የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሰባት
“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር ።” ዮሐ. 7፡1 ።
ጌታችን የሕይወትን ወንጌል ይዞ ወደ ዓለም ሲመጣ ከአለማመን ውስጥ የሚፈልቁ የተለያዩ መስቀሎችን ተሸክሟል ። ሰዎች ልባቸውን አስቀምጠው በጆሮ ብቻ መስማታቸው ፣ ለምድራዊ ጥጋብ ብቻ ጌታን መከተላቸው ፣ ትምህርቱን መቃወማቸውና እውነትን ማስተባበላቸው … እነዚህ ሁሉ የመስቀሉ ክፍሎች ነበሩ ። ተቃዋሚዎች የመጨረሻው አቅማቸውና እርምጃቸው ጌታን ሊገድሉት መፈለጋቸው ነው ። ጌታችን መግደል ወደሚፈልጉት መሞት ፈልጎ አልሄደም ፣ የገዳይነት ዕድሜአቸውን ለማራዘም ወይም የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኙ ለመርዳት ጌታ በይሁዳ መመላለስን አልወደደም ። ለገዳይነታቸው አልተመቻቸም ። ዘወር በማለት በአሳብ ሳይሆን በተግባር ሊቀድሳቸው ፈለገ ። ክፉዎችን የምንረዳቸው ለክፋታቸው ባለመመቻቸት ነው ። ጊዜ ገዳዩን ጲላጦስ ሰማዕት ያደርጋልና ። ጌታችን የሸሸው ርምጃቸውን ሳይሆን ፍላጎታቸውን ነው ። ፍላጎት ወደ ተግባር ይለወጣል ። ያልተገረዘ ፍላጎት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ነፍሰ ገዳይ ይሆናል ። ፍላጎትን ሊቀድስ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ።
እውነትን ገሸሽ ማለት የሚጠናቀቀው በገዳይነት መሆኑን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስትና ምዕራፍ ሰባት ያስገነዝቡናል ። በምዕራፍ ስድስት እውነትን ለመስማት አቅም አጡ ፤ በምዕራፍ ሰባት ለመግደል አቅም አገኙ ። እውነትን ለመስማት ያልቻሉ ሰዎች መግደልን እንዴት ቻሉ ? ስንል እውነት ብርቱ አቅም እንደምትፈልግ ያሳያል ። እውነትን በሥጋ ትከሻ መሸከም አይቻልም ፣ እውነት በመንፈስ ቅዱስ የምንቀበላት አቅም ናት ። መግደል የሟቹን ደካማነት ሳይሆን የገዳዩን አቅም ማጣት የሚያሳይ ነው ። መታገሥ አለመቻል ፣ ማለፍ አለመቻል ገዳይ የሚያደርግ ከሆነ መግደልን የሚወልደው መቻል ሳይሆን አለመቻል ነው ። በገደለ ቅጽበት ሕሊናው ሲታወክ ስናይ ገዳይ የገዛ ሕሊናው ዘመድ እንደማይሆነው እናያለን ። ገዳዮች የባለ ራእዩ ንግግሩና ተግባሩ ብቻ ሳይሆን ህልውናው ሲረብሻቸው ከዚህ በኋላ ልንይዘው አንችልም ብለው ተስፋ ይቆርጣሉ ፤ ስለዚህ እንግደለው ይላሉ ። ገዳዮች ተስፋ የቆረጡ ናቸው ። እኔ በራሴ አልኖርም ፣ እኔ የምኖረው እገሌ ከሞተ ብቻ ነው የሚሉ ገዳዮች ለራሳቸው ክብር የሌላቸው ናቸው ። መኖር በእግዚአብሔር እንጂ በእነ እገሌ ሬሳ ላይ አይደለም ። ገዳዮች ግን እግዚአብሔር እንደሚያኖር አያምኑምና መግደል ከሀዲነት ነው ። ሰውን ገድሎ ከሰው ጋር ለመኖር ማቀድ በእውነት ገዳዮች ሞኝ እንደሆኑ ያሳያል ። በየካቲት 12 ቀን ጣሊያን የጨፈጨፋቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሐውልታቸው ቆሟል ። የገዳዩ የግራዝያኒ ሐውልት ግን ሲቆም በብዙ ሁከት ተነሥቷል ። ሟቾች ተሸናፊ ቢሆኑ ለተሸናፊ ሐውልት አይቆምም ። ገዳዮች ጀግና ቢሆኑ ኑሮ ሐውልት ይቆምላቸው ነበር ። ገዳዮች በሥጋ ጨርሰው በነፍስ የሚወቀሱ ፣ ክፋት የኋሊት እንደሚጥል ማስተማሪያ ናቸው ። በጀግናና በጨካኝ መካከል ያለው ልዩነት ጀግና በልኩ የሚዋጋ ሲሆን ጨካኝ ግን ቀጥሎ እንዲህ ቢያደርገኝስ እያለ ገድሎ እንኳ ዱላ የሚያበዛ ፣ ሬሳ የሚደበድብ ነው ። ነገሥታት እንኳን ባለ ራእይን ወንጀለኛንም የሚገድሉት ስለሚፈሩት ነው ። መግደል አቅም ማጣትና ተስፋ መቊረጥ የሚወልደው የመጨረሻው እርምጃ ነው ።
በዘመናት ሁሉ ባለ ዓላማዎች ተገድለዋል ፣ ዓላማን መግደል ግን አልተቻለም ። ባለ አሳቦች ይሞታሉ ፣ አሳብ ግን አይሞትም ፤ ባለ ራእዮች ያንቀላፋሉ ፣ ራእይ ግን ከመቃብር በላይ ይኖራል ። ገዳዮች የማይገነዘቡት ነገር ቢኖር የአንዳንድ ራእይ ልደት ያለው መቃብር ላይ መሆኑን ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም ።” /2ጢሞ. 2፡9/ ብሏል ። እኔ አልታሰርም አላለም ፣ እውነት ግን አትታሰርም አለ ።ጴጥሮስን የቁልቁሊት መስቀል ተችሏል ፣ እውነትን መስቀል ግን አልተቻለም።
አይሁድ ከብዙ ምልክቶችና ከብዙ ትምህርቶች በኋላ ጌታችንን ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር ። ተምሮም አይቶም ገዳይ መሆን አለ ። ገዳይነት ምርጫ ነው ። በዓለም ላይ የአምላክን ፍቅር ተቋቁሞ ገዳይ የሚሆን ከባድ ልብ ነው ። አብዝቶ የቀረበንን አብዝቶ መራቅ የሰውነት ዋጋችንን የሚያወርድ ነው ። ይንተገተግ የነበረውን የጌታችንን አገልግሎት በሞት ፀጥ ለማሰኘት ይፈልጉ ነበር ። አይሁድ ዓርብ ቀን የመግደል መሻት አድሮባቸው ዓርብ ቀን ጌታን አልሰቀሉትም ። የዓመታት ምኞታቸው ዓርብ ቀን ሞላላቸው ። ኃጢአት ዕድሜው ከጽንስ እስከ ልደት ነው ። ኃጢአት ሳይገለጥ በስውር ፣ ሳይወለድ በጽንስ ሊወገድ ይገባዋል ። ማንኛውም ነገር እርሱን የሚመስል ልደት አለው ። ያልዘሩት አይበቅልምና ። መፈለግ ለመልካምም ለክፉውም ተግባር መሠረት ነው ። አንዳንድ ራእይ ተወልዶ ያድጋል ። አንዳንድ ራእይ ሊገድሉት ሲሉ ይወለዳል ። በዓለም ላይ ያሉ የውቅያኖስ ውኆች ፣ የብዙ ክረምት ዶፎች የራእይን እሳት ሊያጠፉት አይችሉም ። ራእይን የሚያጠፋው ያው ባለ ራእዩ ብቻ ነው ። ጠላቶች ራእይን ማጥፋት አይችሉም ፣ በዚያው ተቃራኒም ራእይ ጠላትን ማጥፋት አይችልም ። ሁሉም በየራሳቸው ህልውናቸው ይቀጥላል ። ለመኖር ያለን ፍላጎት የሚጨምረው መኖርን የሚፈታተን ነገር ሲመጣ ነው ። ጠላቶች ነፍሳችንን ለመቀማት በሚያደርጉት ጥረት ለነፍሳችን ያለን ክብር ይጨምራል ። የፍጥረት ውበት ያለው ንቃት ውስጥ ነው ። አበቦች ሲነቁ ፣ ወፎች ሲነቁ፣ … ሁሉም ፍጥረት ሲነቃ ውበቱ ይታያል ። መንቃት የሚቻለው ጠላት ካለ ብቻ ነው ።
