የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጌታው አንድ አማኙ ሦስት

አንዱን ጌታ ብዙ ዓላማ ያላቸው ሰዎች ይከተሉት እንደ ነበር የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት ይነግረናል ። በዚህ ምዕራፍ ላይ በሦስት ዓይነት ዓላማ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እናገኛለን፡-
1-  እንጀራ ፈልገው የሚከተሉት
2-  በቃሉ ለመጽናናትና ዛሬን ለመርሳት ብቻ የሚከተሉት
3-  የዘላለም የሕይወት ቃል ስላለው የሚከተሉት ናቸው ።
እነዚህ ተከታዮች ለሆድ ፣ ለአእምሮና ለነፍስ የሚከተሉት ነበሩ ። ለሆድ የሚከተሉት ተአምራት ሲያዩ እናንግሥህ የሚሉ ነበሩ ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ካልበሉ የማይስቁ ናቸው ። ለሥጋዊ ኑሮአቸው ስኬት ብቻ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገሰግሱ ፣ ስእለት የሚሳሉ ፣ ደግሰው የሚያበሉ  አሉ ። እነዚህ ሰዎች ቃለ እግዚአብሔርን ስሙ ሲባሉ ፈቃደኛ አይደሉም ። መንፈሳዊ ዲስፒሊን ውስጥ ለመግባት የማይፈልጉ ፣ የሚሹትን ሲያገኙ ነጥቀው ለመሮጥ የተዘጋጁ ናቸው ። እነዚህ የእንጀራ ልጆች ናቸው ። እግዚአብሔር የጸጋ አባት ሊሆናቸው ሲፈልግ እነርሱ ግን የእንጀራ አባት ከሆንከን ይበቃናል እያሉ ይመስላል ። የእንጀራ አባትና የእንጀራ ልጅ የሚያገናኛቸው ባሕርያዊ ልደት ወይም ጽኑ ፍቅር ሳይሆን መኖር ሊሆን ይችላል ። /ሁሉም እንጀራ አባትና ልጆች እንዲህ አይደሉም ። ከወለደና ከተወለደ የሚያስንቁ አሉ/።
በዚህ ምዕራፍ ጌታን የሚከተሉት ሁለተኛዎቹ ወገኖች ፡- ለአእምሮአቸው መረጋጋት ብቻ ጌታን የሚከተሉ ፣ ዕለታዊ መጽናናት ያግኙ እንጂ ስለ ዘላለማዊ ሕይወት የማያስቡ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ጠንከር ያለ የክርስትናን ትምህርት መስማት አይፈልጉም ። ወደ ምሥጢራት መቅረብ አይሹም ። የዛሬ መጽናናትና ነገሮችን መርሳት የሁልጊዜ ፈውስ ይመስላቸውና ከእግዚአብሔር ቤት ይርቃሉ ። ችግራቸው ግን የበለጠ አድጎ ፣ ተሰብረውና ደቅቀው ይመጣሉ ። ብዙ ጊዜ ትላንትን ስለሚረሱ መልሰው ይነጉዳሉ ። ጌታን የገጠሙት ቤተ ክርስቲያንን እየገጠሙአት ነው ። ዛሬም ሰባኪን ከሚሰማ ፣ ፈዋሽ ነኝ አውቅልሃለሁ የሚሉትንና ሞቱን የሚያፋጥኑትን የሚከተል ሕዝብ ይበዛል ። የጥንት ጥንቆላ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ነበር ፣ ዛሬ ወደ ውስጥ እየዘለቀ ነው ። የጥንት ጥንቆላ መጋረጃ ጋርዶ ነበር ፣ የዛሬ ቪዲዮ እየተቀረጸ ፣ ቻናል እየተከራየ ነው ። በሰው ገመና የሚነግዱ ሰዎች በባሕል የተነወሩ ፣ በሕግም የሚጠየቁ ፣ በመንፈሳዊነት የሚወገዙ ነበሩ ። ባሕሉም እየጠፋ ፣ ሕጉም እየላላ ፣ መንፈሳዊ ቤትም የሰው ቤት እየሆነ ብዙ ወገን ተጎድቷል ።
