“ፊልጶስ፡- እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት ።” ዮሐ. 6 ፥ 7 ።
ጌታችን ከሩቅ የሚመጣው ሕዝብ የእኔ ዕዳ ነው ብሎ ያስብላቸው ጀመረ ። ለራሳቸው ሳያስቡ ጌታችን ግን አሰበላቸው ። እነርሱ ሳይደርሱ ምግባቸው ተሰናድቷል ። ስላሰቡ ሳይሆን ስላሰበላቸው ጠግበዋል ። የዓለም ነገሥታት እየመጣ ያለውን ትውልድ ለመቀነስ ሊያስቡ ይችላሉ ። ጌታ ግን ችግሩን ለማራቅ አሰበ ። ጌታ ድህነቱን ይቀንሳል ፣ ሰዎች ድሀ ይቀንሳሉ። ምግብ አምጡ የሚለውን አፍ ለመቀነስ ብዙ ጦርነቶች እንደ ተሰናዱ ፣ ብዙ በሽታዎች እንደ ተፈበረኩ ሲነገር ኑሯል ። በርግጥ የሕዝብ ብዛትን በሚመለከት እግዚአብሔር የመዋለድ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የማሰቢያ አእምሮም ሰጥቶናል ። በአእምሮአችንም ማሰብ ተገቢ ነው ። ጌታችን ከሩቅ እየመጡ ላሉት አሰበ ። ፊልጶስንም አማከረ ። እግዚአብሔር በምክር የሚረዳው ባይኖርም የሚሠራውን ለወዳጆቹ ሳያሳውቅ አያደርገውም ። ምክንያቱም ወዳጅነት ማለት ግልጽነት መሆኑን እግዚአብሔር ያስተምረናል።
ፊልጶስ ሊበቃ የሚችለውን አስልቶ ተናገረ ። ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅ ፣ በምን ያህል መጠንም ማካፈል እንደሚገባ የመጀመሪያውንና የማጠቃለያውን እቅድ አቀረበ ። ሰው እንደ መሆን ማቀድ መልካም ነው ። በሰው እቅድ ላይ ግን እግዚአብሔር ካላቀደበት ከንቱ መሆኑንም ማወቅ ይገባናል ። ሰው ያቅዳል ፣ እግዚአብሔር ይፈጽማል ማለት ትልቅ ንግግር ነው ። ቋሚው ራእያችን ምንድነው ? ከራእዩ ውስጥ ዓላማ ይወጣል ። ዓላማ ዒላማ ነውና ማን ላይ ትኩረት ያደርጋል ? ከዓላማ ውስጥ እቅድ ይወጣል ። እቅድም ጊዜ ፣ ገንዘብና ጉልበትን ለክቶ ያስቀምጣል ። በእቅድ ውስጥም ኪሣራና ተግዳሮት አብሮ መቀመጥ አለበት ። የሚያውቁት ኪሣራና ተግዳሮት የሚጠብቁት መልአክ ያህል ያስደስታል ። ከእቅድ ቀጥሎ ትግበራ ነው ። ትግበራ ደግሞ መገምገም ያስፈልገዋል ። ይህ መደበኛው የሰው አኗኗር ነው ። እግዚአብሔር ግን ሲሠራ ይህን ሁሉ ድንበር አልፎ ነው ።
ፊልጶስ ሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ቢገዛ አይበቃም አለ ። የሚወጣው ወጪ ምን ያህል መሆኑን ለካ ። ቀጥሎ ተቀባዮቹን በምን ያህል መጠን እንደሚያጠግባቸው ጥናት አቀረበ ። ግን በዚህ ሰዓት ውስጥ ሁለት መቶ ዲናር ቢገኝ እንጀራውን ማግኘት ይቻላል ወይ ? ጌታ ስለ አሁን እየጠየቀ ፣ አሁን ለመጋበዝ እያሰበ ነው ። ያለፉትን ሺህ ዓመታት ፣ የሚመጡትን ሺህ ዓመታት አሁን አቅርቦ ማነጋገር የሚችለው አማኑኤል ከፊልጶስ ጋር ነው ። ሁሉ ለእርሱ አሁን ነው ። በዚያ ዘመን የአንድ ሠራተኛ የቀን ደመወዝ አንድ ዲናር ነው ። ማቴ. 20 ፥ 2 ። ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበት በዚህ ጊዜ ከሃምሳ ብር እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ብር የቀን ሠራተኛ ሊከፈለው ይችላል ። ሁለት መቶ ዲናር በሃምሳ እንኳ ብናስበው ለዛሬ አነጋገር አሥር ሺህ ብር ማለት ነው ። ያንን ሕዝብ በመጠኑ ለመመገብ አሥር ሺህ ብር ያስፈልግ ነበር ። ለማጥገብ ከሆነ ግን እስከ ሃምሳ ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል ። በርግጥ ይህ የእንጀራው ሂሳብ ነው ። ማባያ ወጡ ሲጨመር ከሃምሳ ሺህ ብሩ ላይ ምን ያህል እንደሚጨምር አስቡት ። ፊልጶስ ይህ ጥናት አቀረበ ። ተአምራቱ ከተደረገ በኋላ ምን ያህል ነገር እንደ ተደረገ እንዲያውቁ ጌታ አስቀድሞ ጠየቀው ። የተደረገልንን በዋጋው ካላወቅነው አናከብረውም ። ለመሆኑ የተደረገላችሁ ምንድነው ?
