የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሦስቱ መብሎች

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት አስደናቂ የሆኑ መልእክቶች የተላለፉበት ምዕራፍ ነው ። ከምዕራፍ አንድ ጀምሮ ታላላቅ ምሥጢራት እየተላለፉ እዚህ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ። ስለ ቃል ቅድምና ወይም ዘላለማዊ ህላዌ በምዕራፍ አንድ ፣ ስለ እመቤታችን ምልጃና ስለ መጀመሪያው ተአምር በምዕራፍ ሁለት ፣ ስለ ዳግም ልደትና ምሥጢረ ጥምቀት በምዕራፍ ሦስት ፣ ስለ መንፈሳዊ አምልኮና እውነተኛ መገዛት በምዕራፍ አራት ፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜ በሥራ ላይ ስለመሆኑና ኢየሱስ ክርስቶስም ከአብ ጋር ተካክሎ ስለመሥራቱ  በምዕራፍ አምስት ተመልክተናል ። በምዕራፍ ስድስት ደግሞ ስለ ታላቁ ማዕድ እናያለን ። የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት ስለ ሦስት ዓይነት እንጀራ የሚናገር ምዕራፍ ነው ።
1-  የበረከተው እንጀራ
2-  የበረሃው መና
3-  የሕይወት እንጀራ
የበረከተው መና እግዚአብሔር የዕለት አምላክ ወይም የዕለት ቃልና እንጀራን የሚሰጠን መሆኑን ያሳያል ። የበረሃው መና እግዚአብሔር ለዘመናት የሚዘልቅ መጋቢ መሆኑን ያስተምረናል ። የሕይወት እንጀራ ስለ ዘላለማዊ የክርስቶስ ሥጋና ደም ይናገራል ። የበረከተው መና እግዚአብሔር ለአንድ ቀን እንኳ አይጥልም ይለናል ፣ የበረሃው መና እግዚአብሔር ለዘመናት ይንከባከባል እያለ ይጮኻል ። የሕይወት እንጀራ እግዚአብሔር ለዘላለም ይወደናል ይለናል ። የበረከተው መና የእግዚአብሔርን አዛኝነት ፣ የበረሃው መና የእግዚአብሔርን ታማኝነት ፣ የሕይወት እንጀራ የእግዚአብሔርን አፍቃሪነት ይናገራል ። የበረከተው መና እስከ ቤት ያደርሳል ፣ የበረሃው መና እስከ ከነዓን ያደርሳል ፣ የሕይወት እንጀራ እስከ ሰማይ ያደርሳል ። ምግብ ዓላማው ማድረስ ነው ። መኪና ነዳጅ የሚወስደው ለመቆም ሳይሆን ለመሄድ ነው ። የበረከተው መና እግዚአብሔርን ለዕለት ለሚፈልጉ ፣ የበረሃው መና እግዚአብሔርን እስከ ዕድሜአቸው መጨረሻ ለሚሹ ፣ የሕይወት እንጀራ ግን እግዚአብሔርን እስከ ዘላለም ለሚወድዱ የተዘጋጀ ነው ። የበረከተውን መና የበሉ በሥጋ ጀምረው በሥጋ የጨረሱ ፣ የበረሃውን መና የበሉ በእምነት ጀምረው በሥጋ የጨረሱ ፣ የሕይወት እንጀራ በእምነት ጀምረው በእምነት የጨረሱ የተካፈሉትና የሚካፈሉት ነው ። ዛሬ እያስፈራው ጌታ ፣ ጌታ የሚል ሰው አለ ። ትንሽ ልቡ ከተረጋጋ ይረሳዋል ። ነገ እያስፈራው ጌታ ፣ ጌታ የሚል አለ ። ገንዘቡ ጠርቀም ሲልለት ጀርባውን ይሰጣል ። ለዘላለም ሕይወቱ ጌታ ፣ ጌታ የሚል አለ ። ግቡ ሰማይ ነው ። የበረከተውን መና የበሉ ጌታን በአገራችን ንገሥ አሉት ፣ የበረሃውን መና የበሉ መናው ሰለቸን አሉት ። የሕይወት እንጀራ የበሉ ግን የእኔ ዓለም አንተ ነህ አሉት ።
