የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚያደርገውን ያውቃል

“ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን ፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? አለው ።” /ዮሐ. 6፥5/ ።
ጌታችን በተራራ ላይ የተቀመጠው ከበታች ያሉትን በንቀት ለማየት አይደለም ። በተራራ ላይ የተቀመጠው ሕዝቡን በርኅራኄ ለማየት ነበር ። ተራራ የከፍታ የሥልጣንና የልዕልና ምሳሌ ነው ። ተራራ የዘላለማዊነት ተምሳሌትም ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ወደ ከፍታ እስኪወጡ ትሑታን የሚሆኑ ፣ ከፍታ ላይ ከወጡ በኋላ እሳት የሚያዘንቡ አያሌ ናቸው ። “ጅብ እስኪነክስ ያነክስ” ይባላል ። ከነከሰ በኋላ ማንም አያስለቅቀውም ። ጌታ ግን ተራራ ላይም ትሑት ነው ። መውጣትና መውረድ የሌለበት በራሱ የከበረ ንጉሥ ነውና ።  ትሕትና ባሻገር ያለውን ፣ ከተራራው ግርጌ የሚንፏቀቀውን ሕዝብ በአዛኝነት ማየት ነው ። ትሕትና ለወገኔ ምን ላድርግለት እንጂ ምን ያደርግልኛል ? አለማለት ነው ። አንድ ሰው በአደባባይ ሲናገሩ ፡- “የበላይ ለበታች የማያዝንበት ፣ የበታች ለበላይ የማይታዘዝበት አገር አያድግም” ብለዋል ። የበላዮች ለበታቾች መራራት አለባቸው ። ምናልባት የበላዮች ከበታቾች አድናቆት ፈልገው ያንን ሲያጡ ይጨክኑ ይሆን ? “ንጉሥ በግንቡን ሳይታማ አይውልም” ይባላል ። ሰውዬው እንቅፋት ከሥር ወደ ላይ ሲያነሣው ፡- “አወይ ይሄ መንግሥት የት አገር ሄደን እንኑር” አለ ይባላል ። ቢሆንም ሕዝብ ምልስና ገራም ነውና በአባታዊ ስሜት ሲያናግሩት የበለጠ መንገድ ያሳያል ።
ጌታችን ባሻገር ወደ እርሱ የሚመጡትን ሕዝብ አየ ። ገና ሳይደርሱ እርሱ ስለሚበሉት ያስብ ነበር ። ደግሶ ሊቆያቸው ፈለገ ። ማዕድ ቤት በሌለበት ምድረ በዳ ላይ አብስሎ ሊመግባቸው ፈለገ ። እርሱ ተዘዋዋሪ መምህር ነው ። እርሱ ተዘዋዋሪ ሐኪም ነው ። እርሱ ተዘዋዋሪ ምግብ ቤት ነው ። ያለ ዩኒቨርሲቲ ብዙዎችን ሊቅ ያደረገ ፣ ያለ ሆስፒታል ብዙዎችን የፈወሰ ፣ ያለ ሆቴል ብዙዎችን ያጠገበ ነው ። በከፍታ ላይ ሲሆኑ ከታች ያለው አንሶና ደቅቆ ይታያል ። ከፍ ያሉት ዝቅ ያሉትን የሚያዩት እንደዚህ ነው ። እርሱ ግን በመንገድ የዛለውን ፣ በበሽታ የተጥመለመለውን ፣ ወዴት እንደሚሄድ የማያውቀውን ፣ በአገሩም በራሱም ተስፋ የቆረጠውን ያንን ሕዝብ አዝኖለት አየው ። ምንም እንኳ እየመጣ ያለው ሕዝብ ምእመን ለመሆን ያልተዘጋጀ ቢሆንም እርሱ ግን ደግነቱን አላሳነሰባቸውም ። የሕዝቡን ልብ ማወቁ ለመጨከን አላበቃውም ። እንደውም ራራላቸው ። ማወቅ የመራራት እንጂ የጭካኔ መሠረት መሆን የለበትም ። በሰው ዓለም መተዋወቅ ያናንቃል ፣ ያጨካክናል ፣ ያሰዳድባል ፣ ያደፋፍራል ። እግዚአብሔር ሲገለጡለት ነጩን ሸማ ያለብሳል ።