አይሁድ ጌታችንን ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር ። በመቻል ቢሆን መግደል እርሱ ይችል ነበር ። የቻልነውን ሁሉ የቻልነው ስለቻልን አይደለም ማለት ነው ። የሚችሉ በትዕግሥት ስላለፉን ነው ። እንደ ቻሉን ከገባን ክብር ይመጣል ። አሊያ ውርደት ይሆናል ። ትልቁ ትዕግሥት መግደል እየቻሉ መሞት ውስጥ ይገኛል ። በቃሉና በተአምራቱ ሕይወት የሰጣቸውን ጌታ ሊገደሉት ይፈልጉ ነበር ። ጌታችንን ሊገድሉት የሚፈልጉ ሃይማኖት አለን የሚሉ ሰዎች ሲሆኑ ሊገድሉት የሚፈልጉበት ቦታም ያው የሃይማኖት መዲና በነበረችው በኢየሩሳሌም ነው ። እስከዚህ የሚጨክኑ ሰዎች በሃይማኖት ቦታ የተደበቁ ጨካኞች ናቸው ። አንድ ሊቅ ተገፍተው እንደ እብድ ይዞሩ ነበር ። አንድ ቀን እንዲህ ብለው ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ጮኹ፡- “በቆብ ተሸሽጎ አጋሚዶ ሁሉ ፤ አገር ተቃጠለ እየጠፋ ውሉ ።” የሃይማኖት ሰው አጋሚዶ ወይም እሾህ ሲሆን ማን ይፈውሳል ? የሃይማኖት ሰው ወንበዴ ከሆነ ውሉ እየጠፋ አገር ይሰክራል ። በሃይማኖት ሥፍራ ያሉ ጨካኞች በሌላ ቦታ ላይ ላይገኙ ይችላሉ ። ይህ ብዙ ምክንያት አለው ። የመጀመሪያው እግዚአብሔር አልችልም ብሎ ማንንም የማይገፋ አምላክ ስለሆነ ነው ። ሁለተኛው በነፍሱ የጨከነ በማንም ይጨክናል ። ሦስተኛ የላይኛውን ጌታ የተዳፈረ ማንንም አያፍርም ። ሰው ሁሉ በሃይማኖት ይገዛል ፣ ሃይማኖት የማይገዛውን ምን ይገዛዋል ? ቀኑን በሙሉ ፍላት ሲወርድበት የማይበስል አንድ ጥሬ ባቄላ ይገኛል ። ከብዙ ብስሎችም መካከል አንድ ጥሬ ግድ ይገኛል ። የሚበዛው መልካም ነው ። ክፉዎች ስለሚጎሉብንና ስፍራ እየለቀቅንላቸው ስለምንሄድ የበዙ ይመስለናል ። ክፉዎች የማይሄዱት የትም ተቀባይ እንደሌላቸው ስለሚያውቁ ነው ።
አይሁድ ክርስቶስን ስላልዳኑበት ሊገድሉት ይፈልጋሉ ። ዛሬ ያልዳኑበት ነገ ይሰቅሉታል ። መዳን የሚያስፈልገን ገዳይ እንዳንሆንም ነው ። አምነው ያልዳኑበት ክደው ይሰቅሉታል ። ጌታችን ግን በይሁዳ ሊመላለስ አልወደደም ። ይሁዳ ደቡቡ ክፍል ሲሆን የሃይማኖት ሰዎች የሚገኙበት የሃይማኖት መዲና ነው ። ገሊላ ግን የሁሉ ሰብሳቢ የገበሬዎችና የልፋተኞች ቦታ ናት ። ልፋተኞች የሚበሉት እንጀራ ይጣፍጣቸዋል ። ምግቡና እነርሱም ይዋደዳሉ ። ምግቡም ከተመገቡት በኋላ እዚህ ነኝ አይልም ። በሙሉነት ይሐዳቸዋልና መጥፎ ቅርጽ የላቸውም ። ጓደኛቸው ሥራቸው ነው ። የላብ ኑሮ ደስ ይላል ። ሥራን የማያደማ ሰው በብዙ ነገር ሲደማ ይውላል ። ልፋተኞች ጊዜ ስለሌላቸው ስለ ሰዎችና ስለ ፖለቲከኞች