የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመቀመጥ ምሥጢር

“ኢየሱስም፦ ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ አለ ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት ። ወንዶችም ተቀመጡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር ።” ዮሐ. 6 ፡ 10 ።
ከሐዋርያው ፊልጶስና ከሐዋርያው እንድርያስ ንግግር በኋላ ጌታችን የእጁን ተአምራት ለመግለጥ ተነሣ ። እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት ከጌታቸው ጋር በፍቅር ተባብረዋል ። ይህን ሁሉ መመገብ የእኛ ግዴታ አይደለም አላሉም ። አይሆንም የሚል አሳብ ሳይሆን አይበቃም የሚል አሳብ አቀረቡ ። አይሆንም ጥላቻ ፣ አይበቃም ስሌት ነው ። ከጥላቻ ስሌት የተሻለ ነው ። ጌታ እምነት ያደርገዋል ። አቅምን ማየት ማንም ሥጋዊ ፍጡር ሊያንጸባርቀው የሚችለው ሐቅ ነው ። ፍላጎት እያለ አቅም ካነሰ የጎደለው ትንሽ ነው ። ፍላጎት አቅምን ያመጣል ፣ አቅም ግን ፍላጎትን አያመጣም ። ፊልጶስ ያለንን አሟጠን ብንጠቀም የሚል አሳብ ሲያቀርብ ፣ እንድርያስ ደግሞ በመካከላችን ትንሽ አለ ፣ እርሱ የሚበቃን አይደለም አለ ። ጌታ የእንድርያስን አሳብ መነሻ ፣ ትንሹንም ነገር እንደ እርሾ አደረገው ። በመካከል ያለው ትንሽ ነገር ይሻላል ። ካልተጨበጠ ትልቅ የተጨበጠ ትንሽ ይሻላል ። “ብልህ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል” ይባላል ። ማልቀሻ የምትሆነዋን ትንሽ እግዚአብሔር የዘመናት ትንግርት ያደርጋታል ። በመካከላችን ያለው ምንድነው ? ትንሽ ነገር ብቻ ሳይሆን ትንሽ የሚባሉ ብላቴናዎችስ የያዙት ምንድነው ? እያንዳንዱ ሰው ወደ ዓለም የመጣው ከእግዚአብሔር መልእክት ጨብጦ ነው ። ያንን መልእክት የምናገኘው ያን ሰው ስናከብረውና ስንጠብቀው ብቻ ነው ። ይህን ካስተዋልን እያንዳንዱ ሰው በረከታችን ነው ።

ጌታችን ሰዎቹ እንዲቀመጡ አዘዘ ። የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት መቀመጥ ያስፈልጋል ። ያ ሕዝብ ምን እንደ ተመከረለት አላወቀም ። ከእርሱ ግን የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው ። መቀመጥ ። መቀመጥ ብዙ ዓይነት ፍቺ አለው ፡-
·        መንገድን ማቆም ነው ፡- ሰው የእግዚአብሔርን በረከት ለማየትና ለማግኘት መንገዱን ማቆም አለበት ። እግዚአብሔር ይሠራል ፣ የእኛን መንገድ እስክንጨርስ ዝም ይላል ። የራሳችንና የአገራችንን በረከት የምናዘገየው ባለ መቀመጥ ነው ። መቀመጥ ተራ መቀመጥ ሳይሆን የራስን መንገድ ጨርሶ ለእግዚአብሔር መንገድ መልቀቅ ፣ የሚሠራውን ማየት ነው ።
·        ማረፍ ነው ፡- መቀመጥ ማረፍ ነው ። ሰው እንደ ሄደ ቢቀር ይወድቅ ነበር ። መቀመጥ ግን መታደስ ነው ። አንዳንድ የድካም ቀኖችን አስታውሱ ። ከባድ ዝለትና ማረፍን የተመኘንባቸው ብቻ ሳይሆኑ እንደገና የምንበረታ አልመሰለንም ነበር ። ትንሽ ስንቀመጥ ግን ድካሙ ሄዶ ብርታት እንሞላለን ። ተንቀሳቃሽ ስልካችንን አጥፍተን ኃይል እንሞላዋለን ፣ መኪና ሞተሩ ጠፍቶ ነዳጅ ይሞላል ፣ አውሮፕላን አርፎ ጎማው ነፋስ ያገኛል ። ለመሞላት ማረፍ ግድ ነው ። የጸሎት ፣ የንባብ ጊዜዎች ኃይልን የምንሞላባቸው እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሰምተናል፣ በተደጋጋሚ ግን ማድረግ አልቻልንም ።