በኤልያስ ዘመን እስራኤልና ንጉሡ አክአብ በአል ለሚባል ጣዖት ተንበርክከው ነበር ። በአል የዝናብ አምላክ ተብሎ የሚጠራ ነው ። ኤልያስም ለአንዱ አምላክ አምልኮ ቀንቶ በአል ዝናብ ይስጣቸው ብሎ ሰማይን ገዘተ ። ምድርንም አሰረ ። ሰማይ ጠልን ፣ ምድር ዘርን ነፈጉ ። ሕዝቡ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በረሀብና በጥማት ተቆላ  ። የታመኑበት በአልም ዝናብ መስጠት አልቻለም ። የዝናብ አምላክ ተብሎ ስሙን ብቻ ታቅፎ ቀረ ። ኤልያስም እፍኙ ዱቄት በርክቶ ፣ ጭላጩ ዘይት በዝቶለት በመበለቲቱ ቤት መኖር ጀመረ ። እግዚአብሔር ግን ሕዝቡ ቢራብና ቢጠማም እንዳልተመለሰ አየና ራራ ። አባት ልጁን ሲቀጣ ልጁ እልሁ እየጨመረ ከመጣ አባት ዱላውን ያቆማል ። ዱላውን ማቆሙ አባት ልጁን ገዳይ እንዳይሆን ፣ ልጅም በሞኝነት እንዳይሞት ነው ። እግዚአብሔርም ሕዝቡ ላይመለስ በረሀብ ሲጠቁር ግድ አዘነለት ። ኤልያስም ያሰረውን ሰማይ እንዲፈታ እግዚአብሔር ነገረው ። የእግዚአብሔር አሳቡ ሕዝቡ እየበላ ይካደኝ ብሎ ነው ። አዎ ለካዱት እንኳ የሚራራ አምላክ ነው ። በዚህም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስትም ላይ ለማያረኩት ሕዝብ ራራ ።
ገና ወደ እርሱ ሳይቀርቡ ስለሚበሉትና ስለሚያርፉበት አሰበ ። ገና ሳንፈጠር የሚያስፈልገንን ያዘጋጀ እግዚአብሔር እርሱ ነው ። ይህ ያስፈልገናል ብለነው ሳይሆን ያስፈልጋቸዋል ብሎ ሁሉን ያዘጋጀ እርሱ ነው። የምንኖረው የተዘጋጀልን ስላለ እንጂ ለራሳችን ስለ ተጨነቅን አይደለም ። ጭንቀታችን የሚያቀርበው ነገር የለም ። እንደውም የቀረበውን ያርቃል እንጂ። ጌታችን ዓይኖቹን አቅንቶ አየ ። አጠገቡ በነበሩት ደቀ መዛሙርት አልተወሰነም ። ከከበቡት ባሻገር አየ ። እኛም በደቀ መዛሙርት ብቻ እንዳንወሰን ፣ በልጆቻችን ብቻ እንዳንታጠር ፣ ባሻገር ያሉትን ፣ ከሩቅ የሚመጡትን ፣ ገና የሚወለዱትን ማየት አለብን ።
በተራራው ላይ ጌታ የሚመጣውን ሕዝብ ሲያይ ደቀ መዛሙርት የተነሡበትን ቦታ እያዩ ይመስላል ። ጌታ እንዴት ሁሉን አስትቶ የሰጣቸውን ደስታ እያሰቡ ይሆናል ። ሁሉን ይዘን ያጣነውን ሰላም ሁሉን ትተን ማግኘት የሚገርም ነው ። ሁላችን ስለ ራሳችን እናስባለን ፣ እርሱ ግን ስለ ሁሉ ያስባል ። ጴጥሮስ ከተራራው ባሻገር ጥብርያዶስን ሲያይ ምን ይሰማው ይሆን? “የረገጥኩትን መልሼ ከምረግጥበት ከድግግሞሽ ኑሮዬ ፣ እልፍ ከማልልበት የዙረት አምባዬ አወጣኸኝ” እያለ ይሆን ?
