የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ማጠቃለያ/4/

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” ይላል ። ለጉዳዩ አጽንኦት ለመስጠት ነው ። ቀጥሎ ያለውንም በትኩረት እንዲሰሙ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” ይላል ። “እውነት እውነት” ብሎ የነገረንን ነገር “እውነት እውነት” ብሎ መቀበል እርሱ እምነት ይባላል ። አብና ወልድ የክብርና የዘመን እኩያነት እንዳላቸው የነገረንን አሜን ብለን መቀበል አለብን ። ቃል የልብ መልእክተኛ እንደሆነ ወልድም የአብ መልእክተኛ ነው። ቃል የልብ መልእክተኛ በመሆኑ ተግባሩን ፈጸመ እንጂ ማነሱን አላሳየም ። በአንድ ሰው ቃል ውስጥ ልቡን እናያለን ። በወልድ ቃልነትም አብን አይተነዋል ። አብን ሊያሳይ የሚችል ቃል የሆነው ወልድ ብቻ ነው ። እንዲሁም በአብ ክብር ያለ በመሆኑ አብን ሊገልጠው ይችላል ። አብ ማለት ልክ እንደ ወልድ ነው ማለት ይቻላል ። ይህን አምኖ የሚቀበል የዘላለም ሕይወትን ያገኛል ። የዘላለም ሕይወት ማለት የዘላለም ኅብረት ማለት ነው። ከእግዚአብሔር ፊት ሳይታጡ መኖር እርሱ የዘላለም ሕይወት ነው ።
“እውነት እውነት እላችኋለሁ ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።” /ዮሐ. 5፥24/ ። የኢትዮጵያ ሕግ የሚፈልገው ሰው የኢትዮጵያን ድንበር ከተሻገረ በኋላ ያለ ፍርሃት እንደሚኖር እንዲሁም ጌታ ከሞት ግዛት የሚያወጣን እኛን ወደ ሕይወት በማሻገር ነው ። ሞትን የምናመልጠው ሕይወትን በማግኘት ፣ በመሻገር እንጂ በመማር አይደለም ። እዚህ ተቀምጠን የአሜሪካንን ሕግ ብናጠና የሚገዛን የኢትዮጵያ ሕግ ነው ። እንዲሁም በሞት ግዛት ተቀምጦ ስለ ሕይወት የሚያጠና ካልተሻገረ የሚገዛው የሞት ሕግ ነው ። የምናደርገውን ነገር ስናጠናው ውስብስብ ነው ። ቤት መጥረግን ቁጭ ብለን ስናጠናው ከባድ ነው ። ተነሥተን ስናጸዳው ግን የአምስት ደቂቃ ጉዳይ ነው ። ሕይወት የሚቀለው ስናጠናው ሳይሆን ስንኖረው ነው ። ምክንያቱም ሕይወት የተበጀችው ለመንቀሳቀስ ነውና ።
“እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም ። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና።” /ሮሜ. 8፥1-2/። አውጥቶኛል ማለት አሻግሮኛል ማለት ነው ። ኃጢአት ከሚያዝዝበት ፣ ሞት ከሚያንዣብብበት ክልል አውጥቶኛል እያለ ነው ። የኃጢአትና የሞት ሕግ የሚገዛበት ክልል አለ ። ጌታችን በቀኙ ባለው ስፍራ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስቀምጥ ከዚህ ግዛት ውጭ አድርጎናል ። የመሬት ስበት የሚያዝበት ክልል አለ ። ከክልሉ ከወጣን መንሳፈፍ እንጂ መውረድ የለም ። እንዲሁም ጌታችን መንፈሳችንን አሻግሮ በሰማያዊ ስፍራ ስላስቀመጠ ኃጢአት አይገዛንም ። ያን ጊዜ ክርስትና ግብግብ ሳይሆን የመንፈስ ረድኤት ይሆናል ። ወደ ሕይወት የተሻገረ ሰውም ወደ ሞት አይመጣም ። ብዙ መመለሻ ድልድዮች ተሰብረዋል ። ቀይ ባሕር እንደ ተከፈተ ቢቀር ኑሮ ከሦስት ቀን በኋላ እስራኤል እንመለስ ይሉ ነበር ። ቀይ ባሕር መከደኑ መመለሻው ድልድይ መሰበሩ ነው ። ዛሬም በክርስትናችን ጨካኝ እንድንሆን መመለሻ ድልድዮች ተሰብረዋል ። ተመልሰን ብንሄድ የሚጠብቀን ጠላትነት እንጂ ወዳጅነት አይደለም ። ዓለም ከክርስቶስ ወደኋላ የተመለሱትን በደስታ አትቀበልም ። እርሱ ክርስቶስ ቢተዉት የማይተዉ እንደሆነ ታውቃለችና ።
