“ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን ።” ዮሐ. 6 ፡ 11 ።
የቆሙ አምስት ሺህ ሰዎችን በትክክል ማስቀመጥ ለደቀ መዛሙርቱ ትልቅ ሥራ ነው ። ጌታችን ተአምራት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም በልኩ መስጠትን እያለማመዳቸው ነው ። አሁን ደጋሹ ጌታ ነው ፣ አጋፋሪዎችና አሳላፊዎች ግን ደቀ መዛሙርት ናቸው ። አጋፋሪ የሚያስፈልገው ትልቅ ነገር ትዕግሥትና ፊት አይቶ አለማድላት ነው ። ጌታው የሰጠውን እርሱ እንዳያስቀር መጠንቀቅ ያስፈልገዋል ። ለሌላ ድግስ እንዲታመን ለዛሬው ሁሉን መታገሥና ለሁሉ እንደ ተደገሰለት መጠን መስጠት ይገባዋል ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን በአምስት ሺህ ሰዎች አለማመዳቸው ። ነገ ዓለሙን ሁሉ ለማገልገል ይህ የመስክ ጣቢያ ነው ። ማስቀመጥ ቀላል አይደለም ፣ ተቀመጥ ሲባል ምክንያቱን የሚጠይቅ ፣ በትዕቢት የሚተናነቅ አለ ። የጌታን ግብዣ ለማግኘት ግን መቀመጥ ያስፈልጋል ፣ ደቀ መዛሙርት በትክክል እንዲያስተናብሩ መቀመጥ ያስፈልጋል ፣ በልካቸው እንዲጠግቡ መቀመጥ ያስፈልጋል ። ዛሬ ብዙ ልቦች ቆመዋል ። መሬት መቀመጥን የጠሉ ዙፋን ላይ የሚጋደሉ ብዙ የቆሙ ወገኖች ይታያሉ ። እነዚህ ሰዎች ካልተቀመጡ ፡-
· ለራሳቸውና ለወገናቸው የመጣ የእግዚአብሔር ግብዣ ያልፋቸዋል ።
· ሌሎች እንዳያገለግሉ መሰናክል ይሆናሉ ።
· በልካቸው መጠን ሳይጠግቡ ይቀራሉ ።
ሁሉም ራሱን አጽድቆ ሌላውን ከኰነነ ፣ ራሱን ቀብቶ የሌላውን መዐርግ ከገፈፈ፣ ራሱን ሊቅ ብሎ ሌላውን ካደነቆረ የእግዚአብሔር በረከት አይመጣም ። እግዚአብሔር በረከትን የሚያመጣው ላንተ ቀጥሎ ባንተ በኩል ለወገንህ ነውና ወገንህን ከገፋህ በረከቱ አይመጣም ።
ጌታችን ጋበዘ ለመባል አይደለም እንጀራ ያበረከተው ። አምስት ሺህ ጎበዝን እስከ ልኩ አጥግቦ የእጁን ተአምራት አሳየ ። ሴቶች ትንሽ በልተዋል ፣ ሕጻናትም መጠነኛ ጎርሰዋል ። አምስት ሺህ ሰዎች ግን በታወቀ ሆቴል ከተሠራው የተለየ ዋጋ የማይተመንለት ማዕድ ቀርቦላቸዋል ። ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራ የያዘው ብላቴና እርሱ አልተቆጠረም ። ለተቆጠሩት ግን ምክንያት ነበረ ። ሳይቆጠሩ የሚያስቆጥሩ አሉ ። የእኛን ገበታ እኛ የምንመገበው በመጠኑ ነው ። ሌሎች ግን ብዙ ሊመገቡ ይችላሉ ። ለራሳችን ከምናደርገው ለልጆቻችን የምናደርገው ይበልጣል ። እኛ ከምንበላው መጠን ሠራተኞቻችን የሚበሉት ይበልጣል ። አንድ ቅዱስ ፓትርያርክ ድግስ ደግሳችሁ አምጡ ይላሉ ። ብዙ ሰው ይጠሩና ሌላው ሲበላ እርሳቸው ያያሉ። “ቅዱስ አባታችን እርስዎ ላይበሉ ነው ወይ አምጡ የሚሉት” ሲሏቸው ፡- የእኔ ሆድ እነዚህ ናቸው እነርሱ ሲበሉ እጠግባለሁ ይሉ ነበር ። አዎ ሌሎች የእኛን ገበታ ሲበሉ ልንደሰት ይገባል ። ታማኝ ሰጪ ካልሆንን ተቀባይ ልንሆን እንችላለን ። እግዚአብሔር ዕለታዊ ተግባሩ ቦታ ማለዋወጥ መሆኑን ተወዳጅዋ እናት እመቤታችን ድንግል ማርያም ተናግራለች ፡- “በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።” /ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም/ ።