የሦስቱም ማዕድ ባለቤት እግዚአብሔር ነው ። ሰው ሦስት ዓይነት ጥያቄዎች አሉት ፡-
1-  የዕለት ጥያቄ
2-  የዘመናት ጥያቄ
3-  የዘላለም ጥያቄ
 የሰው ልጅ የዕለት ጥያቄው የዕለት እንጀራ ነው ። እንዴት እውላለሁ? በማለት ይጠይቃል ። በይበልጥ ተኝተው ሲነሡ መልሶ ድካም የሚጫጫናቸው ፣ ብርሃን ወጥቶ ሳለ ተስፋ ግን የጨለመባቸው ገና በጥዋቱ ቀኑን እንዴት እውለዋለሁ ? ይላሉ ። ሁሉም ነገር ፍርሃት ፣ ፍርሃት የሚላቸው ፣ መዝናኛውን መጨነቂያ ፣ መሳቂያውን መርሐ ግብር ማልቀሻ እየሆነባቸው የተቸገሩ ቀኑ ግራ ያጋባቸዋል ። ብዙ ወዳጅ ከብቦአቸው ብርድ ብርድ እያላቸው ፣ ብዙ እንክብካቤ ተደርጎላቸው የተጣልኩ ነኝ ብለው የሚያስቡ ፣ በጠላቶቻቸው ፊት ለፊት ዘይት ቢቀቡም እነርሱ ግን ወይኔ እያሉ በራሳቸው ላይ አመድ የሚነሰንሱ ቀኑ ስጦታ ሳይሆን አውሬ ሁኖ ይሳልባቸዋል ። ሞትን ፈርተው ወደ ሞት የሚሄዱ ምስኪኖች ቀኑ ሃያ አራት ሰዓት ሳይሆን ሃያ አራት ዓመት ሁኖ ይሰማቸዋል ። አንድ ወጣትን እንዳናግረው ሰዎች ግድ አሉኝ ። ለመሞት ይፈልጋል ሲሉኝ ቶሎ ማናገር አለብኝ ብዬ ሥራዬን በሙሉ ትቼ መገስገስ ጀመርኩ ። ወጣቱ ጋ ሲደወልለት “ዛሬ አልችልም” አለ ። ምክንያቱ የሥራ መወዳደሪያ አስገብቶ ዛሬ ቃለ መጠይቅ ስላለበት ነው ። አዎ ሞትና ሕይወት የሚጋፉት ሰው ይመስላል ። መሞት ይፈልጋል ግን መኖር ደግሞ ይበልጥ ይሻል ።
ትላንት የሚያደርጉትን ዛሬ ማድረግ ሲያቅታቸው ፣ ግርግር ሱሳቸው እንዳልነበር ከቤት መውጣት ሲያስፈራቸው ፣ በአደባባይ መታየት ስእለታቸው እንዳልነበር ዛሬ ግን መሰወር ሲያምራቸው ፣ በደጎች ጨርሰው በክፉዎች መቅናት ይጀምራሉ ። እነዚህ ሰዎች በየማለዳው ግራ ይጋባሉ ። ስለዚህ አገልጋዩ ጋ ደውለው የሚያውል ቃል ንገረኝ ይላሉ ። እግዚአብሔር ቀኑ ምእት ለሆነባቸው “አጽናኑ ፥ አጽናኑ ፥ አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ” ብሏል /ኢሳ. 40 ፥ 1/ ።
አዎ እነዚህ ሰዎች ሰው ፈርተው ይንቀሳቀሳሉ ፣ ያኛውም ሰው እነርሱን ፈርቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ። ኃይለኝነት ፣ ቊጣ ፣ ግፍ ፣ ሐሜት ሲበዛ ምሥጢሩ ጭንቀት ጨምሯል ማለት ነው ። ባልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ አደጋ ውስጥ የሚጥል ጭንቀት ነው ። ላልሰነዘረባቸው ሰው ቡጢ ፣ ለሚወዳቸው ሰው ጦር የሚሰዱ ሰዎች ምሥጢሩ እውነት ሳይሆን ጭንቀት እያዋራቸው መሆኑ ነው ። እውነትማ ገና ፀሐይ ነው ፣ ቀኑ ያንተ ነው ። ያንተ ባትሆን ንጋት ላይ አረፈ ተብሎ የዕድር ጡሩንባ ተነፍቶልሃል ትላለች ። አዎ የመሸ የመሰለን ማለዳ ብዙ ነው ። የጨለመ የመሰለን ቀትር አያሌ ነው ። የምንሞት ሲመስለን በይበልጥ የምንኖርበት ዘመን