ፊልጶስ ለምን ሁለት መቶ ዲናር አለ ? ምናልባት በሐዋርያት ማኅበር ውስጥ ከዚህ በላይ ገንዘብ ላይኖር ይችላል ። እንጀራ መግዣ የላቸውም ፣ ነገር ግን እንጀራ የሆነውን ጌታ ይዘው ይዞራሉ ። ቢታመሙ ሐኪም ዘንድ የሚሄዱበት ወረት/ገንዘብ የላቸውም ፣ ነገር ግን ፈዋሹ ከእነርሱ ጋር ነው ። እርሱ ለአንዱ ኪኒን መግዣ ለሌላው ጤና ይሰጠዋል ። ብታመም እንኳ መታከሚያ የለኝም እንል ይሆናል ። ስለ ሰጠን ጤና እናመስግን ። ጤና ትልቅ ገንዘብ ነው ። በእውነት ጌታን ይዞ በገንዘብ መመካት አለማወቅ ነው። ደቀ መዛሙርት በጀት የላቸውም ፣ የዓለሙ መጋቢ ግን አብሮአቸው ነው ። እግዚአብሔር ያለ በጀትም እንደሚያኖር ፣ ወጪና ገቢ ሳይመጣጠንም ሕይወት እንደሚቀጥል እኛ ኢትዮጵያውያን ምስክር ነን ።
ፊልጶስ ትንሽ ፣ ትንሽም መስጠት እንደሚያስፈልግ ያመነ ይመስላል ። በትልቅ ልብ ከተሰጠ ትንሽ የሚባል ስጦታ የለም ። ስጦታን ትልቅ የሚያደርገው መጠኑ ሳይሆን የተሰጠበት ልብ ነው ። በርግጥ የአቅማችንን ያህል መስጠት ተገቢ ነው ። ለደከመው ሰው ፣ በመንገድ ለዛለው ፣ በምን አቅም እመለሳለሁ ? ለሚለውም ሦስት ጉርሻ መስጠት ይደግፈዋል ። መኪና በጭላጭ ነዳጅም እቤት ይደርሳል ፣ ነዳጅ ከጨረሰ ግን ይቆማል ። መቆም ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ችግርም ያመጣል ። ሦስት ጉርሻም ማቅረብ ሰውዬውን እቤቱ ያደርሰዋል ። ጌታችን እቤት እንደ መጣ ሰው በምድረ በዳ ላይ እንግዶቹን ለመጋበዝ ፈለገ ። ትልቁ ዓለም የእርሱ ጠባብ ቤቱ ነው ። በምድረ በዳ ላይ አገልጋዮች ቆመው የሚጋበዙ ነገሥታት ናቸው ። ማቴ. 11 ፥ 8 ። ጌታችንም ሕዝቡንም በንጉሥ መዐርግ አስቀምጦ መገባቸው ።እግዚአብሔር እንግዶቹን ወይም ልጆቹን በባዶ መሸኘት አይወድም። ያች ከነናዊት ሴት ልጅህ ባልሆንም ውሻህ ነኝ ፣ ፍርፋሪ በረከትህ ይድረሰኝ ብላለች ። ማቴ. 15 ፥ 27 ። የሚገርመው ፍርፋሪ ያለችው ሥጋዊ ፈውስን ነው ። የገበታው እንጀራ ጌታ በክብር የሚጋብዘው የዘላለም ሕይወት ነው ።
እያንዳንዳቸው ትንሽ ፣ ትንሽ እንዲበሉ አለ ። ፊልጶስ በእኩልነት ስለማስተናገድ እየተናገረ ነው ። ያለው ሀብት ትንሽ ሊሆን ይችላል ። ትንሽ ትንሽ ማካፈል ግን የአሳላፊዎች ድርሻ ነው ። ድግስን የሚያበላሸው አሳላፊ ነው ይባላል ። ለአንዱ የበለጠ ፣ ለአንዱ ያነሰ ይቀዳና ድግሱን ያበላሸዋል ። ነገሥታት አሳላፊ እንጂ ጋባዥ ወይም ጠሪ አይደሉም ። ጠሪው እግዚአብሔር ነው ። በረከቱም በምድር ላይ የተቀመጠ ነው ። ማብቃቃት ግን የነገሥታት ድርሻ ነው ። አሳላፊ ቢያዳላ ያዳላላቸውም የተዳላባቸውም ይነቅፉታል እንጂ አያመሰግኑትም ። እንደውም ተረት ይተርቱበታል ፡-
· “አውራ ዶሮ በሰው ስጥ ሚስቱን ይጋብዛል ።”
· በሙቅ ውኃ የሚታጠብና በሰው ገንዘብ የሚቸር አይሰማውም።”