ደጃች ባልቻና ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተማረኩበትን ቦታ ይጎበኙ ነበር ። ደጃች ባልቻ የማረኩአቸው ሲሰልቧቸው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ግን በደህና ሰው እጅ ወድቀው ነበር ። ምርኮኛ መልሱ ሲባል እነዚህን ሁለት ወጣቶች ለቤተ መንግሥት አስረከቡ ። ወጣቶቹም በብልሃታቸውና በጀግንነታቸው በምኒልክ ቤተ መንግሥት ባለሟል ሆኑ ። ታዲያ ደጃችና ፊታውራሪ የተማረኩበትን ቦታ ሊያዩ ሄዱ ። ደጃች ባልቻም፡- “ፊታውራሪ ይህን ቦታ አስታወስከው ? የተማረክንበት እኮ ነው” ሲሏቸው ፊታውራሪም፡- “ምን የተማረክንበት የተባረክንበትም ነው” ብለው መለሱ ። ፊታውራሪ እዚህ ቦታ በመማረካችን ሥልጣን ላይ ወጣን ማለታቸው ሲሆን ቅኔው ግን የደጃችን መሰለብ የሚያስታውስ ነው ። ጴጥሮስና ደቀ መዛሙርቱ ግን ይህችን ቦታ ሲያስቡ በረከቱ ብቻ ትዝ ይላቸዋል ። የዓለም መባረክ መታረድም አለው ። ብዙ ወጣቶች “ተባረክ” እያሉ ይመርቃሉ ። ሽቅብም አባቶችን ሊሉ ይሞክራሉ ። በረከት ከተሾመ ወደ ታች የሚወርድ ነውና ተገቢ አይደለም ። ተባረክ የሚለው ቃል ግን ታረድ እንደ ማለትም ነው ። ከሆነም “እግዚአብሔር ይባርክህ” ማለት ተገቢ ነው ። እንደ ዘመኑ ሰላምታ መከርከም ተገቢ አይደለም ።
ጌታ ገና የሚወለዱትን ፣ ገና የሚመጡትን ያያል ። ለዘመኑ የሚሆኑም አባቶችና አገልጋዮች ያስነሣል ። ገና ለሚመጡት ማሰብ ያስፈልጋል ። ቤት ስላለ ብቻ ልጅ አይወለድም ። አገርም እንደሚያስፈልገው ማሰብ አለብን ። ልጅ የቤት አባል ብቻ ሳይሆን የአገር ዜጋም ነውና ። ለመጪው ትውልድ እየታሰበ አይመስልም ። እግዚአብሔር የዚህችን ዓለም በረከት ያስቀመጠው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሚመጣውም ትውልድ ነውና መጠንቀቅ አለብን ። እኛ የቤት ሥራችንን ባልሠራን ቊጥር ለቀጣዩ ትውልድም ጫና እናበዛበታለን ። የአባቶችን ዕዳ ልጅ እንደሚከፍል ማወቅ አለብን ። ትርፍ ማቆየት ባንችል ዕዳ እንኳ እንዳንጥል መጠንቀቅ ያስፈልገናል ። አቤት ሕንጻ እየተገነባ ትውልድ እየፈረሰ ያለባት ይህች ጎስቋላ ዓለም ታሳዝናለች ።
ምንም እንኳ እርሱን ፈልገው ባይመጡ እርሱ ግን አሰበላቸው ። ሲመለሱ መንገድ ላይ በረሀብ እንዳይቀሩ ሊጋብዛቸው አሰበ ። ከመምጣታቸው በፊት ያያቸው ከመምጣታቸው በኋላ ያለውን እያየላቸው ነው። ምግቡ ከረሀብ የሚታገሡበት መና ፣ ወደ ቤት የሚመለሱበት ስንቅ ነበር ። አትርፎ የሚቋጥር ጓዳን የሚያውቀው መድኃኔ ዓለም ብቻ ነው ። መምጫችንን ብቻ ሳይሆን መሄጃችንን የሚያውቀው እርሱ ነው ። እርሱ የሚያየው በተራ እይታ አይደለም ።
·        ኦ የክርስቶስ ማየት በፍቅር ለማከም ማየት !