እረኝነት ሕይወታዊ ግንኙነት ነው ። ስለዚህ አንድ ሰው ሁለት እረኞች ሊኖሩት አይችሉም ። ሁለት ቤት የሚያድር ልጅ አንድ ቀን መንገድ ይቀራል ። አንዱ እዚያ አድሯል አንዱ እዚያ ሲል ጅብ ይበላዋል ። በአገልግሎት ውስጥ አንዱ ጋ መርጋት ያስፈልጋል ። የጌታችን ጥሪ ዋስትና ያለው ነው ። ስንቆም የማይቆም ፍቅር ነው ። ጌታችን የራሱ የሆነ ሰፊ ልብ አለው ። ጌታ እንደ አገልጋዩም ስላልሆነ ክርስትና ጣፋጭ ሁኗል ። በሕይወት ውስጥ የምናመልጠው ከፍርድና ከኵነኔም ነው ። ህልውና ለዓለም ትርጉሙ ነበረ ፣ አለ መባል ነው ። በክርስትና ግን ህልውና ከፍርድ ማምለጥ ነው ። የዘላለም ሕይወት ስፍራ ከመያዝ ያለፈ ነው ። ይሻገራል የሚለው አካሉን ሳይሆን መንፈሱን ነው ። መስሪያ ቤት አልቀየረም አቋሙ ግን ተቀይሯል ። ጌታ ለመንፈሳችን መሻገርን ይሰጣል ። ዮሐንስ አምስት ብዙ ቁምነገሮችን የያዘ ነው ።
ምዕራፍ 5፥25 ስናነብ የምንረዳው ነገር አለ ። የእግዚአብሔር ቃል ትዕቢተኞች ባይጠቀሙበትም ትሑታን ግን ሕይወት ያገኙበታል ። ሞት ማለትም ከእግዚአብሔር ርቆ መኖር ነው ። ሞት ጥልቅ ትርጉሙ የነፍስ ከሥጋ መለየት ሳይሆን የነፍስ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት ነው ። መንቀሳቀስ ፣ ስኬታማ መሆን የሕይወት መገለጫ አይደለም ። ያለ እግዚአብሔር የሚኖሩ ተንቀሳቃሽ ሬሳ ናቸው ። የተዋቡ አስከሬንም ናቸው ። የእግዚአብሔር ሥራ የሚጀምረው ከሙታንነታችን ነው ። ጌታችን ያገኘን ሙታን ሳለን እንጂ ታማሚ ሳለን አይደለም ። ከሞት የሚጀምር እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የምንወደውን ሰው ሲሞት እንሸሸዋለን ። ወዲያው ስሙን ትተን ሬሳው እንለዋለን ። ጌታ ግን የአራት ቀን ሬሳን አልዓዛር ብሎ በስሙ ጠራው ።  የእግዚአብሔር ድምፅ የሙታንን መንደር የሕያዋን ሰፈር የማድረግ አቅም አለው ። ሙታን ሰፈር አጠገብ ፣ ላጠገብ ቢኖሩም አያወሩም ። አጠገብ ላጠገብ መተኛት መግባባት አይደለም ። አንዱ አስከሬን ባንዱ ላይ ይጫናል ። ከበደኝ አይልም ። ነገሮች ከብደውን ከሆነ በሕይወት አለን ማለት ነው ። ምክንያቱም ሬሳን ፣ ሬሳ አይከብደውም ። በዚህ ዓለም ላይ ሙታኖች በመቃብር ፣ ተንቀሳቃሾች በአገር ስፍራ ይዘዋል ። ቦታ መያዝ ግን መኖር አይደለም ። አለን ብለን ለሰላምታ መልስ እንሰጣለን ። አለን ግን እየኖርኩ ነው ማለት አይደለም ። ያለን ወይም የምንኖር መሆናችንን የሚለየው ድምፁን መስማት ነው ። ድምፁን ስንሰማ ግን እንኖራለን ። ከእግዚአብሔር ቃልና ሕይወት ያሉትን ሲያጠፉ መደነቅና መክሰስ ተገቢ አይደለም ። ጌታ ስለ ሕይወት የሚጠይቀው ያመኑትን ነው ። ጌታ አይገረምብንም እንጂ ቢገረም በበላነው ልክ ባልወዛነው በእኛ ይገረማል።
ምዕራፍ አምስት ስለ ትንሣኤ ልቡናና ስለ ትንሣኤ ሙታን ይናገራል። ትንሣኤ ልቡና ላላገኙ ትንሣኤ ሙታን ጥቅም የለውም ። ትንሣኤ ሙታን ለሁሉ ሲሆን ትንሣኤ ልቡና ግን ላመኑ ብቻ ነው ። ትንሣኤ ዘለክብርና ትንሣኤ ዘለሐሣር አለ ። መነሣት ብቻውን አርኪ አይደለም ። ለምንድነው ? የተነሡት ማለት ያስፈልጋል ። ዛሬ ብዙ ሰዎች ተነሥተዋል ። አንዳንዱ አዋቂ አንዳንዱ ዐቃቤ ሃይማኖት ሁኖ ተነሥቷል ። መነሣት ብቻውን ግን ክብር አይደለም ። ለሐሣርም የተነሡ አያሌ ናቸው ።
ፍርዱ ዛሬ ነው ። ዕለተ ምጽአት አፈጻጸም ነው ። እርሱ በጎችንና ፍየሎችን ሊለይ ይመጣል ። በግ ሁነው የኖሩትን ፍየል ሁነው ከኖሩት ሊለይ ይመጣል ። በዕለተ ምጽአት ማንንም በግ ወይም ፍየል አያደርግም ። ዛሬ በግ ወይም ፍየል ለመሆን ምርጫው የእኛ ነው ። እርሱ በማንም አይፈርድም ፣ ምርጫችን ግን ይፈርድብናል ። የመረጥነውን ይከፍለናል ። በዚህ ዓለም በግና ፍየል ተቀላቅሎ ይኖራል ። በሚመጣው ዓለም ግን ይለያል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