· ሀብታም ለሰጠ ድሀ ይናደዳል ።”
ትክክለኛ አሳላፊ አለመሆን ሦስት ጠላት ያመጣል ። አንደኛ ደጋሹ ያዝንበታል ። ሁለተኛ የተዳላላቸው ይታዘቡታል ። ሦስተኛ የተዳላባቸውም ያዝኑበታል ። በኃላፊነት ቦታ ሲቀመጡም እንዲሁ ነው ። በእውነት ማስተዳደር ካልተቻለ እግዚአብሔር ያዝናል ። ወዳጅም ማትረፍ አይቻልም። የጉቦ ወዳጅነት የት ሲደርስ አይታችሁ ታውቃላችሁ ? ፊልጶስ አይበቃም አለ፣ ነገር ግን ትንሽ ትንሽ ማካፈል ተገቢ መሆኑን ተናገረ ። “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” ይባላል ። ምድር ለሁላችንም የጋራና የእኩልነት ቤት ናት። አንዱ ያለ ልክ እየበላ አንዱ ጦሙን እንዲያድር እግዚአብሔርም ኅሊናም አይፈቅዱም ። የእኛን ሁለት ልጆች ለማሳደግ ሁለት ሚሊየን ልጆችን በረሀብ መቅጣት ፍትሐዊ አይደለም ። እንደዚህ ያሳደግናቸው ልጆች ምን ዓይነት ሰብእና እንደ ተላበሱ እያየን ነው ። እግዚአብሔር የሚቀጣን በምንጠላው ሳይሆን በምንወደው ነው ። የድሀ መሬት እየቀሙ ሠላሳ የቤት ካርታ መያዝ ምን ጥቅም አለው ? አንድ ቤት ውስጥ ያውም አንድ ሜትር አልጋ ላይ ለመተኛት አገር ካልገዛሁ ማለት በእውነት ሞኝነት ነው ። ካገኘን ለመስጠት እናግኝ ። አሊያ ንጹሕ ድህነት የኅሊና ወቀሳ የለበትም ።
ጌታ ተአምራቱን ያደርጋል ፣ የእኛን እቅድ ግን ይፈልጋል ። መደዴ ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ አይደለም ። ራቅ ብሎ የተቀመጠ የዘላለም ሕይወት አለ ። የምናገለግለው ሕዝብ በፊታችን ነው ፣ እርሱ ዓላማ ይባላል ። ጌታ እቅድ ስናወጣ በጀትን ፣ ስንነሣ ተአምራትን ያደርጋል ። ሁልጊዜ በእቅድ ብቻ መመራት ፣ ሁልጊዜም ተአምራት መናፈቅ ሁለቱም መታከም አለበት ።
ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆን ሕዝብ ጌታና ፊልጶስ ብቻ ያቅዳሉ ። የሚታደጉ ብዙ ሰዎች አያስፈልጉም ። እግዚአብሔር የሚሠራበት አንድ ሰው ግን የተጎዱትን ማዳን ይችላል ። ይህ ሰው ግን ራእይ ያለው መሆን አለበት። በእውነት ባለ ራእዮችን እናደንቃለን ፣ ባለ ራእይ ግን አይደለንም ። ስለ እማሆይ ተሬሣ ስንት ጊዜ ተርከናል ። እርሳቸውን ለመሆን ግን ገና አልተነሣንም ። አንዲት ደካማ መነኩሲት ሚሊየኖችን ማዳን ከቻሉ ሁሉም የቤት ሥራውን ቢሠራ ችግረኛ ባልኖረ ነበር ።
ጌታችን ከሩቅ እየመጡ ላሉት ሕዝቦች አሰበ ። እኛም ለመጪው ትውልድ ልናስብ ይገባናል ። ትውልዳቸን የሚኖርበት ቤት ብቻ ሳይሆን የሚኖርበት መንደርና አገር መሥራት ያስፈልገናል ። ወርቁንም ሚዛኑንም ያጣ ትውልድ እንዳይመጣ ማሰብና መሥራት ያስፈልገናል ። የሰው ብቃት የሚለካው በመውለዱ አይደለም ፣ በማሳደጉና የተሻለች አገር ማውረስ በመቻሉ ነው ።
ራእይ ደግሞስ ዓላማ ሲቀጥልስ እቅድ አለን ?