·        ኦ የክርስቶስ ማየት በረሀብ የደከመውን ለመደገፍ ማየት !
·        ኦ የክርስቶስ ማየት ሰው ሁሉ የፈረደበትን በምሕረት ለመሸኘት ማየት!
·        ኦ የክርስቶስ ማየት “ምን ሆነ” ? ብቻ ሳይሆን “ምን ይሆናል?” ብሎ ማየት
·        ኦ የጌታ ማየት እስክንለወጥ የሚታገሥ ማየት
በመመስገኛው አደባባይ በዓይነ ምሕረት የሚያየው በተራራው ላይ ሁኖም በፍቅር አየ ። ሳያዩት ቀድሞ አያቸው ። በማየት የቀደመው ፣ እስኪያዩኝ አላያቸውም የማይለው እርሱ ቀድሞ አያቸው ። አጋርን በኩሽና የሚያያት አሁንም በምድረ በዳ ስትንከራተት አያት ። “ኤልሮኢ” የተባለው እርሱ አያት ። ምስጋናውንም “የሚያየኝን በዚህ ደግሞ አየሁት” አለች ። ኩሽናም ምድረ በዳም ሁለቱም ተመልካች የሌለባቸው ፣ የሚያጠቊሩ ቦታዎች ናቸው ። እግዚአብሔር ግን ሁኔታው ሳያግደው ያያል ። ዛሬም ድካሙ ያጠቆራችሁ ፣ ምድረ በዳው አሸዋ ያለበሳችሁ ፣ ፊታችሁ የጨለመባችሁ ፣ ቀትር እኩለ ሌሊት የሆነባችሁ እግዚአብሔር ያያችኋል ። ለብዙዎች ደግ ፣ ለመንገደኛ ቸር የሆኑት ሰዎች ለእናንተ የጨከኑባችሁ እግዚአብሔር ግን ያዝንላችኋል ። አጋርን ያሳደዷት አብርሃምና ሳራ ናቸው። እግዚአብሔር ግን ደጎች ያልቻሉትን ሰው ፣ አልችለውም ብሎ አይጥለውም ። ዛሬም እናምናለን ፣ ክርስቲያን ነን እያሉ የገፉአችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁ ። አዎ ድነናል የሚሉ ግን ሲገድሉ የሚውሉ አያሌ ናቸው ። ወንጌልን ሽፋን አድርገው አፍሪካን ሲያስወርሩ የነበሩ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚታገሉ እየበዙ ነው ። ኢየሱስ ዛሬ የመጣ እስኪመስል ያዙኝ ልቀቁን የሚሉ ፣ ትንሽ እውቀት አብሾ የሆነባቸው ፣ ለወላጆቻቸው ምጥ የሚያስተምሩ ልጆች እየፈሉ ነው ። በእነዚህ የተጎዳችሁ ለቤተ ክርስቲያን የሞተላት አምላክ እንደማይጥላችሁ ፣ እንደገና በጠሉአችሁ ፊት እንደሚያከብራችሁ እመኑ ። ብቻ በሃይማኖት ጽኑ ።
የመጣውና እየመጣ ያለው ብዙ ሕዝብ ነበር ። ምናልባት ከሰባት ሺህ እስከ ዐሥር ሺህ ሊሆን ይችላል ። እስራኤልን በምድረ በዳ የመገበ ጌታ እነዚህንም ሊመግባቸው ፈለገ ። እርሱ በዘመናት ያው ነውና ። አጉረምራሚዎቹን እስራኤልን በምድረ በዳ አልጨከነባቸውም ፣ እነዚህን ምልክት ፈላጊዎች ጌታ አልጨከነባቸውም ። እየመጣ ያለው