የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አይቶ አለማመን

“ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ ።” ዮሐ. 6 ፡ 37።
የታደሉ አምነው ያያሉ ፣ ያልታደሉ ደግሞ አይተውም አያምኑም ። አለመታደላቸው እግዚአብሔር ነሥቶአቸው አይደለም ፣ ራሳቸውን ከእውነት ባዕድ አድርገውት እንጂ ። አምነው የሚያዩ ደስታቸው ብዙ ነው ፣ አይተው የሚያምኑም የተሻሉ ናቸው ። የክርስቶስን መነሣት አይሁድ አምነዋል ፣ እንደ ተነሣ ብቻ ሳይሆን ቀድመው እንደሚነሣ አምነዋል ። ይህ እምነታቸው ግን አልጠቀማቸውም ። ክፋት ያለበት እምነት ጥቅም አይሰጥም ። ቶማስ ደግሞ አይቶ አምኗል ። ብፁዓን የተባሉት ግን ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው ።ዮሐ. 20 ፡ 29 ። እነርሱ የታደሉ ፣ የተባረኩና ደስታ የሞላባቸው ናቸው ። አይተውም የማያምኑ አሉ ። እምነት በበጎ ፈቃድ የምንቀበለው እንጂ ጥሶን የሚገባ አይደለም ። እውነት ያስፈቅዳል እንጂ አያስገድድም ። ክርስቶስ ስለ ማንነቱ እንጂ ስለ ተአምራቱ መታመንን የሚፈልግ አይደለም ። ተአምር አይቶ ያመነ ተአምር ሲያጣ ይክዳል ።
ሦስት ዓይነት ግርዶሽ አለ ። መጨፈን ፣ አዚም ፣ ድንዛዜ ። መጨፈን ውጫዊው ዓይን ዐርፎ ውሳጣዊው ዓይን የሚነቃበት ነው ። አዚም የሚታየውን የግልጹን ትቶ ረቂቃን ፍጥረቶችን ማየት ነው ። አዚም ከርኩሳን መናፍስት የሚመጣ ክፉ ጥላ ነው ። አካልን ፣ መንፈስን ሳይቀር ያዝላል ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሊገሠጽ ይገባዋል ። ድንዛዜ ደግሞ ረቂቁንም ግዙፉንም ማየት አለመቻል ነው ። ይህ ከፈተና ፣ ችግርን ከመለማመድ የተነሣ የሚመጣ ነው ። አይሁድ የገጠማቸው የቱ ነው የሚለውን በጣም ሊጠና ይገባዋል ። እውነት ይሆንን ለማለት ዓይናቸውን አልጨፈኑም ። የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ክደዋልና የአምላክነቱን ሥራ እየሠራ ሩቅ ብእሲ ፣ ወልደ ዮሴፍ ይሉታልና አዚም ይዟቸዋል ። ድንዛዜ እንደ ገጠማቸውም ሐዋርያው ተናግሯል ። ሮሜ. 11 ፡ 25 ።መደንዘዝ አንድ ቦታ ላይ ረጅም ሰዓት በመቀመጥ ምክንያት የሚመጣ ነው።በአንድ ዓይነት አስተሳሰብና ችግር ውስጥ በመኖራቸው ድንዛዜ ይዟቸዋል ። መጨፈን የዓለማውያን ተግባር ነው ። አይተው እንዳላየ ማለፍ ይፈልጋሉ ።አዚም አይተው እንዳላየ የሆኑ ወደኋላ የሚመለሱ አማንያን ነው ። ድንዛዜ የአይሁድ ነው ። ምክንያቱም ከአብርሃም ዘር የመጣውን ክርስቶስ ዓለሙ ሲያምነው እነርሱ ጥያቄ ሁኖባቸዋልና ።
ዓይንን መጨፈን ሁልጊዜ ክፉ አይደለም ። የሚሰሙትን ለማዳመጥ ፣ የሚያዳምጡትን ለማሰላሰል ፣ የአሳብ ወርቅ ለመፈለግ ዓይንን የሚጨፍኑ ደጋግ ሰዎች አሉ ። ዓይኑን ጨፍኖ የሚያየውን ከሚያስበው የሚያመዛዝን በጣም ጥቂት ይመስላል ። ሰዎች አትኩረው ለመስማት ዓይናቸውን ይጨፍናሉ ። በሥጋዊ ዓይን ብቻ ላለመወሰን ውስጣዊውን መብራት የሚያበሩት ዓይናቸውን በመጨፈን ነው ። በሚያዩትና በሚሰሙት ላለመፍረድ የሚፈልጉ ሰዎች ዓይናቸውን