የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግዚአብሔር ይፈትናል ወይ ?

 “ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ ።” ዮሐ. 6 ፥ 6 ።
ፈተና ምንድነው ? ፈተና የሚያመጣው መልካም ነገርስ ምንድነው ? እግዚአብሔር ይፈትናል ወይ ?
ፈተና ምንድነው ? ስንል ፈተና መመዘኛ ነው ። ተማሪው በትክክል ያወቀውን ፣ ያወቀው የመሰለውንና ያላወቀውን የሚያጣራው በፈተና ነው ። ፈተና የእውቀትና የእምነት ማጣሪያ ነው ። ዳግመኛም ፈተና መሸጋገሪያ ነው ። ወደ ቀጣዩ ክፍል ወደ ቀጣዩ እውቀት የምናልፈው በፈተና ድልድይነት ነው ። በመንፈሳዊ ሕይወትም ፈተና እውቀታችንና እምነታችን ይለካበታል ። ራሳችንን በትክክል የምናገኘው በፈተና ነው ። ክብደታችንን ወይም ቅለታችንን በፈተና አማካይነት እናውቃለን ። አንዳንድ ነገሮችን ማወቃችንን የምንረዳው በፈተናው ስናልፍ ነው ። ፈተና እርግጠኛ እውቀትን ይሰጠናል ። እርግጠኛ እውቀት ሌሎችን የምናስተምርበት ድፍረት ነው ። ያወቅነው የመሰለንን ነገር እንዳላወቅነው በፈተና አማካይነት እንገነዘባለን ። ለካ እምነት አለኝ እግዚአብሔርን አውቄዋለሁ ማለቴ ሙሉ አልነበረም ወይ? የምንለው በፈተና አማካይነት ነው ። ፈተና ልካችንን እንድናውቅና በእግዚአብሔር እንድንታመን ያደርገናል ። ፈተና መሸጋገሪያ ነው ። ወደ ቀጣዩ እውቀትና ወደ ቀጣዩ ደረጃ የምንሸጋገረው በፈተና አማካይነት ነው ። የአሁኑን ፈተና ካለፍነው ደረጃችን ከፍ ስለሚል ዳግም ላንፈተን እንችላለን ። ያላለፍነው ፈተና እንደሚደገም እንዲሁም ያላሸነፍነውና ያልተማርንበት ፈተናና መከራም የመደጋገም ባሕል አለው ። የትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ብንደርስ ፈተና አይቀርም ። እንዲያውም ፈተናው ጠጠር እያለ ይመጣል ። በተማርነው ነገር ላይ የጥናትና የምርምር ነገር እንድናቀርብ እንገደዳለን ። በመንፈሳዊ ዓለምም ታላላቅ ምክሮችንና የውጊያ ስልቶችን ያስቀመጡልን አባቶች ከፍ ባለ ፈተና ውስጥ ያለፉ ናቸው ። መንፈሳዊው ዓለም በጣም ረቂቅ ነው ። የእያንዳንዱ ቀን ፈተና የመንፈሳዊውን ዓለም አኗኗር እንድንረዳ ያደርገናል ። ኮምፒዩተር እንጠቀማለን ፣ በውስጡ ስላለው መዋቅር ግን በቂ እውቀት ላይኖረን ይችላል ። አለማወቃችን እንዳንጠቀም አላደረገንም ። እንዲሁም በመንፈሳዊ ዓለም ያለው ነገር በሙሉነት አለማወቃችን መንፈሳዊ ሕይወትን እንዳንኖር አያደርገንም ። ስለ ግዙፉ ዓለም እውቀታችን ውስን ከሆነ ስለ ሰማያዊው ዓለም ውስን ቢሆን የሚደንቅ አይደለም ። ፈተናዎች ግን እውቀታችንን ያሳድጉታል ።