ሕዝብ መጥቶ ሳያበቃ ጌታ አሰበለት ። ቀድመን ካልተዘጋጀን ብዙ ዓይነት ጥያቄና ፍልስፍና ይዞ የሚመጣ ትውልድ አለ ። የትላንቱ የፖለቲካ ትራፊ ነበር ። የአሁኑ ግን ኃጢአትን ጽድቅ የሚያደርግ ትውልድ ነው ። በምዕራባውያን ሃይማኖት መሰል ነገር የተለከፈ ፣ በተባራሪ እውቀት የደነገጠ ትውልድ እየመጣ ነው ። ብዙ የነገረ መለኮት ምሁራን ፣ ብዙ የሥነ ልቡና አማካሪዎች ፣ ብዙ ሸፋኝ ካህናት ያስፈልጉናል ። ቤተ ክርስቲያንን አውቀው የማይገልጡአት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሊባሉ አይገባምና ቶሎ ብሎ አሰልጣኞቹን ማሰልጠን ይገባናል ። አሊያ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ይሆናል ነገሩ ።
ወደ እርሱ እየመጣ ያለው ሕዝብ እርሱን ሳይሆን ተአምሩን ፈላጊ እንደሆነ ፣ ተአምር ሲያይ ላንግሥህ የሚል ፣ ተአምር ሲጠፋ ወደ ኋላ የሚመለስ ቢሆንም እርሱ ግን ሳይታዘብ እንደ ሩቅ አገር እንግዳ ሊቀበለው ነው ። መጣሁ ሳይል እየመጡ ነው ብሎ ሊቀበላቸው ነው ። ምን ዓይነት ፍቅር ነው ። በሰው ገበና የሚነግዱ ፣ በሰው በሽታ ማስታወቂያ የሚሠሩ ነቢያተ ሐሰትን ስናይ ጌታችን መጽናናት ይሰጠናል ። በሰው ያዘነ በሰው ላይፈወስ ይችላል ። አምላካችን ግን ይፈውሳል ። እንደዚያኛው ትውልድ የእኛም ዘመን ዘማ ትውልድን የሚያስተናግድ ነው ። ዘማ በአሚኑ የማይጸና ፣ ቃል ኪዳን የሌለው ማለት ነው ። በአንድ አምላክ ፣ በአንድ ጉባዔ ፣ በአንድ እረኛ የማይረጋ ዘማ ትውልድ ነው ።
ወደ ጌታ የሚመጣው ሕዝብ ጌታን አላየውም ፤ ጌታ ግን ያየው ነበር ። እርምጃውን ብቻ ሳይሆን የልቡንም ስሜት ያይ ነበረ ። ለደቀ መዛሙርቱ ግን ለርካሽ ጥቅም የሚመጣውን ያንን ሕዝቡ እዩት አላለም ። እንደውም እንዲያዝኑላቸው ምግብ እንዲያዘጋጁላቸው ተናገረ ። እርሱ ያየውን አያሳይም ። ምን እንስጣቸው ? ብሎ ፊልጶስን ሲጠይቀው ፊልጶስ መልስ እንደሌለው ያውቃል ። ነገር ግን እንዲራራ እያነሣሣው ነው ። ትልቁ ነገር አቅም አይደለም ፣ መራራት ነው ። ስንራራ የመለኮት አቅም ከእኛ ጋር ይሆናል ። ከሁሉ በላይ የሚያደርገውን ያውቃል ። ከሰው ድርሻም ይፈልጋል። አማኒው ግን እግዚአብሔር ከተማውን እንዲያጸዳለት ምነው ዝናብ በዘነበ እያለ ይለምናል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