·        መንገድ መልቀቅ ነው ። ከእኛ ይልቅ ለበረቱ ፣ ጊዜው ለሚረዳቸው ስፍራ መልቀቅ መቀመጥ ይባላል ። ያለፈውን ድካማችንን የምናስከብረው በመቀመጥ ነው ። እንደ ቆምኩ ወይም እንደ ሄድሁ እኖራለሁ ካልን መንገድ የዘጋንበት ትውልድ ይጠልፈናል ። ዛሬ ከትላንት ይልቅ የዛሬዎቹ ናት ። ከወደዱ ለምክር ይጥሩን ፣ እኛ ግን የትላንቱን ልፋታችንን አስከብረን በክብር መቀመጥ ይገባናል ። በእስር ቤት የተቀመጡ ሰዎች ቀድመው ያልተቀመጡና ተተኪውን ያላሰናዱ ናቸው ። ከሁሉ በላይ በድካም ዘመናችን ራሳችንን ፍጹም ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባናል ።
·        ማየት ነው ፡- መቀመጥ መሥራት ሳይሆን ማየት ነው ። የምናየው የራሳችንን ጉድለትና ከእኛ የተሻለ ተሰጥኦ ያላቸውን ጎበዞች ነው ። እነዚህ ጎበዞች እኛን አርአያ አድርገው ማመን ፣ ባለ ራእይ መሆን ፣ መታገል ፣ አገርን መውደድ የጀመሩ ሊሆኑ ይችላሉ ። ልጆቻችን የሚሠሩትን ለማየት መቀመጥ ያስፈልገናል ። ስንቀመጥ ፍጹም የነበርን መስሎን ራሳችንን አታለነው ከነበረ ፈጽሞ እንዳንኮራ ይረዳናል ። ጊዜ ለባለ ጊዜዎች ነው ።
·        ለቀጣዩ የመሰናዶ ቦታ ነው ። መቀመጥ ተቀምጦ ለመቅረት ላይሆን ይችላል ። ለቀጣዩ መንገድ ብዙ ልምድ የምንቀስምበት ነው ። ምናልባት በግፍ ተግዘን ፣ በጉቦ ተወግዘን ፣ ቀን ባበረታቸው ስፍራ ለቀን ይሆናል ። እግዚአብሔር ሠርቶን ሊሠራብን አስቀምጦን ይሆናልና ደስ ሊለን ይገባል ። ሶምሶን አንድ ጊዜ አስበኝ በማለት ከሕይወቱ ይልቅ በሞቱ ብዙ ጠላት ደምስሷል ።
·        ለታላቅ ትንሣኤ መሠረት ነው ፡- ነቢዩ ዳዊት፡- “እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው” ይላል ። መዝ. 77 ፡ 65 ። ይህ ስለ ጌታችን ትንሣኤ የተነገረ ትንቢት ነው ። የወይን ስካር ይዞት የጠላቶቹ መዘባበቻ የሆነ ኃያል ሰው ፣ ደግሞም የተኛ ጎበዝ ሊለቀው እዚህ ቦታ ምን እሠራለሁ ? ቦታዬ አይደለም ብሎ በኃይል ይነሣል ። የሚዘባበቱበትም አሁን ነቅቷልና እንደ ጢስ ይበናሉ ። መቀመጥ የትንሣኤ ዋዜማ ነው ። እንደ ተቀመጡ መቅረት የለም ፣ እንነሣለን ። የተዘባበቱብንን እንበትናለን ።
·        የመጣንበትን ለማሰብም ነው ፡- ንጉሥ ዳዊት የመከራው ዘመን አለፈ ። ለእረኝነት ነጻነት ያጣ አሁን የተረጋጋ ንጉሥ ሆነ ። እርሱ ደግሞ በተራው ኦርዮንን ማስበርገግ ብሎም ለመግደል መጨከን ጀመረ ። የሠራዊት አለቆች ፣ የሕዝብ አእላፋት ከሥራው ጋር ቢተባበሩም እግዚአብሔር ግን ከዳዊት ጋር አልተባበረም ። ነቢዩን ልኮ ከተናገራቸው ነገሮች አንዱ፡- “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር ።”  የሚል ነው። 2ሳሙ. 12 ፡ 7 – 8 ። እግዚአብሔር መንገድ ለጠፋው ንጉሥ የመጣበትን አስታወሰው ። “የምትሄድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አስታውስ” የሚባለው ለዚህ ነው ። መቀመጥ የመጣንበትን ለማስታወስ ይረዳል ።
·        ለመታከም ያግዛል ፡- ሐኪም በቁም አያክምም ። በሩጫም መድኃኒት አያዝዝም ። መቀመጥ ያስፈልጋል ። የማይቀመጥ ሰው በሽታው ላይታከም ይችላል ።
·        ለመመገብ አስፈላጊ ነው ፡- ምግብ አራት ነገሮች አሉት ። መልክ ፣ ጣዕም ፣ መዓዛ ፣ ጥቅም ። ምግብ እነዚህ አራት ነገሮች ካላስተባበረ መመገብ ከባድ ነው ። መልክ ሲያጣ ዓይን ለአፍንጫ ሪፖርት ያደርጋል ፣ አፍንጫም የራሱን ግምገማ ካደረገ በኋላ ለምላስ አሳልፎ ይሰጣል ። ምላስ ካሳለፈ በኋላ ጥቅም ይሆናል ። ለማየት ፣ ለማሽተት ፣ ለማጣጣም ማረፍ ያስፈልጋል ። በየትኛውም ዓለም የምግብ ሰዓት የተከበረ ነው ።
·        የጌታን በረከት ለመቀበል ግዴታ ነው ፡- ጌታችን በረከቱን ይሰጠናል ፣ መቀመጥ ግን ይገባናል ። ይህ መቀመጥ በእምነት ማረፍ ነው ።