ጌታችን ሁለቱን ዓሣና አምስቱን እንጀራ ያዘ ፣ አመስግኖም ለአሳላፊዎቹ ለደቀ መዛሙር ሰጠ ። ደቀ መዛሙርትም ለሕዝቡ ሰጡ ። ይህ ተዋረድ ሁልጊዜም ይኖራል ። ጌታ ለአገልጋዮቹ ፣ አገልጋዮቹም ለሕዝቡ ያድላሉ ። ነገር ግን ለተቀመጡ ሕዝብ ያድላሉ ። ቆመው ቁመት እንለካካ ለሚሉ አይታደልም ። ለትሑታን ፣ እስከ መሬት ዝቅ ላሉት ግን ይታደላል። “የንጉሥ ካህናት ነን” ይላል ቃሉ ስለዚህ ሁላችንም እኩል ነን ። 1ጴጥ. 2 ፡9። ካህን የሚባል የለም ፣ ስያሜውም ስህተት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ ። ካህን ከዕብራይስጥ የመጣ ስያሜ ሲሆን አገልጋይ ማለት ነው ። በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ “የንጉሥ ካህናት” ተብለዋል ። አዎ ልክ ነው ተብለዋል ። ከግብጽ ምድር የወጡ የእስራኤል ልጆችም የካህናት መንግሥት ተብለዋል ። “እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ ።” ዘጸ. 19 ፡ 6 ። ሕዝቡ ሁሉ ካህናት ከተባሉ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ፣ አሮንና ልጆቹን ለክህነት ጥራልኝ ብሎታል ። ዘጸ. 28 ፡1 ። የተዋጀ ሕዝብ ሁሉ ካህን /አገልጋይ ነው ። በልዩ ጥሪ ደግሞ የሚያገለግሉ በብሉይ ኪዳን ሌዋውያን በአዲስ ኪዳን ዲያቆናት ፣ ቀሳውስትና ጳጳሳት አሉ ። አንድ መንግሥት ሕዝቡ ሁሉ ለአገሩ ዘብ መቆም አለበት ሲል ሠራዊት ይበትናል ማለት አይደለም ። እንዲሁም የተዋጁት ሁሉ አገልጋይ ናቸው ሲባል ሙሉ ዘመናቸውን የሰጡ አገልጋዮች የሉም ማለት አይደለም ።
ትንሹን ብዙ ፣ እፍኙን እልፍ የሚያደርገው ምስጋና ነው ። በምስጋና ውስጥ ኃይል አለ ። ምስጋና በዘመናት ሁሉ የማይቻሉ ነገሮች የተቻሉበት መንፈሳዊ ኃይል ነው ። ምስጋና ከእውነተኛ ደስታና ከልባዊ ፍቅር የሚመነጭ ነው ። ምስጋና ተባባሪ የሚፈልግ ፣ ሌላውን የሚጠራ መንፈሳዊ ግብዣ ነው ። ምስጋና የሁለት ቃላት ጥምረት እንደሆነ ይነገራል ። ማሰብና መቍጠር ። ማሰብና መቍጠር ካልቻልን ምስጋና ሊኖር አይችልም ። ምስጋና ጨለማውን ብርሃን ፣ ተራራውን ሜዳ ፣ ደካማውን ብርቱ የማድረግ አቅም አለው ።
በምስጋና፡-
· ኢዮሳፍጥ ሳይዋጋ ድል አገኘ ። 2ዜና . 20 ፡ 20 – 23 ።
· ጳውሎስና ሲላስ ከእስር ቤት ወጡ ። የሐዋ. 16 ፡ 25 – 34 ።
· በሁለት ዓሣና በአምስት እንጀራ ፣ አምስት ሺህ ሰዎች ጠገቡ ። ዮሐ. 6 ፡ 13 ።