በዚህ ዓለም ላይ በዋናነት ፈተና የሚያቀርቡልን ሦስት ወገኖች አሉ ። አንደኛው፣ እግዚአብሔር ነው ። ሁለተኛው፣ መምህራን ናቸው ። ሦስተኛው፣ ሰይጣን ነው ። እግዚአብሔር ይፈትናል ካልን ያስተምራል ማለታችን ነው ። የሚፈትን የሚያስተምር ነው ። ሳያስተምር የሚፈትን ሰይጣን ብቻ ነው ። እግዚአብሔርም ሆነ መምህራን የሚፈትኑን የተጣራ እውቀትና እምነት እንዲኖረን አስበው ነው ። ሰይጣን ግን የምናውቀውና የምናምነው እንዲጠፋን ይፈትነናል ። ሁልጊዜ ፈተና የለም ፣ መምህራን በየሦስት ወር አሊያም በመንፈቅ ይፈትናሉ ። ቀላል ፈተናዎች በወር ውስጥ ይሰጣሉ ። ትንሽ ጠንከር የሚል ደግሞ በሦስት ወር በጣም ከፍ የሚል ደግሞ በመንፈቅ ከፍ ያለ ደግሞ በዓመታት ውስጥ ይመጣል ። በጣም ከፍ ያለው ፈተና ከዚያ ትምህርት ቤት ጋር የምንለያይበት ነው ። እያንዳንዱ ቀን ፈተና አለው ። በቀን አንድ ጊዜ አበድ ብለን እንውላለን ። ይህም ፈተና ነው ። ትንሽ በአሳብ እንሰረቃለን ። ተስፋችን ይላላል ። ይህ ፈተና ቃሉን ያለመመገብ ችግር ነው ። ማንበብ ከብዙ ፈተናዎች ይጠብቃል ፣ ፈተና ከመጣ ደግሞ አቅልለን እንድናይ ያደርገናል ። ታላላቅ ፈተናዎችም ታላቅ የሕይወት መሸጋገርን ይሰጡናል ። ሊነጋ ሲል ይጨልማል የሚባለው ለዚህ አይደል ።
የእግዚአብሔር ቃል፡- “ማንም ሲፈተን፡- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም” ይላል ። ያዕ. 1፥13 ። እግዚአብሔር አይፈትንም አልተባለም ፣ ክፉ ፈተናዎች ግን በእግዚአብሔር አይመጡም ። ለምሳሌ የኃጢአት ፈተናዎች የእኛ መቋጫ የሌለው ምኞታችንና አለመጠንቀቃችን የሚያመጣው ነው ። እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም ይላል ። ልብ አድርጉ ፡- አይፈትንም ሳይሆን አይፈተንም ነው የሚለው ። አንዳንዴ ስንፈተን እንፈትናለን ። ለምሳሌ ትዳራቸውን በክፉ የሚጠረጥሩ ሰይጣን ሲፈትናቸው አብሮአቸው ያለውን መፈተን ይጀምራሉ ። ተፈትነው ይፈትናሉ ። እግዚአብሔር ግን በክፉ አይፈተንም ። መምህር ነውና ይፈትናል ። መምህር የሚፈትነው ተፈትኖ አይደለም ፣ ያስተማርኩትን ምን ያህል ተገንዝበዋል ብሎ ነው ። መምህር ራሱን ተጠራጥሮ አይደለም የሚፈትነው ። ተማሪውን እንደገና ለማስተማርም ነው ። እግዚአብሔርም በፈተና ውስጥ ትምህርትን ያጸናልናል ። ፈተና እንደ ገና መማርም ነው ። ያለፍነውን ፈተና እንረሳው ይሆናል ። የተሳሳትነውን ግን መቼም አንረሳውም ። እግዚአብሔር በፈተና አማካይነት የማይረሳ ትምህርትን ያስተምረናል ። ፈተና ቢያንስ ዳግመኛ ላለመሳሳት አቅም ይሆናል ። ታዲያ መምህሩ የመሸጋገሪያ ፈተናውን አዘጋጅቶ እርሱ ከኋላ ሁኖ ሌሎች ይፈትናሉ ። እግዚአብሔርም ከኋላ ሁኖ ፈተናውን ግን ሌሎች ሊፈትኑን ይችላሉ ። በየዕለቱ የሚዘጋጅ ተማሪ ፈተና አይከብደውም ። እንዲሁም ተዘጋጅተው የሚኖሩ ምእመናን በፈተና ባለ ድል ይሆናሉ ። አስተማሪው ደግ ነው ፣ ደግነቱን ግን በመፈተን ያበላሸዋል ተብሎ አያውቅም ። ያስተማረ ሁሉ ይፈትናል ። ፈተና የጭካኔ መለኪያ አይደለም ። ፈተና በትክክል የማስተማርና የመማር መለኪያ ነው ።
እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን እንደ ፈተነው ተጽፏል ። ኢዮብ እንዲፈተንም ፈቃድ ሰጥቷል ። እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን የፈተነው እምነቱ ለዓለም እንዲገለጥ ነው ። አብርሃም በመፈተኑና በማለፉ የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ ። ያ ፈተና ባይመጣ ኑሮ እስከ ዛሬ የምናወራለት አይኖርም ነበር ። አብርሃም በራሱና በሚስቱ ምኞት የተፈተነበት ጊዜ ነበር ። በዚያ ጊዜ ግን ወደ አጋር ሄደ  ። በትዳሩ ላይ ስህተት ፈጸመ ። እንዲህ ያለው ፈተና ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም ። አብርሃም ግን ልቡ ወደ ልጁ ሄደና እግዚአብሔር አብርሃምን ሊፈትነው ፈለገ፡-  “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።” ዘፍ. 22፥2 ። እግዚአብሔር እንደ አሕዛብ አማልክት የሰው መሥዋዕት የሚቀበል ሁኖ አይደለም ። አብርሃምም ልጁን ለመሠዋት በቆረጠ ጊዜ እግዚአብሔር ረካ ። የልጅ ፍቅር ከእግዚአብሔር ፍቅር አላስቀረውም ። እግዚአብሔር ልዩ ፍቅር እንደሚፈልግ በዚህ ታወቀ ። አብርሃም በመፈተኑ እግዚአብሔርን እንደሚወድ ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ መሆኑ ታወቀ ። በሺህ ዘመናት የሚነሡ አማንያንም ሕይወታቸውን የሚለኩበት መንፈሳዊ ቱንቢ ሆነ ።
ጻድቁ ኢዮብ እንዲፈተን የፈቀደውም ሰይጣን ኢዮብ የሚያመልከው በጉቦ ነው ወይም ስለተሰጠው ነገር ነው ብሎ ስለከሰሰ ነው ። በሌላ አነጋገር አንተ በነጻ የምትመለክ አምላክ አይደለህም ፣ በመደለያ የምትመለክ አምላክ ነህ ማለቱ ነው ። ኤልያስ በእግዚአብሔር ተወራርዶ ከበኣል ካህናት ጋር እንደቆመ እግዚአብሔርም በኢዮብ ተወራርዶ እንዲፈተን ፈቀደ ። ኢዮብ ግን ልጆቹን ፣ ንብረቱን ፣ ጤናውን ፣ ትዳሩን አጣ ። በዚህ ሁሉ ተፈትኖ አለፈ ። ኢዮብ በምድር ላይ የነበረ እስከማይመስል የትዕግሥት ምሳሌ ሆነ ። በዘመናችንም ዳግማዊ ኢዮብ እየተባሉ የተጠሩ ብዙ መከረኞችና አመስጋኞች ነበሩ ። እግዚአብሔር በሁለት ምክንያቶች እንደሚፈትን አይተናል ፡- አንደኛው እምነታችን ለዓለም እንዲገለጥ ፣ ሁለተኛው ተወራርዶብን ይፈትነናል ።