ጌታን የሚከተሉት ሦስተኛ ወገኖች የዘላለምን የሕይወት ቃል ፈልገው የሚያስሱት ናቸው ። እነዚህ አብሮአቸው እያደረ ፣ አብሮአቸው እየዋለ ይናፍቁት ነበር ። ከሦስት እጅ አንዱ እጁ ብቻ በእውነት የሚከተል ነው ። ጥራት ማነስ አለው ፣ ነገር ግን ጠቃሚ ነው ። እነዚህ በአማራጭ ጌታን የሚከተሉ ሳይሆን ብቸኛ ምርጫቸው አድርገው ነው ። በዚህ ምዕራፍ አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ሲተርፉ ከአምስት ሺህ እስከ አሥር ሺህ የሚጠጋው ሕዝብ ወደ ኋላ ተመልሷል ። በተአምራት የበሉት በረከት ፣ የተጽናኑበት ቃል አላነቃቸውም ። ከዚህ በፊት እንደማያውቁት ሁነው ለጌታ ጀርባቸውን ሰጥተውታል ። እርሱ ግን ተራራው ላይ ሁኖ ራሱን ከማሳረፍ እነርሱን ለመመገብ ያስብ ነበር ። የሚነክሰው ያጎረሱት ነው ። የሰጠ ሁልጊዜ እንደ ተጠላ ነው ። ያልሰጠ ይከበራል ። ቢሆንም ጌታችንን ለመምሰል መራራት ይሻላል ።
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት የሚጀምረው ጌታን የእንጀራ አባት ለማድረግ የሚከተሉትን ሰዎች በመተረክ ነው ።
“ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው ።” /ዮሐ. 6፥5/።
ከአምስት ሺህ ለሚበዙ ሕዝብ ምን እናብላቸው ብሎ ማሰቡ ርኅራኄውን ያሳያል ። አብሉኝ እንጂ ላብላችሁ የማይሉ የዛሬ አገልጋዮች ምን ያስቡ ይሆን ? አምስት ሺህ ሕዝብ ቢያገኝ የዛሬው ሰባኪ አብዮት ለመክፈት ይጠቀምባቸው ነበር ። እያንዳንዱ ይህን ያህል ቢያመጣ እያለ ግንባራቸው ላይ ገንዘብ ለጥፎ ያሰላባቸው ነበር ። በቤተ ክርስቲያን የማዕድ አገልግሎት እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ይህ ክፍል ይነግረናል ። ምእመናን ሲመለሱ በባዶ አፋቸው እንዳይመለሱ ማዕድ ማዘጋጀት ተገቢ ነው ። እንዴት ሰው ከወላጁ ቤት ሂዶ ባዶ አፉን ይመለሳል ? በቤተ ክርስቲያን የኖሩ የማዕድ አገልግሎቶች አሉ ። ፀሪቀ መበለት ፣ ሰንበቴ ፣ ማኅበር የሚባሉት የማዕድ አገልግሎት ያለባቸው ናቸው ። አብሮ መመገብ ፍቅርን ይጨምራል ። እነዚህ የማዕድ አገልግሎቶች እየተረሱ ነውና አሳሳቢ ነው ። ፀሪቀ መበለቱም እየቀረ ይመስላል ። ከየቤቱ ዱቄት ለምነው ያንን ዳቤ አድርገው የሚሰጡ እነእማሆይ ዛሬ እየጠፉ ነው ። ሰንበቴውም በከተማ ለቀብር ፣ ለፉካ እንጂ ለፍቅር እየዋለ አይደለም ። የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህንን ሊያበረታቱ ይገባል ።