 በነቢዩ በዳዊትና በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረውን አስታውሱ ። “ዕረፉ ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ ።” ይላል ። መዝ. 45 ፡ 10 ። የእግዚአብሔርን ክብርና ተአምራት ለማየት ማረፍ ያስፈልጋል ። ብዙ ጊዜ የጭንቀት ጸሎታችን ተሰሚነቱ ይዘገያል ። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ይልቅ ችግራችን ትልቅ ስላደረግን ፣ እምነት የጎደለው ጸሎት ስለሆነ ነው ። እግዚአብሔር እየተረበሽንና እየበረገግን እንድንጸልይ አይፈልግም ። አንድ አባት ልጆ ሮጦ እቅፉ ከገባ በኋላ እንዲፈራ አይፈቅድም ። አለሁ ችግርህን ንረገኝ ፣ ማነው የመታህ ይላል ። ልጁ ከአባቱ ይልቅ ያባረረውን እኩያውን ትልቅ ካደረገ አባቱ ይበሳጫል ። እግዚአብሔር ፈጣሪ ነው ። ዓለምና  ሰዎች ፍጡራን ናቸውና እግዚአብሔር ሲያባብለን መንቀጥቀጥ የለብንም ። የእምነት ጸሎት ማቅረብ አለብን ። ብዙ ነገሮች ልባችን ሲነሣሣ ሳይሆን ስንተዋቸው ተፈጽመዋል ። በራሳቸው ሳይሆን ስናርፍ እግዚአብሔር ስለፈጸማቸው ነው ።
በነቢዩ በኢሳይያስም፡- “የእስራኤል ቅዱስ ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና ፡- በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል እናንተም እንቢ አላችሁ”  ይላል ። ኢሳ. 30 ፡ 15 ። መዳን በንስሐና በእምነት ፣ ኃይልም በጸጥታና በመታመን እንደሆነ ይናገራል ። ጌታም በጥብርያዶስ ዳርቻ ሕዝቡን ተቀመጡ አለ ።
መቼም ለምለም ሣር ላይ ተቀምጠን የበላንበትን ጊዜ አንረሳውም ። ብዙ ትዝታዎች አሉን ። ያ ጊዜም በዕድሜአችን ውስጥ በጣት ለሚቆጠሩ ሁነቶች ያከናወነው ነው ። ከተለመደው ኑሮ ወጣ ብለን ፣ ጉዳይ እንደሌለን ዘና ብለን ፣ ከወዳጆቻችን ጋር ሁነን ፣ የተቋጠረውን ምግብ ፈትተን ፣ ፕሮቶኮልን ጥለን ፣ ሁላችንም በእኩልነት መሬት ላይ ተቀምጠን የበላንበት … ያ የሣር ገበታ ፣ ያ ሰማይን ጣራ ፣ ፀሐይን መብራት ፣ ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ዘበኛ አድርገን የበላንበትን ጊዜ አንረሳውም ።  የጌታችን ግብዣም ልክ እንደዚህ የማይረሳ ነበር ። እግዚአብሔር የሚሠራልን እንዳይረሳ አድርጎ ነው ። አንዳንዴ የጸሎት መልሳችን የሚዘገየው ልበ ቢስነታችን እስኪወገድ ነው ። ለልበ ቢሶች ምንም አይደረግም ፣ ቢደረግም አያውቁትም ።
የተቀመጡት ሴቶችና ሕጻናት ቢሆኑም የተቆጠሩት ግን ወንዶች ናቸው። አምስት ሺህ ያህል ነበሩ ። ሴቶችና ሕጻናት ለምን አልተቆጠሩም? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ሴቶች በአደባባይ ለመብላት ይቸገራሉ ። ሕጻናትም ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ይበዛል ። ወንዶች ግን በትክክል ይበላሉ። በትክክል የሚመገቡት እንዲቆጠሩ ታዘዘ ። አዎ በእግዚአብሔር መንግሥት ለመቆጠር መሽኮርመም ፣ መፈርፈር ተገቢ አይደለም ። በትክክል ቃሉን መመገብ ያስፈልጋል ።
 በዘመናት መቆጠር ተከናውነዋል ። መቆጠር ግን የራሱ የሆነ መስፈርት ነበረው ።
1-  ከግብጽ ምድር የወጡት ተቆጥረዋል ።
2-  ለወታደርነት የሚወጡት ተቆጥረዋል ።
3-  በትክክል የተመገቡ ተቆጥረዋል ።
 መቆጠር በሰነድ ፣ በመዝገብ መታወቅ ነው ። የተቆጠረ ነገር ከለላ አለው፣ ቢጠፋ ይፈለጋል ። ለመቆጠር ከዓለም ግብር መለየት ፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት ለመጋደል መጨከን ፣ ቃሉንና ጸጋውን በትክክል ማክበርና መጠቀም ይገባል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