· አልዓዛር ከሞት ተነሣ ። ዮሐ. 11 ፡ 41 ።
· ኅብስቱ ሥጋ አምላክ ፣ ወይኑ ደመ አምላክ ሆነ ። ሉቃ. 22 ፡19።
ከላይ ባየናቸው የተቀደሱ ታሪኮችና ክስተቶች ከድርጊት በኋላ ምስጋና እንደ ቀረበ አናነብም ። ከመደረጉ በፊት የቀረበ ምስጋና ነው ። ከድርጊት በፊትና በኋላ የሚቀርቡ ምስጋናዎች ልዩነት አላቸው ።
ከድርጊት በፊት ማመስገን
|
ከድርጊት በኋላ ማመስገን
|
|
1
|
በሚያደርገው አምላክ ማመን
|
በተደረገው ማመን
|
2
|
በራሱ በጌታ መደሰት
|
በሥራው መደሰት
|
3
|
በእምነት መቀበል
|
ተቀብሎ ማመን
|
4
|
እንደሚደረግ ማመን
|
በተደረገው ማመን
|
5
|
እንደሚችል ማመን
|
በቻይነቱ ማመን
|
6
|
ያለ ጸሎት መልስ መደሰት
|
በጸሎት መልስ መደሰት
|
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራን ከማበርከቱ በፊት አመሰገነ ። ይህ ከእኛ ልምድ ፍጹም ተቃራኒ ነው ። እኛ ከጸሎት መልስ በኋላ እናመሰግናለን ። ምስጋናችንም እንደማበረታቻና ለቀጣይ ቀብድ እንደ መክፈያ ይመስላል ። በሚሰጠው አምላክ ካላረፍን በስጦታው ማረፍ አንችልም ። ምስጋና ፡-
· ባያድነንም ፣ እግዚአብሔር አዳኝ ስለሆነ የሚቀርብ የእምነት ፍሬ ነው ። ሠለስቱ ደቂቅ /ሦስቱ ወጣቶች/ እግዚአብሔርን የሚያምኑት እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ እንጂ ስለሚያደርገው ነገር አለመሆኑን መስክረዋል ። “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል ፥ ንጉሥ ሆይ ! ነገር ግን ፥ ንጉሥ ሆይ ፥ እርሱ ባያድነን ፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት ።” ዳን. 3 ፡17 ።
· ባልገባን ነገር ላይ ምሥጢሩ ለእግዚአብሔር ነው ብለን አክብሮትን መስጠት ነው ። ሙሴ ከአርባ ዓመት አገልግሎቱ ከ120 ዓመታት የኑሮ ልምዱ በኋላም እግዚአብሔርን በሙሉነት ማወቅ አልቻለምና በመጨረሻው ሰዓት እንዲህ አለ ፡- “ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው” ዘዳ. 29 ፡ 29 ።
በምስጋና ፡-
· የደስታ ብርሃን ይፈነጥል ። ምክንያቱም ምስጋና የእግዚአብሔርን ውበት የማየት ውጤት ነውና ።
· የሞት ጠረን ይለቃል ። ምክንያቱም ምስጋና ሕያውን አምላክ ማግኘት ነውና ።
· ጠላት በርግጎ ይጠፋል ፣ እግዚአብሔርም ስለ እኛ ይዋጋል ። ምክንያቱም ምስጋና እግዚአብሔርን ከጉዳያችን በላይ ማላቅ ነውና ።
· የሚነደውን እሳት ያጠፋል ፣ አሊያም እሳቱ እያለ በደህና ያሻግረናል ።
· የወኅኒውን ደጃፍ ይከፍታል ።
· ትንሹን ብዙ ያደርጋል ።
· ነገርን ሁሉ ይለውጣል ።
ጸሎት ጉዳያችንን ለእግዚአብሔር ማሳወቅ ሲሆን ፣ ምስጋና ግን እግዚአብሔርን ለጉዳያችን ማሳወቅ ነው ። በምስጋና ተስፋችን ይለመልማልና ምስጋና እንደ ገና መኖር ነው ።