እየመጣ ነው ። ታዲያ አንድ ጸሎት እንደ ኪራላይሶን መደጋገም ያስፈልገዋል ። “የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባክህ ትዕግሥት ስጠኝ ።” የታገሠ መሠረቱን ወደ ጉልላት ያደርሳል ። የታገሠ ከሚስቱ ይወልዳል ። የታገሠ ጠላቶቹ መልሰው ሰግደው ሲመጡ እንደ ዮሴፍ ያያል ። የታገሠ ጨለማ በብርሃት ፣ ፍርሃት በድፍረት ሲለወጥ ያያል ። የጠላትን ማስፈራሪያ እያዳመጠ ወደኋላ የሚል ግን ያሰበውን ደግ ፣ እግዚአብሔር ያሰበለትን መልካም ሳያገኝ ጠላት ያሰበበትን ክፉ ነገር ይጎነጫል ። አዎ ከልበ አምላክ ዳዊት ጋር፡- “አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ” ማለት ይገባል /መዝ. 117፥17/።
የዕለት እንጀራችንን ስጠን የሚለው ጸሎት የዕለት ቃልህን ለመንፈሳችን፣ የዕለት እንጀራን ለሆዳችን ስጠን ማለት ነው ። አንድ ቀን ትንሽ የሚሆነው እግዚአብሔር በመግቦቱ ከእኛ ጋር ሲሆን ብቻ ነው ። አሊያ እንደ አንድ ቀን ረጅም የለም ። ያስጨነቀን አንድ ከኖርንባቸው ዓመታት ይልቅ ረዝሞብን ያውቃል ። አገልጋዩ አንድ ቀን ካላገለገለ ይደክማል ። ምክንያቱም ሲሰብክ እርሱም ይሰበካልና ። ሴት ልጅ ምግብ የምትሠራው የሚበላ ሰው እቤት ውስጥ ካለ ነው ። የሚበላ ካለ ትሠራለች እርስዋም ትበላለች ። ለሌላው ሲያዘጋጅ ሰባኪውም አብሮ ይበላል ። ያለ እግዚአብሔር ቃል ቀኑ ዕዳ ሁኖ ይውላል ። በየቀኑ የሚተኮስ የጠላት መሳሪያ አለ ። ከጠላት ጋር የሚዋጉ ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ያደርጋሉ ፡-
1-  አካባቢውን የሚመስል ልብስ ይለብሳሉ ። አካባቢውን ስንመስል አካባቢው አሳልፎ አይሰጠንም ። አካባቢውን የሚመስሉት በስካር በዝሙት አይደለም ። እንደውም የብዙ ድሎች መዘግየት ስካርና ዝሙት እንደሆነ በየውጊያው ዐውድ ታይቷል ። ብዙ የጦር ጀነራሎች በሴቶች ተይዘዋል ። አካባቢውን መምሰል ኃጢአት የሌለበት መምሰል እንደሆነ ግልጽ ነው ።
2-  ሁለተኛው ምሽግ ነው ። ምሽግም ረጅም ሰዓት ለመዋጋት ይረዳል ። በጠላት ወረዳ ላይ መንጎማለል አይረዳም ። ፊት ለፊት ሲመጣ እንኳ የሚተኮሰው በርከክ ብሎ ነው ። በርከክ ማለት መጸለይ ነው ። ጠላትን ጥይት አይጥለውም ፣ መንፈስ ነውና ። ለዚህ ነው አባቶች “አቡነ ዘበሰማያት ጥይት ፣ ዳዊት ለሰይጣን ቦንብ ነው” እያሉ ።
3-  ከምሽጉ አጠገብ አሸዋ ይከመራል ። ከጠላት የሚተኮሰው በአሸዋው በርዶና ተቀብሮ ይቀራል ። አሸዋው ጥይት ማብረጃ ብሎም የጥይት መቃብር ነው ። አዎ በየቀኑ የሚተኮሰው የጠላት ጥይት ማብረጃው ቃሉ ነው ። ለዘላለም ብሎ እንጀራ የበላ ለመጨረሻ ጊዜ ብሎ ቁርሱን የቀመሰ ሰው የለም ። ትላንት ቃሉን ሰምቼ እንዴት ዛሬ ደከምኩ? ማለትም ተገቢ አይደለም ። ቃሉ የዕለት እንጀራ እንጂ የዓመት ቀለብ አይደለም ።
