የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የውኃ በዓል

 በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ውኃ ልዩ ትርጉም አለው። ውኃ ንስሐ ፥ ውኃ ኀዘን ፥ ውኃ ደስታ ፥ ውኃ ልደት ፥ ውኃ ክርስቶስ ፥ ውኃ መንፈስ ቅዱስ፥ ውኃ የመጨረሻው ትልቅና ትንሽ ስጦታ ፥ ውኃ መፈወሻ … ነው ። ወንጌሉ የውኃ ወንጌል ብንለው መልካም ነው ። ባለፈው በመልክአ ምድር የኢየሩሳሌም ወንጌል እንደ ተባለ ገልጠናል ። አሁን ደግሞ ከውድ ነገርና ከርካሽ ነገር አንዱ የሆነውን ውኃን ይጠቅሳልና የውኃ ወንጌል ብንለው ያስኬዳል ። ውኃ ሦስት ነገር የለውም ይላሉ ። ውኃ ቀለም ፥ ጣዕምና ሽታ የለውም ። ውኃ ቀለም የለውም መንፈሳዊ ስጦታም ሰውን ከሰው አይለይም ። ውኃ ጣዕም የለውም መንፈሳዊ ነገርም አይሰለችም ። ውኃ ሽታ የለውም ፥ መንፈሳዊ ነገርም ክፉ ጠረንን ያስወግዳል ። ውኃ ቀለም ቢኖረው ቀዩ ጥቁር ፥ ጥቁሩም ቀይ ይሆን ነበር ። መንፈሳዊ ሕይወትም ውስጥን ይለውጣል እንጂ በውጫዊ ማንነት አይለካም ። ውኃ ጣዕም ቢኖረው ይሰለች ነበር ። መንፈሳዊ ሕይወትም ጣዕሙ የሚገለጠው በሰውዬው ላይ ነው ። ውኃ ሽታ ቢኖረው ሽታን አያስወግድም ነበር ። መንፈሳዊ ሕይወትም ለሁሉም የሚስማማ ማንነትን ያጎናጽፋል ። ሽቱ የተቀባ ሰው የማይቀርቡ አሉ፥ በውኃ የታጠበን ሰው ግን አይርቁም ።
ውኃ ቀለም የለውም ከተባለ ይህ ነው መልኩ የማይባለው እጅግ የተራራቀ ቀለም ባለቤት የሆነ ያ ውድ ነጭና ቀይ ነው /መኃ. 5፥10/ ። እጅግ ኃያል ሲባል እጅግ ትሑት ነው ። እጅግ ንጹሕ ሲሆን ትልቅ መሥዋዕት ነው ። ምድራዊ መለኪያ የማይገልጠው በስሜት ወይም በምላስ የማናረጋግጠው የእምነት ነቅዕ በእርግጥም እርሱ የማይደፈርስ ምንጭ ነው ። ሽታ የሌለው ለጤነኛ ለበሽተኛ የሚስማማው ፥ ለጻድቅና ለኃጥኡ የሚያስፈልገው ያ ውኃ ክርስቶስ ነው ።
በዓለም ላይ የመጨረሻው ርካሽና የመጨረሻው ውድ ውኃ ነው ። ርካሽነቱ ሁሉም የሚያገኘው መሆኑ ውድነቱ ያለ እርሱ ሕይወት የማይቀጥል መሆኑ ነው ። ለሁሉ የተሰጠው የአብ የፍቅር ስጦታ ፥ ሕይወት በእርሱ ብቻ ያለች ነቅዐ ጥበብ /የጥበብ ምንጭ/ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ዛሬ በጸሎት በፊቱ ባንቆም አንድ ቀን በፍርድ ዙፋኑ ፊት እንቆማለን ። ቆመንም ሞተንም የምናገኘው የሕያዋንና የሙታን ጌታ እርሱ ነው ። የማይኮራበት ፍላጎት አማኑኤል ነው ። የበቃኝ ኑሮ ምሥጢሩ እርሱ ክርስቶስ ነው ።
   ወንጌላዊው ዮሐንስ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ውኃን ያነሣል ። የዮሐንስ ወንጌል ከዘፍጥረት ጋር ይመሳሰላል ብለናል ። በኦሪት ዘፍጥረት ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ እንደ ነበር ይገልጣል ። በዮሐንስ ወንጌልም ውኃና መንፈሱ ሲዋሐዱ የሚገኘውን ልደት ይናገራል ። በኦሪት ዘፍጥረት “እግዚአብሔርም አለ፦ ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ” ይላል /ዘፍ. 1፥20/ ። በዮሐንስ ወንጌልም ስለ ጥምቀት ሠራዊት ይናገራል /ዮሐ. 3፥5/ ። በዮሐንስ ወንጌል የተጠቀሰው የውኃ ዓይነት ፡-
 
