የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የላከንን እንስማ

“እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ” /ዮሐ. 1፡33/።
መጥምቁ ዮሐንስ አላውቀውም ነበር በማለት ለሁለተኛ ጊዜ ይናገራል። ክርስቶስ ግን ስለሚያውቀው ይደሰታል። ክርስቶስን ማወቅ አስደሳች ነገር ነው። በክርስቶስ መታወቅ ግን የበለጠ ደስ ያሰኛል። ሐዋርያው ስለ ፍቅር በተናገረበት አንቀ  ጹ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡- “ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ” /1ቆሮ. 13፡12/። በዚህ ዓለም ላይ ያለን የትኛውም እውቀት፣ የእውቀት ክፋይ ወይም የሙሉ አጋማሽ ነው። ፍጹም እውቀትን ልናውቅ አንችልም። የእውቀትና የጥበብ አገሯ ሰፊና በዚህ አጭር ዘመንም የማንፈጽመው ነው። ዛሬ የብሉያትን የሐዲሳትን የሊቃውንትን የመነኮሳትን የነገረ መለኮትን የዜማን እውቀት በማወቃችን እንደሰታለን። በሰማይ ስንሄድ ግን የሚያስደስትን እኛ በእርሱ መታወቃችን ነው። በስማችን ሲጠራን፣ ያዘጋጀልንን ክብር ሲያወርሰን ያን ጊዜ እንደነቃለን። አንድ የአገር መሪን ማወቃችን አይደንቅም፣ እርሱ እኛን በማወቁና በስማችን በመጥራቱ ግን እንደነቃለን። እንዲሁም በእግዚአብሔር መታወቃችን ያስደስተናል። መጥምቁ ዮሐንስ አላውቀውም ነበር ካለ በኋላ በክርስቶስ መታወቁ አስደስቶታል።
እግዚአብሔር በማወቅና ባለማወቅ ይመለካል። ያወቅነውን ያህል ስናመልከው፣ ከእውቀታችን የተሰወረውን ደግሞ “አንተ ራስን ታውቃለህ” ብለን እናመልከዋለን። የማውቅህና የማላውቅህ እግዚአብሔር ተመስገን እንደ ማለት ነው። በዚህ ዓለም ላይ ያወቁት ሲያስደስት ያላወቁት ያበሳጫል። እግዚአብሔር ግን በመታወቅም ባለመታወቅም ያስደስታል። ስናውቀው እናመልከዋለን። ከእውቀታችን በላይ ሲሆንብንም “አንተ ትልቅ አምላክ ነህ” ብለን እንደ ገና እናመልከዋለን። እኛም አላወቅነውም። ግን እያገለገልነው ነው። በሰላም ቀን በአጠገባችን እጃችንን እንደ ልጅ ይዞ ሲጓዝ፣ ገደል ላይ ስንደርስ ደግሞ ተሸክሞ ሲያሻግረን አላወቅነውም። ያለ ምክንያት ሲያኖረን፣ የማናውቃቸውን ዘመድ ሲያደርግልን አላወቅነውም። ሕዝቡን ሲያስገዛልን፣ ኃይለኞችን ጎንበስ ሲያደርግልን እርሱ መሆኑ አልገባንም። ነቢዩ ኢሳይያስ ባየው ራእይ ሱራፌል እንዲህ እያሉ ያመሰግናሉ፡- “አንዱም ለአንዱ፡- ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” /ኢሳ. 6፡3/። ይህ ጩኸት ተራ ጩኸት አይደለም። በጣም ስንደነቅ እንደምንጮኸው ያለ ጩኸት ነው። ሱራፌልን ያስጮኻቸው በሰማይ ያለው ድንቅ ነገር ሳይሆን በምድር ላይ ያለው ድንቅ ነገር ነው። ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች። በምድር ላይ ባለው  እያንዳንዱ ተፈጥሮ ላይ የእግዚአብሔር አስደናቂ ጥበብ አርፏል። ያንን ባዩ ጊዜ በጩኸት አንተ ልዩ፣ ልዩ፣ ልዩ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ እያሉ ማመስገን ጀመሩ። በምድር ላይ ያለው መላእክት የሚጠቀሙበት ሳይሆን ለእኛ የተፈጠረ ነው። መላእክት ስለ እኛ እያመሰገኑ እኛ ግን የተሰጠንን ማየት አቅቶን አኩርፈን ተቀምጠን ይሆናል። በገዛ ድግሳችን ሌላው እያመሰገነ እኛ ካኮረፍን እስቸጋሪ ነው። በእያንዳንዱ ቅጠል ላይ የሚደረገው ምርምር ገና አላበቃም። ተሸክመን በምንዞረው አካላችን ላይ ገና ጥናቶች እየተካሄዱ ነው። ምድር ላይ የምናየው ሁሉ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የምስጋና ርእስ ነው። የከበበን ተፈጥሮ፣ በየዕለቱ የሚሆንልን ጥበቃ፣ የምናልፍበት የሕይወት ጎዳና አላወቅነውም። ነገር ግን ለምስጋና የሚጋብዘን ነው።
