የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አላመኑበትም ነበር

“እንግዲህ ወንድሞቹ፡- ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት። ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና ።” ዮሐ. 7 ፡ 3-5 ።
ራስህን ግለጥ እያሉት ወንጌላዊው “አላመኑበትም” እንዴት ሊል ቻለ ? አይሁድ ጌታችንን ለሞት እንደሚፈልጉት እያወቁ ራስን ግለጥ ማለታቸው ለጌታ አለመሳሳታቸውን የሚያሳይ ነው ። እምነት ማለት የሚወዱትን ነገር መጠበቅ ነው ። ስለዚህ አላመኑበትምና የጭካኔ ንግግር ተናገሩ ። ዳግመኛም እየዘበቱ ሊሆን ይችላል ፤ ጌታችንን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲያዩት ሰው ብቻ መስሎአቸው አምላካዊ ክብሩን በመናገሩ አላመኑበትም ነበር ። እምነት ክርስቶስን በታሪክ ውስጥ የተገለጠ አንድ ደግ ሰው ብቻ ሳይሆን ታሪክን የለወጠ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል ። እነርሱ ግን አላመኑበትም ነበር ። ስለ ጌታ የሚያውቁት ትንሽ እውቀት ትልቁን ነገር ሸፈነባቸው ። በምናውቀው ትንሽ ነገር ውስጥ የማናውቀው ብዙ ነገር አለ ። እንኳን ስለ ጌታችን ስለ ተፈጥሮና ስለ ራሳችንም ከምናውቀው የማናውቀው ይበዛል ። የማናውቀው ስለበዛ ማመን አይቻልም ማለት ግን አይደለም ። በቤታችን ስለሚያበራው አምፑል ያለን እውቀት መጠነኛ ሊሆን ይችላል ። በሙሉነት አለማወቃችን ግን መጠቀምን አልከለከለንም ። ብዙ ስናውቅ አለማወቃችንን እናውቃለን የሚባለው ለዚህ ነው ። ጌታችን የማዳኑን ዳርቻ ሲነግራቸው ፣ ለመላው ዓለም መምጣቱን ሲያውጅላቸው ዓለሙ ይዳኝህ ለማለት ይህን የተናገሩ ይመስላል ። ባለ ራእዮችን ግብታዊ እንዲሆኑ ፣ በወንድነት እንዲወጡ መምከር የራእዩ ተቃዋሚ መሆንን ያሳያል ። ጽንስ ለያዘች ሴት ልዩ ጥበቃና ከለላ እንደሚደረግ ራእይን ላረገዙም እንዲህ ሊደረግ ይገባዋል ።
በዚህ ክፍል ላይ ጌታችንን ሊገድሉት የሚፈልጉ አይሁድና ያላመኑበት የቅርብ ዘመዶቹን እናያለን ። ሊገድሉት የሚፈልጉ እኛን ሊጎዳን ይችላል ብለው የፈሩ ናቸው ፤ ያላመኑበት ግን ምንም ሊያደርገን አይችልም ብለው በሕሊናቸው የዘነጉት ናቸው ። ራእይን ይዘን ስንወጣ እነዚህ ሁለት ወገኖች ይገጥሙናል ። የማያምኑ ሲያዝሉ ፣ ተቃዋሚዎች ግን ያበረታሉ ። የማያምኑ ሲንቁ ፣ ተቃዋሚዎች ግን አክባሪዎች ናቸው ። የማያምኑ የትም አይደርስም ብለው ሲዘብቱ ፣ ተቃዋሚዎች ግን ዛሬ ካመለጠን ነገ አንይዘውም ብለው የሚሰጉና ነገን የሚያዩልን ናቸው ። ተቃዋሚዎች ከሌሉ በራሳችን ፍዘት ለመጥፋት ተፈርዶብናል ማለት ነው ።
