የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንፈስ ቅዱስ

“ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ” /ዮሐ. 1፡32/፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ በብዙ እየመሰከረ ነው፡፡ ለሚጠይቁትም ለማይጠይቁትም ስለ መሢሑ ይናገራል፡፡ ስለ ክርስቶስ መናገር ያለብን ለሚጠይቁንና ለማይጠይቁንም ነው፡፡ ወንጌል ሰምተው ለሚቀበሉ ለድኅነት፣ ሰምተው ለማይቀበሉ ለፍርድ ትነገራለችና፡፡ ከምሕረትና ከፍርድ የወጣ ትውልድ ስለሌለ ወንጌል ለሁሉ ይሰበካል ማለት ነው፡፡ ወንጌልን ለማያምኑ ሰዎች የምንናገረው ካሉበት ዓለም የተሻለ ተስፋ የለም ብለው ተቀምጠው ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ ዛሬ ባይቀበሉንም በደስታ መናገር ይገባናል፡፡ ሰዎች ተስፋ የቆረጡ ቀን ምን ልሁን? ሲሉ የነገርናቸው ወንጌል ምርጫ ይሆንላቸዋል፡፡ ማንም ሰው የሰማውን ከኅሊናው የመሰረዝ መብት የለውም፡፡ ልርሳው ባለ ቊጥር ይበልጥ እያስታወሰው ይመጣል። ስለዚህ ወንጌልን በደስታ መናገር ይገባናል። ዮሐንስ ወንጌልን መሰከረ። ወንጌል ማለት ከክርስቶስ ጽንሰት እስከ ዕርገት ያለው የምሥራች ማለት ነው። ወንጌል ክርስቶስ መሆኑን፡- “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ሐዋርያው ይገልጠዋል /ሮሜ. 1፡3-4/። ዳግመኛም፡- “ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት” ይላል /የሐዋ. 8፡35/። ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነበር።
ወንጌሉን የጻፈው ዮሐንስ፣ መጥምቁ ዮሐንስን ምስክር አድርጎ ሲያቀርብ መጥምቁ ዮሐንስ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ምስክር አድርጎ ያቀርባል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ጊዜና ክስተቱን መጥምቁ ዮሐንስ ያብራራል። በርግጥም በጥምቀቱ ላይ የታየው ክስተት የሚረሳ አይደለም። ጌታችንም፡- “አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው”/ማቴ. 3፡15/። የታወቀውና የተረዳው ጽድቅ በሚበልጡን እጅ መጠመቅ ነው። በሚያንሰው እጅ መጠመቅ ግን የላቀ ጽድቅ ነው። ዮሐንስም አላጠምቅም ያለው የክርስቶስን ታላቅነት ተገንዝቦ ነው። ዛሬ ነገሥታትና ባለጠጎች መጥታችሁ አጥምቁልን ቢሉ አይሆንም የምንላቸው ባለቤቱ እንኳ ዮሐንስ ዘንድ ሄዶ ነው የተጠመቀው በማለት ነው። ስለዚህ የጌታችን ትሕትና የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሆነ። ሰው ከሚሄድበት የጽድቅ ርቀት አልፎ ጌታችን ሄዷል። በአዲስ ኪዳን ያለው ትሕትና ለሚበልጡን ብቻ ሳይሆን ለሚያንሱንም ዝቅ ማለት እንዳለብን ያሳያል። ጌታችን በባሪያ እጅ ተጠመቀ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ። ዛሬ እንኳን የተማሪውን የአስተማሪውን እግር የሚያጥብ ይገኝ ይሆን? ክርስትና ግን ክርስቶስ ያሳየን ሕይወት ነው።
ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ ከተከናወኑት ክስተቶች አንዱ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ነው። መንፈስ ቅዱስ የወረደበት መልክ ደግሞ የርግብ አምሳል ነው። ርግብ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ነው ማለት አይደለም። መንፈስ ቅዱስ ግን የወረደው በርግብ አምሳል ነው። መንፈስ ቅዱስ በብዙ ምሳሌዎች ተገልጧል። በዚህ ክፍል ደግሞ በርግብ አምሳል ወርዷል። መንፈስ ቅዱስ ያረካልና በውኃ ይመሰላል /ዮሐ. 7፡37-39/። ያጠራልና በእሳት ይመሰላል /የሐዋ. 2፡3-4/። መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የወረደው ርግብ የዋህ ናት፣ መንፈስ ቅዱስም የዋህ ስለሆነ ነው። ርግብ ፀዓዳ ናት፣ መንፈስ ቅዱስም ንጹሕ ነው። ርግብ ከጎጆዋ አንድ ሣር ቢመዘዝ ጎጆዋን ጥላ አትሄድም፣ መንፈስ ቅዱስም ሰነፉ፣ ደከሙ ብሎ አይለየንም። ርግብ ጎጆዋ ቢፈርስ ጥላ ትሄዳለች፣ መንፈስ ቅዱስም ክርስቶስን ከካድን ይለየናል።
መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱ የኖኅን ዘመን ያስታውሰናል። የኖኅ ዘመን ከመጨረሻው ዘመን ጋር የሚመሳሰል ነው። በኖኅ ዘመን የነበረው ኃጢአትና የወረደው ቅጣት ዓለም አቀፋዊ ነው።በመጨረሻው ዘመንም ዓለም አቀፋዊ ኃጢአትና ቅጣት ስለሚመጣ በኖኅ ዘመን መመሰሉ ትክክል ነው። በኖኅ ዘመን ውኃ ለጥፋትም ለምሕረትም ሆኗል። የኖኅ መርከብ በውኃ ባትንሳፈፍ ኖኅና ቤተሰቡ አይድኑም ነበር። ያ ኖኅ የዳነበት ውኃ የጥምቀት ምሳሌ ነው /1ጰጥ. 3፡20-21/። ኖኅ የጥፋት ውኃ መጕደሉን ለማወቅ ርግብን ሰድዶ የምሥራች ይዛ ተመልሳለች /ዘፍ. 8፡6-12/። የርግብ መምጣት የጥፋት ውኃ መጉደሉን ሕይወት ቀጣይነት ማግኘቱን ያሳያል። ልብ አድርጉ ውኃው የጥምቀት ምሳሌ ነው አልን። ያች ርግብ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት። ጌታችን ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መምጣቱ የኃጢአት ባሕር መጉደሉን ሕይወቱን መቀጠሉን የሚያበሥር ነው። ይልቁንም በኖኅ ዘመን በነበረው ኃጢአት እግዚአብሔር አዝኖ፡- “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና”  ብሎ ነበር /ዘፍ. 6፡3/። የኖኅ ዘመን ትልቁ ቅጣት መንፈስ ቅዱስን ማጣት ነው። አሁን በጌታችን ጥምቀት ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ እግዚአብሔር እንደ ታረቀን ያሳያል። ነቢዩ ዳዊት በንስሐ ጸሎቱ፡- “ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” ብሏል /መዝ. 50፡11/። መንፈስ ቅዱስን ማጣት ሞገስን ማጣት ነው። መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱ፡-
    የኃጢአትና የጥፋት ባሕር መጉደሉን ያሳያል። ስለዚህ ልሻገረው አልችልም ብለን በኃጢአት ስጋት መኖር አይገባንም። የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ መጥቷል። ክርስትናም ቀሊል፣ ቀንበሩም የማያቆስል ልዝብ ሆኗል /ማቴ. 11፡30/።
    ሕይወት መቀጠሉን ያሳያል፡- ክርስትናው የተመሠረተው በልደት ላይ ቢሆን ወደፊት ሞት ያሰጋው መነበር። የተመሠረተው የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ነውና ማንም ሊያቆመው የማይችል የሕይወት ኃይል ሆኗል።
    ለጌታችን ምስክርነትን ይሰጣል፡- መንፈስ ቅዱስ የወረደው የጌታችንን ወልደ እግዚአብሔርነት ለዓለም ለመመስከር ነው። አብ በደመና የምወደው ልጄ ይህ ነው ሲል መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በጣት ጠቅሶ፣ በእጅ ነክቶ ለማሳየት በርግብ አምሳል ወርዷል። ልጄ ነው የሚለውን ድምፅ የሚሰማው ሕዝብ ዮሐንስን ነው እንዳይል መንፈስ ቅዱስ ለይቶ አሳየ።
    በድካማችን ያግዘናል፡- ስንወድቅ፣ ስንዝል፣ ስንሰንፍ፣ በመከራ ውስጥ ስናልፍ መንፈስ ቅዱስ ያዝንልናል፣ ይረዳናል እንጂ አይታዘበንም /ሮሜ. 8፡26-27/። ርግብ ሣር ተመዘዘ ብላ ጎጆ እንደማትቀይር ዛሬ ደከመ ብሎ መንፈስ ቅዱስ አይተወንም።
    መንፈስ ቅዱስ የወረደው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ምስክርነት ከተሰማ በኋላ ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ ሕይወታችን የሚመጣው ክርስቶስ በሕይወታችን ሲከብር ነው።
ምነው በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል የወረደባቸው ሰዎች የሉም ወይ? ብንል አዎ መንፈስ ቅዱስ ቢወርድም ግዳጁን ፈጽሞ ይመለሳል። ካሣ ሳይከፈል መንፈስ ቅዱስ ሊኖር አይችልምና። የኖህ ርግብ ማረፊያ ባገኘች ጊዜ በምድር ላይ እንደ ቀረች መንፈስ ቅዱስም ቅዱሱ የጌታ አካል ላይ አረፈ። ከዚያ በኋላ በምድር ላይ ቀረ። በምድር ላይ ሲቀርም፡-
    የግልና ውስጥ መምህራችን ሆነ /ዮሐ. 14፡26/
    አጽናኝና የመከራ ጓድ ሆነ /ዮሐ. 14፡16/
    የቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ሆነ /ዮሐ. 20፡22፤ የሐዋ. 15፡29/
    ጸጋን ለምእመናን አፈሰሰ /1ቆሮ. 12፡4/
    ወንጌልን ለመመስከር ድፍረትና ጥብዐትን ሰጠ /የሐዋ. 2፡14/።
መጥምቁ ዮሐንስ የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት በማስታወስ ክርስቶስ ታላቅና የመሥዋዕቱ በግ መሆኑን ለዓለም ገለጠ። ስለ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችንም ይመሰክርልናል እንጂ በስብከት ብቻ የተከተልን አይደለንም። በውጭም በውስጥም የሚናገረን አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለ ሰጠን አገልጋዮች ስለ ሰጠን የውስጥ እረፍት መንፈስ ቅዱስ ይመስገን። ዛሬ የደከማችሁና ያዘናችሁ፣ እኔ ሰው አልሆንም የምትሉ፣ ራሳችሁ አላረካ ብሏችሁ የታከታችሁ የምሥራች ደስ ይበላችሁ። መንፈስ ቅዱስ ደከሙ፣ ሰነፉ ብሎ አይተዋችሁም።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