1- የዮርዳኖስ ውኃ ፡-
የዮርዳኖስ ውኃ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ትልቅ ታሪክ ያለው ወንዝ ነው ። ብዙ ምሥጢራት የተፈጸሙበት ፥ ተአምራቶችም የተከናወኑበት ነው ። የእስራኤል ልጆች የተስፋይቱን ምድር ሙሉ በሙሉ እንደ ወረሱ ያረጋገጡት ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ነው ። ዮርዳኖስን መሻገር የበረከትን ምድር ለመውረስ ትልቅ ማሳያ ነው ። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በዮርዳኖስ ወንዝ ነው ። በዚህ ወንዝ ላይ ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጧል ። ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ታውጇል ። የዮሐንስ ወንጌል በመጀመሪያ የሚናገረው ስለ ዮርዳኖስ ወንዝ ነው /ዮሐ. 1፥28/ ።
 
2- የቃናው ውኃ ፡-
ጌታችን ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምር የሠራው በቃና ውኃ ነው /ዮሐ. 2፥1-11/። በቃናው ተአምር እግዚአብሔር ባለቀ ነገር እንደሚሠራ ፥ ጣዕም የሌለውን ነገር ወደ ጣዕም ማምጣት እንደሚችል ያሳያል ። ይልቁንም በጋብቻ ውስጥ በጅምሩ ብዙ ችግሮችን የሚያስተናግዱ ይህን ሁሉ ጉድለት እግዚአብሔር ሊለውጥ በዓላማ ላይ ነውና በጸሎት እንዲጸኑ ያሳያል ።
 
3- የልደት ውኃ ፡-
አዋቂው ኒቆዲሞስ በእውቀት የማያገኘውን በእምነት ግን የሚወርሰውን ልጅነት በውኃና በመንፈስ እንደሚያገኝ የተናገረበት ክፍል ነው ። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከመግባት በፊት ማየት ያስፈልጋልና ጌታችን ያልተወለደ መንግሥቱን አያይም አለ /ዮሐ. 3፥3/ ። ያላየም አይወርስምና በመቀጠል ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም አለ /ዮሐ. 3፥5/ ። ማየት ፍቅር ኅብረት ነው ። ይህ በቤተ ክርስቲያን ይገኛል ። ያንን ፍቅርና ኅብረት በሙላት የምንወርሰው የምድር ጉዞአችንን ጨርሰን ወደ መንግሥቱ ስንገባ ነው ።
 
4- የሰማርያ ውኃ ፡-
ውኃ የሚቀዳው በማለዳ ነው ። ሳምራዊቷ ሴት ግን በቀትር ትገሰግስ ነበር ። ቀትር እንኳን ሌላ ሸክም ተጨምሮበት የለበሱትንም ያስወልቃል ። ያውም በሰማርያ ላይ ቀትር ተጨምሮበት እንደምን ከባድ ነው ። ሳምራዊቷ ሴት ግን የተናቀችና የተጠላች ስለነበረች ከአንደበት እሳት የቀትሩ እሳት ይሻላል ብላ ትገሰግስ ነበር ። የዮሐንስ ወንጌል ስለ ሰማርያ ውኃ ይናገራል ። ሳኦል አህያ ፍለጋ ወጥቶ ንግሥና ይዞ እንደ ተመለሰ ፥ ይህች ሴትም የሚያስጠማውን ውኃ ፈልጋ ወጥታ የሕይወትን ውኃ ይዛ ተመልሳለች ። ትንሽ ፈልገን ብዙ የምንቀበለው ከባለጠጋው ከመድኃኔዓለም ነው /ዮሐ. 4፥7-26/።
 