ጌታችን ራሱን ሊገልጥ እንደሚፈልግ እየተናገሩ ነው ። ራሱንም በትምህርቱና በአዳኝነቱ መግለጥ ይፈልጋል ። ፀሐይ ካልተገለጠች ጨለማ እንደሚወርሰን ክርስቶስም ራሱን ካልገለጠ የድንቁርናና የሞት ጨለማ ይከድነናል ። ዘመነ ሥጋዌው በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ ነው ። ራሱን መግለጥ የፈለገውም ራሱን ካልገለጠ ዓለም ሊያውቀው ስለማይችል ነው ። እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ካልመጣ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ አይችሉም ። በኃጢአት ሽንገላና ባርነት ውስጥ ናቸውና ። ነቢያት መልእክቱን ፣ አዋጅ ነጋሪዎች አዋጁን ይገልጣሉ ፣ ጌታችን ግን ራሱን ለዓለም ይገልጣል ። ሰዎች እርሱን ወልደ አብ ወልደ ማርያም ብለው ካላመኑ አይድኑምና ። ሃይማኖት ከምርምር ለመገለጥ የቀረበ ነው ።
የእነዚህ ወገኖች ንግግር ትክክል ይመስላል ። ራሱን ሊገልጥ እየወደደ በስውር የሚሠራ የለም ። ዓላማ ግልጥ ካልሆነ ተከታይ አያገኝም ። ያልተገለጠ ዓላማም የተዳፈነ እሳት ነውና ሊያሞቅና ሊያበስል አይችልም ። ዓላማችንን ሰዎች ፈልገው ሊያገኙት አይችሉም ፣ ፈልጎ ሊያገኛቸው ይገባል እንጂ ። ጌታችን በገሊላ መቆየትን የፈለገው ያለ ጊዜው መከራ ላለ መቀበል ነው ። ደግሞም ለገዳዮች ላለመመቻቸት ነው ። ያላመኑበት አብሮ አደጎቹ ግን ዘወር ማለቱን ሊያከብሩለትና ሊያደንቁለት አልወደዱም ። ልናርፍበት የፈለግነው ቦታ ሁከት ሲሆን ፣ ይሻላል ያልነው ነዝናዛ ሲሆን ጌታችንን ማሰብ ይገባል ። አብሮ አደጎቹ ከአጠገባቸው እየገፉት ነው ። አብሮ አደጎች ደጋፊ ባይሆኑ ፣ ትንሹ እውቀታቸው ትልቁን ራእያችንን ለመቀበል ቢቸግረው መደነቅ አይገባንም ። ይህ በጌታችንም የደረሰ ነውና ። አብሮ አደጎች በራሳቸው መለካታቸው ፣ የድሮው ማንነታችን ላይ መቅረታቸው ፣ አካላዊ ድካምና ብርታታችንን እንጂ ራእያችንን ማየት አለመቻላቸው ልካቸው ነው ።
ወንድሞቹ የተባሉት በሥጋ የተወለዱት አይደሉም ። አብሮ አደጎቹ ናቸው ። ይህንንም በ “ቃና ዘገሊላ” መጽሐፋችን በስፋት ተገልጧልና እዚያ ላይ ይመልከቱት ። አብሮ አደጎቹ ቤተ ዘመዶቹ የጌታችንን አምላክነቱን አዳኝነቱን አላወቁም ነበር ። እንደ ተራ ሰው መስሎአቸው እንጂ አምላክ በሰው መካከል በለቢሰ ሥጋ እየተመላለሰ መሆኑን አላስተዋሉም ። ተግባሩን ትምህርቱን እያዩ ግን ራሱን ለዓለም የሚገልጥበት ጊዜ አሁን መሆኑን አሰቡ ። ራሱን ለዓለም እንዲገልጥ እንጂ ለእነርሱ እንዲገልጥ አይፈልጉም ። ዓለም ሥራውን አይቶ እንዲያምንበት እንጂ እነርሱ እንዲያምኑበት አይሹም ። በዳስ በዓል ላይ ከመላው ዓለም የተሰበሰቡ አይሁድ ስለሚመጡ  በዚያ ላይ ቆሞ ቢያስተምር መልካም እንደሆነ አሳብ እየሰጡት ነው ። እርሱ ለሥራው አማካሪ የማይፈልግ የሚሠራውንና የሚሞትበትን ጊዜ የሚያውቅ መሆኑን አላስተዋሉም ። አነጋገራቸው ምጸት ይመስላል ። እዚህ እኛ ጋ ታላቅ ተልእኮ አለኝ ከምትል ፣ ለዓለም ነው የመጣሁት እያልህ ለእኛ ከምትነግረን ዓለሙ በይሁዳ አውራጃ በኢየሩሳሌም ተሰብስቧል እዚያ ሂደህ ተናገር እያሉ ይመስላል ። ከእነዚህ ሰዎች ንግግር የምንማራቸው ነገሮች አሉ ፡-
1-  የሩቁ ደቀ መዝሙር ሲሆን የቅርቡ ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል ። ራእይና የወንጌል ማኅበርተኛነት የሚመሠረተው በጉርብትና ሳይሆን በእምነት ነው ።