 ጌታችን የዕለት እንጀራን ይሰጣል ። ቀኑን ከነፍላጎቱ የሚሰጥ እርሱ ነው ። ቀኑን የሰጠ እርሱ በጀቱንም አይነሣንም ። ምነው ያጡ የነጡ ፣ የተራቡ በዝንብ የተወረሩ አሉ አይለም ወይ ? ቢሉ የእነርሱን ድርሻ የእኛን ሲልክ ደርቦ ልኮላቸው ነበር ፣ እኛ አስቀርተንባቸው ነው ። ስለዚህ እኛ እንጀራን እነርሱ ደስታን ፣ እኛ አልጋን እነርሱ እንቅልፍን ይዘዋል ። እንጀራቸውን ስንሰጣቸው ደስታውን ይለቁልናል ፣ አልጋውን ስንዘረጋላቸው እንቅልፉን ይሰጡናል ። ጌታችን በምዕራፍ ስድስት እንጀራ አበርክቶ የራበውንና ሲመለስ የሚርበውን ሕዝብ መገበ ። አንዳንድ ደግ ሰዎች የተራበን ያበላሉ ። በጣም ደግ የሆኑ ደግሞ ቅድም የበላኸው አሁን ይጠፋል መንገድ ላይ ይርብሃል ብለው እንደገና ማዕድ ያሰናዳሉ ። አዎ ፍቅር ካለን፡-
·       ወንዴም እርቦት ይሆናል እንላለን ።
·       ወንድሜ ሲመለስ ሊርበው ይችላል እንላለን ።
ትንሽ ቆየት ያለ ነገር ይመስለኛል ። እንግዳ ሲመጣ ማዕድ ማቅረብ እየተረሳ ነው ። የሚገርመው ቆጥበንም አላተረፍንም ። ሰውን ስንሸኝ ዝርዝር ሣንቲም ለመሣፈሪያ አለህ ይሆን ? ብለን መጠየቅ እየቀረ መጥቷል ። እኛ ከዓይኑ ሰወር ስንልለት ስንቱ በእግሩ ይሄድ ይሆን ? ልብስ ገልጦ ፣ ጓዳን ዘልቆ የሚያይ ጌታ ካላየው ብዙ ሰው ተቸግሯል ። ብዙ የጠገቡ ሰዎች ንግግር ግን የተራቡ ሰዎችን አናግሬአለሁ ። “ሠርቶ አይበላም ወይ ?” ይላሉ ። የሞላለት ሁሉ የሞላለት ይመስለዋል ። የሚያሳስበው ገንዘብ በጨካኝ ሰዎች እጅ እየወደቀ መምጣቱ ነው ። ስለዚህ የድሆች ጉዳት ሊብስ ይችላል።
 የዘመናትን መና በበረሃ የላከ እግዚአብሔር ነው ። ምዕራፍ ስድስት ስለዚህ መብልና መና አውራጁ ማን መሆኑን ይናገራል ። ዐርባ ዓመት በምድረ በዳ የሚመግብ እግዚአብሔር እንዴት ምስጉን ነው ! ከሥር የውርጭ ሰደቃ/ገበታ አንጥፎ ፣ ከላይ የደመና ጥላ ዘርግቶ የሚያበላ ፣ አክብሮ የሚሸከም አምላክ እርሱ ነው ። የጥንት ባላባቶች አሸከር መብራት አስይዘው እራት በመብላታቸው ያንን ዘመን ረግመናል ። ዛሬም በየሆቴሉ እያሽቆጠቆጥን የምናዝዛቸው ከጥንቶቹ በላይ አልሆንባቸውም ወይ ? የጥንቶቹ መብራት ለያዘው ጉርሻ ያጎርሱ ነበር ። እኛም ትንሽ ስጦታ ጣል አድርገን እንወጣ የለም ወይ ? ከጥንቱ የተለወጠ ስያሜ እንጂ ሁሉም ነገር እንደ ድሮው ነው ። ባላባቶች ድሆችን ጭሰኛ አድርገው ያሳርሱ ነበር ። ዛሬም ገንዘብ ካለው አገር ገዝቶ ድሆችን ማፈናቀል ይችላል ። እግዚአብሔር እንደ ጌታ መና አውራጅ ፣ እንደ አሽከር ገበታ አንጣፊ ጥላ ያዥ ሁኖ ሕዝቡን አገለገለ ። እንደ እርሱ ያለ ልዑል ፣ እንደ እርሱ ያለ ትሑት አይገኝም  ። ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ ከፍታንም ዝቅታንም ወርሷል ።