5- የቤተ ሳይዳው ውኃ ፡-
ይህ መጠመቂያ ሕሙማን ፈውስን ለማግኘት የሚከማቹበት ነው ። ውኃውን የእግዚአብሔር መልአክ ሲናውጠው መጀመሪያ የገባው ይፈወስ ነበር ። መጀመሪያ ለመግባት ጉልበት አሊያም ዘመድ ያስፈልጋል ። በዚህ መጠመቂያ ዳር ሠላሳ ስምንት ዓመት ተኝቶ የነበረውን ሰው ጌታችን ፈውሶታል ። ወንጌላዊው ስለዚህ መጠመቂያ ይናገራል /ዮሐ. 5፥2-9/ ። ዛሬም ለመጋፋት ጉልበት ፥ ለመርታት ሰው የለኝም ለሚሉ ፥ ደግሞም ዘመኔ ገፋ ፥ ገሰገሰ እያሉ ለሚተክዙ ዘመን የማያልፍበት ጌታ ከእናንተ ጋር ነው እንላቸዋለን ። ሰው የለኝም ለሚሉም ጌታችን ሰው ሆኖ መጥቷል ።
 
6- አስጨናቂው ውኃ ፡-
ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ላይ በታንኳ ሲጓዙ ማዕበል አስጨነቃቸው ። ጌታ ግን አነርሱ በታንኳ መርገጥ ያቃታቸውን ባሕር በእግሩ እየረገጠ መጣ ። ማዕበሉን ገስጾ ሰላምን ሰጣቸው ። ከፈለጉትም ወደብ አደረሳቸው /ዮሐ. 6፥16-21/ ። ዛሬም በሰላም ጀምረው መሐል መንገድ ላይ ለሚታገሉ ጌታ ይደርስላቸዋል ። ማዕበሉን ገስጾ ሰላምን ለልባቸው ፥ ወደብን ለእግራቸው ይሰጣል ። ወንጌላዊው ስለሚያስጨንቀው ውኃ ይናገራል ። ለመመለስ ብዙ የተጓዛችሁ ፥ ለመጨረስ ማዕበል አላሳልፍ ያላችሁ እግዚአብሔር ደርሶላችኋል በእውነት ደስ ይበላችሁ ።
 
7- የሕይወት ውኃ ወንዝ ፡-
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ በሕይወት ውኃ ወንዝ ተመስለዋል /ዮሐ. 4፥14 ፤ ዮሐ. 7፥37-38/ ። ምንጭ ፍለጋ መጓዝ አያስፈልግም ። እርካታ ፍለጋ መንከራተት አያሻም ። በእግዚአብሔር ስናምን ምንጩን በውስጣችን ይተክለዋል ። ረክተን የምናረካ እንሆናለን ። ድህነት ጭንቀት የሆነባቸውን ያህል ስኬት ክስረት ፥ ብልጥግና ድህነት የሆነባቸው አያሌ ናቸው ።  ለእነዚህ የባለጠጋ ድሆች መፍትሔው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የእነርሱን ችግር የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነውና ።
 
8- የሰሊሆም ውኃ ፡-
ጌታችን በደረቅ ግንባር ላይ ዓይንን ሠርቶ በሰሊሆም መታጠቢያ ታጠብ ባለው ጊዜ ዕውሩ እያየ ተመለሰ /ዮሐ. 9፥1-7/። የፈጠረው እንደገና ፈጠረው ። ዓይን ግንባር ሆኖ አያውቅም ። ይህ ሰው ግን የዓይን ቅርጽ እንኳ የሌለው አሳዛኝ ሰው ነበር ። ጌታችን ግን በምራቁ ጭቃ ለውሶ ዓይንን ሠራና ሂድና ታጠብ አለው ። እያየም ተመለሰ ። ወንጌላዊው ስለዚህ መታጠቢያ ያትትልናል ።
 
9- የክረምት ውኃ ፡-
ጌታችን እርሱና አብ አንድ መሆናቸውን የተናገረው በክረምት ነበር ። በእርግጥ ይህ ምሥጢር ከክረምት ነጠብጣብ ይልቅ ብዙ ነው /ዮሐ. 10፥22-30/ ። ክረምት ሁሉን ያጠግባል ። ሁሉን ስለሚያጠግበው ስለሥላሴ ምሥጢር የተናገረበት ክፍል ነው ። ክረምት የሚያጠግበው እየተጠላ ነው ። ጌታችንም እየጠሉት እንኳ ጥጋብ ነው ። ዛሬ እስራኤል ከፍተኛ ገቢዋ ጎብኚዎች ናቸው ። የሚጎበኙትም የአዲስ ኪዳን መዳረሻዎች ናቸው ። እስራኤል በክርስቶስ አላመነችም ። እርሱ ግን እየካደችው እንኳ እንጀራዋ ነው ።  እኛም እየካድነው እንኳ ስንት ዘመን ተሸከመን ። ስንክደው ያልካደን አምላክ ስሙ ይመስገን ።

ያጋሩ