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት ላይም ጌታ ፊልጶስን ፈተነው ፡- “ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ።”ዮሐ. 6 ፥ 6 ። ይህ ፈተና የፍቅር ፈተናና ፊልጶስን ሊያስደንቀው የቀረበ ነው ። ፊልጶስ ይህ ፈተና ባይቀርብለት ያንን ግምት መገመት አይችልም ። “ፊልጶስ፡- እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት ።” ጠግበው ቢበሉ ደግሞ የአንድ ሺህ ዲናር እንጀራ ይወስድ ነበር ማለት ነው ። ከተአምራቱ በኋላ ምን እንደተደረገ ያውቅ ዘንድ አስቀድሞ ፈተነው ። አንድ ነገር ከመቀበላችን በፊት ፈተና የሚቀድመው ባገኘነው ጊዜ በዋጋው እንድንይዘው ነው ። እግዚአብሔር አክብረን እንድንይዝ የሚፈልገውን ነገር እንዲሁ አይሰጠንም ። ይፈትነናል ። በዚህ ዓለም ላይ ብክነት የድህነት ምንጭ ነውና ። የሌለውና ያለውን ያላወቀ ሁለቱም አንድ ናቸው ።  
ፈተናን በሚመለከት ሁለት ነገሮች ማንሣት አለብን ። የመጀመሪያው ፈተናን ማስቀረት አይቻልም ። ሁለተኛው ፣ ፈተና በራሱ ኃጢአት አይደለም። ሰው የረሀብ ስሜት ሊሰማው ይችላል ፣ ይህ ስለ ተሰማው ኃጢአተኛ አይደለም ። ራቡን ለማራቅ ቢሰርቅ ፣ ቢገድል ግን ኃጢአት ነው። አንድ የጥንት አባት፡- “ወፎች በአናትህ ላይ እንዳይበሩ መከልከል አትችልም ፣ ጭንቅላትህ ላይ ግን ጎጆ እንሥራ ቢሉህ አትፈቅድላቸውም” ብሏል ። ይህ አነጋገር ውልብ የሚሉ ፈተናዎች አሉ ፣ በራሳቸው ግን ኃጢአት አይደሉም ። ዳግመኛም እነዚህ ፈተናዎችን ማስቀረት አይቻልም ማለት ነው ። አንዳንድ ጊዜ ማሰብ የማይገባንን አሳብ እናስብና በራሳችን በጣም እናፍራለን ። መንፈሳዊነታችንንም እንጠራጠራለን ። ነገር ግን ሕሊና አደባባይ በመሆኑ ብዙ ነገሮች ያልፉበታል ፣ ኃጢአት የሚሆነው የሚያልፈውን አሳብ ሁሉ ጎራ በል ስንለው ነው ። ያ አሳብ የእኛ አይደለምና በመረጋጋት ልንገስጸው ይገባናል ። ወደ መቃብር እስክንወርድ ግን ፈተና አለ ።  ስንዴን እናስባት ። ገና ተዘርታ ሳለ አረም አጠገቧ ይበቅላል ። መጣባት እንጂ አልሄደችበትም ። ስትታጨድ ገለባና እንክርዳድ አብረዋት አሉ ። ውድማው ላይ ግን ገለባውን በነፋስ ትገላገላለች ። እንክርዳዱ ደግሞ በባለሙያ ይለቀማል ። እንደ ገና ትፈተጋለች ። ትፈጫለች ፣ ትጋገራለች ፣ ትበላለች ። የምታርፈው ሆድ ውስጥ ስትገባ ነው ። ይህን ሁሉ ሂደት ባታልፍ ስንዴ መሆኗ ይቀራል ። እኛም እስከ ሞት ድረስ ብዙ ፈተናዎችን እናስተናግዳለን ። ከእኛ ፈተና በላይ በፈተናችን የማይርቀን እግዚአብሔር አስደናቂ ነው ።
