውም ደም አፍሳሽ ስላልሆነች ነው ። ገዳይ መሥዋዕት መሆን አይችልም ። ዛሬ ሞት የሚገባቸው የቆሙት ሞት የማይገባቸው ስለ ሞቱ ነው ። የበጎች በር ይህን ያስታውሰናል ። ነጻነት የሰው ልጅ እኩልነት የሚባለው በመላው ዓለም እየተከበረ አይደለም ። ዛሬም ሰዎች ለባርነት ይሸጣሉ ። ይሰቃያሉ ። ነጻነት የተባለውም ሰውን ለኃጢአትና ለሱስ ባሪያ ማድረግ ነው ። እውነተኛ ነጻነት ግን በክርስቶስ ሁኗል ። የወደቀ ትውልድ የወደቀችውን አገሩን ማየት አይችልም ። እንዳይታዩ ነገሥታት ትውልድን በኃጢአት ያውራሉ ። ምዕራፍ አምስት ስለ ቤተ ሳይዳም ይናገራል ። ቤተ ሳይዳ ቤተ ሕሙማን ነበረች ። የሥጋ በሽታ የነፍስ በሽታ ወደ መሆን ያድጋል ። እንዴት ? ቢሉ ምሬት ፣ ኀዘን ያመጣል ። ከዚያ በሽታ ለመዳንም ፈዋሽና ጠንቋይ ሲያስስ ይኖራል ። የነፍስ በሽታም ወደ ሥጋ ይመጣል ። ጤነኛ እግር እያላቸው የሚያነክሱ አሉ ። ተስፋ ካነከሰ እግርም ያነክሳል ። የሥጋ መድኃኒት የተለያየ ነው ፣ የነፍስ መድኃኒት ግን አንድ ነው ። ቤታችን መድኃኒት የምናስቀምጠው ልጃችን እንዲታመም ፈልገን አይደለም። መድኃኒቱን ጌታ የምንይዘውም ድነን ለመቅረት ነው።
የቤተ ሳይዳ ታማሚዎች እምነት ነበራቸው ። እምነት መራመድ ነውና እስከ መጠመቂያው መጥተዋል ። ፈውሱ ግን በእምነት ብቻ ሳይሆን በሁኔታም ላይ የተመሠረተ ነበር ። መልአኩ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ  ይድን ነበር። ፈውሳቸው የሚረዝመው በእነርሱ ብርታትና ድካም ነበረ ። መጻጒዕ ሠላሳ ስምንት ዓመት ቢጠብቅም ዛሬ ቅደም የሚለው አልነበረም ። የበሽታ ሰዓቱም ዓመት ነው ። የመከራ ሰዓት ረጅም ነው ። የደስታ ጊዜ አጭር ነው ። አንዱ ቀን ላንዱ ሰው ዓመት ፣ ላንዱ ዕለት ነው ። አንዲት ልጅ የገና ቀን ቤታቸው ባዶ ነበርና ለሰው ገና ለእኛ ገና/ላለ አድርገህ አንብበው/ ነው ብላለች ።
አንዳንዴ ጎዳናውን ስናቋርጥ ወይም መኪና ይዘን ቀጥ የምንልበት አንድ ነገር ይገጥመናል ። ለደቂቃዎች እንቆማለን ። በደረቱ የሚሳብ ሰው እያለፈ ነው። እያማረርን ነበር ። አሁን ግን ሰውዬው መንገዱን እስኪለቅ ልባችን ያዝናል ። ስላማረርኩህ ይቅር በለኝ እንላለን ። ሰውዬውን አስችሎት እኛን ያስተምረናል ። ሠላሳ ስምንት ዓመት ስለ ታመመ የሚያማርር እንዳለ ሁሉ ሠላሳ ስምንት ዓመት ጤነኛ ስለሆነ የሚያመሰግን ግን የለም ። የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ ጉልበትና ፈቃደ እግዚአብሔር ያስፈልገው ነበር ። በኪኒን ለመዳን የምንሞክረውን ሙከራ ያሳየናል ። ለመታከም ገንዘብ ያስፈልጋል ። ኪኒኑ መዳኛ ሲሆም አዳኙ ግን እግዚአብሔር ነው ።
ትልልቅ ቤቶች ስናይ የደህና ሰው ቤት ነው እንላለን ። የቤቱ ባለቤት ግን ሰው ተኝቶ ከተማውን ሲዞር የሚያድር ዱርዬ ይሆናል ። ደህና ሰው የሚባለው ደህናው ክርስቶስ የደረሰለት ብቻ ነው ። መጻጕዕ ዛሬ ደህና ሰው ሆነ ። ባለጠጋ ማለት ከጌታ የተቀበለ ነው ። ከጌታ የተቀበለው ትንሽ፣ በስርቆት ካመጣው ብዙ ይበልጣል ። መጻጕዕ ሰው የለኝም ሲል ጌታ ሰው ሁኖ መጣለት ። ለአንድ ሳምንት በበሽታ ተኝተን ስንነሣ ዓይናችን ብርሃን ፣ እግራችን መሬት መርገጥ ይረሳል ። ሠላሳ ስምንት ዓመት ታሞ የተነሣው ሰው ግን አልጋውን ተሸክሞ ሮጠ። የጌታ ፈውስ ከቀድሞ ጤንነት በላይ ነው ። ፈውሱ ማገገም የለውም። ከጤንነቱ በላይ አትርፎ ኃይልን ይሰጣል ። በጤናው መሸከም የማይችለውን አልጋ በፈውሱ ያንከበክበዋል ። ትላንት ያጽናኑን ዛሬ ቃል አልቆባቸው ይሆናል። በተራችን እናጽናናቸው ። ትላንት የሰጡን ዛሬ ነጥፈው ይሆናል ። በተራችን እንስጣቸው ። የተሸከመንን እስክንሸከም ድረስ መዳናችንን እውነት እናድርግ ። ፈውስ መራመድ ሳይሆን የተሸከመንን መሸከም ነው ። እግዚአብሔር ይመስገን የሠላሳ ስምንት ዓመቱ ጥያቄ በአንድ ደቂቃ ተመለሰ ። ለዘመናት እስረኛ ንጉሥ ክርስቶስ የሰጠው ምሕረት ደስ ይላል ። ጌታ ባይቆርጠው ደዌው ለመቀጠል ገና አልጠገበም ነበር ። ሰልችቶት የሚሄድ መከራ የለም ። ጌታ ግን የመከራ ዕድሜን ይቆርጣል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