ዮሐንስ አላውቀውም ካለ በኋላ እርሱ ግን ያውቀኛል በሚል ድምፅ የላከኝ እርሱ ነው ብሏል። ዮሐንስ በውኃ ለማጥመቅም ጥሪ ሰምቶ የወጣ፣ የተላከም መልእክተኛ መሆኑን አረጋግጧል። አገልግሎት ጥሪ ያስፈልገዋል። ያለ ጥሪ ማገልገል በእግዚአብሔር ዘንድ እውቅና የለውም። በውኃ ለማጥመቅም ጥሪ ያስፈልጋል። ጥሪን የምናውቀው ብዙ ሕዝብ በማስከተላችን አይደለም። ወይም የቤተ ክህነት ይሁንታ ማግኘታችን አይደለም። እነዚህ የጥሪ ማረጋገጫዎች አይደሉም። ጥሪ በውስጣችን የሚሰማን ድምፅ ነው። ጥሪ እግዚአብሔርን የሚያውቁ አባቶችና አገልጋዮች የሚያረጋግጡልን ነው። ጥሪ የማያስቀምጠን ሁልጊዜ የሚወጋጋን ነው። ዝናን የሚፈልጉ ለመዝፍን ድምፅ፣ ለመግዛት ሥልጣን የሌላቸው ክፍት በር የሚያገኙት የእግዚአብሔርን ቤት ነው። እግዚአብሔርን ለማገልገል ሳይሆን ለዝና በእግዚአብሔር አደባባይ ይንጎማለላሉ። ሁሉንም ነገር በኃይል ያደርጉታል። ጥሪና ጸጋ ከሌለ ሁሉም ነገር በኃይልና በወቅታዊ ርእሶች ላይ የተመሠረተ ነው። ዛሬ ጥሪው እያላቸው የተኙና ያለ ጥሪያቸው የነቁ ሁለት ዓይነት ወገኖችን እናያለን። ጥሪው በውኃ ማጥመቅም ከሆነ በደስታ መቀበል ይገባል። ምክንያቱም ከትልቁ እግዚአብሔር የምንቀበለው ምንም ዓይነት ትንሽ ድርሻ የለምና። በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የምናገኘው በተቀበልነው የጸጋ ዓይነት ሳይሆን በተሰጠን ታማኝ በመሆናችን ነው። ጥሪዎች የሌሉት አገልግሎት የሚስብ ሳይሆን በማስታወቂያ ኃይል የሚንቀሳቀስ ነው። ለእግዚአብሔር ክብርን የሚሰጥ ሳይሆን እኔነትን የሚያጎላ ነው። መረሳትን የሚፈራና በሰው ጉልበት የሚደገፍ ነው።
መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ፡- “እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ” ብሏል /ዮሐ. 1፡33/። ጌታችን ሲጠመቅ የተገለጠው ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለዮሐንስም ነው። ዮሐንስም ገና ለማወቅ ይኖራል። እውቀት አያልቅምና። ዮሐንስ ወደ አገልግሎቱ የገባው በአይሁድ ፈቃድ፣ በሊቃነ ካህናቱ ይሁንታ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ነው። የጠራው መንፈስ ቅዱስ ማስተማር አይደክመውና በጌታችን ጥምቀት ሰዓት ይህ ነው በማለት ስለ ክርስቶስ ይነግረዋል። የክርስቶስ ምልክቱ መንፈስ ቅዱስ ነው። ጌታችን ሲጸነስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው /ሉቃ. 1፡35/። ሲጠመቅም በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት አግኝቷል። ወደ ምድረ በዳም ለመፈተን ሲሄድ በመንፈስ ቅዱስ ነው /ማቴ. 4፡1/። ተልእኮውን ሲጀምርም “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው” ብሏል /ሉቃ. 4፡17/። ከሞት ሲነሣም በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተነሥቷል /ሮሜ. 1፡3/። መንፈስ ቅዱስ ለሕይወታችንና ለአገልግሎታችን እጅግ ያስፈልገናል። ከመንፈስ ቅዱስ የተለየ ማንኛውም እንቅስቃሴ ድል የለውም። ይህንን መንፈስ ቅዱስ ስናምንና ስንጠመቅ ተቀብለነዋል። በየዕለቱም ኃይሉንና ብርታቱን በጸሎት፣ በቃሉና በኅብረት አማካኝነት እንሞላለን። ለሕይወታችን ቅድስናን ለአገልግሎታችን ድልን የምናገኘው በመንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ፣ መካሪ፣ አስተማሪ ነው። እነዚህ ሦስት ነገሮች አስፈላጊና በየዕለቱ የሚያስፈልጉን ናቸው። እናዝናለንና መጽናናት፣ እንስታለንና ምክር፣ አናውቅምና ትምህርት ያስፈልገናል። እነዚህ የሕይወት በረከቶች ከሕይወት መምህር ከመንፈስ ቅዱስ ይገኛሉ።
በጌታችን አገልግሎት እንዳየነው በእኛም አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ያስፈልገናል።
1-  የራእያችን ጽንሰት በመንፈስ ቅዱስ ሊሆን ይገባዋል።
2-  ስለ ራሳችንም እኛ ከምንናገር መንፈስ ቅዱስ ቢናገር ይሻላል።
3-  መንፈስ ቅዱስ ላለ መፈተን ዋስትና አይሰጠንም፣ የድል ዋስትናን ግን እንደሚሰጠን ማወቅ አለብን።
4-  ምንም ከሚኖረን መንፈስ ቅዱስ እንዳለን በማሰብ ለአገልግሎት መድፈር ያስፈልገናል።
5-  ልንጠፋ በተቃረብንበት ነገር መንፈስ ቅዱስ ትንሣኤ እንደሚሰጠን ማመን አለብን።
6-  በመንፈስ ቅዱስ ከተነሣን ማንም ሊያቆመንና ሊሰብረን እንደማይችል መረዳት አለብን።
7-  በየዕለቱ የሚማር ማንነትን ይዘን መቅረብ አለብን።
እግዚአብሔር ይርዳን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