አያቀነቅኑም ። የሃይማኖት ሰዎች ተግባረ ዕድንን አብረው ካልያዙ ሰፊ ጊዜ ስለሚያገኙ ነገር ሲሠሩ ይውላሉ ። ሰነፍ የሚዝናናው የሰውን ቤት እያፈረሰ ነው ። የትኛውም ጎበዝ ሰባኪ በቀን ከአንድ ሰዓት በላይ ሊሰብክ አይችልም ። ትርፍ ሃያ ሦስት ሰዓት ካለው አደገኛ ነገር ውስጥ ይገባል ። አገር ካገር ሲያራብሽ ይውላል ። ስለዚህ ተግቶ መማርና መጻፍ ፣ የሙት ልጆችን መጎብኘትና ሥራ መሥራት ይገባዋል ። ለሃይማኖት ሰዎች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ይገባል ። ብቻውን የማይድን ብቻውን የማይሞት ነውና ። ወይ ገነት ወይ ሲዖል ተጅቦ የሚገባ ነው ።
ጌታችን ለገዳይነታቸው አልተመቻቸም ። ያለ ጊዜው ላለ መሞት ተጠነቀቀ ። ስለዚህ ከይሁዳ ራቀ ። በገሊላ በምእመናኑ አገር መመላለስ ጀመረ ። ካህን ሲያሳድድ ምእመንን ፣ ምእመን ሲያሳድድ ካህንን መጠጋት መልካም ነው ። የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ማብቂያ የለውም ። የዓለም ፖለቲካ ምርጫ የሚባል ነገር ይመጣና ዝም ይላል ። የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ግን ምርጫ የለውምና ሁልጊዜ ትኩስ ወሬ አለ ። ጌታ እንኳ ዘወር ካለ ሁሉንም ፈተና በመጋፈጥ አናሸንፈውም ማለት ነው ። ዘወር በማለት የምናሸንፈው ፈተና አለ ።
የጌታችን ትምህርት እውነት ሲሆን እውነትን ራቁትዋንና እውነትን በካባ በሚፈልጓት መካከል ትንቅንቅ መጥቶ ነበር ። የሚሟገቱት ሰዎች ሙሉ ሐሰተኞች አልነበሩም ። ከፊል እውነትን የያዙ ነበሩ ። ከፊል እውነት ከሙሉ ሐሰት በላይ የሰይጣን ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ። ቦግ ጭልም የሚል ነገር ሰይጣንን ይመቸዋል ። ጌታችን በሩቅ ሁኖ በአደባባይ ያስተማረ ሳይሆን ቀርቦ የእኛን ሥጋ ለብሶ ያስተማረ ነው ። የቱንም ያህል ቅርብ ብንሆን ከጌታችን በላይ ቅርብ መሆን አንችልም ። ሥጋዌው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነበት ትልቅ ምሥጢር ነው ። ኅብረታችንም በጊዜ ውስጥ የሚፈታ ሳይሆን በደምና በሥጋ የተቋጠረ ነው ። ሕግም ፣ ጠላትም ሊለየው አይችልም ። የሚቃወሙትን ሁሉ አልተቀየማቸውም ። ይቅር ብሎ መኖርና ይቅር ለማለት መኖር ይለያያል ። እግዚአብሔር ግን ይቅር ብሎን ሊኖር ኪዳን ገብቷል ። የሰው ሲያልቅ የእግዚአብሔር የሚቀጥለው በኪዳን ፣ በልጅነት ሥርዓት ነው ። የተቃዋሚዎችን የመግደል ፍላጎት ጊዜ ገታው ። ሊገድሉት ቢሹም ሊያደርጉት ግን አልቻሉም ። የሚገድሉና ጥግ ይዘው ሌላው ሲገድል ለማየት የሚናፍቁ ሁለት ወገኖች አሉ ። ሁሉም ነፍሰ ገዳይ ናቸው ። በእግዚአብሔር መንግሥት ብዙ ዓይነት አገዳደል አለ ። ዓለሙ ግን መግደልን በአንድ አንጻር ብቻ ተርጉሞ አልገደልኩም ብሎ ይረጋጋል ።