2-  ለዓለም የሆነ ራእይን መንደር አይሸከመውም ። ትልልቅ ባለ ራእዮችን መንደሩ የሚገፋው ቦታችሁ እዚህ አይደለም እያለ ነው ። ትክክለኛ ያልሆኑ ሰዎች ስለ ተቃወሙን ዓላማችን ትክክል አይደለም ማለት አይደለም ። መንደሩ ስላልቻለን ገፋን ማለት አበቃልን ማለት አይደለም ። ሰዎች የሚገፉን ወደ ትልቁ ዓላማችን ሊያደርሱን ነው ።
3-  አብሮ አደጎችና ዘመዶች ውጫዊ አካላችንን እንጂ ውስጣዊ ዓላማችንን ላይረዱት ይችላሉ ። ዓላማ በነፍስ ዝምድና ካልሆነ በሥጋ ዝምድና የሚታወቅ አይደለም ።
4-  አጠገባቸው ያለውን ባለ ራእይ እየናቁ ዓለሙ ግን እንዲያምነው የሚፈልጉ አሉ ። እነርሱ ወንጌል አይማሩም ፣ ልጆቻቸው ግን እንዲማሩ የሚፈልጉ ፣ እነርሱ አያምኑም ልጆቻቸው ግን ለጨዋነት እንዲያምኑ የሚሹ አያሌ ወላጆች አሉ ።
5-  ሰው ካላመነ ተቃዋሚ ለመሆን ቅርብ ነው ። እውነትን እውነት ካላልን ሐሰትን ሐሰት ለማለት እንቸገራለን ።
6-  ከማሳመን በፊት ማመን ይገባል ። ሳናምን ማሳመን አይቻልም ።
7-  እግዚአብሔር በምክሩ ይመራል እንጂ እኛ በምክራችን አንመራውም።
አለማመናቸውን የገለጡት ፡-
1-  ደቀ መዛሙርትህ በሚለው ቃላቸው ነው ። እኛ ደቀ መዛሙርትህ አይደለንም እያሉ ይመስላል ። እኛም በራእያችን ጉዞ የቅርቡ እየራቀን ፣ የሩቁ እንደሚቀርበን ማስተዋል አለብን ። ራእይ ተግባራዊ ሲሆን ከግምት ውጭ ነው።
2-  ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ ብለው በማዘዛቸው ነው ። ጊዜና ቦታን የሚያውቅ መሆኑን አላመኑም ። አብረውን መሄድ የማይፈልጉ ነገር ግን ሊመሩን የሚሹ ሰዎች ጨካኞች ናቸው ። በራእይ ውስጥ በቀጥታ የሚፋለሙን እንዳሉ ሁሉ ሞታችንን በርቀት እያዩ ለመዝናናት የተሳሳተ መንገድ የሚመሩንም አሉ ።
3-   ራስህን ግለጥ በሚለው ቃላቸውም ነው ። በገሊላ ከምትሰወር ራስህን ብትገልጥ ይሻላል በሚለው ንግግራቸው አላመኑበትም ። ከራሳችን ጋር ለመሆን ፣ ቀኑንም ለማሳለፍ ስንሰወር እምነታችንን ሳይሆን ወንድነታችንን በማነሣሣት ወደ እሳት ሊከቱን የሚሹ ሰዎችን በራእያችን ውስጥ ልንጠነቀቃቸው ይገባል ። እምነታችንን አስጥለው ወንድነታችንን የሚቆሰቁሱ የሞት ቀናችን የራቀባቸው ሰዎች ናቸው ።
4-  መገለጥ እየፈለግህ በገሊላ ተሰውረሃል በማለት ወደ ሞት በመሸኘት በጭካኔ ተናግረዋልና በርግጥ አላመኑበትም ። መገለጥ በጊዜው ካልሆነ አደጋ አለው ። ጌታችን ሥጋ የለበሰው በጊዜው ነው ። ሰዓቱን የማያውቅ ሰው ባለ ራእይ መሆን አይችልም ። ሥራ ለመሥራት ሰዓትን ማወቅ ግድ ይላል ። ገበሬ በበጋ ቢዘራ ፣ በክረምት ለአጨዳ ቢወጣ ጊዜው ስላልሆነ አይሆንም ። ዘሩም ፣ መሬቱም ያው ነው ፤ ጊዜ ግን ይጥለዋል ። ሁልጊዜ የምናየው የሚቃወሙንን ነው ፣ የማያምኑብንንም በጥንቃቄ ማየት ይገባል ። ግብታዊ ሊያደርጉን ፣ እምነትን አስጥለው ገዳይ ሊያደርጉን ይችላሉ ። የማያምኑብን ግን የቅርብ ዘመዶቻችን ናቸው ።  
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