ጌታ የሚያደርገውን እያወቀ የፍቅር ፈተና ግን ያቀርባል ። አባት ልጆቹ የሚሉትን ለመስማት እንደሚያቀርበው ጥያቄ ጌታ ለፊልጶስ አቀረበለት ። እኛ አቅማችንን እያየን ፣ የዘመኑን ሁኔታ እየገመገምን ፣ የአየር ንብረቱን እያጠናን እንሸበራለን ። እርሱ ግን የሚያደርገውን ስለሚያውቅ አይታወክም ። ያስጨነቀን ቢያስጨንቀው ፣ ያወከን ቢያውከው የተሳነን ቢሳነው ምን እንሆን ነበር ? እርሱ ግን ከሁኔታዎች በላይ ነው ። ጌታችን ይህን ጥያቄ ለፊልጶስ ለምን አቀረበለት ? ከፊልጶስ ቀጥሎ እንድርያስም በዚህ ጉዳይ ላይ አለሁ ሲል እናያለን ። ፊልጶስና እንድርያስ ሌሎችን ወደ ክርስቶስ በማምጣት የታወቁ ናቸው ። ስለ ሌሎች ግድ ይላቸዋል ። የመጣውን ትተው ስላልመጣው ያስባሉ ። ከዳነው ያልዳነው ይበዛልና ። ፊልጶስ ናትናኤልን ፣ እንድርያስ ጴጥሮስን ያመጡ ናቸው ። አሁን እየመጣ ላለው ሕዝብ ግድ ሊላቸው የሚችለው እነዚህ ሁለት ልማደኞች ናቸው ። ጌታ የትላንት አገልግሎታቸውን አልረሳም  ። የአንድ ቀን ነው ብሎም ቸል አላለውም ። በሚያስፈልጉበት ቀን ወደ ሥራቸው መለሳቸው ። እርሱ ብቻ የአንድ ቀንን መታመን አይረሳም ።
በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አምስት ሹመኞች አሉ ። ሐዋርያት ፣ ነቢያት ፣ ወንጌላውያን ፣ አስተማሪዎችና እረኞች /ኤፌ. 4፥11/ ። ሐዋርያትና ነቢያት የመሠረት ሥራ ሠርተዋል /ኤፌ. 2፥20/ ። የሕንፃው ሥራ የሚሠራ ግን በሦስቱ ነው ። በወንጌላውያን ፣ በአስተማሪዎችና በእረኞች ። ወንጌላውያን የራቀውን ያቀርባሉ ፣ የጌታ አዋጅ ነጋሪ ናቸውና ። ወይም ይተክላሉ ። አስተማሪዎች ደግሞ የመጣውን ሕዝብ ያጸናሉ ፣ ወይም ያጠጣሉ ። እረኞች ደግሞ በነፍስና በሥጋ እየተንከባከቡ ይጠብቃሉ ። ይቀጣሉ ፣ ይባርካሉ ። ወንጌላውያን ተዘዋዋሪ ናቸው ፣ አስተማሪዎች ትክል ናቸው ። እረኞች የበላይ ጠባቂዎች ናቸው ። ዛሬ እንደ ወንጌላውያን ሰባክያነ ወንጌል ፣ እንደ አስተማሪዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ እንደ እረኞች ቀሳውስትና ጳጳሳት አሉ ። ፊልጶስና እንድርያስ እንደ ወንጌላዊ የራቀውን የሚያቀርቡ ናቸው ። ናትናኤልንና ጴጥሮስን ሲያቀርቡ ጌታ አስተማራቸው ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ አስተዳደራቸው ።
ፊልጶስ በዮሐንስ ወንጌል ላይ በሦስት ዋና ዋና ትእይንቶች ላይ እናገኘዋለን፡-
1-  ናትናኤልን ወደ ጌታ በመጥራት ፡- ያንን ቀና ሰው ናትናኤልን ወደ ጌታ ሲጋብዘው ናትናኤል ብዙ ብሏል ። ጌታ ግን የሰጠው ምላሽ “ፊልጶስ ሳይጠራህ  ፥ ከበለስ በታች ሳለህ ፥ አየሁህ” የሚል ነው /ዮሐ. 1፥ 49/ ። ፊልጶስ የጥሪው መልእክተኛ ነበረ ፣ ጠሪው ግን እግዚአብሔር ነው ። ከፊልጶስ በፊት ያየው ጌታ ነበረ ። ወደ ቤተ ክርስቲያን ካመጡን ሰዎች በፊት ያየን እግዚአብሔር ነው ። እነርሱ ምክንያት ቢሆኑም ጠሪው ግን አንድ ነው ።