ፈተና ከፍዘት/ከመፍዘዝ ያድናል ። ፍዘት መጋጨትን ያመጣል ። ሁሉም ፍጥረት የራሱ ጠላት ባይኖረው ፍዘትና ግጭት በዓለም ላይ ይበዛ ነበር ። ንቃት በራሱ ውበት ነው ። ይህን ንቃት የሚያመጣው ፈተና ነው ። ሁሉም ፍጥረት የራሱ ባላጋራ አለው ። ሰው ብቻ በውስጥና በውጭ የሚሞገት ነው ። ሰው ተጠያቂ ፍጡር በመሆኑ እንደ ፈለገው መኖር አይችልም ። መፈተንና ከፈተና በኋላ መዘመር ለሰው የተሰጠ ክብር ነው ። እግዚአብሔር በእጁ ይዞ እየፈተነን ሊሆን ይችላልና ንቁ እንሁን ። ምናልባት ብዙ በረከት ይዞ ድሆችን ፈተና አድርጎ አስቀምጦብን ይሆናል ። ክብርን ለማፍጠን ፈተናን ቶሎ መሥራት ይገባናል ።
በፈተና ሰዓት ተማሪዎች የተማሩትን በአጭሩ ጨምቀው ይይዛሉ ፣ ያጠናሉ ። በፈተና ሰዓት ማንበብ ላይፈቀድ ይችላል ። እንዲሁም የተማርነውን ዋና ዋና ትምህርቶች በአጭሩ በቃላችን መያዝ ለፈተናው ሰዓት ይረዳናል ። ቃል ያሻግራልና ። በፈተና ሰዓት ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን ከሐሙስ ማታው ጴጥሮስ መማር ያስፈልገናል፡-
1-  ራስን አጽድቆ ሌሎችን መኰነን ፣
2-  ከመጸለይ መላምት ማብዛት ፣
3-  መንፈሳዊውን ውጊያ በሰይፍ መመከት ፣
4-  ከሰቃዮች ጋር ለመስማማት መሞከር ፣
5-  የማይፈራውን መፍራት
6-  አላውቀውም ብሎ መካድ
7-  በመጨረሻ ንስሐ መግባትና አሰላለፍን ማስተካከል ።
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች ሰንሰለታማ ሲሆኑ አንዱ ላንዱ አሳልፎ የሚሰጥ ነው ። ራስን ማጽደቅና ሌላውን መኰነን ፣ ጸሎት ያስረሳል ፣ ጸሎትን መርሳት ሥጋዊ ውጊያ ውስጥ ይከታል ፣ ሥጋዊ ውጊያም ከሰቃዮች ጋር ስልታዊ ግንኙነት ለመፍጠር ያጋልጣል ፣ ስልታዊ ግንኙነትም የማይፈራውን ለመፍራት ያጋልጣል ፣ ከንቱ ፍርሃትም ወይም ፈሪን መፍራትም ለክህደት ያበቃል ። መካሻው ግን ንስሐ ብቻ ነው ። በፈተና መጽናት መልካም ነው ፣ ወድቆ መነሣትም ክብር ነው ።
አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር አጥራችንን ያነሣውና የሁሉ መፈንጫ እንሆናለን ። ይህ ጊዜ ፡-
1-  ያለን የመሰለን ነገር የእኛ እንዳልሆነ እንረዳበታለን ።
2-  ሰዎችን የእኔ ብለን ከመናገር እንድናለን ።
3-  ራሳችንን በማየት እንታረምበታለን ።
4-  ጸጋ እግዚአብሔርን በምልአት እናገኝበታለን ።
5-  ገና በማወቅ ላይ እንዳለንና ሕይወት በየዕለቱ እንግዳ መሆኗን እናውቅበታለን ።
6-  ማነስ ግን ጥራትን እናገኛለን ።
7-  ጠንቃቃና ለተሰጠን ጊዜ ታማኝ እንሆናለን ።
በመጨረሻ እግዚአብሔር በታላቅ በረከትና በእጥፍ ምርኮ ይባርከናል ። ምርኮአችን በሙሉነት እንዲለቀቅም ያለፈውን ዘመን መርሳትና ይቅርታ ማውረድ ይገባናል ። የነቀፉን ሊያወድሱን ፣ የሄዱብን የት ነው ያሉት ? እያሉ ሊፈልጉን ይጀምራሉ ። እግዚአብሔር ፀሐይ ሲያወጣ ማንም በማኩረፍ አያጠልቅብንም ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