ይጨፍናሉ ። የወንድማቸውን ሐፍረት ፣ የአባታቸውን ራቁትነት ላለማየት ዓይናቸውን የሚጨፍኑ እንኳን ሊያሳዩ ራሳቸው ማየታቸውን የሚክዱ ብዙ የሴም ልጆች አሉ ። ሸፋኙ ጌታ ያደረው በሸፋኙ በሴም ድንኳን ነው ። ዘፍ. 9 ፡ 27 ። ዓይናቸውን የሚጨፍኑ ሰዎች የበለው ዘመንን ለማለፍ የታደሉ ናቸው ። የሚያዩትን ደግመው የሚያዩ ድንጋይ ለመወርወር የማይቸኩሉ ናቸው ። የሚሰሙትን ደግመው የሚሰሙ ራሳቸውን ከጸጸት የሚጠብቁ ናቸው ። ስለ አንድ ሰው አንድ ምስጋና ቢነገር ያንን ደግሞ የሚናገር የለም ፣ ስድብ ቢነገር ግን የሚያስፋፉትና ከተሳዳቢው በላይ የሚያወሩት ብዙ ናቸው ። ይህ ዓይንን ጨፍኖ ማሰላሰል አለመቻል ነው ። ታላቅ ጽሞና የሚያደርጉ ሰዎች ዕረፍት ይፈልጋሉ ። ተፈጥሮውን እያዩ ጸጥ የሚሉ ዓይናቸው ያያል ፣ አፋቸው ግን ዝም ብሏል ። ዓይናቸውን ጨፍነው እውነትን የሚያሰላስሉ ደግሞ ወደ ሰማይ ማደሪያ ገብተው የሥላሴን ፍቅር ይቀምሳሉ ።
ሐዋርያው ፡- የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር ፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው ?” ይላል ። ገላ. 3 ፡1 ። በመንፈስ ጀምሮ በሥጋ ፣ በጸጋ ጀምሮ በሕግ ለመፈጸም የሚፈልግ አዚም ገጥሞታል ። አዚም ቀድሞ ያዩት የነበረውን አሁን በመጣ መንፈሳዊ መጋረጃ ማየት አለመቻል ነው ። የገላትያ ሰዎች ጨርሰው ያላዩ አይደሉም ። ያዩትን የተነጠቁ ናቸው።ይህ አዚም ይባላል ። በዓላማ ላይ የተሰቀለውን በዙፋን ላይ የተቀመጠውን በደመና የሚመጣውን ከፍ ያለ ጌታ ማየት አለመቻል አዚም ነው ። ከፍ ያለውን ከፍ አለማድረግ ፣ አቻ የሌለውን ማነጻጸር አዚም ነው ። የገላትያ ሰዎች ከጸጋ ወደ ሕግ እየሄዱ ነው ። የሚገርመው እነርሱ ከአሕዛብ የመጡ በመሆናቸው ሕጉ እንኳ ርስት አይሰጣቸውም ። እስራኤልን አድራሻ ያደረገ ነውና ። ክርስቶስን ማየት ካልቻልን ሕጉ እንኳ አያማጽነንም ። የገላትያ ሰዎች አዚም ውስጥ የገቡት በብሉይ ኪዳን ቀናተኞች ግፊትና ተጽእኖ ይመስላል ። እናምናለን የሚሉ ሰዎች የሚገፉአቸው ወደ አዚም ይገባሉ ። ከአረማውያን ሰይፍ የክርስቲያን ነን ባዮች ክፋት አደገኛ ነው ። በጣም መጠንቀቅና የጠራንን ጌታ ማየት አስፈላጊ ነው ።
ድንዛዜ አንድ ቦታ ላይ ረጅም ጊዜ ከመቀመጥ የተነሣ ለመነሣት አለመቻል ነው ። ይህን ያህል ዘመን የኖርኩለትን ነገር አሁን ከመተው መሞት ይሻለኛል የሚል አስተሳሰብ ነው ። ላለፈው ዘመን ዋጋ መስጠት ተገቢ ቢሆንም ላለፈው የኃጢአት ዘመን ግን ዋጋ መስጠትና በዚያ ለመቀጠል ማሰብ ተገቢ አይደለም ። ድንዛዜ ብዙ ከማየትና ከመስማት የተነሣ ስሜት አልባ መሆንም ነው ። ሁሉን ማየት መልካም ቢሆንም ለአንዳንድ ሰው ግን መኖርን እንዲያቆም ያደርገዋል ። አዲስ ነገር የለም በማለት ሁሉንም በሰለቸ ስሜት ለመቀበል ይዳርገዋል ። ድንዛዜ ከዚህ የባሰ ምን ይመጣል ብሎ በመከራ አለመደነቅና ሁሉን ለመቀበል መዘጋጀት ነው ። ድንዛዜ ክርስቶስን ሁሉ ሲያምነው ቀድመው የተሰበኩ አይሁድ ዕድልን ማሳለፋቸው ነው ። “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