2-  ለአምስት ሺህ ሰው አሁን ለመመገብ ከጌታ ጋር ሲማከር ፡- ጌታ በምክር ረዳት ባይሻም ያማክራል ። የሚያደርገውን ቢያውቅም ለልጆቹ ይገልጣል ። ይህ ከጥንት የነበረ ልማዱ ነው ። “እግዚአብሔርም አለ፦ እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን?”/ዘፍ. 18፥17/። “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።” /አሞ. 3 ፥ 7/ ። “ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን ፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው ።” /ዮሐ. 6 ፥ 5/ ።
3-  አብን አሳየንና ይበቃናል ብሎ ሲማጸን ፡- ፊልጶስ አብ ከወልድ በዘመን የሚበልጥ ፣ በክብር የሚልቅ መስሎት አብን አሳየንና ይበቃናል አለው ። ጌታ ግን በአብ ክብር ያለ ፣ አብን በመልክ መስሎ ፣ በባሕርይ ተካክሎ ያለ መሆኑን ገለጠለት ። ቢሆንም ፊልጶስ የእርካታው ጥግ ያደረገው አብን ማየት ነው ። ምንም ነገር የእርካታ ጥግ መሆን አይችልም ። እግዚአብሔርን ማየት ግን እርሱ የእርካታ ጥግ ነው /ዮሐ. 14 ፥ 8-11 / ።
ጌታ እንጀራ ለመግዛት አላሰበም ። እንጀራ መግዛት ኃጢአት ስለሆነ አይደለም ።  የወቅቱን ጥያቄ የሚመልሰው የበረከት እጁ እንደሆነች ያውቃል። ብዙ ጊዜ በአንዲት ኪኒን የሚወገደውን ሕመም ተአምር እንፈልግበታለን ። መግዣውን ገንዘብና ኪኒኑን ያዘጋጀው እግዚአብሔር እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል ። ሐኪም ቤት መሄድና መድኃኒት መከታተል አለማመን አይደለም ። ሁሉንም ነገር ከሕክምና ተስፋ ማድረግና ሁሉንም ነገር በተአምራት እንዲሆን መፈለግ ሁለቱም ጽንፍ መዳኘት አለበት ። የሰው አቅም የማይችለው ማለት እግዚአብሔር የማይችለው ማለት አይደለም። ሕክምና መጠቀምም እግዚአብሔር አይችልም ማለት አይደለም።
ጌታችን የግዥ እንጀራ ሕዝቡን እንደማይመክተው እያወቀ ፊልጶስን ይጠይቀዋል ። ያንን ሕዝብ የሚችለው የጌታ እጅ ብቻ ነው ። አንዳንድ ጉዳዮች ከሰውና ከገንዘብ አቅም በላይ ናቸው ። እግዚአብሔር ግን የተአምራት እጁን ሲዘረጋ ቀላል ይሆናሉ ። በዚህ ዓለም ላይ ሰዎችና ገንዘብ የሚችሉት በጣም ትንሽ ነገር ነው ። የሕዝብ ችግሮች ነገሥታትን ከሥልጣን የሚያወርዱ ከባድ ናቸው ። ሕዝብ ላንግሥህም ልሻርህም የሚለው የሚደረግለትን በማየት ነው ። ዛሬ ዕድሜ የሚያሳጥሩ ምግቦችን ለመብላት የበቃነው ያልተመጣጠነው የሕዝብ ቊጥርና ነገሥታት ይህ ሁሉ ወፈ ሰማይ ከሚበላቸው ይህን ይብላ ብለው ጥለውለት ነው ። ምግብ በውስጡ ሕይወትና በሽታ የመከላከል አቅም አለው ። ብዛትን ታሳቢ ያደረጉ ምርቶች የምግቡን በሽታ የመከላከል አቅም ነጥቀውት ነው ። የተወጉ ምግቦች ስንቱን እየወጉት እንደሆነ እያየን ነው ። ጌታ ግን ለመንገሥ ሳይሆን ለማጥገብ ለሕዝቡ አሰበ። እርሱ እነግሥ አይል ንጉሥ ፣ አገኝ አይል ባለጠጋ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