“እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ” /ዮሐ. 1፡34/።
መጥምቁ ዮሐንስ የእግዚአብሔር አብንና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ምስክርነት ያየ የሰማ ነው። አብም መንፈስ ቅዱስም ስለ ወልድ መስክረዋል። ዮሐንስ አላውቀውም ነበር ካለ በኋላ አሁን አይቻለሁ አለ። አለማወቅን ወደ ማየት የሚቀይር እግዚአብሔር ነው። አለማወቅ ማለት አለማየት ማለት ነው። ማወቅ ማለትም ማየት ማለት ነው። አንድ ሰው አንድ ነገርን ስላለ ያያል፣ ባይኖር ሊያየው አይችልም። እንዲሁም ስለ ክርስቶስ የነበረውን እውነት እናያለን እንጂ በማየት ለእርሱ የምንጨምረው ክብር የለም። ማየት ህልውናን አያስገኝም፣ ህልውና ግን ይታያል። ዛሬ ያመነው ክርስቶስ የጥንቱ ክርስቶስ ነው። አዲስነቱ ዛሬ የመጣ አያሰኘውም፣ ጥንታዊነቱም ዛሬን የማያዝዝ አያደርገውም። ዮሐንስ ይህን አዲስነትና ጥንታዊነት አየሁት ይላል። ይህን እይታ ያገኘው በአብና በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ነው። አብና መንፈስ ቅዱስ ስለ ወልድ ይመሰክራሉ። የመሥዋዕቱ በግ፣ የመዳን ምክንያት እርሱ ብቻ ነውና። ወልድን ማመን አብንና መንፈስ ቅዱስን ማመን ነው። ወልድን አለማመን አብና መንፈስ ቅዱስንም ሐሰተኛ ማድረግ ነው። ስለ ወልድ መመስከር ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መተባበር፣ በፈቃደ ሥላሴ ውስጥ መሆን ነው።
ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መሰከረ። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ መመስከር ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፡-
– አብ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር የመሰከረው ነው /ማቴ. 3፡17፤17፡5/። በዮርዳኖስ ለዓለም ሊገልጠው፣ በደብረ ታቦር የጴጥሮስን ምስክርነት ሊያጸናው ልጄ ነው አለ።
– ሰይጣን የእግዚአብሔር ልጅነቱን ሊያሳብል ሞከረ። “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ” እያለ ፈተና አመጣ /ማቴ. 4፡6/። የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በዮርዳኖስ የአብን ምስክርነት በመስማት አወቀ። የእግዚአብሔር ልጅነቱን የተጠራጠረ ለእኔ ፈተና ይወድቃል ብሎ ሰይጣን ያምናል። ዛሬም እግዚአብሔር በልጅነት የሰጠንን ፍቅርና ተስፋ ከተጠራጠርን ሳይነኩት እንደሚወድቅ የተገዘገዘ ዛፍ እንሆናለን። እግዚአብሔር ይወደኛል፣ ተስፋውን ይፈጽማል ብሎ ማመን ትልቅ ጉልበት ነው።
– አጋንንት ሳይቀሩ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን ብለው እንደማይቋቋሙት የመሰከሩለት ነው /ማቴ. 8፡29/። ይህ ልጅነት የማይደፈር ግርማ፣ የማይደክም ጉልበት ነው። ይህ ልጅነት ልዑልነት ሳይሆን እኩያነት፣ አልጋ ወራሽነት ሳይሆን ዘላለማዊ አምላክነት ነው።
– ደቀ መዛሙርቱ ማዕበልን የገሰጸው ይህ ኃይሉ መሆኑን አይተው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው የሰገዱበት ነው። ስግደትን የሚቀበልበት ክብሩ የእግዚአብሔር ልጅነቱ ነው። ከአምላክ የተገኘ አምላክ፣ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነውና።
– ጴጥሮስ የተመሰገነበትና የሰማይ መገለጥ የሆነው ያ የቤተ ክርስቲያን የዓለት መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መቀበል ነው /ማቴ. 16፡16/። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ማመን ብጽዕናን ያስገኛል። ወደ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ዓለት ያደርሳል። ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራና ማዕበልን በጽናት የምታሳልፈው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብላ ማመኗ ጽናት ስለሆናት ነው።
– የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ በማለቱ ለሞት ፍርድ የበቃበት ነው /ዮሐ. 19፡7/። በእውነቱ ተከሰሰ፣ በእውነቱ ሞተ። እውነቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ነው።
– የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ከመስቀል ውረድ ተብሎ መዘባበቻን የተቀበለበት ነው /ማቴ. 27፡43/። ቢያንስ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጅነቱ ከመስቀል መውረድና ገዳይን መግደል የሚችል መሆኑን አምነውበታል። እርሱ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም ስለ እኛ በመስቀል ላይ መሞትን መረጠ። በዚህም ታላቅ ፍቅሩን ለእኛ ገለጠ። መሸነፍ በሚመስለው ሞትም ጠላትን አሸነፈ።
– መቶ አለቃው እግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ያመነበት ነው /ማር. 15፡39/። መቶ አለቃው ኢየሱስ ነፍሱን ለአባቱ ሰጥቶ ሲሞት ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ አመነ። የኢየሱስ ሞት አድራሻ ያለው መሆኑን ሲያይ፣ ሞቱ በአባቱ እቅፍ ውስጥ መሆኑን ሲያውቅ የመቶ አለቃው አመነ። የእግዚአብሔር ልጅነታችንን ስንቀበል ብቻ ሞትን በደስታ እንደምንጋፈጣት ያሳያል። እስከዚህ ቀን የነፍስ አድራሻዋ ሲኦል ነበረ። አሁን ግን በኢየሱስ ክርስቶስ የነፍስ አድራሻዋ የአባት እቅፍ ሆነ።
– ከድንግል የተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ስለዚህ ልጅነቱ ከሥጋ ልደቱ በፊት ነበረ /ሉቃ. 1፡35/። የአብ ልጅ የማርያም ልጅ እንደሆነ ማመን እምነታችንን ተዋህዶ ያሰኘዋል። ወልደ አብ በመለኮቱ፣ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ብለንም እናምናለን፣ እናሳምናለን።
– እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አለማመን ፍርድ አለው /ዮሐ. 3፡18/። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በማንነታችን ወይም በጥረታችን ልንገባ አንችልም። ስለዚህ መስፈርት በሌለው እንዲሁ ቸርነት በሚገኘበት በልጅነት እንድንወርስ ተጠርተናል። ልጅነት ወራሽነት ነውና። ልጅ የምንሆነው በልጁ በማመን ነው። በወልድ ውሉድ እንባላለንና። በክርስቶስ ካላመንን ግን መንግሥቱን መውረስ አንችልም።
– የእግዚአብሔር ልጅነቱን ማመን የዘላለም ሕይወት አለው /ዮሐ. 20፡31/። ወንጌላት የተጻፉበት ዓላማም ይህ ነው። ወንጌልን ከታሪክና ከፍልስፍና ልዩ የሚያደርገው በእግዚአብሔር ልጅ በማመን ሕይወት የሚገኘበት መሆኑ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ ማመን ማለት፡-
– አብን አባት ብሎ ማመን ነው። ልጅ በሌለበት አባት መባል የለምና።
– የእኛን የጸጋ ልጅነት አምነን የጠላትን ፈተና ድል የምንነሣበት ነው።
– ማዕበልን መገሰጽ እንደሚችል አይተን ስግደት የምናቀርብበት ነው።
– ከአይሁድ ማኅበር ተለይተን ካመኑት ጋር ባለ አገር የምንሆንበት ነው።
– የትንሣኤውን ኃይል በመተባበር ከሞትና ከኃጢአት ፍርሃት የምንድንበት ነው።
– የሚታየውን ዓለም የምናሸንፍበት ምሥጢር ነው።
– በእርሱ አለኝታነት በሃይማኖታችን የምንጸናበት ነው።
እኛም ከመጥምቁ ከዮሐንስ ጋር ሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እናምናለን፣ እንመሰክራለን። እርሱን የእግዚአብሔር ልጅ ብለን ማመን አብን አባት፣ መንፈስ ቅዱስን ሕይወት ብለን መቀበል ነው። ይህንን ብልጭልጭና ስግብግብ ዓለም የሚያሸንፈው፣ እምቢ አልገዛም ብሎ ሥጋዊ ምኞትን የሚያስክደው ይህ እምነታችን ነው።