 የዘመናት ጥያቄ የብዙ ሰዎች ነው ። እንዴት እኖራለሁ ? ዛሬ ምን እበላለሁ የሚሉ ሰዎችን ያህል እንዴት እኖራለሁ ? የሚሉ አያሌ ናቸው ። ድሆች ስለ ዛሬ ፣ ባለጠጎች ስለ ነገ ይዋትታሉ ። ስለ ነገ የሚያስብ ቢያንስ ለዛሬ የሚበቃ ያለው ነው ። ጡረታው የሚያሳስበው ፣ ቤት አለመሥራቱ የሚያስጨንቀው ነገር ግን ወጥቶ ለመግባቱ እርግጠኛ መሆን ያልቻለው ወገን ብዙ ነው ። ሰው ሞት ላይ ቆሞ ሕይወትን የሚያቅድ ፣ ሕይወት ላይ ሁኖም ሞትን የሚያቅድ ነው ። ለዚህም ዕድርና እቁብ የሚባሉትን ጥንታዊ ባንክ ቤቶች ማስታወስ በቂ ነው ። ዕድር ለሞት ፣ እቁብ ለሕይወት ። ሁለቱም በአንድ ቀን ይከፈላሉ ። ጥዋት እድሩን ፣ ከሰዓት እቁቡን ከፍሎ ይመለሳል ። ሰው በቀን ውስጥ ሞትና ሕይወትን ይኖራል ። አዎ የንግድ ቦታው ሊፈርስ ይችላል ። መሥሪያ ቤቱም ሊዘጋ ጭምጭምታ አለ ። መኖር ግን በመድኃኔ ዓለም ነው ። ዕለትም ፣ የሚመጣውም ዘመን ፣ ደግሞም ዘላለም ለሚያሳስበው መልሱ አንድ ነው ። ባለ ገበታው ክርስቶስ ። በበረከተው እንጀራና በበረሃ መና ምግብ የሰጠ በሦስተኛው ግን ራሱ ምግብ ሁኖ መጣ ።ምዕራፍ ስድስት የዘመናት ጥያቄ ያለባቸውን የሚከራይ ቤት የሚጦር ልጅ የሌላቸውን የሚመክር ነው ።
 የዘላለም ሕይወት የብዙ ሰው ጥያቄ ነው ። አንድ ቀን በኖርን ቊጥር ከምድር እየራቅን ወደ ሰማይ እየቀረብን ነው ። የሰው ልጅ ሞት እያለበት ሞትም አጠገቡ ያለውን ወዳጅ ሲወስድበት እያየ እሞታለሁ ብሎ የማያስበው እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሕይወት ስለፈጠረው ሞት ግን በአቋራጭ የገባ መሰናክል ስለሆነ ነው ። አዎ የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ የዘላለሙ አምላክ ብቻ ነው ። ለዚህም ሥጋና ደሙን ሰጠን ። የፍጡር ሥጋ መብላት እርም ነው ። የክርስቶስን ሥጋ በእምነት መቀበል ግን እርሱ ሕይወት ነው ። ምዕራፍ ስድስት ስለ ሦስቱ መብሎች ይናገራል ። የዕለት ፣ የዘመናት ፣ የዘላለም መብሎች የሚገኙበት ምዕራፍ ነው ።
 ሰውዬው ማዘንጊያ የምትባል ሚስት አገቡ ። ማዘንጊያም እንግዳ መጣና ሁለት እንጀራ አቀረቡ ። ባል ማዘንጊያን ጠየቁ ፣ ለስለስ ባለ ድምፅ “ማዘንጊያ ለእንግዳ ሁለት እንጀራ ይቀርባል ?” አሉ ። ማዘንጊያም “አይበላውም ብዬ ነው” አሉ ። ባልም “ማዘንጊያ ቢበላውስ” ብለው መለሱ ይባላል ። እንግዳውን በሚመለከት ምግብ ማቅረቡ ለዚያ ትዳር ጥያቄ አልነበረም ። አንደኛው ወገን ዓይኑ ይጥገብ ብሎ ወይም ሁለቱንም አይበላውም ብሎ ሁለት እንጀራ ያቀርባል ። አንደኛው ወገን ላይበላው ሁለት እንጀራ ለምን ይቀርባል ? ከበላው ደግሞ ለቤት ምን ይቀራል ? እያለ ያስባል ። አንድ ዓይነት ደግነት ሁለት ዓይነት አስተሳሰብ አለው ። እግዚአብሔር ግን በሥጋም በነፍስም ማዕድ ሲያቀርብልን አይበሉትም ብሎ አይደለም ። ይበሉታል ብሎ ነው ። ሳይጎድልበት የሚሰጥ ነውና ቢበላውስ ? ብሎ አይሰጋም ። ብሉ ፣ ብሉኝም ያለ እርሱ ብቻ ነው ።    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